አንዳንዴ ቤተሰብ ይናፍቅሃል ። ሄደህ ማየት አትችልም ፥ ለነሱ ብለህ ሃሳብህን አትቀይርም! የቀየሩ የሉም ማለት ግን አይደለም ። ለአዲስ አበባ ሴትና ቁርጥ ብለው ፥ ከዳመና ሰንጣቂነት ወደ ህውሓት አዳማቂነት ፥ ወይም አላሙዲን አሳቂነት የተቀየሩ አሳቃቂ አርቲስቶችን ፥ ደዋኪ አክቲቪስቶችን እናውቃለን ። እነሱ በሄዱበት መንገድ መሄድ አንፈልግም ። ቤተሰቦቻችን ስለማይናፍቁን ሳይሆን ፥ የቆምንበት አላማን ማይክሮፎን ይዞ ከመዝፈን ባለፈ ምንነቱን ስለምንረዳ! በህሊናችን ሚዛን ስንመዝነው ፥ እየተገላበጠ የበሰለ ስጋ ተመጋቢውን እንጂ ስጋውን አንዳች ነገር ስለማይጠቅመው ።
እርግጥ ሃገርህ ትናፍቅሃለች ፥ ናፍቆቷን ግን የምትወጣው ብጉር በሚያክል አንጎል ላንተ በታሰበ መፍትሄ አይደለም ። ያገር ናፍቆት ህሊናን የሚመዘምዝ ነገር ነው ፥ ግን ከስቃዩ እረፍት ለማግኘት ጭንቅላትህን በትኩስ ውሃ የሟሟ የጨው ባልዲ ውስጥ አትዘፈዝፈውም ። ወይ ትሄዳለህ ወይ ትቀራለህ ። እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የኔ ውሳኔ
ያለሁበት ቀርቶ ፥ የስቀሩኝን ለመታገል ዘዴ መዘየድ ብሎም እነሱን እንደ ቪኖ ቡሽ መዞ አውጥቶ ወደ ሃገር መግባት የሚል ነበር ። በይበልጥ የአንዳርጋቸው ፅጌን መያዝ ተከትሎ ፥ እንደ መላከ ሞት ያለንበት ድረስ እየመጡ፥ እያወጡ ፥ ሊወስዱን እና ሊያስወስዱን እንደሚችሉ ሲዝቱ በመስማቴ ከመገረም ባለፈ የተገፋ በመሸሽ ሳይሆን የሚገፋውን በመግፋት ብቻ ነው መትረፍ የሚችለው የሚለውን አቋም ሳራምድ ነበር ።
ሰሞኑን በሆነው ግን ሃገሬ መግባት እንደምችል ተረድቻለሁ ። እኔ አስብ የነበረው ፥ በሃገሬ እና በህውሓት ስርአት ፥ አንድ ሰው የሚታይ ፥ ትልቅ ነገር ተሸክሞ እንዲሄድ ከተፈቀደለት ወይ ባለ ሸንኮራ ነው ወይ ህውሓት ነው ። የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ወያኔ « ስንከታተላቸው ነበር » ብሎ የሰራው ዜና ግን በእርግጥ ሃገሬ መግባት እና መውጣት እንደምችል እንድረዳ አድርጎኛል ። ስለዚህ ሻንጣዬን እየሸከፍኩ ነው ።
እርግጥ በህውሓት ዜና መሰረት ፥ « አሸባሪው ቡድንን ከመነሻው እስከ መድረሻው » ሲከታተሉ እንደነበር አትተዋል ። ታዲያ ይህንን አስተዋይነታቸውን ለኛም የሚያደርጉት ከሆነ ለምን ሃገራችን አንገባም ? ጉዳዩ ክትትል ብቻ ይመስላልና ።
ህውሓት ጎረምሳ እርግብ መሆኑንም አውቀናል ። ክትትል !
እንደውም ስንከታተል ነበር የሚለው ዜና « ክትትል » ማለት ምን ማለት ነው ብዬም እንዳስብ አድርጎኛል ። እኔ በግሌ የአርባ ምንጩን ኬዝ ለባት ማን እና ሸርሎክ ሆልመስ አሳልፈን ብንሰጣቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ ።
እንደውም አንድ የሸርሎክ ሆልመስን አባባል ልጥቀስ ፥ እንዲህ ይላል « “How often have I said to you that when you have eliminated the impossible, whatever remains, however improbable, must be the truth»
ምክንያት ሊሆኑ የማይችሉትን ( አይሆኔዎች ) በሙሉ ከ ጥያቄህ ውስጥ ካስወጣህ ፥ የሚቀረው ፥ የማይመስል የሚመስለው እውነቱ መሆን አለበት ።
ስለዚህ ወያኔ አሰበች ። ህዝቡን ጠርንፌ ይዤዋለሁ አለ ፥ ስለዚህም ማንም ሆነ አንዳችም ሰው ከህዝቡ መሃል እኛን ታጥቆ ሊዋጋን አይችልም አለ ፥ ሰራዊቱም ሆነ ህዝቡ የደበቀውን መሳሪያ ሊወጉን ለመጡ ጠላቶቻችን አሳልፎ አይሰጥም አለ ፥ አባባሉ ደሞ « በምንም አይነት አይሆንም » የሚል ቃናን የተላበሰ ይመሰላል ነበር ። ስለዚህ አይሆኔዎቻቸውን ከጥያቄነት አስወጡ ፥ ስለዚህ አሉ « ግንቦት ሰባት ቫስኮ ደጋማ ነው » ከኤርትራ ተነስቶ ፥ በኬኒያ አሳልጦ ፥ በሞያሌ እና ምናምን አድርጎ ፥ አርባ ምንጭ ገብቶ ፥ እስኪገል ፥ እደግመዋለሁ እስኪገል ድረስ እየተከታተሉት ነበር ። ታዲያ እኔ ሃገሬ መግባት የፈለኩት ይሄንን ዜና ስሰማ ነው ።
ኣዎ አንድ አባት ጥይት ሲተኮስ ደንግጠው የሮጡ ያካባቢያቸውን ወጣጦች « ምድረ ፈሳም ፥ አሁን ለጥይት ይሮጣል !» እያሉ ሲወቅሱ ከየት መጣ ሳይባል የመድፍ እሩንታ አካባቢውን ይንጠዋል፥ ታዲያ እኒህ አባት « ይሄኔ ነው መሮጥ » ብለው እግሬ አውጭኝ ። ታዲያ እኛs ምን አልን « ይሄኔ ነው ኢትዮጵያ መግባት !»
ግን ህዝቡ አንድ ነገር እንዲያጤንልኝ ፍላጎቴ ነው ። « አንዳርጋቸውን ከየመን አፍኖ የወሰደው ህውሃት ፥ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ከኤርትራ እስከ አርባ ምንጭ ተከታተለ » የሚለውን ዜና እና ለምን የሚለውንም ሃሳብ በአንድ ላይ !
አሪፍ ቅዳሜ !