Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የህዝብ ደም የፖለቲካ ፀበል አይደለም!

$
0
0

ዱሮ እረኞች በነበርንበት ጊዜ ታላላቆቻችን ይሰበሰቡና እኛን ታናናሾቻቸውንን ጠርተው እርስ በርሳችን ትግል እንድንጋጠምና አሸናፊውም ከዛ ቀን ጀምሮ ላሸናፊው አለቃና አዛዥ እንዲሆን ያደርጉት ነበር፤ ውድድሩ አንዳንድ ጊዜ ከዚህም የከፋ መልክ ነበረው። ተወዳዳሪዎች መደባደሚያ ዥልጥ (የዛፍ ግንጣይ ማለት ነው) ይሰጣቸውና ጎረምሶቹ በተሰበሰቡበት እንዲደባደቡ ይደረጋል። ተጋጣሚዎቹም በፍርሃትና ባልሸነፍም እልህ ከአይንና ጥርስ በቀር አካል ሳይመርጡ ይናረታሉ። ጎረምሶቹ (ባካባቢው አጠራር ውርጋጦቹ) በሳቅ እየተንፈራፈሩ ትርኢቱን በደስታ ይመለከታሉ። ተጋጣሚ ታዳጊዎች ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ስሜት እርስ በእርሳቸው ክፉኛ ይጨፋጨፋሉ። እጅግ የሚያሳዝን ትእይንት ነው። በመጨረሻም አቅም ያነሰውን ተጋጣሚ አሸናፊው፥ እመን፥ እያለ ያለርኽራኼ ይቀጠቅጠዋል። ተሸናፊውም ዱላ እያለቀሰ፥ በቃ አመኛለሁ፥ ይላል። ከዛ ቀን ጀምሮ ጉልቤው በተሸናፊው ላይ አዛዥ ይሆናል።

ብዙውን ጊዜ በታላላቆቻቸው አስገዳጅነት የሚደባደቡት ታዳጊዎች በጣም የሚዋደዱ ባልንጀሮች ስለሆኑ ከግጥሚያው በኋላ፥ ያጣሉን እኮ እነርሱ ናቸው። እኔ አንተን ልመታህና ልጣላህ አልፈልግም፥ ይባባላሉ። ወዲያውም ዘመኑ ያዝመራ ወቅት ከሆነ ባተር ወይም በስንዴ እንኩቶ ይታረቃሉ። “እንኩቶ” ያተሩ ወይም የስንዴው እሸት ከተነቀለ በኋላ ከዱር በሚሰበሰብ ማገዶ ዛፍ ስር በሚላማ እሳት እሸቱን ከነቁሪንባው ወይም እንቡጡንና ተክሉ ከነፍሬው እንደምንጣሮ በማያያዝ እንዲበስል በማድረግ እየታሸ የሚበላ ጣእሙ ደስ የሚል የእሸት ቆሎ ነው። በዝግጅቱ ሂደት እረኞች ግማሹ እሸት፤ ግማሹ ማገዶ ቀሪው ደግሞ እሳት በማምጣት የሚሳተፉበት የህብረት ስራ ነው። ታዲያ በጎረምሶች አስገዳጅነት የተደባደቡም ሆነ በሌላ ምክንያት የተኳረፉ እረኞች የሚታረቁት በዚህ አጋጣሚ ነው። በታላላቆቻቸው ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ሳይፈልጉ የተቀያየሙት ባልንጀሮችና አብሮአደጎች በእንኩቶ ዙሪያ ታድመው ፍቅራቸውን ያድሳሉ። ቀድሞውንም የተጣሉት ተገደው እንጂ በእርግጥም ጠላትነት በውስጣቸው አድሮና ሊጎዳዱ አስበው አልነበረምና ሌሎች በሸረቡት ሴራ ወንድማማችነታቸው እንዲፈርስ አይፈቅዱም።

የረኝነት ዘመኔን ክፉና ደግ ትውስታ የቀሰቀሰብኝ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሽፍታ መንግስታት ሰሞኑን መደለቅ የጀመሩት የጦርነት ከበሮ ድምፅ ነው። እነዚህ መንግስት ተብዬ ቡድኖች በየግላቸው ስውር አጀንዳና ጠባብ የቡድን ጥቅም ወንድማማቹን የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ ዳግም ደም ሊያቃቡ ቡራ ከረዩ ሲሉ በመስማት እረፍት የሚነሳ ብቻ ሳይሆን ህሊና የሚያደማ ክፉ ድርጊtት ነው። ይህ በደምና ባጥንት የተሳሰረና ምኑም ከምኑ የማይለያይ ህዝብ በፊት በደርግ በኋላ ደግሞ በነዚሁ ያዲስ አበባና ያስመራ ጉደኛ ቡድኖች ደም እንዲፋሰስ መደረጉ ሳያንስ አሁን ደግሞ ለሌላ ዙር የእርስ በእርስ እልቂት ሲያዘጋጁት ማየት በእጅጉ ያንገበግባል። ከጦርነትና አፈና ውጪ ህልውና የሌላቸው ቡድኖች ዛሬም ከዛ ሁሉ መከራ በኋላ እንኳን በናፍቆት የሚተያየውን ህዝብ ለየግል የፖለቲካ ግባቸው ጭዳ ሊያደርጉት ራሱ በከፈለው ግብር የሸመቱትን ጠመንጃ እያጎረሱ ነው። ይህን እኩይ ተግባር ማንኛውም ወገን በቸልተኝነት ሊመለከተው ጨርሶ አይገባም። እናም ለሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ ወገናዊ ጥሪ አለኝ።

ወንድማማች ለሆንከው የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰራዊት!

ዱሮም ቢሆን በወንድምህ ላይ ክንድህን ክንድህን የምታነሳበት በቂ ምክንያት አልነበረህም። አለቆችህ በፈጠሩት ያገር ተደፈረ ማጭበርበሪያ ጩኸት ያለአግባብ ተላልቀሃል። በከንቱ በዚያ አሳዛኝና ከንቱ ጦርነት ያለቁትን ከ70000 በላይ ወንድምና እህቶችህን አስብ። ካሳዛኙ የሰው ህይወትና ንብረት ኪሳራ ሌላ የተገኘ ምንን አይነት ትርፍ እንዳልነበረ አስታውስ። እናም በወንድምህ ላይ ክንድህን አታንሳ። ያለፈው ስህተት ሳይታረም ሌላ የታሪክ ስህተት እንዲፈፀም ተባባሪ አትሁን። በዘረኞችና የስልጣን ጥመኞች ሴራ ለሩብ ዘመን ተለያይቶ የነበረው ወንድማማች ህዝብ ለዘለአለም ተቆራርጦ እንዲቀር ባዲስ መልክ ለተወጠነው ሸር ስኬት መሳሪያ አትሁን።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በያለህበት!

የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ እንዲለያይ እንዳልተፈጠረ ልብህ ያውቀዋል። እስካሁን የተካሄዱት ጦርነቶች የገዢዎች እንጂ የህዝብ ጦርነቶች እንዳልነበሩም አሳምረህ ታውቀዋለህ። የእስከዛሬ ግጭቶች ገዢ ቡድኖች ስውር ስሌት የተፈጠሩ እንጂ የህዝብ ቁርሾዎች እንዳልነበሩ ገኻድ ነው። ከዛ ሁሉ እልቂት በኋላ እንኳን ሁለቱ ህዝቦች ቂም ሳይዙ በየአጋጣሚው ለመቀራረብና ለመፈቃቀድ ሲጥሩ መመልከት በልባቸው ተዳፍኖ ላለው ፍቅር ማሳያ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። በመሆኑም በገዢዎች ሴራና የተሳሳተ ፖሊሲ የተበላሸውን ህንኙነት ጠግኖ አዲስ የግንኙነት ታሪክ ለመገንባት ጥረት በሚደረግበት ባሁኑ ወቅት በህዝብ ደም የሚያተርፉ ቡድኖች በጠነሰሱት አዲስ ሰይጣናዊ እቅድ ህዝብ ዳግም ደም ሲፋሰስ በዝምታ መመልከት አይኖርብህም።

ለህዝብ ደም ደንታ የሌላቸው እነዚህ ጦረኛ መንግስታት በሰላም አደባባይ ያጡትን የፖለቲካ ትርፍ በጦር ሜዳ ለመሸመት የሚያደርጉትን ሸብረብ ማስቆም አለብህ። በውስጥና ውጪ ያለኸው ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ሁሉ እነዚህን የጥፋት መንግስታት በቃችሁ ልትላቸው ይገባል። አሁን ለፍቅር እንጂ ለጦርነት የተዘጋጀ ልብ የለንም ሊባሉ ይገባል። እናም በተገኘውአጋጣሚ ሁሉ ይህን አዲስ የጥፋት ጦርነት ዝግጅት ማስቆም አለብህ። ገዢዎች እንዲያተርፉ ህዝብ መክሰር የለበትም። ህዝብ ለህዝብ ፍቅር እንጂ ለቡድኖች ደህንነት የሚከፍለው መስዋእትነት ሊኖር አይገባም። ትርጉም በሌለው ጦርነት የማገዷቸው ታዳጊ ልጆች ሀዘን ሳይወጣልህ ዳግም የምትከፍለው የደም ግብር ሊኖር አይገባም።

በመሆኑም ወንድማማች በሆነው ህዝብ ላይ የፈጸሙት የታሪክ ነውር ሳያሳፍራቸው ዳግም የመዘዙትን  የጥፋት ሰይፍ ወደአፎቱ እንዲመልሱ መገደድ አለባቸው። በሁለቱ ህዝቦች ጠንካራ ትግል ጥፋቱ ባስቸኳይ መቆም አለበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በቸልተኝነት አጥፊ ቡድኖቹ በጀመሩት የጥፋት መንገድ ገፍተው ዳግመኛ ንፁሃን እንዲያልቁ የምንፈቅድ ከሆነ ግን እንደ ቡድን ሳይሆን እንደህዝብ ታላቅ ስህተት በድጋሚ እንዲፈፀም መስማማታችን ስለሆነ ለትውልድ የሚዘልቅ ፀፀት አትርፈን የምናልፍ መሆናችንን ልብ ልንል ይገባል።

የህዝብ አምላክ ወንድማማች ህዝቦችን ይጠብቅ!


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles