Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ምእራባዉያን ለምን ወያኔን ይደግፋሉ ? – ግርማ ካሳ

$
0
0

“ማንም በፍትሕ ሥርዓታችን ጣልቃ እንዳይገባ እንደምንፈልገው ሁሉ እንግሊዝም በሌላ አገር የሕግ ሥርዓት ጣልቃ አትገባም” ሲሉ የእንግሊዙ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃሞንድ፣ አንዳርጋቸው ዙሪያ በሰጡት አስተያየት የገለጹት ነው።

ስለየትኛው የፍትህ ስር’ዓት እንደሚያወሩ አይገባኝም። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሕግ የለም። ያለው “ሕግን” እንደ ዱላ ተጠቅሞ ዜጎችን ማሰቃየትና ማሸበር ነው። ያለው መንግስታዊ ዉንብድና ነው።

አቶ አንዳርጋቸው፣ ከሌሎች በአገራችን ካሉ በሺሆች የሚቆጠሩ እስረኞች የተለየ ነገር አያጋጥመዉም። እንደዉም ባይብስ። በጥሩ ሁኔታ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ለምስክርነት ሲፈለግ፣ ፍርድ ቤት ይቀርብ ነበር። በሕግ መንግስቱ የተደነገ፣ በወዳጅ ዘመዶች የመጎብኘት መብቱ ይከበርለት ነበር። የት እንደታሰረ ይታወቅ ነበር። ያ ባልሆነበት ሁኔታ አንዳርጋቸው ደህና ሁኔታ ላይ ነው ማለት አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ ነው።

የእንግሊዙ ባለስልጣን ይሄን ያጡታል ብዬ አላስብም። ግን ከወያኔዎች ጋር ያላቸዉን ግንኙነት ላለማበላሸት የራሳቸውን ዜጋ ቢጎዳም፣ ወያኔዎችን ማሽሞድሞድን መርጠዋል። እነ ሱዛን ራይስ፣ ወንዲ ሻርመን እንዳደረጉት ማለት ነው።

በለንደን ብዙ ሰልፎች ተደርገዋል። ዉጤቱ እንግዲህ ይሄ ነው። ብዙ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ዉጤቱ ይሄ ነው። በዉጭ ብዙ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፣ በዳያስፖራ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊያን ብንኖርም፣ እንቅሳሴዎቻችን የአለም አቀፍ ማህበረሰብን ማሳመን አልቻሉም። ያለ ማጋነን በዲፕሎማሲው ረገድ መቶ እጥፍ ወያኔዎች በልጠዉናል። አሸንፈዉናል። ይሄንን እውነታ ማመን አለብን። መቀበል አለብን። እዉነታቸው ከመሸሸ እዉነታዉን ተጋፍጦ መፍትሄ መፈለጉ ነው የሚሻለው።

ምእራባዉያን ለሕዝብ፣ ለሰብዓዊ መብት ደንታ ስለሌላቸው፣ የሚያስቀድሙት ጥቅማቸዉን ስለሆነ የምንጮኸውን ጩኸት ለመስማት ጆሮ የላቸውም። የምእራባውያን ትልቁ ኢንተረስት ደግሞ ሽብርተኞችን መዋጋት ነው። ያልተረጋጉ አገሮች ለሽብርተኞች መናኸሪያ እንደሚሆኑም ያወቃሉ። ስለዚህ ለመረጋጋት ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ። ዴሞክራሲ ባይኖርም የተረጋጋች ምስራቅ አፍሪካን ማየት ይፈልጋሉ።

አንድ አሁን በስደት ያለ አገር ዉስጥ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ አመራር የነበረ ሰው የነገረኝን ላካፍላችሁ። በመለስ ዜናዊ ዘመን ነው።

“የሰብአዊ መብት ረገጣ በተመለከተ በደንብ የተቀናበረ፣ በእንግሊዘኛ የተጻፈ ሰነድ አዘጋጅተን ከስቴት ዲፓርትመንት ሃላፊዎች ጋር ቀጠሮ ተይዞልን፣ ወደዚያ ሄድን።በአክብሮት ተቀበሉን። የምንለውን በሙሉ አዳመጡን። ከዚያም በምትሉት በሙሉ እንስማማለን። ትክክል ናችሁ። ግን እኛን አሁን ምን አድርጉ ነው የምትሉን ? እነርሱን ተክታችሁ አገር ማስተዳደር ትችላላችሁ ወይ ? የአገር ደህንነትና ሰላም እንዴት ነው የምታስጠብቁት ? የአገር ደህንነት ፖሊሲ ዙሪያ ያዘጋጃችሁት ሰነድ አለ ወይ ? ብለው ሲጠይቁ እኛ አይነ ለአይን ተያየን። መልስ አልነበረንም” አለኝ።

