Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ግራ ተጋብተው ግራ አያጋቡ (ከይገርማል)

$
0
0

kinijit_logoየተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ ማሩ “ቅንጅት ፓርላማ አልገባም አላለም” በሚል ርእስ አንድ ጽሁፍ በኢትዮሜዲያ ላይ አስነብበውናል:: የተከበሩ አቶ ግርማ ቅንጅት የሚሉት ጠ/ጉባኤውን ከሆነ እውነት አላቸው:: ይህን ለማለት ያበቃኝ አምባገነኖች ራሳቸውን እንደ ድርጅት:  ሌላውን ተከታይና አድናቂ አድርገው የሚያምኑ እንደሆነ ስለሚታወቅ ነው:: እነርሱ ያነሱት ይነሳል የጣሉት ይወድቃል: በቃ እንዲህ ነው:: አቶ ግርማ እንዳሉት ጠ/ጉባኤው ፓርላማ መግባት የለብንም ብሎ አልወሰነም:: የቅንጅት ላእላይ ም/ቤትም ቢሆን ፓርላማ አንገባም ብሎ ወስኗል ማለት አይቻልም::

ምንም እንኳ የመኢአድ ሰወች ፓርላማ መገባት የለበትም በሚል የሞገቱ ቢሆንም አብዛኛው አባል ግን በተቻለ መጠን መኢአዶችን ለማለሳለስ ብዙ መድከማቸው አይዘነጋም:: ራሳቸውን ከጠ/ጉባኤውም ሆነ ከላእላይ ም/ቤቱ በላይ አድርገው የሚመለከቱት የመኢአድ ሰወች የስብሰባውን መንፈስ እንዴት ያውኩት እንደነበር በስፍራው ለነበረ ሁሉ የሚዘነጋ አይደለም:: ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ የሚል ክርክር ይደረግ በነበረበት ወቅት በህክምና ላይ የነበሩት ኢንጅነር ሀይሉ ሻውል ከአሜሪካ (በስልክ) ቅንጅት ፓርላማ የሚገባ ከሆነ መኢአድ ከቅንጅት እንደሚወጣ ነበር የገለጹት::

ፓርላማ መገባት አለበት ሲሉ ይከራከሩ ከነበሩት የመኢአድ ሰወች መካከል አንዱ ሻለቃ አድማሴ ነበሩ:: ሌሎች የመኢአድ አመራሮች አቶ አባይነህና ሻለቃ ጌታቸውን ጨምሮ የሀይሉ ሻውልን አቋም በማስተጋባት ቅንጅት ፓርላማ እንዳይገባ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ነበር:: ከድርጅታቸው የተለየ አቋም ሲያራምዱ የነበሩት ሻለቃ አድማሴ በብዙሀኑ የመኢአድ አመራር ዘንድ እንደ ከሀዲ ስላስቆጠራቸውና ስለተገለሉ ፊት ለፊት መጋፈጡን ሊያቆሙ ተገደዱ::

ኢንጅነር ሀይሉ አቋማቸውን እንዲያለሳልሱ ከቀስተዳመናና ከኢዴሊ ለቀረበላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ መኢአድ እንኳ ፓርላማ ቢገባ እርሳቸው በግል ፓርላማ እንደማይገቡ አስረግጠው በመናገራቸው የተነሳ ሌላ ዘዴ መዘየድ አስፈላጊ ነው ተብሎ ታመነ::

እንደሚታወቀው ሀይሉ ሻወል ማለት መኢአድ መኢአድ ማለት ደግሞ ሀይሉ ሻወል ማለት ነበሩ:: በመኢአድ አሰራር ኢንጅነሩ የፈቀዱት ይሆናል ያልፈቀዱት አይሆንም:: እርሳቸው በግላቸውም ቢሆን ፓርላማ አልገባም ካሉ መኢአድም የርሳቸውን አቋም ተከትሎ እንደማይገባ ግልጽ ነበር:: ይህ አካሄድ ደግሞ ፓርላማ ባለመግባት ውጤት ሊገኝ ይችላል ብሎ ባመነው ህዝብ ዘንድ መገለልን ሊያስከትል ይችላል ብሎ የሰጋው የላእላይ ኮሚቴ መኢአድን በቅንጅት ውስጥ ለማስቀጠል የመደራደሪያ ሀሳቦችን እናቅርብ በሚል 8ቱን ነጥቦች ወደማውጣት አዘነበለ::  ይሁንና መኢአድ ከቅንጅት እንዳይወጣ በሚል የአመራሮችን አቋም ለማለሳለስ ይረዳሉ ተብለው የቀረቡት የመደራደሪያ ነጥቦች ለወያኔ አዲስ የእድል በር ከፈቱለት::

ፓርላማ ከመከፈቱ ከሦስት ቀናት በፊት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመራጮች በቅንጅት ጽ/ቤት ግራውንድፍሎር ውስጥ ስብሰባ አድርገው ነበር:: በወቅቱ ዋናው የመወያያ ነጥብ ሆኖ የቀረበው የአዲስ አበባን ም/ቤት መረከብን የሚመለከተው አጀንዳ ነበር:: አዲስ አበባን መረከብ ያስፈልጋል የሚለው አመለካከት በአመራሩ የታመነበት ስለነበር ውይይቱ ካለምንም ተቃውሞ  በስምምነት ነው የተጠናቀቀው:: ሁሉም ተሰብሳቢ በአንድ ድምጽ ”አዲሳበባን መረከብ አለብን” የሚል ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ስልጣኑንና የምክርቤቱን ቁልፍ  የሚረከቡ ሰዎችን መርጦ አርከበ እቁባይ  ይመራው  ወደነበረው የቀድሞው የአዲስ አበባ ም/ቤት ላከ:: ይኸኔ ነበር በአርከበ እቁባይ ይመራ የነበረው ም/ቤት ”ፓርላማ የማትገቡ ከሆነ አዲሳበባን አናስረክባችሁም” ያለው::

በሌላ በኩል የአዲሳበባ ምክር ቤት ተመራጮች አዲስ አበባን  ሊረከቡ እንደሆነ የሰሙ ለፓርላማ ተወዳድረው  ያሸነፉ የቅንጅት ሰወች ተቃውሟቸውን ለማሰማት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲደረግ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳንና አቶ ልደቱ አያሌውን አነጋግረው ስብሰባው ተደረገ:: በስብሰባው ወቅት የተነሳው ዋናው ጉዳይ

“በአንድ የምርጫ ወቅት አንድን ድርጅት ወክለን ነው ለውድድር የቀረብነው:: የምናሳልፈው ውስኔ አንድ ወጥ መሆን አለበት::  የአዲስአበባ ም/ቤት ተመራጮች ም/ቤቱን የሚረከቡ ከሆነ እኛም ያሸነፍነውን ወንበር ለመረከብ የሚያግደን ነገር አይኖርም”

የሚለው ነበር:: ስብሰባውን የመሩት ሁለቱ ም/ሊቀመናብርት የተሰብሳቢውን መንፈስ ከአመራሩ እምነት ጋር አጣጥመው ማስኬድ ባለመቻላቸው ስብሰባው ካለስምምነት ተጠናቆ ወዲያውኑ ፓራላማ እንገባለን የሚል ፔቲሽን መፈራረም ተጀመረ::

ያ ብልሀት የጎደለው: ሁሉንም አስተያይቶ ማስኬድ ያልቻለው አመራር: የፓርላማ አባላቱን  ሳይቀር ለሁለት እንዲከፈሉ መንገዱን በማመቻቸቱ ፔቲሽን የተፈራረሙት ከሀያ በላይ ሰወች ተመዝግበው ሰኞ እለት  ፓርላማው ሲከፈት በአካል ፓርላማ እንዲገኙ ምክንያት ሆነ::

የአመራሩን ትእዛዝ ተላልፈው በፓርላማ መክፈቻ ስነስርአቱ ላይ የተገኙትን የቅንጅት ሰዎች ማንነት እንዲለዩ የተላኩት ሰላዮች በሰጡት መረጃ በመመርኮዝ ለማስደንበር የተደረገው ሙከራ ትርጉም አልባ ነበር:: በዚህም ምክንያት በተደፈርን ስሜት አንጀታቸው ያረረው ከስህተት ሊማሩ ያልፈቀዱት አመራሮች ፓርላማ በገቡት የቅንጅት አባላት ላይ ”የመረጣቸው ህዝብ ውክልናውን እንዲያነሳ እናስደርጋለን” በሚል ያስወሩት ወሬና ያደረጉት ፍሬ አልባ እንቅስቃሴ በአባላቱ መሀከል የተፈጠረውን ልዩነት የባሰ አሰፋው እንጅ ያስገኘው ጥቅም አልነበረም::

በሌላ በኩል እንደቅንጅት አመራር ሁሉ ኢህአዴግም ፓርላማ የገቡትን የቅንጅት ሰወች ፓርቲያቸውን የከዱ ናቸው በሚል በየተመረጡበት አካባቢ ባሉት የደህንነት ሰወቹ አማካኝነት እንዲወራባቸው ስላደረገ በሁሉም ዘንድ እንዲጠሉና አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ ጣምራ ስራ ተሰራ::

ኢህአዴግ ፓርላማ በገቡት ሰወች ላይ ይህን ሁሉ ያደረገው ፓርላማ መግባታቸውን በመጥላት አልነበረም:: የእኒህ ሰወች ፓርላማ መግባት ልዩነትን በመፍጠር የቅንጅትን አቅም ለመሸርሸር: የፓርቲውን የተሳሳተ አካሄድ ለማሳየትና የራሱን በጎ ጎን ለመገንባት እንደሚጠቅመው አጥቶት ሳይሆን በሁሉም ዘንድ የተገፉት የቅንጅት ሰወች መግቢያ ሲያጡ እጉም ብለው ወደኔ ይሰባሰባሉ ብሎ በማመን ነበር:: በዚህ መሀል ከሁሉም ያጣ ባተሌ ላለመሆን ሲሉ እንደተባለውም በአባልነት ተመዝግበው ወደኢህአዴግ የተጠቃለሉ ነበሩ::

አንድ መታወቅ ያለበት እውነት አለ: ከአያያዝ ጉድለት የመጨረሻው ወዳጅ የመጨረሻው ጠላት ሊሆን እንደሚችል:: ሰወች የሰሩትንና የደከሙበትን ትግል እውቅና መንፈግና አቅልሎ ማየት የሚያደርስባቸው የመንፈስ ጉዳት ቀላል አይደለም::  በአመራር ላይ የሚቀመጡ ሰወች አፋቸው እንዳመጣ የማይናገሩ: የሰወችን ስሜት የሚጠብቁና ፍላጎታቸውንም የሚረዱም መሆን ይኖርባቸዋል:: የሕዝብ ድጋፍ ተችሮት ነገር ግን ብልሀት የጎደለው ቅንጅት በየአካባቢው ያለተመልካች አኩሪ መስዋእትነት ከፍለው ለድል ያበቁትን አባላቱን አሰባስቦ መቀጠል አልችል ብሎ ቀስ በቀስ መፍረስ ያዘ::

አዲስ አበባን ለመረከብ ፓርላማ መግባት አለባችሁ የተባሉት ቅንጅቶች ውሳኔያቸውን ለመከለስ አለመፈለጋቸው አንዱ ትልቁ ችግራቸው ነበር:: አቶ  ግርማ “ቅንጅት ፓርላማ አልገባም አዲስ አበባንም አልረከበም የሚል አቋም አልወሰደም” የሚለው አባባላቸው ትክክል አይደለም::

ኢህአዴግ የተገኘውን ሁሉ ምክንያት ተጠቅሞ ማደናቀፍ ይፈልግ እንደነበር ግልጽ ነው:: ያንን መሰናክል በብልሀት ተሻግሮ ለተሻለ ውጤት መብቃት የተፎካካሪው ድርጅት ድርሻ መሆን ነበረበት:: ኢህአዴግ “ፓርላማ ካልገባችሁ አዲስአበባን አናስረክባችሁም” ሲል ቅድመ ሁኔታ ማመቻቸቱ ሳይሆን ምክንያት ማብዛቱ: ሰበብ መፍጠሩ ነበር::

አንዳንድ የቅንጅት አመራሮችን ግትርነት ጠንቅቆ የሚያውቀው ወያኔ “እኔ ያልሁት ካልሆነ ሞቸ እገኛለሁ” በሚል መንፈስ የሆነ ነገር ያበላሽሉ በሚል መልካም አጋጣሚ እየጠበቀ ነበር::

ሊከሰት የሚችለውን ነገር አስቀድሞ ማስተዋል የተሳናቸው የቅንጅት አመራሮች ናቸው ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጡት:: “ተነጥቀናል የምትሉትን ወንበር ለማስመለስም ይሁን ለወደፊቱ ምርጫ ፍትሀዊነት መሟላት ይገባቸውዋል የምትሏቸው ነጥቦች ላይ ስምምነት ለመድረስ በቅድሚያ ወንበራችሁን ይዛችሁ ነው ልታነሷቸውና ልትከራከሩባቸው የምትችሉት” ሲባሉ ቆም ብለው ማሰብ ነበረባቸው::

ፓርላማ እንግባ ቢሉ መኢአድ እንደሚያኮርፍ የሚያውቁት የቅንጅት አመራሮች ፓርላማ እንድንገባ እኒህ ነጥቦች ሊሟሉ ይገባል በማለት የተሻለ አካሄድ ነው ብለው ቅድመሁኔታ ያስቀመጡት ራሳቸው ቅንጅቶች ናቸው::  አቶ ግርማ እርስዎ የፓርላማ ወንበር ባሸነፉ ጊዜም ቢሆን ፓርላማ እንዳይገቡ ግፊት ተደርጎብወት እንደነበር የሚዘነጉት አይሆንም::

ሌላው የሚገርመው የቅንጅትን  ፓርላማ  ስለመግባትና ስላለመግባት ጉዳይ ሕዝብን ማወያየት አስፈላጊ ነበር ብለው ማመንወ ነው:: እንዴት ያለ ነገር ነው! ሕዝቡ እኮ አንድ ጊዜ መርጧል:: የመረጠው ደግሞ ተመራጮቹ ፓርላማ ገብተው እንዲከራከሩ ነው::  አይደለም እንዴ?

በእርግጥ የህዝብ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በማንኛውም ጊዜ አይከሰቱም ማለት አይቻልም:: ነገር ግን ከምርጫ በኋላ ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ: በግራ እንሂድ በቀኝ: ስብሰባ እንጥራ አንጥራ: – – – እያሉ  በያንዳንዱ ጉዳይ ሕዝብን እንጠይቅ ማለት ሀላፊነትን አለመረዳት የሚሰሩትንም አለማወቅ ነው::

ፓርቲ የራሱ አላማና ግብ አለው:: አላማውን ለማሳካትና ግቡን ለመምታት  የሚነድፋቸው መርሀግብሮችና የሚከተላቸው ስልቶች ደግሞ ይኖሩታል:: ይህን ሲያደርግ ለህዝብ ይጠቅማል ብሎ የያዘውን ጉዳይ ከዳር ለማድረስ ነው:: ሕዝብ ደግሞ የፓርቲውን ፕርግራም አይቶ ይመርጠዋል ወይም ይጥለዋል::

አያያዙን አይተው ጭብጦውን ቀሙት እንዲሉ ቅንጅት ሲንከረፈፍ የጨበጠውን ለቀቀ:: ወዲያና ወዲህ ሲዳክሩ የነበሩት የቅንጅት አመራሮችም በአንድነት መቆም ተስኗቸው አባሉንም: ትግሉንም: ተስፍችንንም በተኑት::

የጠላትን እንቅስቃሴ ገምቶና አስልቶ: ጠንካራና ደካማ ጎኑን ለይቶ ስስ ብልት ፈልጎ በዚያ ለመጠቀም በብልሀት መንቀሳቀስ የማይችል ድርጅት መሞቱ ስለማይቀር የቅንጅትም እጣ ፈንታ ያው ሆነ:: ትግል እንደሚታገሉት አካል ሁኔታ ሊቃኝና የጠላትን አካሄድ እየገመገሙ ለድል የሚያበቃ ስልት ሊነደፍለት ይገባል:: ትግል ውስጥ ገብቶ ከተወደቀ ችግሩ የራስ እንጅ የሌላ ሊሆን አይችልም:: ስለዚህ ይህን ማድረግ ተስኖት የወደቀው ቅንጅት ችግሩ  የራሱ (የአመራሩ) እንደነበር መገንዘብ ያስፈልጋል::


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles