በቅርቡ ብቻ በቴዲ አፍሮ በኩል የቀረቡ አራት የኮንሰርት ጥያቄዎች በአዲስ አበባ መስተዳድር እምቢተኝነት የተነሳ እንዳይከናወኑ መደረጋቸው አይዘነጋም፡፡የአዲስ አበባ መስተዳድር በቴዲ አፍሮ ኮንሰርትና በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ መካከል ልዩነት ባለማየቱ መከልከሉ ይታወቃል፡፡
ለነገሩ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህገ መንግስታዊ መብትና ፓርላማውም ያወጣው አዋጅ ሰልፍ ለማድረግ እውቅና እንጂ ፈቃድ እንደማይጠየቅበት ቢደነግግም የአዲስ አበባ መስተዳድር ሆቴሎችን ለቴዲ ኮንሰርት የአዳራሽ ጥያቄ ሲቀርብላችሁ መጀመሪያ ከእኔ ዘንድ ፈቃድ መጠየቅ ይኖርባችኋል በማለት አዟቸዋል፡፡
ይህ የለየለት አምባገነንነት ቢሆንም ነገሩን ገለልተኛ ሆኖ ለሚመለከተው ሰው አስቂኝ ነው፡፡ሆቴሎቹ አዳራሽ ገንብተው የተከራይ ያለህ በማለት በሚጠብቁበት ሰዓት የመጣላቸውን ሲሳይ እንዳያስተናግዱ መስተዳድሩ በገዛ አዳራሻቸው ‹‹ቴዲ መዝፈን የለበትም››በማለት ይወስናል፡፡
የሆቴሎቹ ባለቤቶች መስተዳድሩን ‹‹እሺ ቴዲ አይዝፈን ነገር ግን እርሱ የእኛን አዳራሽ እንዳይጠቀም በመደረጉ የምናጣውን ገቢ መስተዳድሩ ሊሸፍን ይገባል››በማለት ለመጠየቅና ለማስገደድ የደፈሩም አይመስለኝም፡፡
የሆነስ ሆነና ለአንድ ኮንሰርት የሚወጣውን ወጪና የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ለማሰብ እንሞክር እዚህ ውስጥ መንግስትም አለበት፡፡ነገር ግን ቴዲ መድረክ ላይ ወጥቶ ‹‹17 መርፌ ››ከሚል የሚጎዳው ቢጎዳ ይሻላል ሳይሉ ገዢዎቻችን አልቀሩም፡፡ይህው እስካሁን ግትር እንዳሉ ነው፡፡
ኢትዮጵያንም በዓለም ለኮንሰርት ከመንግስት ፈቃድ የምትጠይቅ አስገራሚ አገር በማለት በጊነስ ቡክ ኦፍ ዲክታተርስ ላይ ሊያስመዘግቧት ተቃርበዋል፡፡
የሆነስ ሆነና ቴዲ ለዘንድሮው ፋሲካ በግዩን ወይም በአንዱ ሞል ከአድናቂዎቹ ጋር እንዳይገናኝ ፈቃድ ቢከለከልም ዕድሜ ለቴክኖሎጂ በኢቢኤስ ብቅ ብሏል፡፡መለኛው ልጅ በቀጣይም ሰዎቹ የሚፈቅዱለት አለመሆኑን በመረዳት ይመስለኛል በዩቲዩብ በኩል እንድንከታተለው ሊንኩን አበጅቶልናል፡፡በሊንኩ የምናገኘውን የቴዲን ፔጅ ሰብስክራይብ በማድረግ ብቻ(ክፍያ አይጠይቅም) አብረነው ልንዘልቅ እንችላለን፡፡
teddyafromusic.com
የበዓሉን ምሽት ጣፋጭ ላደረጉት ኢቢኤሶች ብዙ ምስጋና፡፡ከአሁን በኋላም የተውኩትን የሰይፉ ፋንታሁንን ሾው ጭምር እንደምከታተል ቃል እገባለሁ፡፡