Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ኦነግ ኢህአዴግ የሳለልንን ያክል አስፈሪ ነውን!?

$
0
0

አሁን አሁን በኦሮሚያ ክልል እየተደረጉ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በአደባባይ የኦነግን አርማ ሲያውለበልቡ እያየን ነው። አንዳንዶች በግልጽ ይሄ ነገር አስደንግጧቸዋል። በተለይም ኦነግን ኦሮሚያን ከመገንጠል ጋር አያይዘው የሚያዩት ወዳጆቻችን… ይሄ ነገር ወዴት ወዴት እየሄደ ነው… እያሉ የተቃውሞውን አቅጣጫ በስጋት ሲመለከቱት አይተናል። እንደ እነ ጋሽ ግርማ ካሳ ያሉ ወዳጆቻችንም በግልጹ በተቃውሞው ላይ የኦነግ አርማ ጎልቶ መታየቱ የተቃውሞው መጨረሻ አጓጉል እንዳይሆን… በተለይም ለኢትዮጵያችን አንድነት ትልቅ ደንቃራ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በነገራችን ላይ እኔ የኦነግን አርማ በቅርበት እና በቅጡ ያየሁት በአንድ ወቅት ለስራ ከጭሮ/ አሰበ ተፈሪ ከፍ ብላ በምትገኘው መኤሶ ከተማ እና አካባቢው ለስራ ዞር ዞር ባልኩበት ወቅት ነበር። እንደውም ስለኦነግ አርማ ሲነሳ የማትረሳኝ አንዲት ዕድሜዋ አስር የምትሆን ልጅ አለች፤ አንገቷ ላይ በጨሌ ሰርታ አድርጋው ነበር። ሳየው… አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለማቱ በጣም ሳቡኝ… (እንደምታውቁት የባንዲራ ቀለማት ነገር አይሆንልኝም…. (ምን ያስቃል የምሬን ነውኮ…) እንደውም እነ በሃይሌ፤ ‘’የብሄር ተጸዕኖ ነው’’ እያሉ የባንዲራ ቀለማት መውደዴን ከኦሮሞነቴ ጋር እያገናኙ ሲተርቡኝ ይሁን ብዬ ዝም ብዬ ብዙ ኖሪያለሁ….(ሳጋንንም ለብሄር ብሄረሰቦች ተቻችሎ እና አብሮ መኖር ስል…ብዬ እጨማምራለሁ!)) እና ልጅቷ አንገት ላይ ያየሁት ባረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያማረ የኦነግ አርማ ቢስበኝ… ስጪኝ እስቲ ብዬ ጠየኳት…. ምን ብትለኝ ጥሩ ነው… ‘’ይሄንን የምሰጥህ መጀመሪያ አንገቴን ቆርጠከው ነው’’ ብላ አስደነገጠችኝ። ከዛም አካባቢውን ሲያዞረኝ የነበረው መንገድ መሪዬ ሲነግረኝ እውነቷን ነው… ይሄ አርማ እዚህ አካባቢ እንደ ነፍሳችን ነው የምንወደው… አንተም ብትሆን ከተማ ብትወስደው ያስሩሃልኮ… አለኝ!

ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በኦነግ ላይ ስትሰራ የኖረችው ፕሮፖጋንዳ ከቀድሞው የኦነግ የመገንጠል ፕሮግራም፣ ጋር ተዳምሮ በርካቶች ኦነግ ሲባል ክው ብለው እንዲደነግጡ አድርጓቸዋል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የኦሮሞው ህብረተሰብ ክፍሎች ግን ‘’ኢሾሌ አባኦ ዱፌ ያ ቶሌ’’ እያሉ ከመዝፈን አንስቶ የኦነግን አርማ በየቤታቸው አጣጥፈው በማስቀመጥ እንደ ነፍሳቸው ሲጠብቁት ኖረዋል።

ታድያ ዛሬ ይቺ ቀን ስትመጣ፤ ለተቃውሞ የወጡት ኢትዮጵያውያን የኦነግን አርማ ማውለብለባቸው ለሌላው ኢትዮጵያዊ ስጋት ነው ወይ….? የሚለው ጥያቄ ቢነሳ የኔ መልስ አይመስለኝም ነው።

ብዙዎቻችን ኦነግን የምናውቀው ኢህአዴግ በሳለችልን ሰዕል ልክ ነው የሚመስለኝ፤ እነ አባ ዱላ ገመዳ ስለ በደኖ ጭፍጨፋ ሲጽፉ ነገሩን በሙሉ ኦነግ ላይ ልክክ አድርገው እኛ ከደሙ ንጹህ ነን ሊሉን ፈልገዋል… ነገር ግን ከኢህአዴግ መሰረታዊ ባህሪ ስንነሳ ቅጥፈት ብርቋ አይደለም። የቅርቡን እና ቀላሉን እንኳ ብናይ አቶ አባይ ጸሃዬ ከትላንት ወዲያ ‘’ልክ እናስገባችኋለን’’ ብለው ሲያበቁ ትላንት አላልኩም ብለው ሲክዱን ምንም ደንቀፍቀፍ አላላቸውም፤ አቶ ጌታቸው ረዳም ትላንት ‘’ጋኔን’’ ብለው የተውሳደቡትን ከእንግሊዘኛው ስተረጉመው ተሳስቼ ይሆናል እንጂ…. እንዲህ አላልኩም ብለው ሸምጠጠውናል።

ስለዚህ ስለ ኦነግ ኢህ አዴግ የነገረችንን ነገር ለማመን ከባድ ነው!

ስለ ኦነግ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የኦነግ አመራሮች ሲናገሩ ሰምተናል። እርግጥ ነው…. ኦነግ ሙልጭ ያለ ብሄርተኛ ድርጅት ነው። እንደ ኦነግ እምነት የኦሮሞ ህዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር የሚጋራው ጥያቄ ቢኖርም ለብቻውም የሚያነሳው ልዩ ጥያቄ አለው… ይሉናል። እኔ የኦነግን ፖለቲካ ደጋፊ ባልሆንም ቅሉ፤ ኦነግን እና ሃሳቡን ግን እንደ ጥፋት ሃይል አድርጌ አልቆጥራቸውም። ኦነግ ኦህአዴግ የሳለልኝን ያክል አስፈሪ ነው ብዬ አላምንም!!!

ምርቃት፤

እነነጋገር ከተባለ ከሁሉም ብሄርተኛ ድርጅቶች በላቀ መልኩ የሀገራችንን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማትን ለዛውም በደማቁ ለአርማው የተጠቀመው ኦነግ ብቻ ነው ብለን ብንወራረድ እንሸነፍ ይሆን….

ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!

ድል ለሰፊው ህዝብ!

ብዬ ብሰናብትስ….


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles