የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎች ማየት እወዳለሁ። በተለያዩ አጋጣሚዎች ከልጅ ልጆቻቸው ጋር አብረው ሆነው ፎቶግራፍ ተነስተዋል። ልጆቹ አያታቸው ንጝር ሲያደርጉ ያዳምጣሉ፣ ጉብኝት ሲያደርጉም ያያሉ። ገና ከጨቅላነታቸው የሃገር መሪን ሥራና ኃላፊነት እየተገነዘቡ ያድጋሉ። እርሳቸው ጃንሆይም ቢሆኑ አጼ ሚኒሊክ አጠገብ ፎቶግራፍ ተነስተው እንደነበር አይቻለሁ። አጼ ሚኒልክም አጼ ቴዎድርስን እየተከተሉ አስተዳደርና ፍርድ ተመልክተዋል። ጥሩ ነው፣ መጥፎ ድርጊት አይደለም። እኛም እናትና አባታችንን እየተመለከትን የነሱን ባህርይ ቀድተናል፣ የነሱን ሥብዕና ተላብሰናል። የጃንሆይን ፎቶግራፎች ግን ስመለከት አንድ ነገር ወደ ውስጤ ይወረወራል። ጃንሆይ እነዛን የሚሳሱላቸው እምቦቅቅላዎች ነገ ስደተኞች እንደሚሆኑ ግን ከቶ ያሰቡ አይመስለኝም። እርሳቸው ከአጼ ሚኒልክ የተረከቡትን ሥርዓት እንዲህ በቀላሉ ለልጅ ልጆቻቸው የሚያስረክቡ መስሏቸው ነበር። የአድዋው ጀግና የራስ መኮንን ልጅ፣ ያንን የአጼ ሚኒልክን ስብዕና በዓይን የቃኙ፣ አስተዋይና ብርቱው ጃንሆይ እንዴት የወደፊቱን መተንበይ እንዳልቻሉ ሳስበው ይገርመኛል። የጃንሆይ መንግሥት ሲገረሰስ ልጆቻቸው፣የልጅ ልጆቻቸው ስደተኞችና እስረኞች ሆኑ። ከጃንሆይ ሃገሪቱን የተረከቡት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለፎቶግራፍ ብዙም ጊዜ አልነበራቸውም። የእፎይታ ጊዜ ስላልነበራቸው ልጆቹን ፎቶግራፍም አለስነሱም። ባለቤታቸውም ብዙ አይታወቁም። ቢሆንም ግን ተሰደዱ። ከደርግ ሥርዓቱን የተረከቡት አቶ መለስ ዜናዊ ግን ከሁለቱ መሪዎች ይልቅ ጮሌ ነበሩ። ለልጆቻቸው ፎቶግራፍ አይደለም የሚያወርሱት። ለልጆቻቸው ገንዘብ ለማውረስ ነው የማኦ ሴቱንግን መጽሃፍ ተንተርሰው ያድሩ የነበረው። የማኦ ሴቱንግ መጽሃፍ ስለገንዘብ አያወራም ግን ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ መወለዱን ያብራራል። የደደቢቱ ፈላስፋ አቶ መለስ ዜናዊም ገንዘብ ከጠመንጃ አፈሙዝ ይወለዳልዕ ሲሉ የማኦን ሃሳብ ጠመዘዙት። ሥልጣን የገንዘብ ምንጭ ነውዕ አሉ አቶ መለስ፣ ገንዘብ የኃጢዓት ሁሉ ምንጭ ነው የሚለውን ዘንግተው። ይህን መጻፌ የታሪኩን ሂደት ለማብራራት እንጂ ሙት ወቃሽ ሆኜ አይደለም።
አቶ መለስ ኢትዮጵያን የሚያህል ትልቅ አገር ማስተዳደር እንደማይችሉ ገና ከጠዋቱ ያውቁ ነበር። አቶ መለስ እነ አጼ አምደጽዮንን፣ አጼ ገላውዲዎስን፣ አጼ ሚኒልክን የሚተካ የአመራር ችሎታ ይቅርና በቅርብ በታሪክ ከሚታወቁት ጀግናው ራስ አሉላ፣ ራስ ጎበና ወይም ራስ መስፍን ጋር እንኳን የሚተካከል ያንዲት ሳንቲም ክፋይ ጀግንነትም ይሁን ማስተዋል እንደሌላቸው ስብዕናቸው ጠንቅቆ ያውቃል። አቶ መለስ ከሻዕቢያ ጋር የተስማሙት ትግራይን ታላቋ ትግራይዕ ብለው ከልለው ወይም ገንጥለው ወደብ ለኢትዮጵያ እያከራዩ ገንዘብ እንደ ውሃ ቦና የሚሰበስቡ መስሏቸው ነበር። ይህን ምስጢር የኤርትራም የትግራይም ሕዝብ አያውቅም። አቶ መለስ ስለ ገንዘብ ሲያስቡ ገንዘቡን ለልጆቻቸው እየሰጡ በውጭ ሃገር እያንደላቀቁ ሊያኖሯቸውም ጭምር አስበው ነበር። ይህ ሃሳብ በማኦ ሴቱንግ መጽሃፍ ላይ እንዴት እንደተጻፈ አላውቅም። አቶ መለስ ግን ትርጉሙ ገብቷቸዋል። አጠገባቸው ካሉት ውስጥ ትልቁ አቦይ ካልሆኑ በቀር ተራ ተጋዳላዮቹ ሊገለጽላቸው አይችልም። የአቶ መለስን ራዕይ የሚያውቁት ባለቤታቸው ብቻ ናቸው። እሳቸውም ቢሆን በድንግዝግዙ ነው።
አቶ መለስ ስለገንዘብና ስደት ሲያውጠነጥኑ የመንገዳቸውን መጀመርያ ያደረጉት መውጫ፣ መላወሻ፣ መፈርጠጭያ፣ መጋለብያ መሬቶችን ማፈላለግ ነበር። ይህን ጊዜ የቅዱሳን ምድሯ ዋልድባ፣ የሰሊጥ አምራችዋ ሁመራ፣ የጀግኖቹ ምድር ወልቃይጥ፣ ጠለምትና ጠገዴ ፈረደባቸው። አቶ መለስ ችግር ከመጣ ወደ ሱዳን ለመጠጋት እነዚህን መሬቶች ከትግራይ ጋር መደባለቅ ሊኖርባቸው ነው። እስከዛው ድረስ ግን ለሟን መሬት ይበዘብዛሉ። ፍርጃ ማለት ይህ ነው። አቶ መለስ የማኦ ሴቱንግን መጽሃፍ ብቻ ሳይሆን የኢጣልያ የቅኝ ግዛት ካርታንም ከየትም አፈላልገው ሲያጠኑት፣ ሲያስተውሉት ይኖሩ ነበር። ኢጣልያ በዘር ከፋፍላ ለመግዛት እንዲያመቻት አልያም ከጦር ስትራቴጂካዊነት አኳያ ወድያና ወዲህ አደበላልቃ፣ ከልሳ አከላልሳ የፈጠረችውን የዘር ክልሎች አቶ መለስ ያገናዝቧቸው ነበር። እነዚህ ናቸው የአቶ መለስ ፍልስፍና ፈር ቀዳጆች፣ የቻይናው ማኦ ሴቱንግ ሥልጣን (ገንዘብ) ከጠመንጃ አፈሙዝ ይወለዳል ና የኢጣልያ የዘር ክልል ካርታ። እነዚህ ናቸው አቶ መለስን በደጋፊዎቻቸው ዘንድ እንደ ናፖሊዎን ስትራቴጂካዊ፣ እንደ አዳም ስሚዝ ልማታዊ፣ እንደ ሆ ቺሚንህ ነጻ አውጭ፣ እንደ ኢንቫዮርሜንቱ ሳይንቲስቶቹ ሊቃዊንት ያስባላቸው። በእርግጥ አቶ መለስ እግዚአብሄር የሰጣቸውን አዕምሮ በመልካም ቢጠቀሙበት ኖሮ ለሃገራቸው ይጠቅሙ ነበር። ይህ አለመሆኑ በጣም ያሳዝናል።
ከወልቃይት ብሎግ ባገኘሁት ማስረጃ መሠረት ከአንገረብ ወንዝ በስተ ሰሜን የሚገኙት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ዋልድባ፣ ጠለምት፣ ሰሜን፣ ዋገራ ከአገው ፈላሻ የተወረሰ የራሳቸው ባህል፣ ኃይማኖትና ቋንቋ እንዳላቸው ነው። እነዚህ ሃገሮች በተከዜ በኩል ከትግራይ ጋር ስለሚዋሰኑ የንግድ ልውውጥ ያደርጉም ነበር። የወቅቱ የአክሱም ትግራይ የበላይነት መንፈስ የግዕዝ ትግሬኛ ቋንቋ በተለይ በወልቃይት ውስጥ እንዲሰርጽ ምክንያት ሆኗል። ጠለምትም ከትግራይ በሚሾመው በሹም ጠለምት በመተዳደርዋ እስከ አስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ ለትግራይ አስተዳደር ትገብር ነበር። የኦሮሞ ሕዝብ ከደቡብ ወደ ሰሜን መስፋፋት ሲጀምሩ የአማራ፣ አንጎትና ሸዋ ንጉሳዊ አስተዳደር ተፋለሰ። ሕዝቡም ከአባይ ማዶ ሰሜናዊ ግዛት ትግራይ አጠገብ መስፈር ጀመረ። ነገሥታቱ ኃይላቸው በመመናመኑ ምክንያት ከጣና ሃይቅ ሰሜን በደንብያና ወልቃይት ሠፋሪ የነበረውን አገውና ፈላሻን በመውረር ክርስትያን ኃይማኖትን በግድ እንዲቀበል አደረጉት። ይህ አዲሱ አካባቢ በአማራ ንጉሳዊ አስተዳደር ስር ተማከለ። ቋንቋቸውም ልሳነ ንጉሥ የሆነው አማርኛ ሆነ። ከዚህ ቀደም የነበረው ምዕራብ ተከዜን አስታኮ የነበረው የትግራይ ገዥዎች ተፅዕኖም ፈጽሞ ተቋረጠ። ይህ ሁኔታ ከዘመነ መሳፍንት አንስቶ በአጼ ቴዎድሮስ፣ በትግራዩ ንጉሥ ዮሃንስ፣ በአጼ ሚኒልክ፣ በኢያሱና ዘውዲቱ፣ በቀዳማው ኃይለ ሥላሴና ደርግ ድረስ አንዳች ለውጥ አልተደረገበትም። ጎንደር የኢትዮጵያ ማዕከላዊነቷ ተቋርጦ ዋና ከተማው አዲስ አበባ ሲዞርም እንኳን ይህ ይዞታ ለውጥ አልተደረገበትም ነበር።
ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ዳግመኛ ስትወር ከአንገረብ ወንዝ ሰሜን ያሉትን የጎንደር ክፍለ ግዛት ከኤርትራ ጋር ደባለቀችው። ኢጣልያ ይህን ያደረገችው ወታደራዊ የገዥ መሬት ከመያዝ አኳያና በአካባቢው ያለውን የአርበኞች ትግል ለመቆጣጠር ነበር። አካባቢው በተለይም ሰሜን፣ ጠለምት፣ ወልቃይትና ጠገዴ ከጥንት ጀምሮ የአመጽና የሽፍቶች መሰማርያ ነበር ይባላል። ከአንገረብ ወንዝ ደቡብ የሚገኘውም ታሪካዊው አካባቢ እስከ ሱዳን ጠረፍ ኦም ሃጀር ድረስ የሚያካልለው አርማጭሆ ለኢጣልያ አስጊ አካባቢ ነበር። ፊታውራሪ ውብነህ ወይም አሞራው ውብነህና ቢትወደድ አዳነ መኮንን በዚሁ አካባቢ ሸፍተው ኢጣልያን መውጫ መግቢያ ያሳጡ ጀግኖች ነበሩ። ቢትወደድ አዳነ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሕብረት (ኢዲዩ) መሪ ሆነው ደርግን በመፋለም ላይ እንዳሉ ኢሕአፓ በሰማንያ አራት አመታቸው ሱዳን ድንበር አካባቢ በግፍ ገደለቻቸው።
አቶ መለስ ይህን የኢጣልያ ዘረኛ ካርታ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ በማዋል ግማሹን በጌምድር ከምዕራብ ትግራይ ጋር አደባለቁ። ለሞቹ የአንገረብ ወንዝ አካባቢዎች ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ዋልድባና ጠለምት ከትግራይ ጎን የሚገኙ አካባቢዎች በመሆናቸው ከእሾህ የተጠጉ አጋሞች ሆኑ። የትግራይ ትግርኝ የአቶ መለስ ፕሮጀክት ሕዝቡን በማይፈልገው አሳዛኝ ተፅዕኖ ሥር አምበረከከው። ባጠቃላይ አቶ መለስ በምስራቅ ከቀይ ባህር ጋር ለመገናኘት ጢዮን ወይም መርስ ፋትማን ለማካለል እያሰቡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሱዳን ጋር ለመዋሰን በጋሽና ሰቲት ወንዝ መሃከል ያሉትን አካባቢዎች በመንጠቅ እንዲሁም እስከ ምዕራብ ወሎ ዋግ ክልልን በማስገባት ገንዘብ የማሰባሰብ ዓላማቸውን ያሳኩ ዘንድ የዕብሪት ራዕያቸውን ከፍ አደረጉ። የሠመረላቸው ሰምሮ የተቀረውን የቤት ሥራ ለተባባሪዎቻቸው አስረክበው እስከ ወድያኛው አሸለቡ።
የአቶ መለስና ተባባሪዎቻቸው የትግራይ ትግርኝ ፕሮጀክት በምን ምክንያት ጋብ አለ። አንደኛ አሜሪካ ሶሻሊስታዊ አስተሳሰባቸውን ካቆሙ ሥልጣን ላይ እንደሚያወጣቸው ለአቶ መልሰ በግልጽ ነገረቻቸው። እሺ በማለታቸው አዲስ አበባ ሚኒልክ ቤተመንግሥት በሰላም ገቡ። ሁለተኛ ከአቶ ኢሳያስ ጋር የተማማሉበት ትግራይን ገንጥሎ ወደብ ሸጦ ገንዘብ የመሰብሰብ እቅዳቸው በሌላ አዲስ እድል ተተካ። መላ ኢትዮጵያን ከያዙ በርካታ እንደውም ካሰቡት በላይ ገንዘብ ስለሚያገኙ ወደብ ሽያጩን ናቁት። ይባስ ብለው ከእቶ ኢሳያስ ጋር በገንዘብ ምክንያት ሲጣሉ ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ገብተው ብዙ ሰዎች ተሰዉ። አሰብ የግመል መፈንጫ ነው የምትሆነውዕ ብለው ወደ ማህል ኢትዮጵያ ዘልቀው ገቡ። ያደቆሰ ሰይጣንዕ እንደሚባለው ገንዘብ እያሸተቱ ይበልጥ ወደ መሃል ተሳቡ። ኦርቶዶክስንና አማራን አከርካሪውን ሰብረነዋልዕ አሉ አቦይ ስብሃት የዋልድባንም የመሬት ሸንኮራአገዳ ሊተክሉበት እያሰቡ። ዋልድባ አለቀሰች፣ አነባች ሁለቱን እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ዘረጋች። አቶ መለስና ባለቤታቸው፣ አቶ መለስና ተባባሪዎቻቸው፣ አቶ መለስና ዘመዶቻቸው በኢንቬስትሜንት ስም፣ በልማት ዘፈን ለሟን ኢትዮጵያ ከላይ አርማጭሆ እስከታች ሞያሌ መጠመጧት። ልጆቻቸውን ገንዘብ እየሰጡ በውጭ ያዝናኗቸው ጀመር። የኢትዮጵያ ወጣቶችም ሃገራቸውን እየለቀቁ ሲሰደዱ ልጃቸው መንገድ ዳር እየተጸዳዳች ፎቶ ትነሳ ጀመር። ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ መለስና ጳጳሱ ድንገት ሞቱ። የባለቤታቸው፣ ተባባሪዎቻቸውና ኢንቨስተሮቻቸው ገንዘብ የማሰባሰብ ዘዴና ትልም በአጭረ ተቀጨ። ሌላ ስትራቴጂ የሚያመነጭ ጠፋ። የተማሩ ናቸው ተብለው የተቀመጡትም አቶ ኃይለማርያም ትምህርቱ ተሰወረባቸው። በድንገት ኦሮምያ ላይ አመጽ ፈነዳ። የመለስ ፋውንዴሽን፣ የሼኩ ንብረቶች፣ የውጭ ኢንቬስተሮች ተቋም፣ የልማታዊው ዲያስፖራው ሱቆች በእሳት ጋዩ፣ በድንጋይ ተወገሩ። የአቶ መለስ የብዝበዛ ፍልስፍና በአጭር ሊቀጭ ሆነ። የኦሮምያ ወጣቶች ሆ ብለው ተነሱ። ወተቷን ጠጥተው፣ እሸቷን በልተው ያደጉትን ልማታዊ ኦሮሞዎችንም አስጠነቀቁ። እነዚህ ሁል ያመጹት ወጣቶች የልማቱን ዘፈንዕ እየሰሙ ያደጉ ወጣቶች ናቸው።
ለም በመሆንዋ ከትግራይ ጋር ሳትወድ የተደባለቀችው መሬት ድምጿን ከፍ አድርጋ ጮኸች። ጊዜ ጥሏት ማንነቷን የተነጠቀችው ያች የቅዱሳን መሬት አመጸች። ከወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ የአማራውን ሕዝብ እያፈናቀሉ ከትግራይ ሰዎች እያሰፈሩበት በውሳኔ ሕዝብ (ረፈርንዱም) ስልት አካባቢን ከትግራይ ጋር ለመደባለቅ የወጠኑት ስልትም ተቀባይነት የለውም። ይህ ቢደረግ ታሪክ ትፋረዳለች፣ ዋልድባ ታለቅሳለች፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች። እርሱ አምላክ ከላይ ከከፍታው መብረቅ ያወርዳል። ያች መውጫ፣ መላወሻ፣ መፈርጠጭያ፣ መጋለብያ ተብላ በግፍ የተወሰደች የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት ለም መሬት፣ ለቅዱሳኑ ኪዳናት ባለአደራ የሆነችው ዋልድባም ጭምር መወለጃ መሆኗ ቀርቷል። እናንተ እብሪተኞች ያጽመ ርስት ይዞታዎቼን ልቀቁልኝ አለች።
ከላይ እንዳነሳሁት ጃንሆይም፣ ኮሎኔል መንግሥቱም አቶ መለስም ለልጆቻቸው ያሰቡ አይመስለኝም። የጃንሆይ ልጆች፣ የልጅ ልጆች ስደተኞች ሆኑ። የኮሎኔል መንግስቱም ልጆች እሳቸውም ስደተኞች ሆኑ። የአቶ መልሰ ልጆች ግን ስደተኛ እንኳን ሆነው መኖር የሚችሉ አይመስለኝም። አባታቸው ሥጋዊ ኑሯቸው የሲዖል ኑሮ እንደሆነባቸው አሸለቡ። ልጆቻቸውም ገንዘብ ታቅፈው ወደ ውጭ ሊኖሩ የሚችሉበት የዓለም ክፍል የለም። የአለም አቀፍ ህግ ተሻሽሏል። ባለቤታቸው፣ ሌሎቹም የራዕዩ ወራሾች በሁመራ አግርገው ወደ ሱዳን እንዳይፈረጥጡ ወደ ማህል ተስበው እግሮቻቸው በዝርፍያ ከተሠሩት ሕንፃዎች መሠረት ጋር አብሮ ወደ መሬት ተቀበረ። እጆቻቸው ከንግድ ቤቶቻቸው ግድግዳና ከኤፈርቱ የሙስና ኃብት ጋር ተጣበቁ። እንዴት ይውጡ፣ ወዴት ይሰደዱ። ቢሰደዱም ያሰደዷቸው ወጣቶች በየትኛውም የዓለም ክፍል ይጋፈጧቸዋል። አሁንም መከራ እያዩ ነው።
ከእሾህ የተጠጉት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ዋልድባ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አለቀሱ። ኦሮምያም አነባች፣ ተጋጠች፣ ከብቶቿ ታለቡ፣ ወርቋ ተዘረፈ። መላ ኢትዮጵያ ቆሰለች። ለአቶ መለስና ተባባሪዎቻቸው ሥልጣኑን ለሕዝቡ በሠላም እንዲያስረክቡ አሁንም ዕድሉን አልተነፈጉም። ይህ ካልሆነ ውሎ አድሮ ምን እንደሚፈጠር ሳይገነዘቡት አይቀሩም። የዝርፍያ፣ የቀማኝነትና የቁማር ፖለቲካ አሜሪካ የቱንም ያህል ቢረዳው መጨረሻው አያምርም።
እባክህ እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ከስቃይ አውጣት። መች ይሆን ሕዝብህ እፎይ የሚለው፧