Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ጥልያን እና ጣዩ መንግስት!

$
0
0

አባቴ ደጋግሞ እንዳጫወተኝ ጣሊያን ወረራ ሲያደርግ እርሱ የስምንት አመት ልጅ ነበር። ቢሆንም ግን ሃገሩን ከወራሪዎች ለመከላከል እርሱ እና የእድሜ እኩዮቹም አልሰነፉም ነበር። ቀን ቀን ለጣሊያን እና ለባንዳዎቻቸው እንቁላል በመሸጥ እግረ መንገዳቸውን ስለላ እያደረጉ ይውሉ እና አመሻሹ ላይ እናታቸው ለአርበኛው አባታቸው የምታዘጋጀውን ስንቅ ለማድረስ ወደ ጫካ ወርደው ስንቅም መረጃም አቀብለው ይመለሳሉ።

ታድያ አርበኞቹ እነ ፈይሳ ጣሊያን የት እንደዋለ እና የት እንዳመሸ ከልጆቹ እነ ቶላ ባገኙት መረጃ መሰረት በአሳቻ ሰዓት ብቅ ብለው እምሽክ አደርገውት ተመልሰው ከምሽጋቸው ይገባሉ… እንዲህ እያለ እያለ ጣሊያን አምስቱንም አመት እንቅልፍ ሳይወስደው… በመጨረሻም ወደ ሃገሩ ነካው!

‘’ዛሬ ጦርነታችን ከድህነት ጋር ነው!’’ ይልሃል ኢህአዴግ ራሱ ለድህነት ዳርጎህ ሲያበቃ! የገበሬውን መሬት ለውጪ ሀገር ኢንቨስተሮች ሸጦ ገበሬውን ወደ ጥበቃ ሰራተኝነት ለውጦት ድህነትን ነው ዛሬ የምንዋጋው… እያለ ሲያጭበረብረን ኖሮ ገበሬው ሲባንን ድህነትን ሳይሆን መዋጋትስ ‘’ስፖንሰሩን ነው’’ ብሎ ይሄው ዛሬም ኢትዮጵያውያን እምቢኝ ብለዋል።

ጣሊያን ዕድሜ ጾታ ሳይለይ ታላቅ ጭፍጨፋ ያከናወነው ሞገስ አስገዶም እና አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኔን እና ጭፍሮቹ በተሰበሰቡበት ቦንብ ጥለውባቸው ታላቅ ጉዳት ካደረሱባቸው በኋላ ነበር።

ዛሬ መንግስት ከህዝቡ ጋር እልህ ለመጋባት ህጻናትን እና አረጋውያንን ሴት ከወንድ ሳይለይ ለመጨፍጨፍ የቦንብ ጥቃት አላስፈለገውም እራሱ ቦንብ የሆነ መንግስት ፍንዳታ የሆኑ ባለስልጣኖች አሉት። የዘጠኝ አመት ወንድሟ በጥይት ሲመታ አስከሬኑን ለማንሳት ጎንበስ ያለች ሌላ ህጻን በመንግስት ጥይት ስትመታ የምናየው… በርግጥም በዚህኛው ዘመን ለመሆኑ ጥርጣሬ አለን!

ጣዩ መንግስት ቢያውቅበት አሁንም ቢሆን በጣሊያን አይን እንዳናየው ጊዜ አለው። በኦሮሚያ ክልል ኮሽ ባለበት ሁሉ ጥይት እየተኮሰ ንጹሃንን ከመግደል እንደ ‘’ኦፌኮ’’ የመሳሰሉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ወደ ህዝቡ እንዲሄዱ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ህዝቡ የራሴ የሚለውን አዲስ አስተዳደር እንዲሰይም ያለማወላወል መፍቀድ! እንዲሁም ለቆሰሉ እና ለሞቱ ኢትዮጵያውያን ካሳ መካስ በገፍ የታሰሩ የነጻነት ጠያቂዎችን መፍታት…

እምቢ ካለ ግን እንኳንስ ኢህአዴግን ጥሊያንን አስወግደናል! (ልል ነበር እኔ ውጪ ሀገር ነኝ ለካ… (በሌላ ቅንፍ እነርሱም እኔ ነኝ!!!)) እና ጣዩ መንግስት ሆይ ሁሌ እየጣሉ መኖር ከባድ ነው! መውደቅም አለ እና… መሬቱን ገለባ ያድርግልህ!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles