Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

አራት የሰቆቃ ዓመት በህወሓት እስርቤት (በየነ ገብራይ ከደንማርክ)

$
0
0

ክፍል 19 ፣ ወደ ፍርድቤት መመላለስና የፍርድቤቱ የመጨረሻ ወሳኔ

Woyane Prison

ባታ እስርቤት ከሰኞ እስከ ዓርብ ማታ እስረኛው ወደየክፍሉ ከተካተተ በኋላ በማግስቱ ወደ ፍርድቤት የሚቀርቡ እስረኞች በየክፍላቸው ስማቸው ይነበብና በማግስቱ ጥዋት በፖሊስ ታጅበው ጎንደር ፒያሳ እየተባለ የሚጠራ የንበረው ቦታ ወደ ነበረው ፍርድ ቤት መጓዝ የተለመደ ነበር። እኛ የኢህ አፓ አባላትና የደርግ አባላት የታሰርንበት ክፍል ወደ ፍርድቤት የሚቀርብ ስላልነበረ ለ4 ወር ያህል ጊዜ ማንም የሚመጣ አልነበርም። የፖሊስ ምርመራ ከተደረግልን ከሁለት ወር በኋላ ግን አንድ ምሽት አንድ ፖሊስ ማታ ላይ ወደ ክፍላችን መጥቶ የ5ታችን ስም ካነበበ በኋላ በማግስቱ ወደ ፍድቤት እንደምንሄድ ነገረን። ከ5ታችን አንዱ እግሩ በ1971 በወልቃይት በኢዴህ ሰዎች አስተባባሪነት በቆላ ወልቃይት በደለሳ ቖቓሕ በተካሄደው ጦርነት እግሩ ተቆርጦ በሰው ሰራሽ እገር የሚሄድ ስለነበረ እሱ እስከ ፕያሳ በእግሩ ለመጓዝ እንደማይችልና እሱ ቀርቶ 4ታችን ብቻ መሄድ እንችላለ ወይ የሚል ጥያቄ ለፖሊሱ አቅርበንለት ፖሊሱ እሱን መወሰን የምችለው ፍድቤቱ ስለሆነ ነገ የግድ መሄድ አለበት፣ በእግሩ መጓዝ የማይችል ከሆነ ለሱና አጅቦት ለሚሄድ ፖሊስ ጋሪ መከራየት ትችላላችሁ አለን።

በማግስቱ ከቁርስ በኋላ ወደ ፍርድቤት የምትሂዱ ውጡ የሚል በየክፍሉና በግቢው ሁሉ ከተነገረ በኋላ ወደ ፍርድቤት የምንሄድ ከእስረኛው ግቢ ወጥተን በአስተዳደሩ ግቢ ተሰበሰብን። ሁሉም መሰባሰቡ ከተረጋገጠ በኋላ እስረኛው በሁለት ረድፍ እንዲሰለፍ ተደረገ፣ አንድ ፖሊስ ከፊት፣ የተወሰኑ ፖሊሶች ከሁለቱ ጎን ሆነው አንድ ሌላ ፖሊስ ከኋላ ሆኖ ከባታ ትልቁ በርን አልፈን ወጣን። በየመንገዱ የነበሩቱን ሰዎች ከፊት የንበረው ፖሊስ ከመንገዱ ገለል እንዲሉ እያስደረገ፣ ሰዉ በየመንገዱ ዳር ሆኖ እየተመለከተን ከባታ እስርቤት ተንስተን የፋሲል ግንብን አልፈን ፒያስ ደርሰን አንድ ግቢ ውስጥ እንድንገባ ተደረገ። ያ እግሩ የተቆረጠውና በጋሪ እንዲሄድ የተደረገው ጓድም በጋሪ ቀድሞን ደርሶ እዛው ግቢ ውስጥ ጠበቀን።

እግቢው ላጭር ጊዜ ከጠበቅን በኋላ አንድ ፓሊስ ስማችን ጠራንና 5ታችን የኢህ አፓ አባላት አንድ ላይ አንድ ክፍል ውስጥ እንድንገባ ተደረገ። ያ ባታ እስርቤት ከሁለት ወር በፊት ቃላችንን የተቀበለን ፖሊሲና አንድ ወጣት ሴት ዳኛ የዳኛ ልብሳቸውን ለብሰው አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ጠበቁን። እክፍሉ ገብተን በራፉ አጠገብ እንደቆምን ዳኛዋ የ5ታችን ስም ካነበቡና መቅረባችንን ካረጋገጡ በኋል ለፖሊሲ ምርመራው የት ላይ ደርሷል የሚል ጥያቄ አቀረቡለት። ፖሊሱ ምርማራው እንደቀጠል ነው፣ ጉዳያቸው ቋራ ድረስ በመሄድ ስለሆነ የምናጣራው ምርመራው ገና ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም፣ ስለሆነም ገና ተጨማሪ ጊዜ ያስፈገናልና ክበርት ዳኛ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጡን እጠቃለሁ አለ። ዳኛዋም ለፖሊሱ በጠየቀከው መሰረት የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶሃል፣ ስለሆነም እናንተም አሁን ወደ ማረፊያ ቤቱ ትመለሱና ከ14 ቀን በኋላ ተመልሳችሁ እንድትቀቡ ብለው ከክፍሉ እንድንወጣ አዘዙ። ከፍርድቤቱ ከመውጣችን በፊት ለክብርት ዳኛ መግለጽ የምንፈልገው ሃሳብ ስላለን እንዲፈቀድልን በትህትና እንጠቃልን የሚል ጥያቄ ስላቀረብን ዳኛው ባጭሩ አንዳችሁ አቅርቡ ሲሉን፣ እኔ በመጀመሪያ ቋራ ድረስ ጉዳዩን ለማጣራት ካስፈለገ ቋራ ድረስ መኬድ ያለበት የአንደኛ ጓድ ጉዳይ ብቻ ለማጣራት ነው መሆን ያለበት። የ4ታችን በስም በመጥቀስ የ4ታችን ጉዳይ ለማጣራት ከሆነ ፖሊሱ መሄድ ያለበት ቋራ ሳይሆን ሱዳን ገዳሪፍ ከተማና የተዋባ የስደተኞች ሰፈር ነው።

ምክንያቱም 4ታችን የዛሬ 1ዓመት ከ4ወር በፊት ከሱዳን በሱዳን የደህንነት ሰዎች ታፍነን ለህወሓት መተማ ላይ ተርክበን አዘዞ፣ 06 ፣ መቐለ ማእከላዊ እስር ቤት ስንከራተት የቆየንና አሁን ደግሞ ባታ እስር ቤት የምንገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ገና በደርጉ አገዛዝ ዘመን የለቀቅንና በስደት ዓለም ከ10 ዓመት በላይ ትደርና ኑሮ መስርተን ስንኖር የነበርን ሰዎች ስለሆን ክቡር ፍርድቤት ይህን አውቆ ፖሊሱ የማጣራቱን ሂደት እቀጥለዋለሁ ካለ ወደ ሱዳን ሂዶ እንዲያጣራ እንዲያዝልን በትህትና እንተይቃለን አልኩ። ዳኛዋም ቅድም ባልኩት መሰረት ከ14 ቀን በኋላ እንድትቀርቡ ለዛሬ በዚህ አብቅተናል ሲሉን፣ ሌላም ተጨማሪ ችግር አለብንና ችግራችንን ለክቡር ፍርድቤት ለማስረዳት ይፈቀድል የሚል ጥያቄ በድጋሚ አነሳን። ዳኛዋ ምንድነው ችግራችሁ ሲሉን፣ አንደኛው ጓድ እግሩ የተቆረጠና ከባታ ወደ ፒያሳ መመላለስ ስለማችል ዛሬ ለሱና ለአጃቢው ለጋሪ ከፍለን ነው ያስመጣነው፣ ስለሆንም የጉዳያችን ምርመራ አንድ ዕልባት እሰክሚያገኝ ጓዱን በየጊዜው እየከፈልን በጋሪ ማመላለስ ስለሚከብደን ወደ ፍርድቤት ስንጠራ ጓዱ እዛው ባታ ቀርቶ 4ታችን ብቻ እንድንመላለስ ለእስርቤቱ ትእዛዝ እንዲያስተላልፉልን በትህተና እንጠይቃለን አልን። ዳኛዋም ጥያቄያችንን ተቀብለው ከመጀመሪያዋ ቀን በኋላ ወደ ፍርድቤቱ ስናደርገው የነበረ መመላለስ 4ታችን ብቻ እንዲሆን ተደረገ።

ከ14 ቀን በኋላ በድጋሚ ወደ ፍርድቤት ስንቀርብ ያ መጀመሪያ የመረመረን ፖሊስና እኒያ መጀመሪያ ያገኘናቸው ወጣት ሴት ዳኛ እክፍሉ ውስጥ ጠብቀውን ዳኛዋ ምርመራው ምን ላይ ደረሰ ብለው ፖሊሱን ሲጠይቁት ፖሊሱ ገና በማጣራት ላይ ነን፣ የማጣራቱ ሂደት ገና ስላላለቀም ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን አለ።ዳኛዋም ያለ ምንም ጥያቄ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ በጠየቀው መሰአት ተጨማሪ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶታል ብለውን ምንም ሳንናገር ወጥተን ሄድን። ከ28 ቀን በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ ስንቀርብም ያ የተለመደው ፖሊሲና ዳኛዋ ሌላ ተጨማሪ 14 ቀን ተስማምተው ከ32 ቀን በኋላ እንድንቀርብ ተወሰነ። ዳኛዋም ፖሊሱም አድርጉ የተባሉትን ለእንጀራቸ ሲሉ እያደረጉ የነበሩ ምስኪኖች መሆናቸው ገና እኛን ማየት ሲጀምሩ ከፊታቸው በግልጽ ይነበብ ስለነበረ በኛ በኩል ምንም ሳንላቸው በየ14 ቀኑ መቀጠሩ ቀጠለ። 4ኛ፣ 5ኛ እያለ በየ14 ቀን ከባታ ወደ ፒይሳ መመላለሱ ለ19 ጊዜ በየ14 ቀኑ ሳይቋረጥ ቀጠለ። እኛም፣ አንደኛ ከእስርቤቱ ወጣ ብለን የውጩን አየር ለመቀበል፣ እግራችንን ለማፍታታትና ከተማውንና ህዝቡን ለማየት መመላለሱን ስላልጠላነው ዝም ብለን ቀጠሮ አላችሁ የተባልን ቀን ሁሉ ከባታ ወደ ፒያሳ በየ14 ቀኑ መመላለሱ ለ9 ወር ያህል ጊዜ ሳናቋርጥ ቀጠልን። በ20ኛው ቀጠሮ ዳኛዋ ፊት ስንቀር ዳኛዋ የናንተ ጉዳይ ከዚህ ፍርድቤት ዓቅም በላይ ስለሆነ ጉዳያችሁ ለከፈተኛ ፍርድቤት ተላልፏል፣ ከፈተኛ ፍርድቤት ጉዳያችሁ ለማየት በሚችልበት ጊዜ ወደዛ እንድትቀርቡ ለእስርቤቱ ትእዛዝ ይልካልና እስከዛው እዛው ጠብቁ ብለው ከ9 ወር ማመላለስ በኋላ አሰናበቱን።

ወደ ባታ እስርቤት እንደተመልስን ስለ ከፍተኛ ፍርድቤት ምንነትና ወደ ፍርድቤቱ ስንቀርብ ምን ማለት እንዳለብን ከአንዳንድ ስለ ፍርድቤቱና ህግ ከሚያውቁ እስረኞች ስለ ህጉና ምን ማለት እንዳለብን ምክር ጠይቀን አስፍላጊ ዝግጅት ሁሉ አደረገን የከፍተኛ ፍርድቤት ጥሪ መጠባበቅ ጀመርን። ከአንድ ወር በኋላም ከፈተኛ ፍርድቤት እንድንቀርብ ተደርጎ ለ21ኛ ጊዜ ከባታ ወደ ፒያሳ ሄድን። በ21ኛ ጊዜ የቀረርብንበት ፍርድቤት 3 ዳኞች የነበሩት፣ ዳኞቹ የሚቀመጡበት ቦታ ከፍ ብሎ፣ ባለጉዳዮች የሚቆሙበትና ተመልካች ህዝብ የሚቀመጥበት ቦታ ተለይቶ የተዘጋጀበትና ሰፋ ያለ ኡነትም ፍርድቤት የሚመስል ነበረ። በክፍሉም በርከት ያለ ታዛቢ ህዝብ ነበር። ወደ ፍርድቤቱ እንደገባን ሶስቱ ዳኞች ከቦታቸው ተቀምጠው አንድ የሆነ ካባ የሚመስል ነገር የለበሰ ሰው ከነሱ ዝቅ ብሎ ተቀምጦ ተመለከትን። እኛ መያዝ ያለብን ቦታችን ከያዝን በኋላ ከሶስቱ ዳኞች ማኸል ላይ የተቀመጡት ዳኛ ስማችንን አንብበው መቅረባችንን ካረጋገጡ በኋላ ዝቅ ብሎ ተቀምጦ ለነበረው ካባ የለበሰ ሰው፣ ዓቃቤ ህግ ክስህን ማቅረብ ትችላለህ አሉት። ዓቃቤ ህግም ከተቀመጠበት ተንስቶ እነዚህ ሰዎች መንግስት ያቀረበለትን የሰላም ጥሪ ረግጦ መንግስትን በጠመንጃ ሃይል ለመጣል እየታገለ ያለ ጸረ ሰላም የሆነው ኢህ አፓ የሚባል ድርጅት አመራር አባላት መሆናቸውን ደርሰንበታል፣ በግልም ሆነ በቡድን ስለፈጸሙት ዝርዝር ወንጀል ግን ፖሊስ ገና ምርመራውን አሟልቶ ስላልጨረሰ፣ ጉዳያቸው ገና በማጣራት ላይ ነን። የሰዎቹ ጉዳይ ለማጣራት ደግሞ እስከ ቋራ ደረስ ሁሉ መሄድ ስለሚያስፈልግ ደግሞ ክቡር ፍርድቤት ረዘም ያለ ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን በማት ሃሳቡን አቀረበ።

ዳኞቹ የዓቃቤ ህጉን የክሱ ጭብጥ ካዳመጡ በኋላ፣ የማኸል ዳኛው ወደ ሌላ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት፣ ዓቃቤ ህግ የሀገሪቱን ሰላም ማወክ በሚል ከባድ ክስ ነው የመሰረተባችሁና የግድ ጠበቃ ያስፈልጋችኋልና ጠበቃ ራሳችሁ መቅጠር ትችላላችሁ ወይስ መንግስት ይቅጠርላችሁ የሚል ጥያቄ አቀረቡልን። አስቀድመን እኔ ሁሉንም ወክዬ እንድናገር በተስማማነው መሰረት እኔ ክቡር ፍርድቤት ለመናገር ይፈቀድልኝ ብዬ ጠየቅኩ። ሶስቱ ዳኞች ትንሽ በሹክሹክታ ከተነጋገሩ በኋላ የማኸል ዳኛው መናገር የፈለግከውን አሳጥረህ መናገር ትችላለህ አሉኝ። ክቡር ፍርድቤት ጠበቃ የስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለውን ከመወሰናችሁ በፊት መንግስት እኛ ላይ ስለፈጸመው ዘግናኝ ግፍ ትንሽ እንድል እንዲፈቀድልኝ በትህትና እጠይቃለሁ ሲል፣ ዳኛው ቀጥ አሉኝና፣ በርግጥ 5ታችንም አዎ የኢህ አፓ አባላት ነን። 4ታችን ኢትዮጵያን ለቀን በስደት ሱዳን መኖር ከጀመርን ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠርን ኢትዮጵያን ከ10 ዓመት በላይ ረግጠን የማናውቅ ዜጎች ነን። 4ታችን በ1984 ግንቦት መጨረሻ ከሱዳን ገዳሪፍ በሌሊት ከተኛንበት በሱዳን ደህንነቶች ታፍነን መተማ ላይ የሱዳን ደህንነቶች ለህውሓት አስረክበውን አዘዞ፣ 06 ፣ መቐለ ማእከላዊ እስርቤት፣ አሁን በመጨረሻ ደግሞ ባታ እስርቤት ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በመንከራተት ላይ ያለን ንጹሃን ዜጎች እንጂ ጸረሰላም የሆን ሰዎች ፈጽሞ አይደልንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ጸረ ሰላም ተግባር መፈጸም ቀርቶ እኛ ኢትዮጵያን ከ1970ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ከለቀቅን በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ የረገጥናት በ1984 ግንቦት እንደ እስረኞች እንጂ እንደ ነጻ ዜጎች ወይም እንደ ታጠቁ ታጣቂዎች ፈጽሞ አይደልም። ከዚህ በተጨማሪ ዓቃቤ ህግ እንዳለው አንዳችንም የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል ኣይደልንም፣ በርግጥ በተለያየ የፓርቲው የተለያየ የሃላፊነት እርከን ላይ ስንሰራ የነበርን ሰዎች ብንሆንም አንዳችንም የከፈተኛ አመራር አባል አይደለንም። በተጨማሪም ከ5ታችን አንዱ ብቻ ነው ከቋራ በኢህ አሰና በህወሓት ሰራዊት መካከል በተደረገወ ጦርነት የተማረከውና የሰራዊቱ አባል የነበረው፣ 4ታችን ከ1970ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ በኋላ ከፓርቲው የውጭ ክፍል እንጂ ከሰራዊቱ ጋራ ምንም ግኑኝነት የለንም። ፍርድ ቤቱ ካስፈለገው ኢህ አፓ ፈጽሞ ጸረ ሰላም ሃይል አንዳልሆነ፣ አሁን በቋራና አከባቢዋ በኢህ አሰና በህወሓት መካከል እየተካደ ያለው ጦርነት በህወሓት ፍላጎትና እቅድ መሰረት እንጂ በኢህ አፓ ፍላጎትና እቅድ እንዳልሆነ ከነማስረጃው በሰፊው ለማሰረዳት እንችላለን። ስለሆንም ዓቃቤ ህግ የአራታችን ጉዳይ ማጣራት ካስፈለገው ሰዎቹን መላክ ያለበት ወደ ቋራ ሳይሆን ወደ ሱዳን በተለይ ደግሞ ወደ ገዳሪፍ ከተማና የተዋባ የስደተኞች ሰፈር ነው መሆን ያለበት አልኩኝ።

ዳኞቹ በነገሩ ግራ ተጋብተው ትንሽ ካንሾካሸኩ በኋላ እዛው እኛና ታዛቢው ህዝብ ፊት በመንሸኳሸክ ለረጂም ጊዜ መነጋገሩን ስላልፈልጉ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ተመልሰን እንመጣለን ጠብቁን ብለው ከፍርድ ቤቱ በጓሮ በር በኩል ወጥተው ሂዱ፣ እኛም ቁመን ከነበርንበት ቦታ ላይ ከነበሩ አግዳሚ ወንበሮች ተቀምጠን መጠባበቅ ጀመርን። በግምት ከአንድ ሩብ ሰዓት በኋላ ዳኞቹ ተመልሰው ሲመጡ ሁሉም እክፍሉ የነበረ ሰው ተንስቶ ከተቀበላቸው በኋላ ታዛቢዎቹ ሲቀመጡ እኛ እንደቆምን የማኸል ዳኛ ጉዳያችሁን መርምረንና አጥንተን እንዴት እንቀጥላለን የሚለውን ለመወሰን ከ28 ቀን በኋላ እንድትቀርቡ ወስነናልና ከ28 ቀን በኋላ ቅረቡ ብለውን ወደ ባታ ተመለስን። ከ28 ቀን በኋላ ወደ ከፍተኛ ፍርድቤቱ ስንመለስ ልክ እንደገባን የማኸል ደኛ ፍርድቤቱ ዓቃቤ ህግ እናንተ ላይ ያቅረበው ክስና እናንተ በክሱ ላይ ያቀረረባችሁትን ተቃውሞ በጽሞና ከመረመረ በኋላ አሁንም ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልገው በሙሉ ድምጽ ተስማምቷል። ፍርድቤቱ ምርመራውን ካበቃ በኋላ ወደ አንድ ውሳኔ ይደርሳል። ያ ፍርድቤቱ የሚደርስበት ውሳኔም እዛው በእስርቤቱ በእስርቤቱ አስተዳዳሪዎች አማካይነት ይነገራችኋል። ስለሆነም እናንተ ከንግዲህ ወደ ፍርድ ቤቱ መመላለሱ አያስፈልጋችሁም፣ ውሳኔያችሁ እዛው እስርቤት ሆናችሁ ተጠባበቁ ብለዉ አሰናበቱን። ከባታ ወደ ፒያሳ በየሁለት ሳምንት ለአንድ ዓመት ያህል ከተመላለስን በኋል ጉዳዩ በእንዲህ ዓይነት መልክ ተጠናቆ የፍርድቤቱ በእስርቤት ውሳኔያችሁ ይነገራችኋለል የተባልነውም ምንም ውሳኔ ሳይነገረን በባታ እስርቤት 3 ዓመት ያለ አንዳች ጥያቄና ግኑኝነት እንዲሁ አለፈ።

በክፍል 20 ፣ በባታ እስርቤት የ3 ዓመት ቆይታና፣ ከ3 ዓመት ቆይታ በኋላ በድንገት ተፈትታችኋል የሚለው ውሳኔ በተመለከተ በክፍል 21 ይጄላችሁ እቀርባለሁ። እስከዛው በቸር ሰንብቱ።
በየነ ገብራይ ከደንማርክ
btesfu45@gmail.com
0045 20545658


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles