* ግንቦት 20 ሲከበር
* አሸርጋጁ አደባባይ
* የግንቦት 20 ፍሬዎች
ልክ የዛሬ 25 ዓመት … የድሉ እወጃ !
=======================
በዚያች ቀን ነፍስ ያወቅን ሁላችንም የምናስታውሳት አዋጅ ተነገረች …” የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባ ሬዲዮ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲል ተቆጣጥሮታል ፣ ግንቦት 20፣ 1983 ዓ.ም ! ”
ዛሬ ማለዳ …
=========
25 ዓመት የድል ነጻነት ኢዮቤልዩ የድል በአላቸውን የሚያከብሩት የኢህአዴግና ሹማምንትና ደጋፊዎች በአደባባዩ ተገኝተዋል ፣ በኢህአዴግ ከፍተኛ ሹማምንት ፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ታድመውበታል …ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ኋይለ ማርያም ደሳለኝ ድሮ ሀገሬው ” ሰው በላ ” እያለ ያወግዘው የነበረበትን ቃል ተጠቅመው ዛሬ እሳቸው “ሰው በላ ” ያሉት ደርግ የተገረሰሰበትን የግንቦት 20 የኢህአዴግ የኢዩቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ንግግር እያደረጉ ነው … የ25 ዓመቱ የሰመረ የልማት ትራንስፎርሜሽን ስኬት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተዘረዘረ ነው ፣ በንግግራቸው ባይመስጥም በ25 ዓመታት ተደረጉ ያሏቸው እድገቶች ፣ ልማቶች ፣ የተፈጥሮ አደጋ ጋር የተደረገው ፈታኝ ግብግብ ፣ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ፣ የመልካም አስተዳደር ግንባታ ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማጥፋት እየተደረገ ስላለው ትግል ዘራዘሩ …እንዲህ የሚሏት ሀገር ሀገሬ ስለመሆኗ ተጠራጠርኩ ፣ የሆነው እውነት ከሆነ መልካም ነው ስል በትዝብት አንገቴን ደፋ አድርጌ ቆዘምኩ …
ከ25 ዓመቱን የኢህአዴግ አገዛዝ 4 ያህሉን አመታት ብቻ በሀገር ቤት ሆኘ የማውቅ ፣ ከ20 ዓመት በላይ በሳውዲ ስደት የከተምኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ ! 25 ዓመቱን አገዛዝ ፣ ኢትዮጵያውያንን እንደ መረጃ ተቀባይና አቀባይ ማሰብ በራሱ ያማል …እናም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያሉት እድገት እያለ ዛሬ ድረስ ፣ ድህነት ፣ የኑሮ ውድነት ፣ መልካም አስተዳደርና ፖለቲካው ገፍቶት ከሀገር የሚሰደደው ዜጋ እልፍ አእላፍ እየሆነ በመጣበት የታሪክ አጋጣሚ የጠቅላያችን ንግግር አልገባኝ አለ ! የእድገት ትሩፋቱ ተጠቃሚዎች ከመላው ሀገሬ ምን ያህሉ ናቸው? በ25 ዓመቱ አገዛዝ መብታችን ይከበር ባሉ የተረገጡት ፣ በጻፉና በተናገሩ ወጣትነታቸውን እድሜ የተቀሙ ፣ ለአመታት ለእስር የተዳረጉ ፣ በህገ መንግስቱ የተሰጠው መብት ይከበር ባሉ ወህኒ የወረዱ … እኒህኞቹስ ? አልኩ … አዎ በአሉ የእነሱ ሊሆን አይችልም ! ድፍን 20 ዓመት በአረብ ሀገር ስደት የተጎሳቆሉት ፣ አሁን ድረስ የመብት አስከባሪ አጥተው ለሚንገላቱት ” በአሉ በአላችን አይሆንም !” ቢሉ አልፈርድባቸውም ፣ በአንጻሩ ” በ25 ዓመቱ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ተጠቅመናል” ያሉ ሰንጋ አርደው በዓሉን ቢያከብሩት አይደንቀኝም ፣ ተጠቅመዋልና ! ለእኔ ቁም ነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብዛኛው ሀገሬ የመጣው ድል አብዛኛው ሀገሬ ተጠቃሚ ነው ወይ? የሚለው ነው ! ታዲያ ተጠቃሚ ከሆነ ሰው ሞትን እየተጋፈጠ ለምን ስደትን ይመርጣል ? ይህ አልገባኝ ብሏልና ዛሬም አጠይቃለሁ !
አሸርጋጁ አደባባይ …
==============
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግን አብቅቶ ትርኢት መታየት ሲጀምር የመስቀል አደባባይ ትዝ አለኝ …አሸርጋጁ አደባባይ ያልኩትን የመስቀል አደባባይ ” ይህ የተረገመ አደባባይ !” አልኩት በልቤ … መንግስት በሄደ በመጣ ቁጥር ሰው ተመርጦ ፣ በደቦ ተጠርቶ ፣ ይሰበሰብበታል ፣ ሰው ተመርጦ ” … ይህን መፈክር በል ፣ ይህን መፈክር ያዝ … በዚህ ሂድ … ” ይባልና እንደ እውነተኛ የህዝብ ስሜት ይነገርበታል … ይህ አደባባይ ፣ ሀገሬው በኑሮ ውድነት ፣ በፖለቲካው ግለት እየታመሰ መሪዎች የሚመሯት ሀገር እድገቷ የመጠቀ ፣ መጻኤ ህይወቷ ብሩህ እንደሆነ የሚደሰኩሩባት አደባባይ በእርግጥም የመቀል አደባባይ መባል አልነበረበትም ! ቢያንስ ለሰው ልጅ ድህነት ምልክት የሆነው የመስቀሉ በዓል የሚከበርበት ቦታ ከዘመነ ደርግ እስከ ኢህአዴግ የውሸት ዲስኩር መናገሪያ ፣ የውሸት ሰልፍና ሽለላ ማሳያ አደባባይ ባልሆነ በመረጥኩ ስል ከራሴ ጋር ተሟገትኩ …
በአደባባዩ የብሔር ብሔረብ ብዝሃ ህዝብ …ትርኢቱ እንደ ቀጠለ ነው ፣ በስደቱ አለም የ 20 ዓመት መብት ማስከበር ክሽፈት ምስክር ነኝና ጠባቂ ባጣው ስደተኛ የሆነው ሁሉ ከፊቴ ድቅን አለ …
ግንቦት 20 ሳስተሰውስ ደግሞ ደርግ ትዝ አለኝ ፣ ደርግ ክፉ ነበር ፣ እንኳንም ወደቀ ! በደርግ ግፍና ጭቆና ተማርራችሁ ስለ እውነተኛ ዲሞክራሲ ደክማችሁ ላለፋችሁ ፣ ጭቆናን ተጸይፋችሁ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ስትሉ ከአባገነኑ ደርጋ ጋር ለተፋልማችሁ ክብር አለኝ ፣ እንኳን ደርግ ከወደቀበት 25 ዓመት አደረሳችሁ !
…ግን የታገላችሁበት ፣ የመጣው ድል ከብዝሃነት እስኪደርስ የሆነው ያኮራል አልልም … ሌላው ቀርቶ ሀገር የተባለውን ያህል ካደገች ለምን ሰው ይሰደዳል ? አልኩ ፣ እንደሞኝ ነገር ደጋግሜ የጠቅላያችን የዛሬ ንግግር አስታውሸ … ከራሴ ጋር መጃጃሉን ተውኩት ፣ ዝግጅቱን መከታተሉንም አቁሜ ራሴን አቀርቅሬ የአረብ ሀገሩ ስደትና የግንቦት 20 ፍሬዎች ስል በማለዳ ወጌን መሞነጫጨር ቀጠልኩ … ! የግንቦት 20 ፍሬዎች … ይቀጥላል !
ቸረ ያሰማን
ነቢዩ ሲራክ
ግንቦተ 20 ቀን 2008 ዓም