የፖለቲከ ስህተትና የሳንባ ነቀርሳ ጠንቆች የተመሳሳይነት ባህርይ አላቸው፡፡ ሁለቱም ችግሮች በለጋነታቸው ወቅት ከተነቃባቸው ችግሮቹን የማስወገድ ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ችግሮቹ ሥር ከሰደዱ በኋላ የሚደረገው መሯሯጥ ግን ፈውስ የማስገኘቱ ሁኔታ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ሊሆን ይችላል፡፡(ማርጋሪት ታቸር የእንግሊዝ ጠ/ም የነበሩ)
ፓርቲ የምርጫ ቦርድ የምዝገባ ምስክር ወረቀት መያዝ አይደለም፤ አርማና ማህተም ቀርጾ ቢሮ መክፈትም አይደለም፤አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ መግለጫ መስጠትም አይደለም፡ ወዘተ፡፡ በዚህ ለሚስማማ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ፓርቲ የለም፡፡ ስለሆነም በሌለ ነገር ላይ ምንም አይባልም ተብሎ ዝም ሲባል የዝምታን ግድብ የሚያፈርሱ ጉዳዮች ያጋጥማሉ፡፡
ሰሞኑን የሰማያዊ ሰዎች (ልብ በሉ ፓርቲ አላልኩም) ጉዳይ ከሀገር ቤት ጋዜጦችና ማንም አንደፈለገው ከሚፈነጭበት ማህበራዊ ድረ ገጽ አልፎ ብዙ አድማጭ ያላቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ራዲዮኖች ዜና ለመሆን መብቃቱ ነው የእኔን ዝምታ አስጥሶ ይህችን አንድጽፍ ግድ ያለኝ፡፡
ከሰማያዊ ሰፈር የምንሰማው ባለፉት ሀያ አመታት ስንሰማ ከኖርነው በቃላትም በድርጊትም አንዳችም ልዩነት የሌለው ነው፡፡ፖለቲከኞቹ በሽታቸውን አያውቁም ቢያውቁም አምነው ትክክለኛውን መድሀኒት ለመውሰድ አይደፍሩም፡፡በመሆኑም ስራቸው ሁሉ መካሰስ መወነጃጀል መፈራረጅ ማገድ ማባረር ወዘተ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በሽታውን ይበልጥ ያብሰውና ስብስቡ ፓርቲ የሚል ስም ይዞ ግን ፓርቲ ደረጃ ሳይደርስ ይሞታል አልያም የአልጋ ቁራኛ ይሆናል፡፡
ሰሞነኛው የሰማያዊ ሰፈር ዜናም ታገዱ ተባረሩ፤ ውሳኔውን ተቃወሙ፤ ኦዲት ኮሚሽን ውሳኔውን አገደ፤ወዘተ የሚል ነው፡፡ ይህ በምንም መልኩ ስብስቡን ከበሽታው ሊያድነውና ከሞት ሊታደገው አይችልም፡፡አበው ውኃን ከጥሩ ነገርን ከስሩ አንደሚሉት ዘለቅ ብሎ ወደ ውስጥ ጠልቆ የበሽታውን ምንነትና አንዴትነት መመርመር ደፈር ብሎም መድሀኒቱን ለመውሰድ መዘጋጀት ከሌለ ዋይታውን አቁሞ ለቀብሩ መዘጋጀት ነው፡፤
የዚህ ጽሁፍ አላማ አውቀውት ግን ድፍረት በማጣት አለያም ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ሆኖባቸው ያላወቁትን በሽታቸውን ከነምክንያቱና ምልክቱ በማሳየት በርግጥ ችግሩ የየግል ጉዳይ ሳይሆን ስብስቡን መታደግና በሂደትም ወደ ፓርቲ ደረጃ ማሸጋገር ከሆነ ደፍረው በበሽታቸው ላይ አንዲነጋገሩ መድሀኒቱንም ሁሉም አንደ ህመማቸው መጠን አንዲወስዱ ለማበረታታት ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ ፈቃደኝነቱም ዝግጁነቱም ድፍረቱም ያላቸው ምን ያህል ሰዎች ይኖሩ ይሆን የሚለው ስጋቴ ነው፡፡ ቢሆንም ቀብሩ ላይ ከማልቀስ ከበሽታው እንዲፈወስ የሚቻለውን ማድረጉ ይሻላልና የአኔን ልወጣ፡፡ ይህች ጽሁፍ በበቂ ማስረጃ ላይ የተመሰረተች እንድትሆን ስለ ሰማያዊ ካለኝ እውቀት በተጨማሪ ወደ ኋላ ተመልሼ ጽሁፎችን ለማየትና ከአባላቱና ከአመራሮችም ጥቂቶችን ለማነጋገር ሞክሬአለሁ፡
ሰማያዊ የታመመው ወፌ ቆመች ሳይባል ነው፡፡ ለዚህ ያበቁት ምክንያቶች ደግሞ ፤
1–የግንቦት 2004 ሰላማዊ ሰልፍ፤
ሰማያዊ የፓርቲነት ምስክር ወረቀት አግኝቶ ሁለት ዓመት ሳይሞላው የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ውጤታማ ሆነ፡፡ ይህ ሰልፍ ከምርጫ 97 በኋላ የመጀመሪያ በመሆኑም ለሰባት አመታት የተዘጋውን የሰላማዊ ሰልፍ በር ያስከፈተ የሚል ቅጽል ተሰጥቶት የመገናኛ ብዙኃን አብይ ትኩረት ሆነ፡፡ የስብስቡ አባላት በተለይም በመሪነት ቦታ የነበሩት ሰልፉን ውጤታማ ያደረገው ከእነርሱ ስራ በላይ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት (የሙስሊሞች ተቃውሞ) መሆኑን እያወቁ ቢያውቁም የእነርሱ ስራ የፓርቲያቸው ጥንካሬ የመሪዎቹ ብቃት አንደሆነ አድርገው ተኮፈሱ ተኩራሩ፡፡ በዚህም ገና ወፌ ቆመች ሳይባሉ ፓርቲ ለመሆን የሚያበቃቸውን ድርጅታዊ ስራ ሳይከውኑ በሽታው ጀመራቸው፡፡
2-የሊቀመንበሩ የአሜረካ ጉዞ፤
ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከአሜሪካ የተመለሱት ለ “ፓርቲያቸው” ገንዘብና ቁሳቁስ ለራሳቸው ደግሞ ማን አህሎኝነት ይዘው ነው፡፡ ከዲያስፖራው የተለገሳቸው አክብሮት አድናቆት ሙገሳና ጭብጨባ ከሚችሉት በላይ ሆነና ራሳቸውን የሰማዊ ብቸኛ ሰው አድርገው አንዲያዩ አበቃቸው፡፡
3- ሊቀመንበሩ በተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች መጋበዝ፡፡
አስቀድሞ የግብዣው ዓላማ ምንድን ነው፤ ከእኛ የሚፈልጉት ምን ይሆን እኛስ ከዚህ የምናተርፈው ነገር አለ ወይ ብሎ ከግንኙነቱም በኋላ ከዴፕሎማቶቹ ምን ተረዳን፤ ከእኛ ምን አገኙ እኛስ ምን አገኘን ወደ ፊት ከእኛ ስለሚፈልጉት ነገርስ ምን ተረዳን ወዘተ ብሎ ሂደቱን ገምግሞ ለበለጠ ስራ ከመዘጋጀት ይልቅ ሰማያዊ ተለይቶ የተጋበዘው ጠንካራና አማራጭ ሊሆን አንደሚችል በመገንዘባቸው ነው የሚል አብጠት ተፈጠረና ስራ ቀርቶ ወሬው ሁሉ ይሄ ሆነ፡፡
4-የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ የግልም የጋራም ኃላፊነታቸውን አለመወጣት፤
ስራ አስፈጻሚው በመተዳደሪያ ደንብ ላይ የሚገለጹ ኃላፊነቶቹን አንዲወጣ የእያንዳንዱ የስራ አስፈጻሚ አባላቱ ብቃት ትጋትና ራስን ለትግሉ መስጠት ወሳኝ ነው፡፡ በአንጻሩ እያንዳንዱ የሥራ አስፈጻሚ አባል የተመደደበበትን የየግል ኃላፊነት አንዲወጣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴውና የሊቀመንበሩ ድርሻ ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን በአመራር ላይ የነበሩ ሳይቀሩ ይህ እንዳልነበረ ነው የሚናገሩት ፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚታዩትና የሚሰሙት ሊቀመንበሩ ብቻ መሆናቸውም የሥራ አሰፈጻሚ አባላቱ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ እንዳልነበረ የሚያረጋገጡ ናቸው፡፡ ይህም ስብስቡ መተዳደሪያ ደንቡን አክብሮ በመመሪያ እየተመራ የሚሰራ ሳይሆን በፍላጎትና ስሜት ብቻ የሚጓዝ እንደነበረ ያሳያል ፡፡ ዛሬ ሰበብ ሆኖ የሚነገረው የገንዘብ ጉዳይ ከመነሻው የገንዘብ አጠቃቀም መመሪያ ቢኖር እዚህ ደረጃ ባልተደረሰ ነበር፡፡
ሌሎች ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም በዚህ ይብቃኝና የበሽታውን ምልክቶች በመጠኑ ላሳይ፡
1 -ከሰማዊ በቀር ሌላ ፓርቲ የለም፤
ፓርቲ ለመባል የሚያበቃ ደረጃ ላይ ያልደረሰው ሰማያዊ ሌሎቹን በሙሉ ፓርቲ አይደላችሁም በማለት ገና ወፌ ቆመች ሳይባል ግጭት ውስጥ መግባቱ፡፡
2-ፍረጃና ውንጀላ-
የሚነሱ ሀሳቦችንና ጥያቄዎችን በውይይት መፍታት የሚባል ነገር ጠፍቶ ወገን ለይቶ ቡድን መፍጠር መወነጃጀልና መፈራረጅ ከዚህም አልፎ ለአንድ ዓላማ በአንድ ፓርቲ የተሰባሰቡ ሰዎች አንደ ደመኛ ጠላት መተያየት፡
3-በጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ መለያየት፡
የአንድ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ መቼ አንዴት በማንና ለምን አንደሚጠራ መተዳደሪየ ደንቡ ስለሚወስን ልዩነት ሊፈጥር አይችልም፡፡ የሰማያዊ አባላት በ2006/07 ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራ አይጠራም በማለት የከረረ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው የበሽታቸው አንዱ ምልክት ነበር፡፡ በወቅቱ አንደሰማነው የአይጠራም ባዮቹ መከራከሪያ የሰማያዊ እድሜ የሚቆጠረው መስራች ጉባኤው ከተካሄደበት ሳይሆን ምርጫ ቦርድ ሰርተፍኬት ከሰጠበት ግዜ ነው የሚል መሆኑ በሽታቸው ስር እየሰደደ ለመሄዱ የሚያሳይ ነበር፡፡
4-ውይይትን አሻፈረኝ ማለት፤
2006 ላይ በወቅተቱ ለነበረው የቁጥጥር ኮሚሽን ክሶች ቀረቡ፡፡ ኮሚሽኑ ክሱን ካጣራ በኋላ የርሱ ውሳኔ ዘላቂ መፍትሄ እንዳማያመጣ በመረዳት የፖለቲካ ችግር መፍትሄ የሚያገኘው በውይይት ነውና የውይይት መድረክ ይዘጋጅ የሚል ሀሳብ ሲያቀርብ አንወያይም ውኔህን አሳውቀን የሚል ምላሽ ነው ያገኘው፡፡ በዚህም ኮሚሽኑ የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና የተቀጡትን ሰዎች ገለጸ፡፡ ነገሩን ይበልጥ አከረረው፤ መጠላላቱን አከፋው እንጂ መፍትሄ አልሆነም፡፡
5-ምርጫ 2007-
ሰማያዊ ለምርጫ 207 ዝግጅት እንዳልነበረው ያቀረባቸው እጩዎች አብዛኛዎች ከአንድነት የገቡ መሆናቸው ብቻውን በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ለምን አልተዘጋጀም ሳይዘጋጅስ ለምን ምርጫ ገባ፤ በደል ደረሰበኝ እያለ እስከ መጨረሻው በምርጫው ለምን ቀጠለ ከምርጫው ምን አተረፈ ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች አመራሮቹ ሳይቀሩ በቂ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ይህ ለህዝብ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ለአባላቱና ለአመራሩ ጭምር ግልጽ ካልሆነ የበሽታ እንጂ የሌላ ምልክት ሊሆን አይችልም፡
6-ጠቅላላ ጉባኤ-
እነዚህና ሌሎች የበሽታ ምልክቶች በግልጽ እየታዩ ባለበት ወቅት የተጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ ተበተነ ከማለት ያለፈ ተግባር ሊያከናውን አለመቻሉ የሰማያዊ በሽታ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ቢሆንም በተለይ አመራሩ በሽታውን ለማግኘትና መድሀኒት ለመፈለግ ፍላጎትም ዝግጅትም አንደሌለው ያሳየ ነበር፡፡
የሥነ ሥርዓት ኮሚቴም ሆነ የቁጥጥር ኮሜቴ ውሳኔ የበሽታውን ምንነትን የደረሰበትን ደረጃ ለማወቅ አይስችልም፡፡ በዚህ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤ ቢጠራም መድሀኒት አይሆንም፡፡ እኔ ግን እላቸዋለሁ ደፈር በሉና ቀናነቱም ይኑራችሁና እኔ ያነሳሁዋቸውንና ከዚህም የሚልቁትንና እናንተ የምታውቁዋቸውን ለበሽታ የዳረጉዋችሁን ምክንያቶች በቅጡ መርምሩ ተነጋገሩ፣ ከዛም መድሀኒት ፈልጉ፡፡ ደረጃው ይለያይ አንደሆነ አንጂ በበሽታው ያልተለከፈ አይኖርምና ሁላችሁም እንክብሉን ለመውሰድ ተዘጋጁ፡፡ በውስጥም በውጪም ያላችሁ አባላትም ሆናችሁ ደጋፊዎች ጎራ ለይታቹሁ በሽተኞቹን ወደ መቃብር የሚገፋ ሆይ ሆይታችሁን አቁሙና በሽታቸውን እንዲያውቁ መድሀኒቱንም እየመረራቸውም ቢሆን አንዲውጡ ለማበረታታትም ከቻላችሁ ለማስገደድም ትጉ፡፡ ይህ ካልሆነ የቻላችሁ በአካል ያልቻላችሁ በማህበራዊ ድረ-ገጽ ለቀብሩ ትገናኛላችሁ፡፡ እኔ ግን ፈጣሪ መልካሙን ለመስማት ያበቃን ዘንድ እመኛለሁ፡፡
The post ሰማያዊ ይድን ይሆን? – ይገረም አለሙ appeared first on ሳተናው .