Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የሲቪሉ ሰራተኛ ኑሮ በሁለቱ ዘመናት

$
0
0

ከ25 ዓመታት በፊት አንድ የኮሌጅ ዲፕሎማ የነበረው አስተማሪ ሲቀጠር የመነሻ ደመወዙ 347 ብር ነበር። ይህን ገቢ በወቅቱ ከነበረው የዶላር ምንዛሬ አንጻር ስናየው 173.5 ዶላር ይመዝን ነበር። ይህ አስተማሪ ገና ሲቀጠር የቀን ገቢው 5.8 ዶላር ነበር ማለት ነው። ከፍ ያለ ነበር። ከ25 አመት “እድገት” በሁዋላ በህወሃት ኢህዓዴግ ዘመን አንድ የኮሌጅ አስተማሪ ዲፕሎማውን ይዞ ሲቀጠር 1663 ብር ቢከፈለው አሁን ባለው ምንዛሬ ሲታይ 77.3 ዶላር ያገኛል። ይህ ማለት የቀን ገቢው በዶላር 2.57 ሳንቲም ነው ማለት ነው። ይህ ማለት የደርግ ጊዜው አስተማሪ ደመወዝ ከህወሃት ኢህዓዴግ ጊዜ አስተማሪው ደመወዝ  ከሁለት እጥፍ በላይ ይበልጣል ማለት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የድህነት ወለል የሚባለው ሁለት ዶላር አካባቢ ሲሆን ይህ በህወሃት ኢሃዴግ ዘመን የኮሌጅ ዲፕሎማ የያዘው አስተማሪ በዚያው በድህነት ወለል አካባቢ ነው ማለት ነው። ነገር ግን በደርጉ ጊዜ ከሃያ ዓምስት ዓመት በፊት የነበረው ዲፕሎማ አስተማሪ  በቀን የሚያገኘው ገቢ ወደ 6 ዶላር የሚጠጋ ሲሆን እጅግ በተሻለ ህይወት ውስጥ የነበረ በዓለም አቀፍ የገቢ መለኪያም የተሻለ ገቢ የነበረው ነበረ።

በአሁኑ ሰዓት አንድ የሁለተኛ ደረጃ አስተማሪ ሲቀጠር 2197 ብር የሚያገኝ ሲሆን ይህ ማለት 102 ዶላር ማለት ነው። ይህ መምህር  በቀን 3.40 ሳንቲም የሚያገኝ ሲሆን በደርግ ጊዜ ዲፕሎማው ወደ 6 ዶላር የሚጠጋ በቀን ያገኝ ስለነበር በደርጉ ጊዜ የነበረ ያ ጀማሪ የዲፕሎማ መምህር የዛሬውን የዲግሪውን መምህር ክፍያ በጅጉ ይበልጠዋል። በዚህ ቀላል መንገድም ሆነ በፈለገው የኢኮኖሚክ  ሞዴል ብናሰላው በህወሃት ኢህአዴግ ጊዜ ያለው ሲቪል ሰራተኛ ገቢ ከደርጉ ጊዜ መምህር በጅጉ ወርዶ እናያለን።  በደርግ ጊዜ አንድ የሁለተኛ ደረጃ አስተማሪ ሲቀጠር የቀን ገቢው ወደ ዘጠኝ ዶላር የሚጠጋ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የሚቀጠረው መምህር 3.40 ሳንቲም ብቻ በመሆኑ ልዮነቱን ማየት ይቻላል። የነዚህን የሁለት ዘመናት መምህራን ለማወዳደር አንዱ ሌላው ነገር ደግሞ የግሽበትን (inflation) ጉዳይ አንስተን ነው። በደርግ ጊዜ ያ 347 ብር ያገኝ የነበረ መምህር አንድ ዳቦ በአስር ሳንቲም ይገዛ ነበር፣ አንድ እንቁላል በአስር ሳንቲም ይገዛ ነበር። አሁን 1663 ብር የሚያገኘው ደግሞ አንድ ዳቦ በአማካይ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ቢገዛ አንድ እንቁላል ሶስት ብር ይገዛል። በሃያ አምስት ዓመታት እንቁላል የ3000% ጭማሪ ሲያሳይ ዳቦ በ1500% ጨምሯል።

የመምህሩ ገቢ ደግሞ የዋጋውን ግሽበት የሚፎካከር ሆኖ አያድግም። ደመወዝ ደግሞ አራት መቶ ፐርሰንት ገደማ ብቻ ነው ያደገው። ለናሙና በጠቀስናቸው እንቁላልና ዳቦ የዋጋ ጭማሪ ጋር የደመወዙ ጭማሪ ሲወዳደር ከፍተኛ ክፍተት (gap) የሚያሳይ ሲሆን ይህ ክፍተት ነው የመምህሩን ትዳር የማሸነፍ አቅም መድከም የሚያሳየው። ዳቦና ደመወዝ ሲወዳደሩ ዳቦ በአንድ ሺህ ፐርሰንት ቀድሟል። እንቁላልና ደመወዝ ሲወዳደሩ እንቁላል ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ፐርሰንት በላይ ቀድሞ ሄዷል። እናም የዛሬው መምህር ቁርሱን እንቁላል በዳቦ ለመብላት ይሄን ያህል ደክሟል ማለት ሲሆን በአንጻሩ የደርጉ ጊዜ መምህር በየቀኑ ያለ አሳብ መመገብ ይችላል። የደርጉ ጊዜ መምህራን በተለይ በገጠሩ አካባቢ ህብረተሰቡ ቤት ይሰጣቸው ስለነበር የቤት ኪራይ አያስቡም። ከተማም ቢሆን የቤት ኪራይ ኑሯቸውን የሚፈታተን ባለመሆኑ ከቁም ነገር አይቆጥሩትም ነበር። የህወሃት ኢሃዴግ ጊዜ አስተማሪ በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚኖረው ኑሮ ምን ያህል እንደሚከብደው መገመት አያዳግትም። በደርጉ ጊዜ የነበሩ መምህራን ደመወዛቸው ከኑሮው ጋር ከዓለም አቀፍ የድህነት ወለል አንጻር ከፍ ያሉ ስለነበሩ ለቤተሰብ አምሳም፣ መቶም ብር ከዚያም በላይ ተቆራጭ አድርገው ይጦሩ ነበር። የህወሃት ኢሃዴግ ጊዜ አስተማሪ ለቤተሰቡ ተቆራጭ አድርጎ መርዳቱ ቀርቶ እሱ ራሱን ችሎ መኖር ከብዶት ይታያል። አሁን የመምህሩን ኑሮ ከደርግና ከአሁኑ ጋር እያወዳደርኩ የምገልጸው ለናሙና እንጂ አጠቃላይ የሲቪል ሰራተኛው ኑሮ በዚህ ችግር የሚገለጽ ነው። የኢትዮጵያ ሲቪል ሰራተኛ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በዚህ መንግስት በጣም የተጎዳና ሲታለል የኖረ ነው። ያሳዝናል። ኑሮ እንዲህ ቁልቁል ሲሆን ገቢ እንዲህ ቁልቁል ሲሆን … እውነተኛ ፓርላማ ቢኖር ይህ ጉዳይ ከባድ አገራዊ ጉዳይ ሆኖ ክርክር ሊደረግበት መፍትሄ ሊሰጠው ይገባ ነበር።

እዚህ ጋር አንድ የሚነሳ ነገር ይኖራል። የመምህሩ ደመወዝ ከደርግ ጊዜው ጋር ሲነጻጸር በአሃዝ ጨምሯል። ነገር ግን በዶላር ሲሰላ ደግሞ እየቀነሰ መጥቷል፣ ከግሽበቱ ጋር ሲሰላ ደግሞ ከዛሬ ሃያ አምስት አመት ከነበረው ጋር ሲታይ አስደንጋጭ ለውጥ አለ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ልንል እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጀ የኢትዮጵያ መንግስት ደመወዝ የሚጨምርበትን ስልት ማወቅ አለብን። የኢትዮጵያ መንግስት ደመወዝ የሚጨምረው አገሪቱ ስላደገች አይደለም። ጭማሪው ሃገሪቱ የተሻለ አምርታ ያ ምርት ወደታች መንቆርቆር ስለጀመረ አይደለም። ጭማሪው የምርት (GDP) መጨመር ያመጣው ሳይሆን መንግስት የሆነ ዘመን ላይ የህዝቡን የተቃውሞ ስሜት ያይና ይህንን ተቃውሞ የሚያበርድበትን መንገድ ያስባል። እናም ለደመወዝ ጭማሪው ሲል ብቻ ገንዘብ በገፍ ያትማል። በመሰረቱ የአንድ ሃገር የገንዘብ ህትመት መጠን የሚወሰነው በሃገሪቱ አጠቃላይ ምርት (GDP) መጠን ነው። ገንዝብ ማለትም የአንድን ሃገር ጠቅላላ ምርት ወይም  GDPን   የምናካፍልበት መሳሪያ ነው እንጂ በራሱ ወረቀት ነው። መንግስት ለዚህ ብዙ ግድ የለውም። ታዲያ መንግስት ገንዘብ በገፍ ያትምና ለጊዜው ለሰራተኛው ከፍ ያለ ቁጥር በማሳየት የሲቪሉን ሰራተኛ አፍ ለመያዝ ይሞክራል።  ነገር ግን የቁጥሩ ጭማሪ እድገትና ብዙ ምርት ገፍቶት የመጣ ባለመሆኑ መንግስት ደመወዝ በጨመረ በማግስቱ ሁሉ ነገር ይጨምራል። ኑሮ ውድነቱ ሰማይ ይደርሳል። ለምን ይሄ ሆነ ስንል ከፍ ሲል እንዳልነው ጭማሪው በህትመት ላይ ያተኮረ እንጂ የሃገር እድገት ውጤት ባለመሆኑ ነው። የተመረተው ምርት በሃገሪቱ ከታተመው ገንዘብ ጋር ስለማይመጣጠን ብሮች ይጋሽባሉ። ዋጋ ያጣሉ ማለት ነው።

ስለዚህ የኢትዮጵያ የሲቪል ሰራተኛውን ደመወዝ ጉዳይ ስናይ የሰራተኛው ሪል ገቢ አየቀነሰ ይሄዳል እንጂ እየጨመረ አይሄድም። የጨመረው ከላይ የምናየው ቁጥሩ ሲሆን ከግሽበት አንጻር ሲሰላ ግን ከደርጉ ጊዜ መምህር የአሁኑ መምህር ገቢ በጣም ቀንሷል። እንዲህ እየሆነ ነው ላለፉት ሃያ አምስት አመታት የኖረው። ህወሃት ኢሃዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ደመወዝ ይጨመራል ነገር ግን ደመወዝ በተጨመረ ቁጥር የሰራተኛው ኑሮም ከአምናው ዘንድሮ እያቃተው የመጣበት ምስጢር መንግስት ቁጥር እያሳየ አንደኛ ገቢው በዶላር ሲሰላ እየወረደ ይሄዳል ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ ደግሞ ጭማሪው እድገት የገፋው ባለመሆኑ ከግሽበቱ ጋር ተፎካክሮ ሊቆም አልቻለም። አንዱ የምርት ውጤት ከህዝብ ብዛት ጋር ሳይጣጣም ቀርቶ የመጣው ችግር ሲሆን ሌላው ችግር ደግሞ ያለችውን ሃብት ወደ አንድ አቅጣጫ የማዛወር ስራ እየተሰራ ስለሆነ ነው። መንግስት ያለችውን ምርት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊያከፋፍል ቢችል አገሪቱ ይህን ያህል የሚያመረቃ እድገት ስላላሳየች አጥጋቢ ደመወዝ ባይገኝም ከደርግ ጊዜ ግን ሊቀንስ አይገባውም ነበር። ኢትዮጵያ በእርዳታ መቀበል ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ቀዳሚ ናት። በአሁኑ ሰዓትም የመንግስትን ባጀት ከ  50-60%  የሚደርሰውን የሚሸፍነው ከተባበረችው አሜሪካ፣ ከአወሮፓ ህብረትና ከሌሎች ለጋሾች በሚገኝ ርዳታ ነው። ኢትዮጵያ በዓጼ ምኒሊክ ዘመን ራሷን የቻለች አገር የነበረች ሲሆን በአጼ ሃይለስላሴ ዘመንም የተሻለች የተከበረች አገር ነበረች። በደርግ ጊዜ በእርዳታ ላይ መደገፋችን ከፍ ብሎ የታየበት ዘመን ሲሆን ከእርዳታ የሚገኘው የመንግስት ባጀት ሽፋን ግን ዝቅተኛ ነበር። ደርግ በህይወት ዘመኑ ያገኘውን ርዳታ የአሁኑ መንግስት በአንድ አመት ጊዜ አግኝቶታል። በዚህ መንግስት ግን ከፍ ሲል እንደገለጽነው ከግማሽ አካላችን በላይ በርዳታ ላይ የተደገፍን ሲሆን ይህ ርዳታ ቢያቆም የሃገሪቱ መንግስት ሊፈታ ይችላል።