“እኛ ከዲሞክራሲ በፊት መረጋጋት እንዲኖር ነው የምንፈልገው።መረጋጋት ጠፍቶ ሰላም አሰጠባቂ ሆነን መሄድ አንፈለግም። ኢትዮያ እንደ ሶማሌ stateless እንድትሆን አንፈለግም። አሉን” ሲልም ይህ ወንድም፣ ምእራባዉያን ወያኔን የሚደገፉት አማራጭ ስላጡ እንደሆነ አክሎ ገለጸልን።

የተወሰኑት ደግሞ በምእራባዊያን በጣም ከምትነቀፈዋ፣ በተባበሩት መንግስታት ስሟ በመጥፎ ከምትጠራዋ ከኤርትራ ጋር በመሆናቸው ከወዲሆ ተቀባይነታቸውን አጥተዋል። ኮንግረስማን ክሪስ ስሚዝ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሊያቀርቡ የነበረዉን ሕግ፣ ለምን እንደማያቀርቡ ሲጠየቁ፣ አንዳንድ የተቃዋሚ ቡድኖች ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ስላላቸው፣ ኤርትራ ደግሞ አካባቢዉን እያተራመሰች ያለች አገር በመሆኗ እንደተቸገሩና እጆቻቸው እንደተያዙ መግለጻቸዉን መረጃዎች ደርሰውኝ ነበር።

ወያኔዎች አንዴ ቻያና አንዴ ሌላው ጋር እያሉ ደብል ጌም እንደሚጫወቱባቸው ምራባዊያን ያውቃሉ። ግን በተቃዋሚው ጎራ ያለው፣ ከመቃወምና ብሶት ከማሰማት ፖለቲካ ያልተላቀቀ ነው። አማራጭ ሆኖ አልቀረበም። የተበታተነና የተከፋፈለ ነው። ታዲያ እንዴት ይስሙን ?

እንግዲህ እዉነታው ይሄ ነው። እኛ ራሳችንን ንቀን፣ እኛ ለራሳችን ሳናስብ፣ ሌሎች ለምን አላሰቡልንም ብለን መከራከር አንችልም።

በዳያስፖራ ያሉ ሃይላት ከመከፋፈል ወጥተው ተቀናጅተው፣ በስሜትና በሆታ ላይ ሳይሆን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የዉጭ ዲፕሎማሲ ቢያደርጉ፣ በአገር ቤት ያሉ ደርጅቶች ተሰባስበው አንድ አማራጭ ኃይል ቢሆኑ፣ የምእራባዉያን አመለካከት የተለየ ይሆን ነበር።

ለዚህም ነውም ብዙዎቻችን በዉጭ አገር ያሉም በአንድ ላይ ተሰባብሰው ውጤት የሚያመጣ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሰራ አንድ የጋራ ግብረ ሃይል እንዲፈጠሩ ግፊት ስናደረግ የነበረው። እነ ኦባንግ የደብዳቤ ናዳ ይልካሉ በዚህ በኩል፣ ግንቦት ሰባት በዚያ በኩል የሚጽፉትን ይጽፋሉ። የሸንጎን፣ የሽግግር ምክር ቤቱን …የመግለጫ ጋጋታም የምናወቀው ነው። እንደ አል ማሪያም ያሉ ምሁራን በየጊዜው የተለያዩ ትንታኔ ያቀርባሉ። ግን በአዉሮፓም ሆነ በአሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ጠንካራ ሕግ እንዲወጣ ማስደረግ አልቻልንም። መጮህ ብቻ ነው ስራችን። ያ መለወጥ አለበት። ሁሉንም ያሰባሰበ አንድ ጠንካራ የጋራ የዲፕሎማሲ ግብረ ኃይል ያስፈልጋል። አለበለዚ ያፈረንጆች በተናጥል ስንቀሳቀስ “አናንተ ደግሞ ማን ናችሁ ?” ብለው ይስቁብናል እንጂ የምንፈይደው ነገር አይኖርም።

በአገር ቤት ሰማያዊ ፓርቲ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ አሁን ደግሞ “ነጻነት” የሚባል ሌላ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ተመስርቷል። ብዙ ፓርቲዎች አሉ። እነዚህ የአንድነት ሃይሎች መሰባሰብ አለባቸው። ሲሰባሰቡ ሪሶርሳቸዉን በደንብ መጠቀም ይችላሉ። የተማሩ፣ የበሰሉ ሰዎችን ይስባሉ።፡አማራጭ ፕሮግራሞችን መንደፍ የሚችሉ ብቃት ላላቸው ኢትዮጵያዉያንም ቤት ይሆናሉ። ያኔ ስብስቡ በሕዝብ አመኔታ ያገኛል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles