Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

5ኛው ዙር የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

$
0
0

በብዙ ትግል ጥረትና ድካም ስንት ወጪ ወጥቶበት የተዘጋጀው የማኅበረ ቅዱሳንን 5ኛው ዙር ዐውደ ርእይ እንደጠበኩት አላገኘሁትም፡፡ ጎበኘሁት ከፍቶኝ አዝኘም ወጣሁ!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ከዐውደ ርእዩ ሥያሜ ተነሥቸ በዚህ ዐውደ ርእይ ላይ ቤተክርስቲያን አሁን ያለችበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ማለትም ከደረሱባት ከባባድ ፈተናዎች የተነሣ የደረሱባትን ጉዳቶች፣ በግንባር የሚጠብቃትን ከባባድ ችግሮችና ፈተናዎች ለጎብኝዎች በሚገባ ያስገነዝባል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡

አገዛዙ “የኦርቶዶክስን አከርካሪ ሠብረናል!” በማለት እስከመግለጽ ያደረሰውን የጥፋት ድል “ወያኔ ይሄንን ይሄንን አደረገ” ባይሉም እንኳ የደረሰውን ጉዳት ግን መናገር ማሳወቅ ይጠበቅባቸው ነበር ሊያደርጉት ግን አልቻሉም፡፡ ይሄ ቀርቶ እኔ ምን እንደሆኑ አላውቅም ሌሎች ሊገለጹ የሚችሉ ነገሮችን እንኳ መግለጽ አልቻሉም፡፡

ተሽለው ያየሁት በዐውደ ርእዩ ላይ ሊገለጽ የሚገባውን ያህል ባይሆንም በተሻለ ሁኔታ የተሐድሶ መናፍቃንን ሕገወጥና አጋንንታዊ እንቅስቃሴን ተኩሎቻቸውን እያሰለጠኑ እንዴት ወደ ቤተክርስቲያን አስርገው እንደሚያስገቡ በምስለ ትዕይንት (በቪዲዮ) በተደገፈ መረጃ ማሳየታቸው ነው፡፡

የሚገርመው ይሄንን ያደረጉ ሆኖ እያለ የቤተክርስቲያን አባላት (የምእመናን) ቁጥር ያሽቆለቆለበትን ምክንያት ሲገልጹ ግን ምን ይላሉ “ሩቅ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎችን መድረስ ባለመቻሉ ነው!” በማለት ትክክለኛውን የችግሩን መንስኤ ወይም ምክንያት ከመግለጽ በመታቀብ አስቂኝ የሆነ ምክንያት ሰጥተው አረፉት፡፡

ቤተክርስቲያን በብዙ ሚሊዮን (አእላፋት) የሚቆጠሩ በጎቿ በተኩሎቹ በመናፍቃን እንደተበሉባት በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ሆኖ እያለ ማኅበረ ቅዱሳን ይሄንን እውነት ለመግለጽ ለማሳወቅ ለማስረዳት አንደበቱ ከተሸበበ ካልቻለ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ዐውደ ርእዩ እየተደረገ ያለው በከባድ ፍርሐትና ጫና ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡

ሌላው ያስከፋኝ ነገር ቢኖር “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅዱሳን ሐዋርያት ምንትስ እያለች ሰዎችን ትሰብካለች፣ የሰዎችን ታሪክ ትተርካለች፣ በስማቸው ዝክር ዘክሩ ምንትስ እያለች ታስተምራለች እንጅ ኢየሱስን አትሰብክም!” ለሚለው ከወንጌል የሚጻረር የመናፍቃን ክስ በተደጋጋሚ እየተነሣ አባቶች ሳይቀሩ እልህ በተናነቀው ስሜት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ክርስቶስን እንደምትሰብክ ማሳያዎችን እየጠቀሱ ለማስረዳት ጥረት ሲደረግ ተመልክቻለሁ፡፡ ይሄ በጣም አስከፍቶኛል ስሕተትም ነው፡፡ ስሕተት የሚሆነው ለዚህ ክስ መልስ በሚሰጥበት ወቅት “ኧረ እኛም እንሰብካለን!” የሚል ቅኝት ስላለው በተዘዋዋሪ መናፍቃኑን “ክርስቶስን ትሰብካላቹህ!” የሚል እውቅና የሚሰጥ አኪያሔድ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ክርስቶስ አንድ ነው እንጅ የክርስትና ሃይማኖት ነን በሚለው ድርጅት ቁጥር ልክ “ክርስቶስ እንዲህ ነው! እንዲህ አይደለም!” እያሉ እንደሚሰብኳቸው የተለያዩ ዓይነቶች ክርስቶሶች መዓት ዓይነት ክርስቶስ የለም!

“የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና” ዕብ. 13፤7-9

“…ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ። እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና” ማቴ. 24; 24-27

ሲጀመርም ጥያቄው ወይም ክሱ የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮ የሚጻረር አጋንንታዊ ጥያቄ ወይም ክስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የነቢያት የቅዱሳን ሐዋርያት እያለች ገድላቸውን መተረኳ በስማቸውም ዝክር (መታሰቢያ) መዘከሯ ክርስቶስ በወንጌሉ “እኔን የመቀበላቹህ ማረጋገጫው ይሄ ነው!” ስላለና ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበላችን ማስረጃ ምስክር ማረጋገጫ ስለሆነ ነው፡፡ መናፍቃኑ ደግሞ ይሄንን አለማድረጋቸው እንደ ክርስቶስ ቃል ክርስቶስን ያለመቀበላቸው ማረጋገጫው ነው፡፡ ይሄንን ያልኩት እኔ ሳልሆን በቅዱስ ወንጌሉ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ ሐዋርያቱን ትዕዛዝ ሰጥቶ ወደ ዓለም በላከበት ባሰማራበት ወቅት፡፡

“እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም”  ማቴ. 10፤40-42

እንግዲህ የኢየሱስ ወንጌሉ የሚለው ይሄንን ነው፡፡ ይሄም በመሆኑና የኢየሱስንም ቃል ሳትሸራርፍ አሟልታ መፈጸም ማክበር መጠበቅ ስላለባት ነው ቤተክርስቲያን በነቢያቱ፣ በደቀመዛሙርቱ፣ በቅዱሳን ሐዋርያቱ ስም ዝክር የምትዘክረው ስለ ክርስቶስ ሲሉ የተጋደሉትንም ገድል (በሕይዎት የተተረጎመ ወንጌል) ጽፋ የምትተርከው፡፡ ከላይ እንዳነበባቹህት የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እነሱን ሳይቀበሉ፣ በስማቸው ሳይዘክሩ ኢየሱስን መቀበል ስለሌለ ስለማይቻል ነው፡፡

ስለሆነም ነው ከላይ ክሳቸውን ከክርስቶስ ወንጌል ጋር የሚጻረር አጋንንታዊ ክስ ነው ያልኩት፡፡ ላይ ላዩን ሲያዩት ለክርስቶስ ኢየሱስ የመቆርቆር ስሜት ያለው ይመስላል ውስጡ ግን የክርስቶስን ቃል ወንጌልን የሚጻረር በመሆኑ መርዝና አጋንንታዊ ነውና “እኛም…” በማለት ይሄንን ክስ እያነሡ ማንጸባረቅ ክሱን ከትክክለኛ ቦታ እንደተነሣ ትክክለኛ ጥያቄ ስለሚያስመስል መልሱ መሰጠት ካለበትም በዚያ ቅኝት መሆን ስለሌለበት ይሄም መታረም ይኖርበታል፡፡

ሌላው ገለጻ በሚያደርጉበት ጊዜ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ የምንትስ ቤተክርስቲያን የሚል የቃላት አጠቃቀም ተመልክቻለሁ፡፡ ቃሉ የሚለው አንዲት ቤተክርስቲያን፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ መንገድ ብቻ መኖሩን ነው፡፡ ኤር. 6፤16 ኤፌ. 4፤5 ይሁ. 1፤3

በመሆኑም እነሱን መጥራት ካስፈለገ ካቶሊካዊያን፣ ፕሮቴስታንታዊያን ወዘተረፈ. በማለት መጥራት ይገባል እንጅ በኑፋቄ እየተጠለፈ በየዘመኑ እየተገነጠለ የወጣውን ሁሉ የምንትስ ቤተክርስቲያን፣ የምንትስ ቤተክርስቲያን ካልን ቤተክርስቲያንንም እራሳችንንም ማስዋሸት የእግዚአብሔርንም ቃል ማስተባበል ነውና ይሄም ሌላው መታረም ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው እዚያ ቦታ ሊቀርቡ የሚችሉ ንዋዬ ቅድሳት በሙሉ የቀረቡ ሲሆን ትእምርተ ኪዳኑን (የቃልኪዳን ምልክቱን ማለትም ሰንደቅ ዓላማውን) ግን አላቀረቡትም፡፡ ይሄም ወያኔን ያስከፋብናል ተብሎ ወያኔን በመፍራት ከቀሩት ነገሮች አንዱ መሆኑ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዐውደ ርእዮች ግን በሚገባ ከበቂ ማብራሪያ ጋር ቀርቦ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥታት ሰንደቅ አላማውን ከቤተክርስቲያን ወሰዱ እንጅ ቤተክርስቲያን አይደለችምና ከእነሱ የወሰደችው ይሄ መደረጉም ስሕተት ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ከጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አንሥቶ እስከ ጉልላቷና መንበረ ታቦቷ ድረስ ከጥንት ጀመሮ የእነዚህ ሦስት ቀለማት ማኅተም በተለያዩ መልኩ አሠራሩና ጥበባዊ ስልቱ እንዲያርፍበት ይደረጋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በዘፍ. 9÷8-17 ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር በኖሕ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ ዓለምን ዳግመኛ በጥፋት ውኃ ላያጠፋት ቃል ሲገባለት ለገባው ቃል ኪዳን ምልክትና ምስክር ትሆን ዘንድ “ቀስቴን በደመና ላይ እዘረጋለሁ የምሕረት የቃል ኪዳን ምልክት ትሁን!” እንዳለው እናያለን፡፡

አንዳንድ ሰዎች ታዲያ ሰንደቁ ቀስተ ደመና ከሆነ ለምን ሦስት ቀለማት ብቻ ሆነ? በቀስተ ደመና ውስጥ ያሉት ቀለማት ሰባት ናቸውና የሚሉ አሉ፡፡ እርግጥ ነው አትኩረን ላየነው በቀስተ ደመና ውስጥ ያሉ ቀለማት ሰባት ናቸው፡፡ ነገር ግን አራቱ ቀለማት የሚፈጠሩት በውሕደትና በውርርስ እንጅ እንደ ሦስቱ ቀለማት ማለትም እንደ ቀዩ ቢጫውና አረንጓዴው በራሳቸው ህልው ሆነው አይደለም፡፡ ቀዩ ከቢጫው ቢጫው ከአረንጓዴው ጋር ባለው መጋጠሚያ መጋጠሚያቸው ላይ በንክኪው ውሕደት ሲፈጥሩ የሚፈጠሩ ሁለት፡፡ እንዲሁም ከቀስተ ደመናው ላይና ታች ከሰማዩና ከመሬቱ ቀለማት ጋር ባለው መወራረስ ደግሞ ሌላ ሁለት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ በድምሩ 4ቱ ቀለማት ከአረንጓዴው ከቢጫውና ከቀዩ ውጭ ያሉት በራሳቸው ህልው የሆኑ ሳይሆኑ በእነዚህ በሦስቱ ቀለማት ተጽዕኖ የሚፈጠሩ በመሆናቸው ቤተክርሲቲያን ሦስቱን ዋነኛ የቀስተ ደመናውን ቀለማት ብቻ ልትወስድ ችላለች፡፡ በመሆኑም የቀስተ ደመናው ቀለማት በጉልህ የሚታዩት ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ሦስቱ ቀለማት ናቸው እንጅ ሰባት ቀለማት አይደሉም ማለት ነው፡፡

በተጨማሪም  ሦስቱ  ቀለማት ሦስት መሆናቸው በቤተክርስቲያን ካላቸው የምሥጢር ትርጉም አንዱን ብቻ ስጠቅስ የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ መሆኑ ወይም መሆናቸው ነው ትላለች ቤተክርስቲያን፡፡ ማለትም ሥላሴ (እግዚአብሔር) አንድም ሦስትም ናቸው ወይም ነው፡፡ የሚለውን ምሥጢረ ሥላሴን ለማጠየቅ ነው፡፡ ቀስተ ደመና ከቃል ኪዳን ምልክትነቱም በላይ የልዑል እግዚአብሔር የክብሩ መገለጫም ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስና ነቢዩ ሕዝቅኤል በየራእዮቻቸው ልዑል እግዚአብሔር በክብርና በሚያስፈራ ግርማ በዙፋኑ ላይ ሆኖ ዙሪያውን በሚያምርና ኅብር ባለው የቀስተ ዳመና ጸዳል ተከቦ ተመልክተውታል፡፡ ራዕ ዮሐ 4÷2-3 ትን ሕዝ 1÷26-28

እንግዲህ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን ምልክት ነው ያለውን በጉልህና በግልጽ የሚታዩትን በራሳቸው ህልው የሆኑትን ሦስት ቀለማት በመውሰድ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር እንደተሰጣት የቃል ኪዳን ምልክቷ አድርጋ በመውሰድ ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ትጠቀምበታለች፡፡ ለምሳሌ በሀገር ላይ አንዳች ችግር፣ መዓት፣ ቁጣ በሚከሰትበት ጊዜ ማለትም ጦርነት፣ ረሀብ፣ ድርቅ፣ በሽታ፣ ቸነፈር የመሳሰሉት ችግሮች ሲፈጠሩ ምንም እንኳ ቀይ ቢጫ አረንጓዴው ትእምርተ ኪዳኑ (የቃል ኪዳኑ ምልክት) የተሰጠው “መላ ዓለምን የሚያጠፋ የጥፋት ውኃ ዳግመኛ በሰው ልጆች ላይ ላያመጣ” ቢሆንም ይህችን የቃል ኪዳን ምልክት አንድ ጊዜ “የምሕረት የቃል ኪዳን ምልክት” ብሏታልና እነዚህ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜም በምሕላ ጸሎት (ወር በገባ ከ1-7 ባሉት ቀናትና ከላይ የተገለጹት ችግሮች በሀገር ላይ ሲከሰቱ የሚጸለይ የጸሎት ዓይነት) ጊዜ ፈጣሪን ከቁጣህ ተመለስ፣ በምሕረትህ አስበን፣ በቸርነትህ ጎብኘን፣ ቃልኪዳንህን አስብ!  ለማለትና ለምሕረት የገባውን ቃል አስቦ ምሕረት እንዲሰጠን ለማድረግ በጸሎቱ ሰዓት ትእምርተ ኪዳኑን ከሥዕለ አድኅኖና ከመስቀሉ ጋር ተይዞ በዐውደ ምሕረት ላይ እየተወጣ ሥርዓተ ጸሎቱ ይደረጋል፡፡

ቤተክርስቲያን በዚህ መልኩ ከጥንት ጀምሮ ስትገለገልበት እንደቆየች በአድዋ ጦርነት ጊዜ በተንቀሳቃሽ ድንኳን እየተቀደሰ አብሮ ዘምቶ ከነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ድሉን እንዳገኙ ዐፄ ምኒልክ ቀይ ቢጫ አረንጓዴውን የቃል ኪዳን ምልክት ሰንደቅ (ትእምርተ-ኪዳን) አንሥተው “ከዛሬ ጀምሮ ይህች ሰንደቅ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ትሁን!” ብለው እዛው ካሉበት አድዋ አወጁ፡፡

በእርግጥ በአዋጅ በይፋ አይሁን እንጅ ከዚያ ቀደም የነበሩ ነገሥታትም በጣም ከጥቂቶቹ በስተቀር ካህናት ማለትም ቢያንስ ዲያቆን ያልነበረ የለምና በዚህ ቅርበታቸው ይህንን ትእምርተ ኪዳን (ሰንደቅ) እንደ ሀገር ሰንደቅ አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ቀረብ ያሉትን ለማንሣት ዐፄ ቴዎድሮስን ከሳቸውም በኋላም ዐፄ ዮሐንስ 4ኛንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይሄ ለቤተክርስቲያን ከንዋየ ቅድሳት የመጀመሪያው የሆነው ንዋየ ቅዱስ በግልጽ በይፋ በአደባባይ በበዓላትም ሆነ በአዘቦት ቀን አገልግሎት እየሰጠ ያለው ጎንደርና አክሱም ብቻ ነው፡፡ በሌሎቹ ግን በወያኔ ካድሬ ካህናት የተነሣ ጠፍቷል፡፡ የአጋንንት አምላኪዎችና የአሕዛብ ምልክት የሆነው ኮከብ የተለጠፈበት ነው አብያተክርስቲያናቱን ሁሉ ሞልቶት ያለው፡፡ እናም በዐውደ ርእዩ ላይ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ዐውደ እርዮች ሁሉ ይህ ንዋየ ቅዱስ አለመቅረቡ ስሕተት ነው፡፡

ወያኔ በገዛ ሕገ መንግሥቱ ላይ እንዳስቀመጠው “መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም!” ይላልና ለሃይማኖታዊ አገልግሎት የምንገለገልባቸውን ንዋየ ቅድሳቶቻችንን ይሄንን ተጠቀሙ ይሄንን አትጠቀሙ ሊል የሚችልበት መብት ፈጽሞ ስለሌለው በዚህ ንዋየ ቅዱስ ከመገልገል መታቀብ አይገባም ነበረ፡፡ እንዲያው ነገሩን አልኩ እንጅ ወያኔ የትኛውን ሕግ አክብሮ ያውቅና!

ሌላው በቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚታወቀው ሁሉ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዐውደ ርእዮች የምሥራቅ አብያተክርስቲያናት ወይም አኃት አብያተክርስቲያናት በመባል የሚታወቁት አምስት ነበሩ፡፡ እነሱም የኢትዮጵያ፣ የግብጽ፣ የአርመን፣ የሶሪያና የሕንድ ናቸው፡፡ እዚህኛው ዐውደ ርእይ ገለጻ ሲደረግ ስንሰማ ግን ስድስት አድርገዋቸው አረፉት፡፡ ግራ ገብቶኝ ቆየሁና “ደሞ ማን ተጨምሮ ነው ስድስት የተሆነው?” ብየ ገለጻው ካለቀ በኋላ ባነሩን (የማስታወቂያ ሸራውን) ተጠግቸ ተመለከትኩት፡፡ ስድስተኛ ተብላ የተጠቀሰችው “የኤርትራ ቤተክርስቲያን” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም ገለጻ ለሚሰጡት ወንድሞች ፍጹም ስሕተት መሆኑን ገለጽኩላቸው፡፡

ይሄ እንግዲህ ሌላኛው ወያኔን በመፍራት የተፈጠረ ለውጥ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ላይ በጊዜያዊ የታሪክ አጋጣሚ የግዛት አንድነቱ ስለፈረሰ ብቻ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም እንደተከፈለች እየቆጠርን አኃት እያልን ቁጥር የምንጨምር ከሆነማ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናትንም ያሉበትን ሀገር ስም እየጠራን የእከሌ የእከሌ እያልን አኃት አብያተክርስቲያናት እያልን እንጥራቸዋ ታዲያ!

ይሄንን ስል እዚያ ኤርትራ ያሉ ሀገሪቱ ከመከፈሏ በፊት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ገዳማት አብያተክርስቲያናት አባቶችና ምእመናን የነበሩት ዛሬ ላይ ፓትርያርክ ሠይመው እየተገለገሉ መሆኑን አጥቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን ይሄ የሆነው በፖለቲከኞች ጫናና ግፊት በመሆኑ ለዚህ ሕገ ወጥ ተግባር እውቅና ሰጥቶ እነሱ የሚሉትን ተቀብሎ ማስተጋባት ፍጹም ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያን ካርታ (ምስለ ምድር) በሚያሳዩበት አጋጣሚ ሁሉ የተገነጠለችውን ኢትዮጵያን ነበር የሚያሳዩት፡፡

ይሄንን ማድረግ አልነበረባቸውም፡፡ ምክንያቱም የትኛውንም ሙዚየም (ቤተ ቅርስ) ብትጎበኙ ተሰቅለው የሚታዩት የኢትዮጵያ ካርታዎች (ምስለ ምድሮች) ሙሉው ወይም ያልተቆረጠችውን ኢትዮጵያን ነው፡፡ ሙዚየሞች (ቤተ ቅርሶች፤ ቤተ መዘክር የሚለው ቃል ትክክለኛ ቃል ስላልሆነ ነው፡፡ ቤተ መዘክር ማለት የመታሰቢያ ቤት ማለት ስለሆነ) ካላቸው ቅርስን የመጠበቅና ጠብቆም የማኖር የማስጎብኘት የማስዋወቅ ተግባርና ኃላፊነት የተነሣ ነው ይሄንን ማድረግ የቻሉት፡፡

ማን እንዳወናበዳቸው ባላውቅም ከሁለት ሦስት ዓመታት ወዲህ ተውት እንጅ አርበኞችም በየበዓላቶቻቸው ይዘውት ይወጡት የነበረው ሙሉዋን ኢትዮጵያና ንጹሑን ሰንደቅ ነበረ የታሪካቸው አካልና የተጋደሉለት እሴት በመሆኑና ታሪካቸውን መዘከር ካለባቸው ማድረግ የሚገባቸውና ያለባቸው ይሄንኑ በመሆኑ መብታቸውም ስለሆነ ነው፡፡

ቤተክርስቲያንም ከማንምና ከምንም በላይ ሙዚየም (ቤተ ቅርስ) ቢሏት ሙዚየም (ቤተ ቅርስ) አርበኛ ቢሏት አርበኛ ናትና ሙሉ የኢትዮጵያን ምስለ ምድር የማሳየት መብት ነበራት፡፡ የምትመራበት ሱታፌን (አንድነትን) መሠረት ያደረገው የክርስቶስ አስተምህሮ በመሆኑም ከቤተቅርሶቹና ከአርበኞቹ በላቀ የሚመለከታት የሚገዳት እሴት ነውና ሙሉዋን ኢትዮጵያን መጠቀም ትችል ነበረ፡፡ መብት የሚጠበቅባት ሀገር አይደለችም እንጅ ሀገራችን፡፡

ሌሎችም እዚህ ልገልጻቸው የማልፈልጋቸው አንዳንድ ያልወደድኳቸው ገለጻዎችንም ታዝቤያለሁ፡፡ አንድ ግን ሳላስተላልፈው ማለፍ የማልፈልገው መልእክት ቢኖረኝ፡- እራሱን የቤተክርስቲያን ግንባር ቀደም ጠላትነት ባሰለፈ የጥፋት ኃይል በወያኔ ፍላጎትና ፈቃድ እየፈሰስን ታዲያ እንዴት ብለን ነው ቤተክርስቲያንን አፍጥጦ ከመጣባት የመጥፋት አደጋ ልንታደጋት፣ የቤተክርስቲያንን ጥቅም ፍላጎት ልናስጠብቅ የምንችለው? የውሽማ ለቅሶ እያለቀስን ወደ መቃብሯ ለመሸኘት ካልሆነ በስተቀር፡፡

ለዚህ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት እስካልቻልን ጊዜ ድረስ መልሱ “ፈጽሞ ቤተክርስቲያንን መታገድ አንችልም!” የሚለው ነው የሚሆነው፡፡ አሁን በዚህ ጊዜ ቤተክርስቲያን እንዲህ ተሰባብራ መላወስ አቅቷት በምትንጠራወዝበት ሰዓት ጉዳት ሕመሟን፣ ጭንቅ ችግሯን ደፍረን መናገር መጮህ ያልቻልን መቸ ልንናገረው ነው?

ይሄ ቤተክርስቲያንን ከጥፋት የመታደግ ተልእኮ በቁርጠኝነት ደፍሮ በመውጣት በቆራጥነት ካልሆነ በስተቀር ራስን ለአደጋ ለጉዳት ለእንግልት ላለበዳረግ እጅግ እየተጠነቀቁ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሊወጡት የሚቻል ተልእኮ ነው ወይ? መልሱ በፍጹም አይደለም ለሚለው ነው፡፡ የቤተክርስቲያንን ታሪክ አገላብጠን ብናይ የምንረዳው እውነት ቢኖር ይሄንን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ከብዙ የአውሮፓ ሀገራት ልትጠፋ የቻለችውና በመናፍቃን የተወረሰችው በዚህ ዓይነት ራስ ወዳድነትና ፍርሐት ሳቢያ ነው፡፡ እንዲህ ብለንማ ነው ይሄው ለዚህ ስብራቷ ሕመሟ ድቀቷ የዳረግናት፡፡ ከዚህ መማር እንችላለን በዝምታችን፣ ዓይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን በማለፋችን፣ ኃላፊነታችንን ግዴታችንን መወጣት አመለቻላችን ቤተክርስቲያንን ሲጠቅማት፣ ሲያሰፋት፣ ሲያሳድጋት ነው እያየን ያለነው??? ይሄ አኪያሔድ እንዳላዋጣ ቤተክርስቲያንን እየገደላት እንደሆነ እያወቅንም ሞታ እስክትቀበር ድረስም በዚህ እንቀጥል ነው እያልን ያለነው???

ልብ የሚለው የለም እንጅ ይሄ ሁኔታ በዐውደ ርእዩ ላይ መታየቱ ራሱ የዐውደ ርእዩ አንድ አካልና ቤተክርስቲያን በምን ዓይነት ፈተናና ችግር እንዳለች የሚያሳይ አንዱ ትዕይንት ነው፡፡ “የዚህ ዐውደ ርእይ ስኬት ምንድን ነው?” ከተባለም ይሄንን ችግር በሚገባ ማሳየት መቻሉ ይመስለኛል፡፡

በመጨረሻም ይሄንን ዐውደ ርእይ እንድትጎበኙት እየጋበዝኩ በመጀመሪያው ዐውደ ርእይ ላይ ያጋጠመኝን አንድ አሳዛኝ ገጠመኝ ባጭሩ ጋብዣቹህ ልጨርስ፡፡ ከዛ በፊት ግን ከዐውደ ርእዩ አንጀቴን ከበሉኝ ትዕይንቶች አንዱን ልጥቀስ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ጠንካራና አስመስጋኝ የሥራ ክንውን ከሚታይበት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ህልውና የጀርባ አጥንት የሆኑት በሀገራችን በተለያየ ስፍራ የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ያውም የማስመስከሪያዎቹን መምህራንና ተማሪዎችን በአካል አቅርቦ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያኑ እንዴት ባለ ሁኔታ የመማር ማስተማር ሒደቱን እንደሚከውኑ፣ ያሉባቸው ችግሮች፣ ከማኅበረ ቅዱሳን እየተደረገላቸው ያለው ቋሚ ድጋፍ ምን ያህል ከመጥፋት እንደታደጋቸው አንጀት ከሚበላውና እጅግ ከሚያስቆጨው የዐውደ ርእዩ ክፍሎች አንዱ ነበር፡፡

በመጀመሪያው ዐውደ ርእይ ላይ የእኔ ሦስት ሥዕለ አድኅኖዎች ቀርበው ነበር፡፡ ከሦስቱ አንዱ ከዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 12ን እና 13ን መሠረት ባደረገ የተሣለ የቅዱስ ሚካኤል አውሬውን 666ን በእሳት ሰይፉ አንገቱን ቆርጦ ሲዖል ሲወረውር የሚያሳይ ሥዕል ነበር፡፡

እና እላቹህ ይህ ሥዕለ አድኅኖ ቦታውን ይዞ እንዳለ ዐውደ ርእዩን መርቀው ሊከፍቱ አባ ጳውሎስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መምጣት፡፡ መርቀው ከከፈቱ በኋላ እየተዘዋወሩ በሚጎበኙበት ወቅት ከዚህ ሥዕል ጋር ፊት ለፊት መፋጠጥ፡፡ አባ ጳውሎስ ሥዕሉን እንዳዩት የመረበሽ ስሜት ይታይባቸውና ሥዕሉ እንዲነሣ አዘው ይሔዳሉ፡፡ አባ ጳውሎስ የአውሬው መንፈስ ያለባቸው የአውሬው አገልጋይ አልነበሩ? ለዛ ነው መረበሻቸውና ሥዕሉን መጥላታቸው፡፡ እናንተ ኢሉሚናቴ የምትሉት ማለቴ ነው፡፡

በማግስቱ ስሔድ ሥዕሉ የለም፡፡ ልጆቹን ስጠይቃቸው ዲ/ን ዳንኤል ነው ያነሣው አሉኝ፡፡ እዛው ነበረና ጠየኩት፡፡ የት ወስዶ ወሽቆታል መሰላቹህ ከተከፋች በሩና ከአዳራሹ ግድግዳ ጣብቂያ እንደ ቆሻሻ ክርታስ ወስዶ ወሽቆታል፡፡ በጣም ደነገጥኩ! “ምነው? ለምንድን ነው የተነሣው እዚህስ የተጣለው?” ስል ጠየኩት፡፡ “አይ አባቶች ይነሣ ስላሉ ነው” አለኝ “ለምንድነው ይነሣ ያሉት?” ስል ጠየኩት “የቤተክርስቲያናችን ሥዕል አይደለም! ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን አልጠበቀም! ብለው ነው” አለኝ በምን ምክንያት ነው የቤተክርስቲያናችን ሥዕል አይደለም፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን አልጠበቀም! ያሉት?” ብየ እንደገና ጠየኩት መልሱ አጭር ነበረ “እኔ እንጃ!” አለኝ፡፡

ከዚያ በኋላ ይሄ ሥዕል ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን ዐውደ ምኅረቱ ላይ ተሰቅሎ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ታሪኩ ረጅም ነው ላሳጥርላቹህ አባ ጳውሎስ ትዕዛዝ ሰጥተው የወያኔ አገልጋይ እንደሆኑ የሚታወቁ የልደታ ቤተክርስቲያን ካህናት ሥዕሉን ከቦታው አውርደው ነዳጅ አርከፍክፈው አቃጠሉት፡፡ አቤት የአባ ጳውሎስ ድፍረትና ኃጢአት የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቃጠሉት፡፡

ይሄንን ሥዕል ብዙዎቻቹህ የምታውቁት ይመስለኛል፡፡ በፖስተር (በተለፋጭ ወረቀት) ወጥቶ ነበር፡፡ ታዋቂው መምህር የናቴ ልጅ ቀሲስ መንግሥቱም “ተዐቀብ ዉሉደ እምየ!” በሚለው ስለ አውሬው 666 ማንነትና የጥፋት ሥራ በተነተኑበት መጽሐፋቸው የውስጠኛው ገጽ ላይ ሥዕሉ አለ፡፡ ስለ ሥዕሉም ግሩም የሆነ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡

እናም እባካቹህ ያለው ሁኔታና ውጊያው ከማን ጋር እንደሆነ እባካቹህ ይግባን! ቆራጦች እንሁን! ይሄንን የቤተክርስቲያን ፈተና ቆራጦች ሆነን ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ካልሆነ በስተቀር በማስታመም በመለማመጥ በፍጹም የምንወጣው የምናሸንፈው አይደለም እንንቃ! እንንቃ! እንንቃ! እንቁረጥ! እንቁረጥ! እንቁረጥ!

መድኃኔዓለም ክርስቶስ የቅድርስ ቤተክርስቲያንን ጠላቶች እንደጉም አብንኖ እንደጢስ አትንኖ ያጥፋልን! ጉልበታቸውን ቀጤማ ያድርግልን! ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከጥፋት ይታደግልን! ቤተክርስቲያን በሌሎች ሀገራት ጠፍታ በመናፍቃን ተወርሳ “ነበረች” እየተባለ እንደሚወራው ሁሉ በሀገራችንም ጠፍታ በመናፍቃን ተወርሳ “ነበረች” ተብሎ ከመነገር ያውጣልን! እኛም አሁን እያደረግነው እንዳለው ኃላፊነታችንን ከመወጣት ታቅበን ርቀን ተሰብስበን ለቤተክርስቲያን ጥፋት ተጠያቂዎች ከመሆን ሠውሮ ታድጎ እንደ እዱሳን አባት እናቶቻችን ኃይልን፣ ጽናትን፣ እልህን፣ ቅንአትን፣ ፍቅርን፣ ቁርጠኝነትን ሰጥቶን አስታጥቆን ሞልቶን ኃላፊነታችን እንድንወጣ ያድርገን ያስችለን ያብቃን አሜን!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles