በፍቅር ለይኩን*
“… When he saw a poster, Mussolini Invades Ethiopia, he was immediately seized by a violent emotion. At the moment, he writes, it was almost as if the whole of London had suddenly declared war on me personally. For the next few minutes I could do nothing but glare at each impassive faces, wondering if these people could realize that wickedness of colonialism, and praying that the day might come when I could play my part in bringing about the downfall of such a system. … I was ready to go through hell itself, if need be, in order to achieve my object.”
ዕውቁ ፓን አፍሪካኒስትና የ”ጋና የነጻነት አባት” በሚል ቅጽል የሚጠራው ዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ በሚያደርገው ጉዞው በለንደን ከተማ ባደረገው አጭር ጊዜ ቆይታ ያስተዋለው፣ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ምልክት፣ የጥቁር ሕዝብ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ቅርስና ማንነት መገለጫ፣ የነጻነት የተስፋ ምድር- ከነዓን ተደርጋ የምትቆጠረው ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ በግፍ የመወረር አስደንጋጭ ዜና፣ መርዶ በውስጡ ያሳደረበትን ስሜትና ቁጭት “ጋና” በሚል ርዕስ በጻፈው የሕይወት ታሪኩ መጽሐፍ ያሰፈረውን በጥቂቱ የቀነጨብኩት ነው።
ታሪክ እንደሚነግረን ብቸኛዋ በነጻነቷና በልዑላዊነቷ ጸንታ የቆየችው ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ መወረሯ አፍሪካንና መላውን ጥቁር ሕዝብ ያሳዘነ፣ ያስቆጨና ያስቆጣ መርዶ ወይም ክፉ ዜና ነበር። ዶ/ር ንኩርማ በዚሁ በላይ በጠቀስኩት የሕይወት ታሪኩን በጻፈበት መጽሐፉ፣ በለንደን The International African Friends of Abyssinia የሚል ፀረ-ፋሽስትና የኢትዮጵያን መወረር በጽኑ የተቃወመ ማኅበር ተቋቁሞ እንደነበር ያትታል። እንዲሁም ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በስደት ወደ ለንደን በመጡ ጊዜም በወቅቱ ለትምህርት በእንግሊዝ አገር የነበረው ኬንያዊው ፓን አፍሪካኒስት ወጣቱ ጆሞ ኬንያታ፣ “የእንኳን ደህና መጡና እኛ አፍሪካውያን ልጆችዎትም አብረንዎት ነን!” የሚል ስሜት ቀስቃሽና ወኔ የተሞላበት ፀረ-ፋሽስት ንግግር ማድረጉንም ዶ/ር ንኩርማ ጨምሮ ይገልጻል።
ይህን የታሪክ ሐቅ በጥቂቱ ቀንጭቤ ለጽሑፌ መግቢያ ይሆን ዘንድ ማስቀደሜ አለምክንያት አይደለም። በጀግኖች ልጆቿ መሥዋዕትነት በነጻነቷ ተከብራና ታፍራ የኖረች ኢትዮጵያ ለዚህ ክብር ያበቋትን ጀግና ልጆቿን የዘከረችበትን በዓል ከሰሞኑ አክብረናል። የ፸፭ኛው ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የአርበኞች መታሰቢያ/የነጻነት ድል በዓል በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቶ ባሳለፍነው ሐሙስ ሚያዚያ ፳፯ ቀን የሃይማኖት አባቶችና ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር አምባሳደር ሙላቱ ተሾመ፣ የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ ኢጣሊያ አምባሳደር፣ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር እንግዶችና ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በአራት ኪሎ የነጻነት ሐውልት አደባባይ በደማቅና በታላቅ ሥነ ሥርዓት አክብረናል።
በዛሬው በዚህ ጽሑፌ ከዚህ የአርበኞቻችን/የነጻነት ድል መታሰቢያ በዓል ጋር በተያያዘ ጥቂት ነገሮችን ለማንሣት ወደድኹ። ይህ የድል በዓል ለቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች፣ ለአብነትም ያህል በውይይት መድረኮች፣ በዐውደ ርእይ፣ በገቢ ማሰባሰቢያና በመሰል ዝግጅቶች ነው ነበር ሲከበር የቆየው። ከዚሁ በዓል ጋር በተያያዘም በተለይ ሚያዚያ ፳፭ ቀን በአፍሪካ አንድነት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን/ECA መስብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን በተደረገው የታሪክ ሲምፖዚየም ላይ ለመገኘት ዕድሉን አግኝቼ ነበር።
ይህ የታሪክ ሲምፖዚየም በዚህ አዳራሽ እንዲደረግ ያስፈለገበትን ዋንኛ ምክንያት የበዓል ዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ የኾኑት የቀድሞው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ በለጠ ጌታቸው በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር። ይህ አዳራሽ ከዛሬ ኀምሳ ዓመታት በፊት ገደማ በአገራችን ንጉሥ- በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ መሪነትና አስተባባሪነት ነጻ የወጡ የአፍሪካ አገሮች አንድነታቸውን ለዓለም ያሳዩበትና ኅብረታቸውን የመሠረቱበት ታሪካዊ አዳራሽ ነው።
እንደ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ፣ ጋናዊው ዶ/ር ክዋሜ ንኩርማህ፣ ኬንያዊው ጆሞ ኬንያታ፣ ሴኔጋላዊው ፕ/ት ሴዳር ሴንጎርን የመሳሰሉ ፓን አፍሪካኒስት አቀንቃኝ መሪዎች አፍሪካ አንድነቷንና ኅብረቷን በማጽናት ሌሎች በቅኝ ግዛት ቀምበር ሥር እየማቀቁ ያሉ አፍሪካውያን ሕዝቦች ነጻ እንዲወጡ ድምፃቸውን በኅብረት ሆነው የሚያሰሙበትን መድረክ ዕውን ያደረገ ታላቅ አዳራሽ ነው።
ይህ ዛሬ የአርበኞቻችንን ድል መታሰቢያ ለመዘከር የተሰበሰብንበት ታሪካዊ አዳራሽ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ነጻ መውጣት የከፈሉትን መሥዋዕትነትና ያደረጉትን ብርቱ ተጋድሎ የሚዘክር፣ የእኛ፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ሕያው ቅርስ፣ የትውልዶች አሻራና መታሰቢያ ነው… ። በማለት ነበር በአድናቆት የገለጹት።
አቶ በለጠ በንግግራቸው መካከልም ለእነዚህ የታሪክ ባለውለታዎቻችን ተገቢውን ፍቅርና ክብር መስጠትና እንዳለብን በጽኑ ያሳሰቡበትና በተለይም ደግሞ በአሁን ጊዜ በአገራችን ታሪክ/የታሪክ ዕውቀት እምብዛም ቦታ የማይሰጠው፣ ትውልዱም ለታሪኩና ለቅርሱ የማይቆረቆር እየሆነ ያለበትን አሳዝኝ የሆነ አካሔድ መግታት እንዳለበት አሳስበዋል። በዓይነ አፋርነት ተሸብቦ፣ ድምፁ የማይሰማው የአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ ትምህርት ክፍልም በዚህ ጉዳይ ላይ በርትቶ መሥራት እንዳለበት ያስተላለፉት መልእክታቸውም አብዛኞቻችንን የመድረኩ ታሳታፊዎችን ያስማማ ነበር።
ለዚህ ለአንድ ቀን በተካሔደው የታሪክ ሲምፖዚየም ላይ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ምሁራን የጥናት ወረቀት ያቀረቡ ሲሆኑ በቀረቡት ጥናቶች ላይ ውይይት ተካሂዶባቸው ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ኢንጂነር ብርሃኑ ግዛው ከቅድመ-ወረራ እና ድኅረ-ወረራ ኢጣሊያ፣ አገራችን ኢትዮጵያ የነበራትን ሁለተናዊ ገጽታ ኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ መከላከያ፣ ትምህርትና ሥልጠና … ወዘተ የሚያሳይ ከ፸ ዓመት በፊት በጀርመን የፊልም ባለሙያ በተቀረጸ ዘጋቢ/ዶክመንታሪ ፊልም በማስደገፍ ያቀረቡት ንግግር የትናትናዋን ኢትዮጵያን ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ጋር በማነጻጸር ለማየት ያስቻለ ነበር።
በተመሳሳይም እንግሊዛዊው ፕ/ር ኢያን ካምፔል በስላይድ ፎቶ ግራፎች አስደግፈው ስለ ፋሽስት ወረራና የአርበኞቻችን ተጋድሎ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እጅግ የሚያስደምም ነበር። በተለይም ደግሞ ፋሽስቱን ግራዚያኒን ለመግደል የተደረገውን ሙከራና ኢትዮጵያውያን የውስጥ አርበኞች ለአገራቸው ነጻነት ያደረጉትን ተጋድሎ ትኩረት አድርገው ያቀረቡት ጥናት ብዙዎችን ያስደሰተ ነበር።
በመቀጠልም የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተሾመ ገ/ማርያም፣ ‹ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር የሕግ ድጋፍ ነበራት ወይ?!› በሚል ባቀረቡት የጥናት ወረቃታቸው፣ ኢትዮጵያም ሆነ ኢጣሊያ አባል በሆኑበት በባለ ቃል ኪዳን አባል አገሮች/League of Nations ስምምነት መሠረትም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ የኢጣሊያ ወረራ ምንም ዓይነት የሕግ ድጋፍ እንደሌለውና የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ የዐድዋውን ሽንፈት ለመበቀል ያደረጉት መሆኑን ነበር በሰፊው ያብራሩት። አቶ ተሾመ የቀድሞ ኢትዮጵያውያን አርበኞችን ታሪክ በሚገርም፣ በሚደንቅ ሁኔታ መድረኩ አልበቃ ብሎአቸው እየተንጎራደዱ፣ በሚደንቅ ወኔና በሰሜት ውስጥ ሆነው ነበር ለተሳታፊዎች ሲገልጹ የነበሩት።
ከሰዓት በኋላ ጥናት ወረቃታቸውን ካቀረቡት መካከል ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት አያታቸው ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ነጻነት ያደረጉትን አስተዋጽኦ በሚገባ አብራርተውታል። ለኢትዮጵያ ታሪክና ባህል የተለየ ክብር ያላቸው ሲሊቪያ ፓንክረስት ፋሽስት ኢጣልያ አገራችንን ወረረ ጊዜ በለንደን ከተማ አደባባዮች ፀረ-ፋሽስት ሆነ ሰላማዊ ሰልፎችን በማስተባበርና በመምራት፣ ለአርበኞች ገንዘብ በማዋጣት፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወረራውን እንዲያወግዝ ድምፃቸውን በማሰማት የኢትዮጵያ የመቼም ጊዜ ባለውለታ መሆናቸውን ያስመሰከሩ የነጻነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ ሴት መሆናቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ታሪክ ዕውቅ ምሁር የሆኑት ልጃቸው ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስትና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሪታ ፓንክረስትም ከሦስት ዓመት በፊት በሮማ ለፋሽስቱ ግራዚያኒ የቆመውን መታሰቢያ ሀውልት በመቃወም በለንደን ከተማ የፀረ-ፋሽስት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው እንደነበር እናስታውሳለን።
እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በማቋቋምና በፋሽስት ወረራ ወቅትም ከጥቁር አንበሳ ማኅበር አርበኞች ጋር በመሆን ተጋድሎ ያደረገው አፍሪካ አሜሪካዊው ኮ/ል ጆን ሮቢንሰንም በዛ ክፉ ቀን ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር በጸናት የቆመ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ ባለውለታችንና ጀግናችን ነበር። በጽሑፌ መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከጋናዊው ዶ/ር ንኩርማ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ሲሊቪያ ፓንክረስት፣ አፍሪካ አሜሪካውያን አንስቶ እንደ ሜክሲኮ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ … ያሉ አገራት በዛ ክፉ ቀን አብረውን የቆሙ የቁርጥ ቀን ወዳጆቻችንና ባለውለታዎቻችን ናቸው።
በአፍሪካ አንድነት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተደረገው የታሪክ ሲምፖዚየም ላይ የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን እንደገለጹት በቅርቡ ለኢትዮጵያ ነጻነት አስተዋጽኦ ያደረጉ አገራትና ጀግኖች የሚዘከሩበት፣ ምስጋና እና አድናቆት የሚቀርብበት መድረክ እንደሚኖር ገልጸዋል። በእርግጥም ይህ መሆን ያለበት እንደሆነ ይሰማኛል። የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማኅበርም ይህን የምስጋና ዝግጅት በቶሎ እንደሚያደረግው ተስፋ እናደርጋለን።
በዚህ በኢ.ሲ.ኤ. አዳራሽ ለአንድ ቀን በተካሔደ የውይይት መድረክ ላይም ኢጣሊያ በወረራው ወቅት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ላደረሰችው ግፍ፣ መከራና ጭፍጨፋ ካሣ ልትከፍል ይገባታል የሚል ሐሳብም ተነሥቶ ነበር። ይህ ለበርካታ ጊዜያት በተለያዩ መድረኮች በተነሣው ሐሳብ ላይ በመመርኮዝ የማኅበሩ ፕ/ት ልጅ ዳንኤል ጆቴ አንድ ትልቅ ቁም ነገር አንስተው ነበር።
ይኸውም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የ፸፫ኛ ዓመት የድል መታሰቢያ በዓል ባከበረበት ወቅት “The Era of Reconciliation” የሚል መሪ ቃል በዓሉ መከበሩን በማንሣት በመንግሥትም ሆነ በኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማኅበርና በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲፕሎማሲያዊ ትግል የአክሱምን ሀውልት ማስመለስ እንደተቻለ ሁሉ ሰላማዊ በሆነ ትብብርና ግንኙነት ከኢጣልያ መንግሥት በወረራው ወቅት ላደረሰው ውድመትና ጥፋትም ማድረግ የሚገባውን ሁሉ እንዲያደርግ ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል። ለአብነትም አሉ ልጅ ዳንኤል ጆቴ- ከሰሞኑን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢጣሊያ ፕሬዝዳንት በአገራችን ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በአራት ኪሎ በሚገኘው የአርበኞች መታሰቢያ ሀውልት ላይ በመገኘት የአበባ ጉንጉን ማኖራቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጀግንነት፣ ይቅር ባይነትና ሰላማዊ መሆኑን ያስመሰከረበት ዲፕሎማሲያው ድል ነው። ሲሉ ነበር ያስታወሱት፣ ያወደሱትም።
በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ካልነኳቸው በስተቀር በሌላው ላይ የማይደርሱ ለነጻነታቸው ቀናኢ፣ ሃይማኖተኛ፣ ሰላማዊ፣ ጀግና፣ የአኩሪ ታሪክና ቅርስ ባለቤት ሕዝቦች መሆናቸውን ታሪክ የመሰከረው ሐቅ ነው። የዚህ የጀግኖች አባቶቻችን አኩሪ ታሪክ ተካፋይና ወራሽ የሆንን እኛ ለዚህ ክብር ያበቁንን የባለውለታዎቻችንን ታሪክ ከፍ ማድረግ፣ ተገቢውን ፍቅርና ክብር ልንቸራቸው ይገባል።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የእነዚህ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ታሪክና ቅርስ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ቤተ-መዘክር/ሙዚየምን እና ቤተ መጻሕፍት ለመገንባት እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ሁላችንም ባለን አቅም በሙያችን፣ በእውቀታችን፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍና ትብብር በማድረግ ከጀግኖቻችንና ከባለውለታዎቻችን ጎን በመቆም ታሪካዊ ግዴታችንና ሓላፊነታችን እንወጣ በማለት ልሰናበት።
ፍቅርና ክብር ለዚህ ነጻነትና ክብር ላበቁን ጀግኖች አርበኞቻችን ሁሉ!
*በፍቅር ለይኩን በጎንደር ክፍለ ሀገር በበለሳ፣ በእብናት፣ በሊቦ፣ ባጃን አሞራ በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ወረራ ጊዜ ገና በልጅነታቸው ከጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጋር በመሆን በዱሩ በገደሉ የተጋደሉት የጀግናው አርበኛ የመ/አ ወርቁ ደስታ ጣሹ ልጅ ሲሆኑ፣ በሕይወት የሌሉትን አባታቸውን ተክተው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባል ናቸው፤ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በHistory and Heritage Management ከደቡብ አፍሪካው የኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በAfrican Museum and Heritage Studies Program ሁለተኛ ድግሪያቸውን የሠሩ የታሪክና የቅርስ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው።