ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ንግግር ሲያደርጉ (ፎቶ ጉዳያችን)
ንቁዎቹ ወጣቶች
ቅዳሜ፣ግንቦት 27/2008 ዓም በኦስሎ ኖርዌይ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከኤርትራ በረሃ፣ ታዋቂው የምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚክስ ምሁር) እና የ”ራዕይ ኢትዮጵያ” (Vision Ethiopia) ሊቀመነበር ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ከአሜሪካ እና የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እህት ወ/ሮ ብዙአየሁ ፅጌ በተገኙበት ልዩ መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር። ዝግጅቱ የኖርዲክ አገሮችን ያካተተ ሲሆን ከስዊድን የመጡ እና ከኖርዌይ ከተሞች ኦስሎ፣በርገን፣ትሮንዳይም እና ስታቫንገር ከስምንት ሰዓታት በላይ የግል መኪናቸውን ነድተው እና በባቡር ተሳፍረው የዝግጅቱ ታዳሚ የሆኑ ነበሩ።በእዚህ ዘገባ አጠናቃሪ ግምት የቆመውን ሳይጨምር ወንበር የያዘ ብቻ ከአምስት መቶ በላይ ታዳሚ በእርግጠኝነት የተመለከተ ሲሆን የተሳታፍውን ቁጥር ባጠቃላይ ከስምንት መቶ በላይ እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚናገሩ አሉ። እዚህ ላይ ግን ተሳታፊው ከግማሽ በላይ በጣም በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው። በወጣቶቹ ላይ የታየው በቁጭት እና ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ያሳዩት ተሳትፎ ታዳሚውን ሁሉ ያስደመመ እና ልዩ ስሜትን የፈጠረ ነው።ከእዚህ በተጨማሪ የሴቶች ተሳትፎ በእያንዳንዱ የመርሃ ግብሩ ሂደት ላይ መታየቱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ንግግራቸውን ሲጀምሩ የመጀመርያ ትኩረታቸውን እንደሳበው ሲገልጡ ”በየትኛውም የዓለም ክፍል ስሄድ እንደ ዛሬው የኖርዌይ ዝግጅት ከፍተኛ የሴቶች ተሳትፎ የታየበት አላጋጠመኝም። በእውነት የኖርዌይን ብቻ ሳይሆን የስካንድንቭያን አገሮች ለሴቶች የሚሰጡትን ትኩረት ‘ሪሊ’ በደንብ የተረዳችሁት እና በተግባር እያሳያችሁ እንደሆነ ነው የምመለከተው።በእዚህም በጣም ተደስቻለሁ” ብለዋል።
በእዚህ ዝግጅት ሶስት ነገሮች ጎልተው ወጥተዋል እነርሱም የፕሮፌሰር ብርሃኑ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ደቡብ አፍሪካ ከነበረችበት የዘር አድልዎ ስርዓት ጋር በማነፃፀር ያቀረቡት ድንቅ ትንተና፣ የፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው የኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ማኅበረሰብ የትግል ሂደት እና ለኢትዮጵያ ያለው ጉልህ ድርሻ ያብራሩበት ንግግር እና በገቢ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር ላይ የነበረው የኅብረተሰቡ እጅግ አስገራሚ ተሳትፎ የሚሉት ናቸው። በእዚህ ዘገባ ላይ በአብዛኛው ለማትኮር የተፈለገው በንግግሮቹ ላይ ነው።
አዳራሹ
መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት አዳራሹ ውስጥ ስገባ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰው ቦታውን ይዟል።በግራ እና በቀኝ በኩል ትልልቅ የቪድዮ መመልከቻ ስክሪን ላይ የዲና አንተነህ ”እጄን ሰጠሁ ተማርኬ” የተሰኘው የኦሮምኛ ሙዚቃ ቅኝት እና ውዝዋዜ አዳራሹን አድምቆታል።ዲና ሁለት እጇን ወደላይ እያጣመረች እያሳየች ማዜሟን ቀጥላለች።ዝግጅቱን በደንብ ለመመልከት የሚመቸኝ ቦታ ላይ ለመሆን ከኃላ ረድፍ ካለው ወንበር ተቀመጥኩ። ቦታው በቀኝ በኩል ከተከፈተው የአዳራሹ በር የሚመጣው ለሰስ ያለ ንፋስ 27 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የደረሰውን የዕለቱን የኦስሎ ሙቀት እንደሚከላከል ገብቶኛል።ወድያው ከጎኔ እድሜው ከ23 የማይበልጠው ኦስሎ የማውቀው ወጣት ከሁለት ሌሎች ወጣቶች ጋር መጣ እና ተቀመጠ።ሰላምታ ከሰጠሁት በኃላ በተገናኘን ቁጥር አንድ ሁለት እያልን የምንቀላለደውን ቀልድ ተጀማመርን።በመካከል ስለ ፕሮፌሰር ብርሃኑ አድናቆቱን ከገለጠልኝ በኃላ በስሜት ሆኖ እንዲህ አለኝ ”ትናንት አርብ እለት ፕሮፌሰርን ኦስሎ ከተማ ውስጥ ከአንድ ሰው ጋር ድንገት አላገኘው መሰለህ?” አለና እንባው በደስታ ቅር እያለ ቀጠለ ” ብታይ እንዴት እንደተደሰትኩ? ሳገኘው ጥምጥም አላልኩበትም? በሕይወቴ የተደሰትኩበት ቀን ነች ትናንት …..ትቀልዳለህ? እኔ በጣም የማደንቀው እና የምወደው ሰው ነው።ይታይህ ስንት የወያኔ ባለስልጣናት ተሸማቀው እየሄዱ እርሱ በነፃነት ከአንድ ሰው ጋር በነፃነት ሲሄድ ….መንገድ ላይ ያገኘው ሁሉ እንዴት እያቀፈ እንደምስመው ብታይ ፈረንጆቹ ገርሟቸው ያዩናል” ወጣቱ ውስጡን ለመግለፅ በተቸገረ ስሜት ፕሮፌሰሩን እንዴት እንዳቀፈው ማቀፍ እንዴት እንደሆነ እኔን እየቸመቀ እያሳየ አወጋኝ። በሃሳቤ ሲያወራኝ በምናቤ ኢትዮጵያውያን እንዲህ በመንገድ ላይ ስናገኘው አቅፈን ሰላም የምንለው መሪ መች እናገኝ ይሆን? እያልኩ እያሰላሰልኩ የሆታ ድምፅ ከታችኛው አዳራሽ ክፍል ተሰማ።በመቀጠል የአዳራሹ ድምፅ ማጉያ አስተጋባ። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ፕሮፌሰር ጌታቸው ወደ አዳራሹ እያመሩ መሆኑ ተነገረ።ወደ በሩ ስመለከት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በቀኝ በኩል ያነገቱትን ቦርሳ እንደያዙ በወጣቶች
”ምናለ ጀግናው ምናለ፣
አገሬን ለሰው አገሬን ለሰው አልሰጥም አለ።”
እያሉ እና በሆታ ታጅበው ወደውስጥ ዘለቁ።ሁለቱም ፕሮፌሰሮች መድረክ ላይ ከወጡ በኃላም ጭብጨባው ጋብ አላለም።ከመቀመጫው የተነሳው ሕዝብ ማጨብጨቡን ቀጠለ።ቀጥሎ የአርበኞች ግንቦት 7 የኖርዌይ ሰብሳቢ ዶ/ር ሙሉ ዓለም መርሃ ግብሩን ለማስተዋወቅ የድምፅ ማጉያውን በእጃቸው በትንሹ እየቆረቆሩ ሁሉም እንዲቀመጡ በምልክት እያሳዩ ካስቀመጡ በኃላ የእንኳን ደህና መጣችሁ አጭር ንግግር አደረጉ።
እያሉ እና በሆታ ታጅበው ወደውስጥ ዘለቁ።ሁለቱም ፕሮፌሰሮች መድረክ ላይ ከወጡ በኃላም ጭብጨባው ጋብ አላለም።ከመቀመጫው የተነሳው ሕዝብ ማጨብጨቡን ቀጠለ።ቀጥሎ የአርበኞች ግንቦት 7 የኖርዌይ ሰብሳቢ ዶ/ር ሙሉ ዓለም መርሃ ግብሩን ለማስተዋወቅ የድምፅ ማጉያውን በእጃቸው በትንሹ እየቆረቆሩ ሁሉም እንዲቀመጡ በምልክት እያሳዩ ካስቀመጡ በኃላ የእንኳን ደህና መጣችሁ አጭር ንግግር አደረጉ።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው በአዳራሽ ውስጥ
የሁለቱ ፕሮፌሰሮች ንግግር
”የወያኔ መንግስት ተናግቷል” ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው
ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ንግግር በፊት ንግግር ያደርጉት የቪዥን ኢትዮጵያ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ሲሆኑ ፕሮፌሰሩ በተለይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ አፅንኦት ሰጥተው በሰፊው አብራርተዋል።በንግግራቸው ላይም ”ወያኔዎች ጠንካራ እንደሆኑ ሊነግሩን ይሞክራሉ ሆኖም ግን የወያኔ መንግስት ተናግቷል” ካሉ በኃላ ለእዚህም የምጣኔ ሃብቱ ድቀት እና ድርቁን ብቻ ብንመለከት ወዴትም የሚያስኬድ ደረጃ ላይ አለመሆናቸውን አብራርተዋል። የማኅበራዊ ሳይንስ እንደሚያሳየው ከ20% በታች ውክልና ያለው ኃይል ስልጣን ላይ ከወጣ በስልጣን ላይ ለመቆየት ያለው ብቸኛ አማራጭ አምባገነን መሆን ብቻ መሆኑ ያስረዱት ፕሮፌሰር ጌታቸው ወያኔ የትግራይን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን እንደሚያምኑ እና በእዚህ የማኅበራዊ ሳይንስ ስሌት እንሄድ ብልን እንወክለዋለን የሚሉት ከ7% እንደማይበልጥ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንመስርት ቢሉ በብዙሃን ድምፅ ስለሚሸነፉ ፈፅሞ ሊያደርጉት አይችሉም በማለት አብራርተዋል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው በመቀጠል የኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ማኅበረሰብን የመብት ትግል ትልቅ ዋጋ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበው በትናንትናው እለት በእነ አቶ በቀለ ገርባ ላይ ፍርድ ቤት በባዶ እግር የመቅረብ ሁኔታ የስርዓቱ የወረደ አስተሳሰብ መገለጫ መሆኑን እና በየትኛውም ዓለም የእዚህ አይነት ድርጊት አለማየታቸውን እና ኢራቅ ላይ ብቻ አንድ ጊዜ በሳዳም ሁሴን ላይ ያውም በግማሽ ልብስ እንዲታይ ተደርጎ እርሱም ከዓለም ዙርያ ከፍተኛ ወቀሳ ማስከተሉን አብራርተዋል። የወቅቱ ሁኔታ ሲገመግሙ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ”ወቅቱ ነባራዊ የትግል ሁኔታዎች ሁሉ የትሟሉበት” ነው ብለዋል።በኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ማኅበረሰብ ትግል በተመለከተ የእዛኑ ቀን ጧት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ጋር ሆነው ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር መሪ አቶ ሌንጮ ጋር ኦስሎ ላይ ሲወያዩ እንደነበር ገልጠው በውይይታቸው ላይ አቶ ሌንጮ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያዊነት የመቀበል ጉዳይ ምንም ጥያቄ እንደሌለው እና ይህም ለእራሱ ለኦሮሞ ሕዝብ ሲባል ድርጅቱ አበክሮ እንደሚሰራበት እንዳስረዷቸው ገልጠዋል።
”የአገራችንን ችግር በስደት አናመልጠውም።ማንም ፈረንጅ ከእዚህ ችግር አያወጣንም።አገራችንን በክብር መረከብ አለብን።” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
ከፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው በመቀጠል መድረኩን የያዙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ነበሩ።መድረኩን እና አድማጫቸውን ለሰዓታት በጉጉት ወጥረው የመያዙ አቅም ያላቸው ድምፀ ጎርናናው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ንግግራቸውን የጀመሩት ወደ ኦስሎ ከመጡ በኃላ ወዲያው ያደረጉት ከኖርዌይ ባለስልጣናት ጋር በኖርዌይ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ መነጋገራቸውን እና ለኖርዌዮች ሊረዱት ይችላሉ ባሉት መንገድ ስለ ኢትዮጵያ ችግር ያስረዱበትን መንገድ አብራርተዋል።በመቀጠል የንግግራቸው ዋና ፍሬ ሃሳብ ስለነበረው የኢትይጵያን የአሁኑን የወያኔ ስርዓት ከፈረሰው የደቡብ አፍሪካ የዘር-መድሎ ስርዓት ጋር ያለውን ተመሳሳይነት፣የባሰ የሆነበትን መንገድ እና የትግል ስልቶቹን ዝምድና በሚገባ አብራርተዋል።
የደቡብ አፍሪካ የፈረሰው የዘር መድሎ ሥርዓት እና የወያኔ ስርዓት አንድነት እና ልዩነት
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የደቡብ አፍሪካን የዘር መድሎ ስርዓት የሚመሳሰልባቸውን ሁለቱ የስልት መንገዶች እንዲህ አብራርተዋል።
1ኛ/ የስነ-ልብና ጦርነት በብዙሃኑ ላይ ማድረግ
ነጮች ጥቂቶች ነበሩ።ታድያ እንዴት ብዙሃኑን ጥቁሮች እረግጠው ገዙ? ብለው ከጠየቁ በኃላ መልሱ የነጮች በጥቁሮች ላይ ያደረጉት የስነ-ልቦና ጦርነት አንዱ መሆኑን ሲያብራሩ ጥቁሮችን መጀመርያ ያደረጉት ጥቁሮች እኔ ለነፃነት ብቁ ነኝ እንዴ ? ብለው እራሳቸውን እንዲጠይቁ እና አለመሆናቸውን እንዲያስቡ የተደረገ የስነ-ልቦና ተፅኖ መኖሩን አብራርተው በተመሳሳይ ደረጃ ወያኔ በሕዝቡ ላይ ለነፃነት ብቁ እንዳልሆነ የረቀቀ የስነ-ልቦና ዘመቻ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።
2ኛ/ በጎሳ መከፋፈል
በደቡብ አፍሪካ ዘረኛው መንግስት አንዱ የተጠቀመበት መንገድ እራሳቸው ጥቁሮችን በጎሳ መከፋፈል እርስ በርስ እንዲጋጩ ማድረግ ነበር።በተመሳሳይ መንገድ ወያኔም እየሰራበት እንደሚገኝ ገልጠው የደቡብ አፍሪካ ትግልም እነኝህን ችግሮች አስታኮ ትግሉን በሶስት መንገዶች መቅረፁን አብራርተዋል።
የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ሶስቱ የትግል መንገዶች
ፕሮፌሰር ብርሃኑ የደቡብ አፍሪካ ትግል የተከተላቸው መንገዶች ሶስት እንደነበሩ አብራርተዋል። እነርሱም:
- ሕዝባዊ እምቢተኝነት በአገር ውስጥ፣
- ሕዝባዊ እምቢተኝነት በውጭ አገሮች እና
- በማንዴላ የሚመራው የመሬት ላይ የትጥቅ ትግል የሚሉ ነበሩ።
የደቡብ አፍሪካ ትግል ከላይ የተጠቀሱትን መንገዶች ይያዝ እንጂ የአገር ውስጡ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ግቦቹ ሁለት ነበሩ። እነርሱም መጪዋ ደቡብ አፍሪካ በዜግነት ላይ የተመሰረተች ትሆናለች የሚል እና አንድ ሰው አንድ ድምፅ ይኖረዋል የሚሉ ነበሩ። የውጭው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በተለይ አለምን ያነቃነቀ እና ዋና ትኩረቱ በዓለም ላይ ያሉ ታላላቅ ኩባንያዎች በደቡብ አፍሪካ ኢንቨስት በማድረግ የዘር-መድሎ ስርዓቱን እንዳይደግፉ ማድረግ ነበር። ሆኖም ግን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይህንን ሁሉ በደል እያዩ ደቡብ አፍሪካ ላይ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ያፈሱ ነበር። ሶስተኛው የትጥቅ ትግሉ ከጎረቤት አገሮች በመነሳት የደቡብ አፍሪካን ዘረኛ መንግስት ሰላም የመንሳት አላማ ነበረው። ይህ ትግል በተለይ በደፈጣ ውግያ የደቡብ አፍሪካውን ስርዓት ሰላም የነሳ እና ከጎረቤት አገራቱ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባበት ነበር።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ የሶስቱን የደቡብ አፍሪካ የትግል ስልት ካነሱ በኃላ ከሶስቱ የትኛው የተሻለ ስልት ነበር? የትኛውስ የበለጠ አስተዋፅኦ አደረገ? በማለት ከጠየቁ በኃላ መልሱን ሲመልሱ አንዳቸው ከአንዳቸው ይበልጣሉም ያንሳሉም ማለት እንደማይቻል አብራሩ። ሶስቱም እርስ በርስ ተደጋግፈው ነው ውጤት ያመጡት።በውጭ ያለውን ድጋፍ በማስቆም የአገር ውስጡን እምቢተኝነት መደገፍ ተችሏል።በትጥቅ ትግሉ እረፍት ነሺነትም ለድል መቃረብ ተችሏል በማለት የደቡብ አፍሪካን ሁኔታ ከገለጡ በኃላ ከእኛ ጋር ያለውን ልዩነት እና አንድነት እንዲህ አብራርተዋል።
የወያኔ ስርዓት እና የደቡብ አፍሪካ የዘር መድሎ ስርዓት ተመሳሳይነት
የወያኔ ስርዓት የደቡብ አፍሪካው ስርዓት ያለው አንድነት ሁለቱም መሰረታቸው በዘር ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣በምጣኔ ሀብት፣ፖለቲካውን እና ያዩትን ሁሉ ለመቀራመት ያላቸው ፍላጎት እና በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግድያ ፣እስር በዋነኛነት ይገለጣል።በእዚህ ተመሳሳይ ለትግሉ በእኛ በአርበኞች ግንቦት 7 በኩል የቀየስነው የትግል ስልትም ሶስቱን ማለትም ሕዝባዊ እምቢተኝነት በአገር ውስጥ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በውጭ አገር እና መሬት ላይ የሚደረግ የትጥቅ ትግል የሚሉት ናቸው። ሶስቱም አንዳቸው ከአንዳቸው ተደጋግፈው የሚሄዱ መሆናቸውን በሰፊው አብራርተዋል።
የደቡብ አፍሪካ የዘር መድሎ ስርዓት ከወያኔ የተሻለባቸው መንገዶች
ፕሮፌሰር ብርሃኑ የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ ስርዓት ከወያኔ የሚለይባቸው እና የተሻለባቸው መንገዶችን እንደሚከተለው አብራርተዋል።
ሀ/ በደቡብ አፍሪካ ስርዓቱ አፓርታይድን በሕግነት አውጥቶ ስለ አወጣው ሕግ ይከራከራል እንጂ ያወጣውን ሕግ ሰርዞ ወይንም የሌለ ሕግ ትጠቅሶ አይከራከርም ነበር። በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ በሕግ ተደንግጎ ነበር። ስለሆነም ስርዓቱ የቆመው ላወጣው ሕግ ነበር።ወያኔ ግን ያወጣውን ህገ መንግስት በመጣስ ሕግ የሚያሰቃይ ነው
ለ/ የደቡብ አፍሪካ ስርዓት ስለ ውደፊቷ ደቡብ አፍሪካ ይወያይ ነበር።ቢያንስ ወደፊት የጎደለውን ማሟላት ያለባት ደቡብ አፍሪካ መኖር አለባት በማለት በእስር ቤት ከሚገኙት ማንዴላ ጋር ማቆምያ የሌለው ግን እስር ቤት እየሄደ ይወያይ ነበር።ይህ ማለት ስለተባበረች ደቡብ አፍሪካ መጨነቅ ነበር። የወያኔን ስርዓት ብትመለከቱ ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ የሚባል ራእይ የላቸውም።ስለመተባበር፣ህብረት ወዘተ ምንም የማይጨነቁ ናቸው።
ሐ/ በደቡብ አፍሪካ የፍትህ ስርዓቱ ላይ መንግስት እጁን አያስገባም። ይልቁንም መንግስት ብዙ ጊዜ የተረታባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።ይህ ብቻ አይደለም የአፓርታይድ ስርዓት ከበርካታ የሰራተኛ ማኅበራት ጋር የገጠሙት አመፆች የሰራተኛ ማኅበራቱ የነበረውን የሕግ ስርዓት ተንተርሰው ስለሚንቀሳቀሱ ነው። የወያኔ ስርዓት ስትመለከቱ የፍትህ ስርዓቱን በሙሉ ደምስሶ በእራሱ የያዘ እና መቀለጃ ያደረገ ነው።ተመልከቱ! ከደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓትም ምን ያህል የከፋ ስርዓት ላይ እንደሆንን።
መ/ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ስንመለከት በአፓርታይድ ዘመን ዓለም ድምፁን ያሰማው ለምሳሌ ትልቁ ከሚባለው የሻርፕቪል እልቂት ላይ የሞተው የሰው ቁጥር 64 ሰው ነበር።በእዚህ ብዙ አገሮች ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቆሙ ሆነዋል።እኛ ጋር በ1997 ዓም ብቻ እራሳቸው እንዳመኑት 197 ሰው ሲገደል ዓለም ለእኛ አይጮህም።ጋምቤላ ከ400 ሰው በላይ ሲያልቅ ዓለም አይናገረም። በቅርቡ በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ ከ500 በላይ ሲገደሉ ከ30ሺህ በላይ እስር ቤት ስታጎሩ ዓለም እንዳልሰማ ዝም ብሏል። ካሉ በኃላ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በመቀጠል እንዲህ አሉ:
”ስለሆነም አሁን ዓለም ተቀይሯል።ማንም ፈረንጅ ለእኛ ችግር ከእኛ በላይ ማንም መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።ነፃነት አጥተህ መብላት መጠጣትህ ሰው አያደርግህም።” ብለዋል።በመጨረሻም ስለ አርበኞች ግንቦት 7 መጪ የትግል ሂደት ሲያስረዱ ይህንን ብለዋል:
መጪው ትግላችን ትግሉን በድንበር አካባቢ ማቆየት ሳይሆን ወያኔ በር ድረስ ማድረስ ነው።እዚህም አብዛኛውን የወያኔ ኃይል ለትግሉ ማሰለፍ ነው።ይህ ትግል ወያኔዎችን እራሳቸውን አሳምኖ ለሕዝብ እንዲቆሙ ማድረግ መቻል አለበት። እናንተም ስታገኙዋቸው ደግግማችሁ ጥቂቶች ስለሚሰሩት አስረዷቸው። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር እኛ ፀብ የለንም።የእኛ አላማ እንደ ወያኔ ተቋማትን ማፍረስ አይደለም። ያሉትን ጠብቀን የተሻሉ መገንባት ነው።እኛ ከድል በኃላ አሁን ያለውን ሰራዊት የምናፈርስበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።
የስብሰባው ተሳታፊዎች በከፊል
ከሁለት ሚልዮን ብር በላይ
ከፕሮፌሰር በኃላ ንግግር በኃላ አንድ ድንገተኛ እና የሁሉንም ስሜት የገዛ ጉዳይ ተፈጠረ።ከመድረክ መሪው አንድ ”ሰርፕራይዝ” እንዳለ እና እርሱም እራሱ እንዳላወቀው ተናገረ። በመቀጠል አንድ ወንድ እና አንድ ፊታቸው በግልጥ የማይታይ ሴት ወደ መድረኩ ወጡ እና ለፕሮፌሰር ሰላምታ አቀረቡ። በመቀጠል ፊታቸውን ሲያዞሩ ማንነታቸው ታወቀ። የአንዳርጋቸው ፅጌ እህት ወ/ሮ ብዙአየሁ ፅጌ ከለንደን ሌሊቱን ተነስተው ኦስሎ ገብተው ኖሯል። ሁሉም ተነስቶ በእረጅም ጭብጨባ ተቀበላቸው። ብዙዎች ወ/ሮ ብዙአየሁን ሲመለከቱ ፊታቸው በእንባ ታጠበ።መድረክ ላይ ፕሮፌሰር ብርሃኑን ጨምሮ የስሜት መለዋወጥ ይታይ ነበር።በተለይ ወ/ሮ ብዙአየሁ ስለ አቶ አንዳርጋቸው ያቀረቡት ግጥም ስሜት የሚነካ ነበር።
በመቀጠል በአቶ አምሳል እና አቶ ሚልዮን አስተባባሪነት የቀጠለው የጨረታ እና የገቢ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር ተደረገ። ስለ እዚህኛው መርሃ ግብር የተገኘውን ገንዘብ ብቻ መጥቀሱ ብዙ ይናገራል። የተገኘው ገንዘብ በኖርዌይ 800,162 ክሮነር ወይንም ከ97ሺህ ዶላር በላይ ወይንም ከ2 ሚልዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ መሆኑ በራሱ ብዙ ይናገራል።
ለጨረታ የቀረበው ስዕል
ባጠቃላይ ግንቦት 27/2008 ዓም የተደረገው የኦስሎው አርበኞች ግንቦት 7 ዝግጅት በሁሉም መልኩ እጅግ የተዋጣለት ነበር። ይህ ሲባል በአገር ቤት የሚኖረውን ሕዝብ ነፃነት ማፈን የለመደ ወያኔ የስብሰባውን አዳራሽ ለማስከልከል የከሰረ ሙከራ ማድረጋቸው ከመድረክ ተነግሯል።በተለይ የእዚህ አይነቱ ሁኔታ የህዝቡን ቁጣ በእጅጉ አንሮታል።በዝግጅቱ መጨረሻ ላይ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ፣የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ እና በኤርትራ ስላለው ሁኔታ ከአስራ ሁለት በላይ ጥያቄዎች ተጠይቀው በፕሮፌሰር ብርሃኑ ምላሾች ተሰጥተዋል።ፕሮፌሰሩ በመጨረሻ የቀረበላቸው ጥያቄ ”አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ለማስፈታት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር የሚደረግ ግንኙነት አለ ወይ?” የሚል ሲሆን ፕሮፌሰር አጭር እና ግልፅ መልስ ነበር የሰጡት። ” የለም! አንዳርጋቸውን ሰልፍ አያስፈታውም ፈረንጅም አይደለም! አንዳርጋቸውን የምናስፈታው እኛው ነን!” ነበር ያሉት።በእዚህ ንግግራቸው የአቶ አንዳርጋቸው ባለቤት ወ/ሮ ብዙአየሁ ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ አዳራሽ ያለውን ሕዝብ እንዲነሳ አድርገውታል። የመጨረሻው የእዚህ መርሃ ግብር ሥራ የነበረው የተለያዩ ሃይማኖቶች ፀሎት እንዲያደርጉ ማድረግ ነበር። በእዚህ መሰረት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣የፕሮቴስታንት እና የሙስሊም የሃይማኖት አባቶች በእየተራ ፀሎት እንዲያደርጉ ወደ መድረኩ እንዲመጡ መጋበዛቸው በመርሃ ግብር መሪው ተገልጧል።