ወደ ስራተኛው ደመወዝ እንመለስና ያለችውን ሃብትና እርዳታ በተገቢው መንገድ ስለማንካፈል  ከደርጉ ጊዜ ሰራተኞች ኑሮ ያሁኑ ከእጥፍ በላይ ወድቋል:: ለዚህም ሌላው ምክንያት ደግሞ ለሰራተኛው የተወሰነ ቁጥር እያሳዩ በዘዴ የሃብት ዘረፋ እየተደረገ ስለሆነ ነው። ሲቪል ሰራተኛው በየዓመቱ እየደከመ የሚሄድበት ምስጢርም ከሰራተኛው ጉልበት ላይ እየቀነሱ የነ ኤፈርትን ሃብት እያደለቡ ስለሆነ ነው። ሲስተማቲክ የሃብት ዝውውር ይባላል ይህ አይነቱ ዘዴ። የህወሃት ካምፓኒዎች በጣም እያደጉ ሃብት እየጨመሩ ሲሄዱ ሰራተኛው ትንሽ የቁጥር ጨዋታ እያየ ነገር ግን ከአምናው ዘንድሮ ትዳር የማሸነፍ አቅሙ እየወረደ ያለው በዘዴ የጉልበት ዋጋ ዝውውር እየተደረገ ስለሆነ ነውና ሲቪል ሰራተኛው ለመብቱ ሊታገል ይገባዋል።

ዋናው ነገር መንግስት አስር ጊዜ በኢኮኖሚ አደግን እያለ የሚለው ነግረን ነገር ተጽእኖው በሲቪሉ ሰራተኛ ላይ አይታይም።  አይታይም ብቻ ሳይሆን ሰራተኛው በዘዴ እየተዘረፈ ድህነት እየጨመረ ነው የመጣው።ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ በተመለከተ በሌላው ዓለም ባልተለመደ ሁኔታ በሁለት ጎራዎች ከፍተኛ ክርክር ይታያል። ክርክሩ ኢትዮጵያ በያዘችው የእድገት አቅጣጫ ሳይንስ ላይ ሳይሆን እድገት በኢትዮጵያ አለ የለም በሚል ነው። ለዚህ ነው በሌላው  ዓለም የተለመደ ክርክር አይደለም የሚያስብለን። መንግስትና ደጋፊዎቹ ሽንጣቸውን ገትረው ባለፉት ሃያ አመታት በተለይም ባለፉት አስር አመትታ ከፍተኛ እድገት አሳይተናል፣ እድገቱ ደግሞ በፍጥነቱ ከዓለም ከፍተኛ ደረጃ ይዟል፣ ከአፍሪካ አንደኛ ነን እነ ጋና፣ ሞሪሺየስ፣ አንጎላ ሁሉ እኛ ያሳየነውን ፈጣን እድገት አላሳዩም የሚል ነው። በጥንድ ቁጥር ነው ያደግነው የሚል ነው። ይህን የሚቃወመው ሰፋ ያለው ማህበረሰብ ደግሞ አንዳንዴ ያፌዝበታል አንዳንዱ ደግሞ ከመንግስት ሰዎች ጋር ሸንጡን ገትሮ ይከራከራል። ክርክሩን አስደማሚ የሚያደርገው በራሱ እድገት አለ የለም የሚለው ነገር መከራከሪያ መሆኑ ነው። ልክ እድገት የማይጨበጥ የማይዳሰስ ይመስል ክርክሩ መነሳቱ አስደማሚ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ትንሽ ምክንያታዊ መሆን የፈለጉ ወገኖች እድገትና ልማት የሚሉትን ጽንሰ ሃሳቦች ይከፋፍሉናል በኢትዮጵያ ውስጥ እድገት አለ ነገር ግን ልማት የለም የሚል ነው። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እድገት የሚለውን አሳብ የሚገልጹት ጠበብ አድርገው ነው። እድገት ማለት  የGDP  ጭመራ ማለት ነው በአጭሩ። በየዓመቱ GDP   ከጨመረ የኢኮኖሚ እድገት ታየ ለማለት ያስችላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የኢኮኖሚ ልማት ሲሉ በአብዛኛው ተቀባይነት ያለው አሳብ ልማት ማለት ልክ እንደ ኢኮኖሚ እድገት በቀላሉ የሚለካም አይደለም። ሰፋ ያለ ጽንሰ ሃሳብ ሲሆን ዋናው ጉዳይ ግን ያ አለ የተባለው የኢኮኖሚ እድገት ያመጣቸውን ተጽእኖዎች የሚመለከት ነው። ተጽእኖው ከሚገለጽባቸውን ጉልህ ጉዳዮች ደግሞ በአብዛኛው HDI (Human Development IndeX) በመባል የሚታወቀውን መለኪያ ያካትታል። ይህ ማለት በአንድ ፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ያሉ ዜጎች  በሶስት ዋና ዋና አቅጣጫ (Dimension) ለውጥ ሲያሳዩ ማለት ነው። እነዚህ ጉዳዮች አንደኛ ረጅም እድሜ (long and healthy life) ሁለተኛ የእውቀት የትምህርት ልማት ሶስተኛ የኑሮ ደረጃ (A decent standard of living )  ናቸው። የኢኮኖሚ እድገት ሲባል እንግዲህ የሃገሪቱ እድገት በነዚህ አቅጣጫዎች የዜጎችን ህይወት ሲቀይር ነው ማለት ነው። ዞሮ ዞሮ የኢኮኖሚ እድገት ወይም የ GDP  ጭምራ አላማ በዚህ ዓለም ላይ ለሰው ልጆች እድገትን ለማምጣት በመሆኑ ብዙ ጊዜ ስለ ሃገር እድገት ሲነሳ የ GDP  ጭመራው ብቻ ሳይሆን HDI መሻሻልን ይመለከታል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድግጅቶችና አብዛኛው ድሃ የሚባለው ህዝብ ብዙ ጊዜ እድገትን ከHDI ጋር እንዲያያዝለት ይፈልጋል። ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ አንድ መንግስት የኢኮኖሚ እድገት ማምጣቱን እንደ ድል አድርጎ ቢጨፍር አብዛኛውን ህዝብ አያስደምመውም። አብዛኛው ህዝብ የሚደሰተው ያ እድገት በHDI ላይ ተጽእኖው ሲያርፍ ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ እንመለስና መንግስት ከፍተኛ እድገት አስመዝግቢያለሁ ይላል። ነገር ግን ከፍ ሲል እንዳየነው እድገቱ በሲቪል ሰራተኛው ላይ አይታይም። ሰራተኛው ባለበት እንኳን ሳይቆም ከግሽበቱ አንጻር ገቢው ከደርግ ጊዜው መምህር በጣም ቀንሷል:: ይሁን እንጂ መንግስት አድጊያለሁ ይላል። እድገት ብቻ ሳይሆን ልማትም ታይቷል፣ የገበሬው ህይወት ተቀይሯል፣ የሰራተኛው ህይወት ተቀይሯል፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተሻሽሏል ባይ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ መንግስትን ከፍጹም ተጠያቂነት በተወሰነ ደረጃ ሊያተርፉት የሚሹ አካላት እድገት አለ ነገር ግን ልማታዊ ያልሆነ እድገት ነው ያለው ይላሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛው ህዝብ ይህ ክርክር አንጀቱ ጠብ አይልም። ዋናው ጉዳይም ይሄ አይደለም። ይልቅ ፍትሃዊው ጥያቄ  መንግስት እድገት አለ ከአፍሪካም ከዓለምም አንደኛ ወጥተናል ካለ እሺ በጣም ጎበዝ ደስ ይለናል በል እንግዲህ ያንን እድገት በገበታችን በገቢያችን ላይ አሳየን፣ በማህበራዊ ተቋምት አቅርቦት ስፋት አሳየን የሚለው ጥያቄ ሚዛን ይደፋል። በመጀመሪያ ግን አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንዳሉት መንግስት እድገት አለ ሲል እድገቱ ከየት እንደመጣ ይጠየቃል። ከመንግስት አካላት ውስጥ የሚሰሙ ካሉ ይመልከቱት:: መንግስት የሚለው ለዚህ እድገት ግዙፉን ድርሻ የተሸከመው ግብርናው ነው። ግብርና መር ፖሊሲ እንዳለው የሚናገረው መንግስት ግብርናችን አገራችንን በጥንድ ቁጥር አሻግሯል የሚል ነው። እዚህ ላይ ታዲያ አጥብቆ ጠያቂዎች ጠይቀውታል። ለመሆኑ ግብርናው ሃገሪቱን ለአስር አመት ዝንፍ ሳይል እንዲህ ለማሳደግ የሚችለው እንዴት ነው? ቢያንስ በግብርናው መሪነት  ከፍተኛ ለውጥን ለማሳየት የሚከተሉት ጉዳዮች መገምገም አለባቸው።

አንደኛው ገበሬው ዘምኗል ማለት ነው። የጎልማሶች ትምህርት ተሻሽሎ ገበሬው ቴክኖሎጂዎችን የመቀበል አቅሙ ዳብራል ማለት ነው። ከትምህርት የተነሳ ኢኖቬቲቭ ሆኗል ማለት ነው።

ሁለተኛ ብዙ ያልታረሱ ለም መሬቶች ታርሰዋል ማለት ነው። ምርት ይጨምር ዘንድ አንዱ ነገር ገበሬው እርሻውን ማስፋት ችሏል ማለት ነው።የመስኖ ልማት ተስፋፍቷል ማለት ነው።

ሶስተኛ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ተሻሽሎ የመሬቱ ለምነት ጨምሯል ማለት ነው

አራተኛ ከፍተኛ የሆነ የእርሻ ግብዓት፣ እንደ ዩሪያ፣ ዳፕ፣ ምርጥ ዘር፣ ፔስት ሳይድ፣ የምርት መሳሪያዎችን ተጠቅሟል ማለት ነው።

አምስተኛ የግብርና ምርት ውጤት ኤክስፖርት በጣም አድጓል ማለት ነው።

እነዚህን ነጥቦች ስንገመግም በርግጥ ግብርናው ይህን ጥንድ ቁጥር እድገት አምጥቷል ወይ የሚለውን መላምት እውነትነት ያረጋግጥልናል። በአጭሩ ለማየት ያህል የጎልማሶች ትምህርትን በተመለከተ በደርጉ ጊዜ ተጀምሮ የነበረው የመሰረተ ትምህርት ፕሮግራም በዚህ መንግስት በመደምሰሱ ማንበብና መጻፍ የጀመሩ ጎልማሶች 60% ደርሶ የነበረው በአሁኑ ጊዜ መጻፍና ማንበብ ጀምረው የነበሩ ሁሉ ወደ መሃይምነት ተመልሰው ወደ  37.5% ዝቅ ብሏል። ይሄ በዓለም አልታየም:: በዚህ በኩል መንግስት ገበሬውን አክስሮታል እንጂ አላተረፈም ስለዚህ ዘመናዊ ትምህርት በዚህ እድገት ውስጥ ሚናው አይታይም። በርግጥ የልማት ሰራተኞችና የግብርና ባለሙያዎች ገበሬውን በሙያ ለማገዝ ይጥራሉ ይሁን እንጂ ባለመማሩ ቴክኖሎጂን በቀላሉ በመቀበሉ ላይና በፈጠራ አቅሙ ላይ ጉልህ ሚና ይጫወት የነበረው ትምህርት አላደገምና በዚህ በኩል ለዚህ እድገት ትምህርት አስተዋጾው የለም ማለት ነው።

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ምርት ሊያድግ የሚችለው በርግጥ የገበሬው ይዞታ ተስፋፍቶ ያልታረሱ መሬቶች ታርሰው ከሆነ ነው። የሃገሪቱን ዋና ዋና ምርት በተመለከተ ከ90% በላይ የሚሆነውን ምርት የሚያመርተው ገበሬ በአማካይ አንድ ሄክታር መሬት የሚያርሰው ገበሬ ነው። ታዲያ እጅግ ብዙውን የሚያመርተው ያ አንድ ሄክታር የሚያርሰው ገበሬ ከሆነና ይህ ገበሬ ደግሞ መሬት መሸጥም ሆነ መግዛት ስለማይችል መሬቱ አይሰፋም አይጠብምና እንዴት ሆኖ ነው ምርት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምረው። በርግጥ በቆላው አካባቢ ሰፋፊ ለም መሬቶች ታርሰዋል።  ነገር ግን ከባለፈው አስር ዓመት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ለም የሆኑ መሬቶችን መንግስት ለመሬት ነጣቂዎች በመስጠቱ እነዚህ መሬቶች ታረሱ ማለት የሃገሪቱን ምርት ሊያሳድጉ ነው ማለት አይቻልም። ስለሆነም  ያን ያህል ከባድ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል እርሻ በአነስተኛ ያዡ ገበሬ ዘንድ  ስላልሰፋ ያን ያህል ምርት ተመረተ ለማለት አይቻልም።

በግብርና ኤክስፖርቶቻችን ዘንድ ብዙ የምንደገፍ ሲሆን ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ውጤቶች ተደማምረው ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ነው የምናገኘው። የሚያሳዝነው መንግስት ራሱ ወደብ አልባ ያደረጋት ኢትዮጵያ ይህቺን ለፍታ ጥራ የላከቻትን የግብርና ምርት ገቢ መልሳ ለወደብ ትከፍላለች። እዚያው ወደብ ላይ የውጭ ንግዳችን ይቀራል። ጂቡቲ ከፍተኛውን ድርሻ ስትይዝ፣ ሱዳን፣ ሶማሌላንድና ኬንያም ትንሽ ትንሽ ይካፈሉናል። ገማቾች እንደሚሉት ለጂቡቲ ብቻ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለወደብ እንከፍላለን። ይህ ደግሞ በልማት ላይ ከባድ ተጽእኖ አለው።

የማዳበሪያና የእርሻ ግብዓቶችን ጉዳይ ስናይ ደግሞ ፍላጎቱ የጨመረ ቢሆንም ያን ያህል ከባድ ለውጥን ሊያመጣ የሚችል እድገት እንዳላሳየ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በሌላ በኩል በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ሜትሪክቶን ለም አፈር እየታጠበ የሚሄድባት አገር በመሆኗ እርሻው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለመለወጥ ጉልበት ያንሰዋል::  ሃገሪቱ የመስኖ ልማትን ችላ ያለች በመሆኗ ዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ በሆነ ግብርና ይሄን ያህል እድገት ማምጣት አይቻልም። አስር በመቶ የሚሆነውን እንኳን በመስኖ ማልማት ያልቻለ መንግስት ግብርናው አደገ ማለት ተቀባይነት የለውም። ኢትዮጵያ ከብዙ ሃገራት የተሻለ የዝናብ መጠን በዓመት በዓማካይ ብታገኝም ስርጭቱ ችግር ስላለበት ማለትም አንዳንዴ በሃይል ይወርድና መሬቱን ይሸረሸራል፣ አንዳንዴ በቂ ዝናብ አይዘንብምና የግድ በከርሰ ምድርና በመስኖ ካልተደገፈ ግብርናው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ቀርቶ ጎታች ነው የሚሆነው። የእስንሳት ሃብታችንን ስናይ ምንም እንኳን በቁጥር ከአፍሪካ አንደኛ ብንሆንም ነገር ግን የተሻሻለ መኖ ባለመኖሩና ርባታው ባለማደጉ በግብርናው ላይ ይሄ ነው የሚባል ጉልህ ተጽእኖ አያመጣም። በአጠቃላይ የግብርናውን ጓዳ ጎድጓዳ ስናይ ይሄን ያህል አመርቂ የሆነ ውጤት ከግብርናው ሊገኝ የሚያስችል ሁኔታ የለም። ከፍ ሲል እንዳልነው ዘጠና ዘባት በመቶ የሆነውን ሰብል የሚያመርተው ገበሬ መሬቱ አይሰፋም አይጠብም። አይሸጥም አይገዛምና ይህ በሆነበት አገር ምርት የሚፈለገውን ያህል ሊጨምር አይችልም።

መንግስት ኢንዱስትሪው ነው ይህን ለውጥ ያመጣው ብሎ ስላልተከራከረ ብዙ ማለት አያስፈልግም። ኢንዱስትሪውና ማንፋክቸሪንጉ ያለው አስተዋጾ ገና ስላላደገ አምስት በመቶ የሚሆን አስተዋጾ እንኳን ስለሌለው ይህ ጥንድ ቁጥር እድገት ከዚያ አካባቢም እንዳልመጣ ይታወቃል። ሰርቪስ ሴክተሩ ከግብርናው ቀጥሎ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የተሸከመ ቢሆንም ይህም በሃጋሪቱ ውስጥ አሁን የሚነገረውን ጥንድ ቁጥር ያለው እድገት ለማምጣት አይችልም። በመሆኑም  ይህ እድገት ከየት መጣ? ተብሎ መንግስት ቢጠየቅ ምላሽ አይኖረውም። በጣም ሲበሳጭ እድገት ማሳያ ብሎ የሚገልጸው አንዱ የመንገዶች ስራና ከተሞች አካባቢ ያሉ የኢንፍራስትራክቸር ለውጦችን ነው። በርግጥ የሚታዩ እነዚህ መንገዶችና ህንጻዎች ከዚህ ከጥንድ ቁጥሩ ጋር በተያያዘ የመጡ እድገቶች አይደሉም። ይህ የሚታየው መንገድ ስራ በአብዛኛው በእርዳታና በብድር የሚሰራ ነው። አንጻራዊ በሆነ መንገድ የማህበራዊ ተቋማት ግንባታዎች ቢታዩም በአብዛኛው ከብድርና እርዳታ ጋር የተገናኙ ናቸው እንጂ የእድገቱ ውጤቶች አይደሉም። ገና ኢትዮጵያ የዛሬ ሰላሳ አርባ አመት የምትከፍለው የብድር እዳ ነው።

መቼም ስለ እድገት ስናወራ ስለ ኢኮኖሚ ልማት ማንሳት የግድ ነውና መንግስት በኢኮኖሚ ልማት በኩልም ተሳክቶልኛል ይበል እንጂ ከእድገቱ ባለ ድርሻ ሊሆን የሚገባው  ሰፊ የሆነው ገበሬ ይህ የጥንድ ቁጥር እድገት አርሶታል ወይ? ካልን ችግሩ ደግሞ በገበሬው ይብሳል። ከፍ ሲል እንዳልኩት ገበሬው የመሬት ባለቤት ባለመሆኑ ከይዞታው አይፈናፈንም። ይዞታው አይጨምርም። የገጠመው ችግር ምንድን ነው? ልጆች ይወልድና ሲደርሱ ይሻሙታል። ያቺኑ መሬት ስድስት ቤተሰብ ይዞ ይኖራል። ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ይሆንበታል። አንዳንዴም ከዚያች ቁራጭ መሬት ላይ የሚያገኘው እህል አመቱን ሙሉ ስለማይመግበው እርዳታን ጠባቂ ይሆናል። ከሁለት እስከ አራት ወር በዓመት ርዳታን ይፈልጋል። በመሆኑም የገበሬው ኑሩ ዛሬ ከመቼውም የበለጠ ከፍቷል። እንደ ድሮው ልጁን ትምህርት ቤት ልኮ ልጁ ኮሌጅ በጥሶ ደመወዝ ቆርጦ ይጦረኛል የሚል ተስፋ የለውም። አስተማሪው ልጁ እንኳን አባትና እናቱን ሊረዳ ራሱንም ትዳር ያንገዳግደው ይዟል። አብዛኛው ገበሬ በተለይ በደጋ ያለው ኑሮው ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል።አንዱ ለዚህ ችግር የዳረገን ነገር በርግጥ የህዝብ ብዛትም ነው። መንግስት በቤተሰብ እቅድ ረገድ የሰራው ስራ የለም። ይህ መንግስት ስልጣን ከያዘ ወዲህ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት ብቻ የኢትዮጵያ ህዝብ በሃምሳ አምስት ሚሊዮን ጨምሯል። የሚገርመው ነገር  በዚህ ሃያ አምስት አመት የመጨመረው ህዝብ ብዛት የአፍሪካን የአስራ አምስት አገራትን ህዝብ ተደምሮ ያክላል። እነዚህ አሃገራት ሴራሊዩን፣ ሊቢያ፣ ማእከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ሞሪታኒያ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ጋምቢያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሌሴቶ፣ ጋቦን፣ ጊኒ ቢሻው፣ ሞሪሺየስ፣ ስዋዚላንድ ናቸው። የነዚህ ሃገራት ህዝብ በሙሉ ተደምሮ ወያኔ ከመጣ የጨመረውን የህዝብ ብዛት ያክላል። የነዚህ አገሮች የቆዳ ስፋት ተደምሮ የኢትዮጵያን አምስት ጊዜ ያክላል። የሰው መብዛት በአንድ በኩል ሃይል ቢሆንም ነገር ግን በዚህ የመሬት ፖሊሲ በታሰረች አገርና በብሄር ፌደራሊዝም በተኮለኮለች አገር እንዲሁም ኢኮኖሚው ከህዝብ ብዛቱ ጋር አብሮ በማያድግበት አገር ህዝቡን ለድሃነት የሚያጋልጥ ነገር ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ስናይ መንግስት በጥንድ ቁጥር እያደግን ነው ቢልም ይህ እድገት ግን በዘዴ ሲቪሉን ሰራተኛ ደሙን እየመጠጠ ያለ ነው። ሰፊውን ገበሬ ደሙን እየመጠጠ ያለ ነው። አነስተኛ የሆኑ ነጋዴዎች ከህወሃት የንግድ ድርጅቶች ጋር መወዳደር ስለማይችሉ የነሱንም ደም የመጠጠ ነው። መንግስት ይህንን ያፈጠጠ እውነት ምንም ሊያደርገው አይችልም። እጅግ ብዙ ድሃዎችን እያፈሩ፣ የሲቪል ሰራተኛውን ጉልበት እየሰረቁና ሃብት በዘዴ እያዛወሩ አንድ የጠገበ ሃብታም ማፍራት እድገት አይደለም። ስለሆነም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚታዩ ግንባታዎች ከሙስና የተራረፉ የብድርና የእርዳታ ውጤቶች ሲሆኑ ሌላው የሃገሪቱ ሃብት ግን እንደነ ኤፈርት አይነቶቹ የህወሃት ድርጅቶች ሰብስበውት ይታያል። በዚህ መሃል በጣም የተጎዳው ሲቪል ሰራተኛውና ገበሬው እንዲሁም ድሃው ነጋዴ ነውና ይህ የህብረተሰብ ክፍል ለለውጥ መነሳት ይኖርበታል።


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles