Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ለኦሮሞም፣ አማራም ሌም በትንሹ ኢትዮጵያዊነት በትልቁ ሐበሻዊነት እሱነቱ ነው! [ሰርጸ ደስታ ]

$
0
0

UNIty  - satenaw 9ቋንቋችን ብዙ ነው! ዘራችን ድብልቅልቅ እንጂ አንድ ነው፡፡ ታላቁ ነብየ እግዚአብሔር ኤርምያስ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነበር ዥንጉርጉርነቱን …. ይለናል፡፡ ጥንታዊው እትም ኢትዮጵያዊ አበባ መልኩን ነበር ዥንጉርጉርነቱን ይቀይር ዘንድ ይቻለዋልን? ይላል፡፡ ቃሉ በትክክለም ሐበሻ (ድብልቅልቅ) የሚለውን ቃል ለመጠቆም ነው፡፡ በኤርምያስ ዘመን ኢትዮጵያውያኖች ከሌሎች ሕዝቦች የተለየ መልክ እንዳላቸው መጻፉ ልዩ ሕዝብነቱን ለማሳየት ነው፡፡ አማራም ኦሮሞም፣ ሶማሌም፣ ሌላውም ኢትዮጵያዊ ሐበሻ ነው፡፡ የሐበሻ ምድር ሰፋ ብሎም የመንን፣ሱዳንን፣ ጥንታውያን ግብጻውያንን  ሁሉ ያካትታል፡፡ ዛሬ በጠባቧ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ በተለይ በጣም በዘር የተቀራረበ ግን በቋንቋ የበዛ ሕዝብ እንደሆነ ለማስተዋል ኢትዮጵያውያንን በቀጥታ ዞሮ በማየት አስገራሚ የሕዝቡን ትስስርና የመልክ፣ የባሕልና ሌሎችም እሴቶች መጋራትን መየት በቂ ነው፡፡ በዘር ኦሮሞ፣ አማራ፣ጉራጌ ምናምን የሚባል ሕዝብ እንደሌለ ባውቅም ዛሬ ላይ በዘረኝነት በጠበብነበት በተለከፍንበት ዘመን ይህንን ስናገር ማን ይቀበለኛል፡፡ ፍጹም ኦሮሞኛ ተናጋሪው ቄለም ወለጌ በደም ሰሜን ጎንደሬ ጋር አስገራሚ ቅርርብ ቢኖረው አያስገርምም፡፡ ኦሮምኛም አማርኛም ቋንቋዎች እንጂ ዘር አይደሉም፡፡ ከጥቂት ዘመናት በፊት ዛሬ አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ አካባቢዎች ብዙ ሌሎች ቋንቋዎች ይነገሩበት እንደነበር ማንም ማስተዋል አልቻለም፡፡ ዛሬ ኦሮምኛ በሚነገርባቸው ብዙ ቦታዎች እንዲሁ ብዙ ሌላ ቋንቋዎች ይነገርበት እንደነበር ማሰብ አልፈለግንም፡፡ ሸዋን ላስተዋለው ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ጥቁር እንጭኒ የጉራጌ ሕዝብ እንደነበር ቢታወቅም ከዛ ቀደም ግን አማራ፣ ትግሬ ከመባሉ በፊት ሊሆን ይችላል የሐበሻ ነገስታት ዘሮች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ግንደበረት በግልጽ በ15ኛው መቶ የሸዋ ነገስታት የነበሩ የእነ አጼ ልብነድንግል ዘሮች እንደሆኑ በግልጽ በታሪክ የተመዘገበ ነው፡፡ ወንጪን ለተመለከተ ዛሬም ድረስ ከኦሮምኛው ገንጠል ያለ ዜይ የሚናገሩ ሕዝቦች ያሉበት ከሰሜን መጠተው የሚኖሩ ጥንታዊያን ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ነው፡፡ የዜይ ሕዝብን በዝዋይ ደሴቶችም እናስታውስ፡፡

የጋፋት፣ የዳሞት እና የመሳሰሉት ቋንቋዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጎጃም፣ ወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች እንደሚነገሩ ይነገራል፡፡ እዛው ጎጃም እንቀጥልና እስከቅርብ የሚታወቁ ሌሎች ቋንቋዎች እንደነበሩ እናያለን፡፡ ኦሮምኛ በብዙ ወሎ፣ ጎጃምና፣ ጎንደርም እንደሚነገር ለማስተዋል የአንዳንድ አካባቢዎችን ሥም በኦሮምኛ ቃል ተሰይመው እናያለን፡፡ ወሎ እስከቅርብ ጊዜ ኦሮምኛ በሥፋት የሚነገርበት ነበር ዛሬ ጠቦ በከሚሴና ባቲ ቢወሰንም፡፡ ይሄ ሂደት እንጂ የብሔረሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ከመዳወላቡ የተነሳ ኦሮሞ ሰሜን ሄዶ ሳይሆን ከመሠረቱም የዚህ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይልቁንም ከሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል ምን አልባትም ከኤርትራ ቀይባሕር ወደ ደቡብ ተጉዘው እንደገና ወደ ሰሜን ሲመለሱ ልክ እንደ አዲስ ሕዝብ ታይተው በታሪክ ስህተት እንደተፈጸመ ለሚያስተውል ብዙ ጠቋሚ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ እውነት በታሪክ ተመራማሪ ነን በሚሉ አልሰማንውም፡፡ ይልቁንም የሚመነዝረንን ያልሆንውን እንደሆንን ይነግሩናል፡፡

በደቡብ ሂዱ ኮንሶን ከኩናማ ቢመሳሰል ለምን ይገርመናል? ደራሼ ከሺናሻ መግባባት በሚችሉበት ደረጃ ቋንቋቸው ቢሚመሳሰል ምን ያስገርማል?  ኮሬ (ደቡብ-አማሮ) መሠረታችን ሰሜን ኢትዮጵያ እንደሆነ ቢነግሩን ለምን ይደንቀናል?   ወላይታና ሌላውም እንዲሁ፡፡

እንዲህ ተወሳስበን ያለን ሕዝቦች ዛሬ በምንናገረው ቋንቋ ብዛት ራሳችንን መንዝረን ትንንሽና አቅመቢስ ሆንን፡፡ ኢትዮጵያዊነት በትንሹ ሐበሻዊነት በትልቁ በትክክልም ማንነታችን ነው፡፡ አማራና ትግሬ አበሻ ኦሮሞ፣ ከምባታ ሐበሻ ያልሆነ ሕዝብ አይደለም፡፡  አሁን አሁን እየወጡ ያሉ ሳይንሳዊ የመለዘር (ጄነቲክስ) ጥናቶች በግልጽ የሚናገሩት የኢትዮጵያን ሕዝብ አስደናቂ የዘር መወሳሰብን ነው፡፡

ዛሬ ላይ በቋንቋችን ብዛት ራሳችንን መንዝረን ትንንሾችና አቅመቢስ መሆናችን ሳያንስ ለሌላውም ግራ አጋቢዎች ሆነናል፡፡ ሰሞኑን በየአገራቱ የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችን ለተመለከት ማንነታችንን ለመረዳት ያዳግታል፡፡ ዘጠኝ ሆነን ሰላማዊ ሰልፍ ብንወጣ ዘጠኝ የተለያየ ባንዲራ አለን፡፡ ባንዲራ ማለት አገርን የሚወክል ምልክት ነው፡፡ ለብዙ ኦሮምኛ ተናጋሪው ዲያስፖራ የአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራ ያስደነብረዋል፡፡ ይህ ባንዲራ የአባቶቹ አጥንትና ደም ምልክት እንደሆነ ማሰብ አልፈለገም፡፡ ወያኔና አጋሮቹ ከዚህ ነጥለውታል፡፡ ሌላውም እንደዚያው፡፡ በሌላውም እንደዛው ነው፡፡ አንድ የሚያደርገን በትንሹ ኢትዮጵያዊነታችን በትልቁ ሐበሻዊነታችን ነው፡፡ ይሄ በእንዳቸውም በየአገራቱ የተደረጉ ሰልፎች ላይ ሲንጸባረቅ አይታይም፡፡ መፈክሮቹም አሳዛኝና የዘሬን ብተው ይመንዝረኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ናት! ኢትዮጵያ የአማራ ናት! …. ምን አመጣው? ነው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ዝርዝር ለማሳወቅ? እንድህ በወረደ ዘረኝነት ዘቅጠንና በዘረኛው ቡድን  መንፈስ ተጠምቀን አንድነት አለን ብንል እንኳን የሚያስብ ሰው ይቅርና የምናልፍባቸው የሰላማዊ ሰልፍ ጎዳናዎች ይታዘቡናል፡፡ ያለኢትዮጵያዊነት ነጻነት አለ ብላችሁ የምታምኑ ቆይታችሁ ታዩታላችሁ፡፡

ኦሮሞ፣ አማራ፣ ምናምን እያለ ጀምሮ ሻምቡ፣ ሐረቶ፣ ሞጣ ዳሞት እያለ እንዴት ስርቻ ውስጥ እንደገባን ያለፍንባቸው 25 የጎጠኝነት አመታት ግልጽ አሳይተውናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያባነነው ይሄ ነው፡፡ ለዲያስፖራው ከአገር ሲወጣ የሰፋትን የሰፈሩን አስተሳሰብ አሁንም እዛው ሲድፈነፈን እናየዋለን፡፡ ችግሩ በተፈጠረበት መንገድ ችግርን መፍታት አይቻልም ይለናል ታላቁ ምሁር አይንሽታይን(አይንስታይን)፡፡

ለኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ይህ የቁርጥ ቀን ነው! አቅማችንን ላሳጣን ዘረኝነት ባርነት እየተገዛን ነጻነት የለም፡፡ ነጻነታችንን ያጣንው በዘረኛና አረመኔ ቡድን ነው! 25 ዓመት አረመኔውን ቡድን ዕድል የሰጠው ሕዝብን በዘር በመሸንሸኑ እንደሆነ እያወቅን ራሳችንን ከዚህ ልክፍት ሳናጸዳ ወያኔን መኮነን አዚም ካልሆነ ምን ይባላል? ኢትዮጵያ የኦሮም ናት! የአማራ ናት! ብሎ መፈክር ምን የሚሉት ነው? ማን አደለችም አለ? ችግሩ ራሳችንን ከኢትዮጵያዊነት አመክነን እንጂ! ኢትዮጵያ የዜጎቿ ሁሉ ነች! ሌላም ሕዝብ ወደፊት ይመጣባታል ኢትዮጵያዊ ተብሎ ይኖርባታል! ከጥንትም ጀምሮ ኢትዮጵያ እንዲህ ነች! እባካችሁ ዲያስፖራዎች ተለመኑን የሕዝብን መከራ አታራዝሙ! ከመቼውም ይልቅ ኢትየጵያዊነት የተፈለገበት ወቅት አሁን ነው! በአረመኔ አገዛዝ ሥር ሆኖ ነብሱን እየሰጠ ስለሚታገለው ሕዝብ ብዬ እለምናለሁ! አንድነታችን ቢያንስ በኢትዮጵያዊነት ካሌለ ጉልበት የለንም፡፡ ሕዝብ አፋጣኝ የትግል ውጤት ይፈልጋል! ኢትዮጵያዊነታችንን መጠበቅ ካልቻልን ኦሮሞነት፣ አማራነት ሌላውም ቀጥሎ እየተሸራረፈ ወደየ መንደሩ እንደሚመነዘር እመኑኝ፡፡ በእርግጥም በ25ዓመታቱ የዘርኝነት አገዛዝ ምልክቶቹን በግልጽ አይተናል፡፡ ወያኔ በትክክልም የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡ የአገሬ ልጆች፣ ኢጆሌ ቢያ አባካችሁ! ተለመኑ የሕዝባችን ሰቆቃ ይመመን!

እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ

ሰርጸ ደስታ

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles