ኢሳት ዜና :-~ በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ ከሚከበረውን የፋሲካ በአል ጋር ተያይዞ የቅቤ እና የዶሮ ዋጋ የተጋነነ ጭማሪ ሲያሳዩ፣ በብዙ የክልል ከተሞች ደግሞ ዘይት እስከናካቴው ጠፍቷል። በአማራ ክልለ በሚገኙ ከተሞች ደግሞ፣ ከዘይት በላይ ውሃ ማግኘትም እየቸገረ ነው። ዛሬ በአዲስአበባ ሳሪስ እና ሾላ ገበያዎችን የቃኘው ዘጋቢያችን እንደገለጸው፣ የምግብ ቅቤ የችርቻሮ ዋጋ በኪሎግራም ከ250 እስከ 300 ብር በመሸጥ ላይ ነው ። ከበአሉ በፊት የቅቤ ዋጋ በኪሎግራም ከ200 ብር የዘለለ አልነበረም ብሎአል። የአንድ አበሻ ዶሮ ዋጋ ከ350 እስከ 400 ብር እየተጠየቀ ሲሆን፣ እምብዛም በኢትዮጵያ ባይለመድም የተዘጋጁ የአበሻ ዶሮዎች በሱፐርማርኬቶች ከብር 120 እስከ 150 በመሸጥ ላይ ናቸው። እንዲሁም ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ20 እስከ 25፣ ነጭ ሽንኩርት ከ75 እስከ 85 ፣ ቃሪያ በኪሎ ከ30 እስከ 50 ፣ ቲማቲም በኪሎ ከ18 እስከ 20 ፣ አንድ እንቁላል ከብር 3 ከ70 እስከ 3 ከ 85 ሳንቲም በመሸጥ ላይ ነው።በሾላ የበግ ገበያ ከብር 2 ሺ እስከ 3 ሺ 500 አነስተኛና መካከለኛ በግ ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ ከፍ ያለ ሙክት እስከ 7 ሺ ብር ዋጋ እየተጠየቀበት ነው። ይህም ሆኖ የዛሬው የበግ ዋጋ አንጻራዊ በሆነ መልኩ መረጋጋት እንደታዬበት ዘጋቢያችን ገልጿል።
~ የፌዴራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቀድሞ የጉምሩክ ኃላፊ በነበሩት አንደኛ ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታውና ግብረ አበሮቻቸው ላይ ከተከሰሱባቸው አስራ ሰባት ክሶች በተወሰኑት የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፎባቸዋል። 1ኛ ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር፣ 2ኛው ተከሳሽ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ የባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ 3ኛው ተከሳሽ አቶ በላቸው በየነ የኦዲት ዳይሬክተር፣ እንዲሁም አቶ ማሞ አብዲ የታክስ አማካሪ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባል እና ጸሃፊ ሆነው ስርተዋል።
~ ባለፈው የካቲት ወር በዱባይ የተደረገውን የምግብ ኤግዚቢሽን ለመካፈል ያቀኑ 6 የኢትዮጵያ ነጋዴዎች፣ የተበላሸ ስጋ አቅርበዋል በሚል ለሁለት ወራት ያክል ከአገር እንዳይወጡ ታግተውና ሁለቱ ነጋዴዎች ደግሞ በተደጋጋሚ ሲታሰሩ መቆየታቸውን ተከትሎ ቤተሰቦቻቸው ጭንቅት ውስጥ መግባታቸውን በተደጋጋሚ ከገለጹ በሁዋላ፣በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስና በኢህአዴግ መንግስት መካከል በተደረገ ስምምነት፣ ክሳቸው መነሳቱ ወደ አገራቸው መሄድ እንደሚችሉ እንደተፈቀደላቸው ታውቋል። ነጋዴዎቹ ከዚህ ቀደም በአለማቀፍ የንግድ ስርአት ውስጥ ባልተለመደ መልኩ በቁጥጥር ስር መዋላቸው፣ የመነጋጋሪያ አጀንዳ ሆኖ ከርሟል።እና ሌሎችም ዜናዎች …