ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣው የዓለም የነዳጅ ዋጋ አሁን ደግሞ ሊብስበት ነው፡፡ በኢራን ላይ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ትናንት በመነሳቱ በዓለም ገበያ ለአንድ በርሜል ድፍድፍ ዘይት የሚከፈለው ዋጋ ከ31 ዶላር ወደ 28 ዶላር ገብቷል፡፡ ይህ በአንድ ቀን የታየ የዋጋ ልዩነት ለወደፊቱ እየባሰ ሊሄድ እንደሚችል የዓለም የኢኮኖሚ ጠበብት በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡
በኢኮኖሚክስ Principle መሰረት ዋጋ ሲቀንስ የፍላጎት መጠን ይጨምራል፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅምም ይጨምራል፡፡ ዋጋውን ተከትሎ በአቅርቦት ላይ የሚደረግ ቅናሽ ካልታየ በዚያው ዋጋ ብዙ ምርትና አገልግሎት መግዛት ይቻላል፡፡ አቅራቢው ምርቱን የሚጨምር ከሆነ ደግሞ (በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ በመነሳቱ የነዳጅ አቅርቦቱ መጨመሩን ልብ ይሏል) ገዥው የሚገዛው ምርትና አገልግሎት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ እጥረት የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ “ነዳጅ” እጅግ ወሳኝ ከሚባሉ ሸቀጦች መካከል አንዱ በመሆኑ የዋጋው መቀነስ በሌሎች ምርቶችም ላይ የዋጋ መቀነስን ማስከተሉ የማይቀር ነው (“እንዴት” ለሚለው መልሱን ለናንተ ትቼዋለሁ፤ ይህ ማንም ሰው ሊረዳው የሚችል rudimentary economics ነው እንጂ የኒውክለር ሳይንስ አይደለም)፡፡
በሀገራችን የሚተመነው የነዳጅ ዋጋ ግን “ፍላጎት” እና “አቅርቦት” የተሰኙትን ወሳኝ የኢኮኖሚክስ እርከኖችን የሚከተል አይደለም፡፡ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ነበር የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጣሪያ የነካው፡፡ ባልሳሳት በዚያን ጊዜ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ዘይት ዋጋ 138 ዶላር የደረሰ ይመስለኛል (አንድ ወዳጄ 168 ዶላር ነበረ ብሎኛል)፡፡ በወቅቱ በሀገራችን ውስጥ የቤንዚን ዋጋ በሊትር ሰባት ብር በመግባቱ “ጉድ ነወ” ያላለ ሰው አልነበረም፡፡ ከዓመት በኋላ ግን የዓለም ኢኮኖሚ ግልብጥብጡ ወጥቶ የነዳጅ ዋጋ መንሸራተት ጀመረ፡፡ እነሆ በዚያን ጊዜ የጀመረ እስከ አሁን እየተንሸራተተ 28 ዶላር ገብቷል፡፡ በኛ ሀገር ውስጥ ግን የዓለም ዋጋን ተከትሎ የተደረገ ማስተካከያ አለን??… እስቲ መልሱልን እባካችሁ፡፡
የዛሬ ዘጠኝ ዓመት የነበረው የነዳጅ ዋጋ በዓለም ደረጃ በ400% ቀንሶ እኛ ሀገር የሚከፈለው ተመን ሰማይ ጠቀስ ነው፡፡ እስቲ ጉዳችንን እዩት፡፡
(ምንጭ: አፈንዲ ሙተቂ/Afendi Muteki ፌስቡክ ገጽ)
<!–
–>