ቴውድሮስ አድሃኖም ምን አጥተው ኢትዮጲያን ጠሏት!?
ዶክተር ቴውድሮስ አድሃኖም ሰሞኑንን የአለም ጤና ድርጅትን በሃላፊነት ለመምራት ሃገሪቷ የሰጠቻቸውን ሃላፊነት ወደ ጎን ትተው (እንኳንስ ሌላ የሰሞነ ግንቦት ሃያን ሽርጉድ ሁሉ ትተው) በምረጡኝ ቅስቀሳ ተጠምደዋል። በሌላ አባባል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውጪ ውጪውን እያዩ ነው
ዶክተሩ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን በበላይነት በመሩ ጊዜ ከህዝብ ከተዋወቁ በኋላ፤ አሁን ደግሞ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው የፌስ ቡክ አካውንት ሳይቀር ከፍተው የራሳቸውንም የሃገራቸውንም ‘’መልካም ገጽታ’’ ለመገንባት ‘ኮመንት’ ‘ከስታተስ’ ሲጥሩ ስናይ ሰውዬው ከሌሎች ባለስልጣናት በተለየ ውሃ የሚያነሱ (ደህና) ሳይሆኑ አይቀሩም ብለን የጠረጠርን ሰዎች አለን። (ቅንፍ ውስጥ ገብተን ስናንሾካሹክም ርግጥ ነው ዶክተሩ መርፌ መስካት እና ፌስ ቡክ ልይ መሰካት (ይቺኛዋ ሰ ትጠብቃለች) እርሱ ላይ መልካም ይሆኑ እንደሆን እንጂ ሌላው ፖልርቲካዊ እውቀት ላይ *‘’ድክሞ’’ እንደሆኑ የተረዳነው፤ በባለፈው ምርጫ ክርክር ጊዜ ነበር። ምነው እንኳ ሰውዬው የሚናገሩት ነገር አይደለም ከዶክተር ከፕሮፌሰር (ሳሞራው እንኳ የማይጠበቅ አይደለም ብለን እኮ ተሸማቀንላቸው ነበር እኮ))
*በዚህ ጽሁፍ አግባብ ‘’ድክሞ’’ ማለት በአራዳ ብሄረሰብ ቋንቋ የደከመ በቂ መሰናዶ ያላደረገ ለተፎካካሪነት የማይበቃ ማለት ነው።
እኒህ ሰው የሀገሪቱ ቁንጮ ባለስልጣናት ከሚባሉት መካከል ሆነው ‘’ብላ ጠጣ ነገር አታምጣ’’ ከሚባልበት የኢህአዴግዬ እቅፍ ውስጥ አሻግረው ደጅ ደጁን ምን አሳያቸው? ላገለግላት ቃል እገባለሁ ብለው እጃቸውን ሰቅለው ቃል የገቡላት ኢትዮጵያንስ ለማን ትተው ነው የአለም ጤና ቢሮ ሃላፊ ለመሆን ልምምጥ የገቡት? የሚሉትን ነገሮች ሰሞኑን ሳንሰላስል ሰንብቼ ነበር።
ምስኪን ሃገራችን በአሁኑ ጊዜ በርካታ አምራች ዜጎቿን በተለየያየ ሰበባ ሰበብ ታጣለች። በአመት ከአምስት ሺህ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን የሞሉት የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ ደርሷቸው ወደ አሜሪካ ለማቅናት ሻንጣቸውን ሲሸክፉ፤ በሃገሪቱ አስተዳደር ተማረው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ተባረው፣ በኑሮ ውድነት ተስፋ ቆርጠው እና በወዘተ ወዘተ ሆነው የሃገሪቷን ‘’ለአስር አለቃዎች አስረክበው’’ የሚኮበልሉ ዜጎች ቁጥር የትየ ለሌ ነው።
ከዚህ በፊት ኬኒያ በነበርኩ ጊዜ ተቀማጭነታቸውን ናይሮቢ ባደረጉ አለም አቀፍ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን አግንቼ ምሳ ጋብዘውኝ እኔም ጥያቄ ጋብዣቸው ነበር። የምሳውን ነገር እዚህ ባናነሳውም እኔ ያነሳሁላቸው ትያቄ እንደሚከተለው ዕናምጣው…. ይሄ ሁሉ ባለሟል ሃገሩን በማገልገል ፈንታ እዚህ የመስራቱ ምስጢር የተሻለ ደምወዝ ለማግነት ነውን…? ብያቸው ነበር። መላሾቼ እንደነገሩኝ በርግጥ የደሞዙ ነገር አንዱ ሳቢ ከሚባሉት ነገሮች መካከል ቢሆንም በዋናነት ግን አብዛኛዎቹ በአለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ‘’እውቀት ጢቅ’’ የሆኑ የሃገራችን ሰዎች ሃገር ቤት የሞያ ነጻነት ባለመኖሩ ምክንያት እንዲሁም በፖለቲካው ዘርፍ የኢህአዴግ ነገረ ስራዋ አይጥመንም (አታሰራንም፤ አሳር ታበላለች እንጂ (ይቺን እንኳ እኔ ነኝ የጨመርኩላቸው( በርግጥ እነርሱም ቢያነቡኝ እንኳን ጨመርክልን ኧረ ማለታቸው አይቀርም) ብቻ እንደዛ በሚል የፖለቲካ መለየት ሳቢያ ነው ሃገራቸውን ማገልገል እየቻሉ ካገራቸው ተገልለው በአለም አቀፍ ጉዳዮች ተጠምደው የሚኖሩት።
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን የሞላላቸው ከሚባሉ የሃገራችን ሰዎች መካከል አስር ብንጠራ አናጣቸውም። ካጣናቸው እንኳ ለስራ ውጪ ሃገር ሄደዋል ማለት ነው… (ብለን እንቀልድ እና ወደ ቁምነገሩ እናምራ!
እኒህ የሞላላቸው ሰውዬ የሃገር ውስጥ ሃላፊነታቸውን ትተው ውጪ ውጪውን ምን አሳያቸው? ደሞዝ አነሳቸው…. !? የስራ ነጻነት አጡ? ወይስ ሃገሪቷ አስጠላቻቸው….? ለመሆኑስ ምን አድርጋ ኢትዮጵያን ይጠሏታል። ይቺ ሃገር በአሁኑ ጊዜ እንኳንስ እርሳቸውን ይቅርና፤ የጨበጡት እና የጠቀሱትን ሰው እንኳ አንቀባራ ይዛላቸው አይደለምን? እና እኒህ ሰው ሃገሪቷ የሰጠቻቸውን ስራ (ምንም እንኳ እኛ ሴራ ብንለውም) እርሳቸው እና ኢህ አዴግ እንደስራ ይዘውት እየሰሩት ነውና… ይሄንን ሁሉ ስለምን ይተዉታል?
ርግጥ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ ደሞዝ ያንሳል። ነገር ግን እኛ ሃገር በዋናነት የሚሰራው ይቺን ምስኪን ሃገር ‘’ቀድሞ የነበረ ክብሯን ለመመለስ’’ (በነገራችን ላይ ይቺን ነገር ኢቲቪም ሰሞኑን እያለን ነው) እና ሃገሪቷ ከሰዉ ሃገር እኩል ቆማ ለማየት እንጂ ለደሞዝ አይደለም። በተለይ እንደ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አይነቱ አይነቱ ‘’ታጋይ’’ ለደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ሃገሪቱ የምትሰጠውን ሃላፊነት ትቶ ወደሌላ ማየት በትዳር ላይ እንደመማገጥ ነው የሚታየው። ለመሆኑስ ባለስልታኖቿ ሳይቀሩ ሊያገለግሏት የማይፈልጉት ኢትዮጵያ ማነው ሊሰራላት የታጠቀው…. አንድ ወዳጄ ይሄው እየሰሩላት ነውኮ… ብሎ ሲያሽሟጥጥ ይታየኛል…)
የአቶ ቴውድሮስ በሃገሪቱ ቁልፍ ስልጣን ላይ ሆኖ ደጅ ደጁን ማየት ከሀገራቸው ይልቅ የራሳቸውን ዝና እና ብር የሚያሳድዱ ራስ ወዳድ ከመሆናቸው የመጣ ካልሆነ፤ ስለ እናት ድርጅታቸው ኢህአዴግዬ የታያቸው ወይም የቀፈፋቸው አንዳች ክፉ ነገር እንዳለ የሚያሳይ ነው። እንደርሱ ከሆነ እውነታቸውን ነው ማምለጥ ነው የሚበጀው ሌላው ነገር በኋላ ይታሰብበታል… (እንበላቸው ይሆን!?)