(ሳተናው) የግብጹ የውሃ ሚንስትር ሙሐመድ አብደል አቲ ትናንት ማክሰኞ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ከሱዳኑ አቻቸው ሞታዝ ሙሳ ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያው የአባይ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸውን ዝግ ስብሰባ ማድረጋቸውን የሁለቱ አገራት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
በዝጉ የሁለቱ አገራት የውሃ ሚንስትሮች ስብሰባ በዋናነት ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ የምትገኘው ግድብ በአባይ ወንዝ የታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽእኖ ለማጥናትና ለመነጋገር መሆኑ የተወሳ ሲሆን በግድቡ ዙሪያ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሞያዎችም አስተያየቶችን መሰንዘራቸው ተሰምቷልለለ
ባሳለፍነው የየካቲት ወር ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን ከሶስቱ አገራት በተውጣጡ ባለሞያዎች የሶስትዩሽ ኮሚቴ በማቋቋም ሁለት የፈረንሳይ አማካሪ ቡድኖችን በመቅጠር ግድቡ በታችኞቹ የወንዙ የተፋሰስ አገራት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽእኖ በማጥናት እንዲያርቡ ማዘዛቸው ከተነገረ ጀምሮ የሁለትዩሽ ግንኙነቶች ቀርተው ነበር፡፡
በካርቱም ስብሰባ ያካሄዱት የውሃ ሃብት ሚንስትሮች ዛሬ በሚጀምረው አህጉራዊ ስብሰባ ለመካፈል አዲስ አበባ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡
የአባይ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ግብጽ በአባይ ወንዝ ይገባኛል የምትለውን አመታዊ 56 ቢልዩን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ግድቡ ሊቀንስብኝ ይችላል የሚል ስጋቷን ስታቀርብ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡የአዲስ አበባው መንግስት በበኩሉ ግድቡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ብቻ የሚውል በመሆኑ የውሃው መጠን አይቀንስም የሚል ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ምንጭ ካይሮ ፖስት