Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የህጻናቱ እናቶች አባሽ ያጣ እንባ

$
0
0

afar

(ሳተናው) የሙሉጌታ ካሳ የስራው አሳዛኝ አካል በድርቁ በተጎዳው የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ወደሚገኘውና ወደሚሰራበት የጤና ክሊኒክ በአስከፊ ሁኔታ ሰውነታቸው ገርጥቶና ሞት አፋፍ ላይ ደርሰው የሚመጡ ህጻናትን መቀበሉ አይደለም፣ ህጻናቱ አገግመው ወደቤታቸው እንዲሄዱ ሲነገራቸው ከወላጆቻቸው የሚሰማው ምላሽ ስራውን እንዲጠላው ያደርገዋል፡፡
‹‹እናቶቻቸው ወደቤታቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አይሆኑም ምክንያቱም ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚያስችላቸው ምንም ነገር በቤታቸው ውስጥ የለም፡፡ወላጆቻቸውን ከእነርሱ ልጆች በከፋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ተከታታይ ድጋፍ ማግኘት ይገባቸዋል በማለት ልናሳምናቸው እንሞክራለን ይህ ግን ልብን ይሰብራል››ይላል፡፡
በሁለት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ባለመዝነቡ የተነሳ ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ በምግብ እጥረት ተሰቃይተው ወደ ክሊኒኩ ይመጣሉ፡፡ወደክሊኒኩ በአብዛኛው የሚመጡ ህጻናት ድርቀት ያጠቃቸውና ምግብ ለመመገብ የማይችሉ ናቸው የሚለው ሙሉጌታ በአሁኑ ወቅት የህጻናቱ ቁጥር በታህሳስና ጥር ወር ከነበረው በብዙ እጥፍ መጨመሩን ያወሳል፡፡
በአፍሪካ ሁለተኛውን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያስመዘገበችው ባለ95 ሚልዮን ህዝቧ ኢትዮጵያ በ50 ዓመታት ውስጥ አይታው የማታውቀውን ድርቅ አስተናግዳለች፡፡የአገሪቱ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 10.2 ሚልዮን ኢትዮጵያዊያንን ለመመገብ 1.4 ቢልዩን ዶላር እርዳታ ጠይቀዋል፣ ይህም ከሶሪያና የመን በመለጠቅ የአለማችን ትልቁ የእርዳታ ጥያቄ በመሆን ተመዝግቧል፡፡
የአለም የምግብ ፕሮግራም እንዳስታወቀው ከሆነ የተጠየቀው እርዳታ እስከ ግንቦት ወር መድረስ ካልቻለ በህጻናቱ ላይ እየደረሰ የሚገኘው የአልሚ ምግብ እጦት ወደከፍተኛ ደረጃ ይሸጋገራል፡፡
ሙሉጌታ በሚሰራበት የጤና ክሊኒክ እናቶች መሬት ላይ አንሶላዎቻቸውን በማንጠፍ ብርድልብሶችን ለብሰው ተቀምጠዋል፣አንዳንዶቹ ለህጻናቶቻቸው በተዘጋጀ ንጹህ አልጋ አጠገብ ቁጢጥ ብለው ልጆቻቸውን በእጆቻቸው ደግፈዋል፡፡
በግድግዳዎቹ ላይ የተሰቀሉ ምልክቶች ህጻናቱ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከሆነ አንቲ ባዮቲክ፣በፕሮቲን፣ቫይታሚንና ሚኒራል የበለጸገ ወተት ፣ ወደ ሁለተኛ ደረጃ የተሸጋገሩ ደግሞ ከፍተኛ ኃይል ሊሰጣቸው የሚችልን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንደሚገባቸው ይገልጻል፡፡
ደብሬ መኩሪያ ወደ ክሊኒኩ የመጣችው ከአምስት ቀናት በፊት ነበር፡፡የስምንት ወር ልጇ ታመን እጅግ በመዳከሙ ርዳታ ፈልጋለች፡፡ቤተሰቧ ካገኘው የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ሬሽን በተጨማሪ በቆሎ ለመግዛት የሚያስችላትን ብድር አግኝታለች፡፡ነገር ግን ይህ በቂ እንዳልሆነላት ትገልጻለች ‹‹እነርሱን የምመግብበት ምንም ነገር እጄ ላይ የለም››ብላለች፡፡
የአልሚ ምግብ እጦት ፍርሃት
እርዳታና የሎጀስቲክ አቅርቦት አለመኖር ለኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ ፍላጎት ዋነኛ መሰናክሎች ሆነዋል፡፡በኢትዮጵያ መንግስት በሬሽን መልክ የተከፋፈሉ የምግብ ዘይት፣ ጥራጥሬዎችና በመኪና እና በአህያ እየተጓጓዙ የተከፋፈሉ የመጠጥ ውሃዎች ችግሩን መወጣት አልቻሉም፡፡
የአለም ምግብ ፕሮግራም ከመጪው ግንቦት ወር ጀምሮ ተጨማሪ 7.6 ሚልዩን ዜጎች የምግብ ርዳታ የሚፈልጉ ይሆናሉ ብሏል፡፡አልሚ ምግቦች የሚያስፈልጋቸው ህጻናት ቁጥርም በአስገራሚ ሁኔታ ያሻቅባል በማለት አስጠንቅቋል፡፡
‹‹ሁኔታው አስቸኳይ ምላሽ ማግኘት የሚገባው መሆኑን እናውቃለን፡፡የምግብ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ለህጻናት የሚሆን አልሚ ምግብ አለማግኘት ደግሞ የበለጠ ያስጨንቀናል››የሚሉት የአለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጆን አይሊፍ ናቸው፡፡‹‹ምግቡ ከግንቦት በፊት የማይደርስ ከሆነም የአልሚ ምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር ከምንገምተው በላይ ይሆናል››ብለዋል፡፡
የመጨረሻው አማራጭ
በአቧራማው የአማራ ክልል ዋግ ህምራ ዞን የሚገኙ እናቶችና የጤና ክሊኒኩ ሰራተኞች ለቶማሰን ሮውተርስ ፋውንዴሽን ለመጨረሻ ጊዜ መንግስት ካከፋፈለው ሬሽን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በቂ የምግብ እርዳታ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የ30 ዓመቷ ሃና መኮንን በጥቅምት ወር የአንድ ዓመት ልጇ አልሚ ምግብ በማጣቱ ስለጫጨባት ወደ ጤና ክሊኒኩ አምጥታዋለች ‹‹የማስተዳድረው ቤተሰብ ብዛት አራት ነው ነገር ግን ያገኘሁት የምግብ እርዳታ ለሁለት ሰዎች የሚሆን ነው››ትላለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የለጋሾች እጅ ካልተዘረጋለት ህዝቡን ለመመገብ ከራሱ ካዝና እንደሚያወጣ ሲናገር ይደመጣል፡፡የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእርዳታ ማስተባበሪያና የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ምትኩ ካሳ ‹‹ነገሮች በጣም ተባብሰው መጥፎ ደረጃ ከደረሱ የሚኖረው አማራጭ ይህንን ማድረግ ብቻ ነው ››ይላሉ፡፡መንግስት እስካሁን 380 ሚልዮን ዶላር ካለፈው የሐምሌ ወር ጀምሮ ወጪ ማድረጉንም የኮሚቴው አባል ይናገራሉ፡፡
የሴቭ ዘ ችልድረን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጆን ግርሃም በበኩላቸው ‹‹ሁላችንም የኢትዮጵያ መንግስት ክፍተቱን ይሞላል በማለት እንደ ሞኝ እየጠበቅነው እንገኛለን ነገር ግን ክፍተቱ ከፍተኛ መሆኑ ደግሞ ያስጨንቀናል››ብለዋል፡፡
ምንጭ ኦል አፍሪካ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles