Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

በቲያንስ ሱቆች ፒራሚዳዊ የሽያጭ ስልትን ተግብረዋል በሚል በወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

$
0
0

ከቲያንስ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር ውል በመፈፀም በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች በከፈቱት የሽያጭ ሱቆች የፒራሚድ የሽያጭ ስልትን ተግብረዋል በሚል በወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

የፌዴራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ከትላንት በስቲያ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ጀምሮ ዛሬ ለፌዴራሉ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ተለቀው ምርመራው እንዲካሄድ አዟል።

የባለስልጣኑ መርማሪም ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢለቀቁ የተጀመረውን ምርመራ የሚያስተጓጉል በመሆኑ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል።

ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ ወንድምኩነኝ ወልደማርያም፣ 2ኛ ተመስገን በላይ፣ 3ኛ ይታገሱ ሌሌሳ፣ 4ኛ ሀና አፈወርቅን ጨምሮ 11 ግለሰቦች ናቸው ዛሬ የፈደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት።

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን መርማሪ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ 10 ስአት ላይ በኢትዮጵያ በንግድ ህግ የተከለከለውን የፒራሚድ የሽያጭ ስልትን ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም ሸማቾች ባወጡት ገንዘብ ልክ ምርት ባለመስጠት፣ በግብይት ወቅት የማጭበርበር ድርጊት ፈፅመዋል በማለት ነው 11ዱ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ የጀመረው።

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች በተለያዩ ቦታዎች ከ2003 ዓ.ም እስከ የካቲት 2008 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የንግድ ህጉን በመተላለፍ የፒራሚድ ሽያጭ ስልትን ተግባራዊ ማድረጋቸው በምርመራ ሂደቱ መረጋገጡን ነው የባለስልጣኑ መረማሪ ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት።

በተለይም ተጠርጣሪዎቹ ከቲያንስ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር ውል በመፈፀም የተጨማሪ ምግቦች እና ኮስሞቲክስን የማከፋፈል ሽፋን በማደረግ፣“ከእኛ ጋር በአሻሻጭነት ብትሰሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታም ትሆናላችሁ፣ በሸጣችሁት ልክ ኮሚሽን ይከፈላችኋል፣ ወደ ውጭ ሀገር እንልካችኋለን፣ መኪና ትሸለማላችሁ” እና መሰል ማማለያዎችን በመጠቀም ሸማቾችን በማታለል የመመዝገቢያ እና የአባልነት ክፍያ በመጠየቅ በፒራሚዳዊ ሽያጭ ስልት በርካታ ገንዘብ መሰብሰባቸውም ተገልጿል።

የፒራሚድ የሽያጭ ስልት እንዳይታወቅባቸው ጥቂት ምርቶችን በማቅረብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሸማቾች ላይ ጉዳት አድርሰዋልም ነው ያለው መርማሪው።

በዚህ ስልት ከሸማቾች የሚሰበሰበውን ገንዝብ ለራሳቸውና በአማላይነት ለሚሰሩላቸው ግብረ አበሮቻቸው እንደሚያከፋፍሉትም ተጠቅሷል።

በዚህም የባለስልጣኑ መርማሪ በ11ዱ ተጠርጣሪዎች ላይ የጀመርኩት ምርመራ ውስብስብ በመሆኑ፣ በቅንጅት የሚሰሩ ግለሰቦች እና በቲያንስ ኢትዮጵያ ላይ የጀመርኩትን ምርመራ ለማጠናቀቅ፣ ድርጊቱ ለረጅም ጊዜ ሲፈፀም የመጣና ተጠርጣሪዎቹ የገንዘብ አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ መረጃ ያሸሹብኛል የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ ለፍርድ ቤቱ የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የፈደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ተፈተው ምርመራው ቢካሄድ ጉዳት እንደሌለው በመጥቀስ እያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ዋስትና በማቅረብ ከማረሚያ ቤት ውጭ ሆነው ምርመራው ይካሄድ በሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በትዕዛዙ ላይ ቅር የተሰኘው የፌዴራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን መርማሪም ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቋል።

በመሆኑም 11ዱም ተጠርጣሪዎች የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከስአት በኋላ በይግባኙ ላይ ውሳኔ እስኪሰጥ ድርስ በማረሚያ ቤት እንደሚቆዩ ለማወቅ ተችሏል።
dd011ec1ab769e4740c81b926379b51e_L


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles