የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከነገ ጀምሮ በሚያካሄደው ስብሰባ በፖለቲካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክር የማዕካለዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ አለምነው መኮነን ማምሻውን ለኢዜአ እንደገለፁት ማዕከላዊ ኮሚቴው ባለፉት ስድስት ወራት በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች የተያዘው እቅድ አፈፃፀም ከሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ግብ አንፃር በመመዘን ይገመግማል፡፡
በተለይም በህዝቡ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየትና በመፍታት በኩል የተከናወኑ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ማዕከላዊ ኮሚቴው በጥልቀት ይመረምራል፡፡
ከኢሊኖ ክስተት ጋር በተያያዘ በክልሉ ለችግር የተጋለጠውን ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ህዝብ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ባለበት አካባቢ ተረጋግቶ እንዲኖር የተደረገውን ድጋፍና የተገኘውን ተሞክሮ ኮሚቴው ይመለከታል፡፡
በገጠር የመስኖ ልማትን በተደራጀ አግባብ በማከናወንና በመኸር ወቅቱ የተከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም ውይይት እንደሚካሄድባቸው አቶ አለምነው ጠቁመዋል።
” በበጋው ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራን አጠናክሮ በማስቀጠል ድርቅን በዘላቂነት ለመከላከል የተቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ በኩልም ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ ማዕካለዊ ኮሚቴው ይገመግማል” ብለዋል።
በከተማውም ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ዘርፎች በማሰማራት የስራ እጥነት ችግርን ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት እንደሚፈተሽም ተመልክቷል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ከቅማትን ማህበረሰብ ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ግጭትና የአፈታት ሂደቱን ማዕከላዊ ኮሚቴው እንደሚገመግመው አቶ አለምነው ጠቁመዋል፡፡
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከየካቲት 24/2008ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ስብሰባ የቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥም ሃላፊው አስታውቀዋል።
በአማራና በትግራይ ክልሎች በጠገዴና ፀገዴ ወረዳ ነዋሪዎች የተከሰተውን ወቅታዊ ችግርም በሰከነ መንገድ ለመፍታት የሁለቱ ክልሎች የአስፈፃሚ አካላት በጉዳዩ ዙሪያ መምከራቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም በሁለቱ ኩታ ገጠም ወረዳዎች ተሰሚነት ያላቸውን ሽማግሌዎች በመምረጥም ጉዳዩን በድርድር እንዲቋጩት አቅጣጫ ተሰጥቶ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከሁለቱ ክልሎች የተወጣጣ ኮሚቴም ተቋቁሞ በጉዳዩ ዙሪያ እየተነጋገረ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በቀጣይም ህዝቡ በቀጥታ እንዲመክር በማድረግ መፍትሄ እንደሚሰጠው አቶ አለምነው አብራርተዋል።
ምንጭ፡ ኢዜአ