“ትግሪኛ የሚናገሩ ደርጎች” – ግርማ ካሳ
“ትላንት ራያ አላማጣ ወረዳ፣ በመረዋ አከባቢ፣ ልዩ ስሙ ሶረያ በተባለ የገጠር መንደር ከሶስት ቀናት በፊት የተነሱና እጅግ ልብን የሚያደሙ ፎቶግራፎች” በሚል ጦማሪ Ztseat Saveadna Ananya የለጠፈዉን አነበብኩ። “በዳስ፣ በጠራራ ፀሐይ የሚማሩ፣ የተጎሳቆሉ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ሁኔታው ሑሉ አእምሮን የሚረብሽ ነው” ሲልም ያይውን እና የታዘበው ለአንባቢያኖቹ አካፍሏል።
“መረጃዎች እንደሚያሳዩት በትግራይ ክልል 700 ገደማ የዳስ ትምሕርቤቶች አሉ፤ ይህም ከክልሉ እሩብ የሚሆኑ ትምሕርት-ቤቶችን ያጠቃላል፡፡ትግራይ ውስጥ በየትኛውም ወረዳ፣ በየትኛውም ዞን ብትሔዱ እንዲህ ዐይነቶቹ ትምሕርትቤቶች ታገኛላችሁ፡፡” ሲልም ችግሩ በመላው ትግራይ እንደሆነ ይናገራል።
ሕወሃት ትግራይን ከተቆጣጠረ ወደ 27 አመት አካባቢ አልፎታል። ሙሉ ኢትዮጵያን ደግሞ ከገዛ 25 አመተ በቅርቡ አከበረ። አንዳንድ ወገኖች ሕወሃት ከትግራይ ስለመጣ፣ በትግሬዎች ላይ ጥሩ ያለሆነ አመለካከት ያደረባቸው አሉ። አንዳንዶቹ ፣ በዘረኝነት በሽታ ከመበከላቸው የተነሳም ጸረ–ትግሬ አቋማቸዉን በይፋ የሚጽፉም አሉ።
በሜዳ ላይ ያለው እዉነታ ግን በጣም የተለየ ነው። ሕወሃት የትግራይ ህዝብን የጠቀመ ሳይሆን ጥቂት “ትግሬዎችን” ቱጃሮች ያደረገ ነው። በሕወሃት አገዛዝ የትግራይ ህዝብ እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኖ ደህይቷል። በቅርቡ በነበረው የረሃብ አደጋ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የትግራ ሕዝብ ነው ለዉህ ችግር ተጋልጦ የነበረው።
እንግዲህ ይሄ መከራዉን እያየ ያለ ህዝብ ነው ፣ ይሄ በሕወሃት ራሱ ላለለፉት 27 አመታት እየተገረፈ ያለን ህዝብ ነው፣ ከህወሃት ጋር አገናኝነትነው በርሱ ላይ ያለንን አመለካከትት የምናቆሽሸው?
ወገኖች የትግራይ ህዝብ ሕወሃቶችን “ትግሪኛ የሚናገሩ ደርጎች” የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል። የትግራይ ህዝብ ከሕወሃት ጎን ሳይሆን ከኢትዮጵያ አንድነት ጎን የቆመ፣ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር የተዋለደ፣ የተጋባ፣ ለዘመናት በሰላምና በፍቅር የኖረ ህዝብ ነው። የሕወሃት እኩይ ተግባራት አይምሯችንን ሊያጨለም፣ አስተሳሰባችንን ሊበክል አይገባም። በወህኒ በግፍ እየማቀቀ ያለዉን የወንድሜን ዮናታን ተስፋዬ አባባል ልዋስና “ሁሉም ለኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ለሁሉም” ነው። ኢትዮጵያውን እንወዳለን እያልን የተወሰኑ ኢትዮጵያዉያንን የምንጠላ ከሆነ ኢትዮጵያን አንወድም !!!!