Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

“የልጄን ነገር አደራ! እባክህ ነፍሴን አሳርፋት"እናት ሎሜ ረጋስ

$
0
0

የማለዳ ወግ …

* በኀዘን የሚላወስ እንስፍስፍ የእናት አንጀት

* የኮንትራት ሠራተኛዋን እህት ቤዛን አፋልጉኝ!

ነቢዩ ሲራክ

ሆዴን ያላወሰው የእማማ ሎሜ አደራ

Beza Ashenafi Engida and her mother Lome Regass. እህት ቤዛ አሸናፊ እንግዳ እና እናት ሎሜ ረጋስ

የእናትን መሪር ኀዘን ሰምቼ ሆዴ ተላውሷል፣ የእናትን ጥልቅ ጭንቀቷ፣ ያለ አባት በአሳር በመከራ ያሳደገቻት የእናትን ሎሜ መሪር ኀዘን ተረድቼ ሕመም መታመሜ እውነት ሳለ፤ በዝምታ እየቆሰልኩ ማስረጃና መረጃ ፍለጋ መዋተቴ ሕመሜን አክብዶታል። ከጉያዋ ወሽቃ፣ በትንፋሿ አሙቃ፣ ስታገኝ በደስታ፣ ስታጣ ተከፍታ፣ ድሃ አደግ ቤቷን አሟሙቃ፣ ነገ ልጆቿን ለወግ ለማዕረግ የማድረስ ምኞት ተስፋን ሰንቃ፤ ተስፋዋን የተነጠቀች እናት እንባ ውስጤን አድምቶ አቃጥሎታል። እናት ዛሬ ማለዳ በላኩልኝ መልዕክት እንዲህ ይላል “የልጄን ነገር አደራ! እባክህ ነፍሴን አሳርፋት” …


ሰው ሆዬ ሲጨንቀው እኔ መረጃን ከምንጩ ከማሰራጨት ባለፈ ሁሉን ማድረግ የሚቻለኝ አድርጎ ይስለኛል፤ እኔ ግን አቅሙ የለኝም! መረጃዎችን ለወገናቸው ጥቅም ቅድሚያ ከሚሰጡ የመንግሥትና የድርጅት አባላት በሚስጥር፤ ከቀሩት ወገኖች በአደባባይ የሚደርሰኝ መረጃ የተጣሰው የስደተኛ መብት ይከበር ዘንድ ሁሌም የመረጃ ጉልበቴ ነው! ያገኘኋቸውን መረጃዎች እያጣራሁ ሰሚ ቢገኝ አቀርባቸዋልሁ! ከዚህ ባለፈ ጉልበት የመርዳት አቅሙ እንደሚገመተው የለኝም!

በተለያዩ አቅጣጫዎች መረጃን ፈላፍየ የማግኘቴን ያህል ግን ለመብት ማስከበሩና ለመፍትሔው የመንግሥት ተወካይ የቆንስልና ኤምባሲ ሰዎች እንጅ፤ እኔ አቅም ሥልጣኑ የለኝም … በመንግሥት ተወካዮቻችን በኩልማ መረጃን ለማግኘት እንኳ ከአንድ ተራ ዜጋ ያነሰ መብት እንዳለኝ ስንቶች እንደሚረዱ አላውቅም! መረጃ በማቀበሌ ብቻ “መንግሥትን አትወድም፤ ተቃዋሚ ነህ” የሚሉኝ ካድሬዎች አንድ መረጃ ሳቀርብ በአካልና በዋትሳፕ በቡድን ተሰባስበው “በነቢዩ ጽሁፍ ላይ እንዝመት፤ መልስ እንስጠው!” ከማለት ውጪ፤ እኔ የማነሳቸውን ጉዳዮች እንኳ መርምረው ስለሰብዐና ብለው፣ ፈጣሪን ፈርተው በስደት የተጨነቀ ወገናቸውን አይደግፉም፣ ስለሰብዕና የቆመው፣ ወገኑን የደገፈውን በስውር ያሳድዱታል፣ ለእነሱ ሁሉም ነገር ድርጅታቸው ነው። እነሱ እንዲህ ናቸው! …

እኔ የሆነና የተጨበጠ ግልጽ ያለ መረጃ ሳቀርብ እነሱ የተንሸዋረረ ስም ማጥፋቱ ልማድ አድርገውታል! … በዚህ መካከል የተገፋው ወገን ድምጽ ከፍ ብሎ ይሰማኛል! የእናት ሎሜ ረጋስ የአደራ መልዕክት ደግሞ የእኔን የጨካኙን ልብ አርዶታል፤ ሆዴን ያላውሶታል … እኒህን እናት ምን ላድርጋቸው? ከሰሞኑ በውስጤ እየተብላላ ሰላም የነሳኝ እንደ እናት ሎሜ ረጋስ እዚህ ደረጃ ያልደረሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቻቸውን በኮንትራት ልከው ደብዛው የጠፋባቸውን በገጠር ያሉ እናቶችን አሰብኳቸው … ታምሜ ሰንበትኩ፤ በቤቴ ውስጥ ሳይቀር ሰላም አጣኝ፤ ሕመሜን ተረድቶ የሚያክመኝ ባጣም፤ ችየው የእናት ሎሜን አደራ ለመወጣት የቤዛን ታሪክ በጨረፍታ አሳውቃችኋለሁ!

እህት ቤዛን ሳውዲ ያደረሳት መንገድ …

በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኘው እህት ቤዛ አሸናፊ እንግዳ፣ ከአሰላ ተነስታ በቦሌ አየር መንገድ በኩል ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ሳውዲ ዐረቢያ ያቀናችው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር። ከዚያ ወዲህ ብዙ ጊዜ ከቤተሰቧ ጋር ትገናኝ ነበር። መስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ከእህቷ ጋር ከተገናኘች ወዲህ ግን ድምጿ ጠፍቷል። ቤተሰቦችዋ ከወሰዳት ኤጀንሲ እስከ ሳውዲ አሰሪዋ ድረስ በየአቅጣጫው ሲያፈላልጓት ሰንብተው ለመጨረሻ ያገኘኋት በአሰሪዋ በኩል መረጃ ተገኘ። አሰሪዋ የቤዛን ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን አስረድተው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሞቷን እንዲያረጋግጡ አሳወቋቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ስለ አሟሟቷ ምንም ማስረጃ ሳያቀርብ ቤዛ ራሷን ሰቅላ መግደሏን ለቤዛ ቤተሰቦች አረዷቸው። እናትና የቀሩት ቤተሰቦች ከኀዘኑ በላይ ሞተች የተባለበት መንገድና ስለመሞቷ የፎቶም ሆነ የሰነድ መረጃ አለመቅረቡ ኀዘናቸውን መሪር አደረገው። የቤዛ ቤተሰቦች በዚህ ሁኔታ የሚይዙ የሚጨብጡት አጥተው “አስከሬንዋ ይላክልን፣ አስመጡልን” ብለው ሲጠይቁ “የቤዛ አስከሬን ተቀብሯል“ የሚል መልስ ተሰጣቸው። ሞተች የሚለውን ማመን የገደዳቸው እናት ሎሜ ረጋስ መላው ቤተሰብ በቤዛ ዙሪያ የሆነውን በጥርጣሬ ማየት ጀመሩ። ወላጅ ቤተሰብ ሳይጠየቅና ሳይፈቅድ ምን ሲባል የቤዛ አስከሬን ሳውዲ ላይ ተቀበረ? ለምን? እንዴት? ይህን የቤተሰብ ውል ያለው ጥያቄ ነው፤ ቤተሰብም እኛም ወላጅ ቤተሰብ ሳይጠየቅና ሳይፈቅድ ምን ሲባል የቤዛ አስከሬን ሳውዲ ላይ ተቀበረ? ለምን? እንዴት? እንጠይቃለን!

የቤዛ ቤተሰቦች በተለይም እናት ሎሜ እርማቸውን ሊያወጡ በማይችሉበት መንገድ በኀዘን ላይ ኀዘን ተደራረበ፤ ተጫነባቸው። ቤዛ ራሷንና ድሃ አደግ ቤተሰቧን ለመደገፍ ሕጋዊ በተባለው ኤጀንሲ ቪዛ ይዛ ለሥራ ወደ ሳውዲ መላኳ እውነት ነው። በተላከችበት ሀገር በሥራ ላይ እንዳለች ስለመሞቷ ቤተሰብ ባይጠይቅ፤ የተገኘው መረጃም ላይገኝ ይችል እንደነበር ቤተሰቦችዋ ያስረዳሉ። ሞታለች የሚለው መርዶም ድፍንፍን ያለ መሆኑ ቤተሰቡን ግራ አጋብቶታል። የተነገራቸው መረጃ የተዛባ ነው እስከ ማለት ደረሰዋል። በዚህ የመከራ አጣብቂኝ ለወደቁ ቤተሰቦች ከቀናት በፊት የለቀቅኩት የአሚናት መረጃ ተስፋን አጭሮባቸው እኔኑ ማፈላለግ ጀመሩ። በእርግጥም ሞታለች ተብሎ ተነግሯቸው በኀዘን ተቀምጠው እርማቸውን ባወጡ በሁለት ዓመታት አሚናት መዲና በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተገኝታለች። በውል የማይታወቅ የመኪና ግጭት አካሏ ጉዳት ከደረሰባት ከሁለት ዓመት በኋላ አሚናት በአብሮ አደጓ በእህት ሀድያና በቀሩት ወገኖቿ ትብብር ሀገር ቤት ገብታለች፣ ለሀገሯ ምድር በቅታለች። ከእናቷና ቤተሰቦቿን ተቀላቅላለች። የአሚናት እውነት የቤዛን ቤተሰቦች ልጃቸው በተመሳሳይ መንገድ እንደ አሚናት ትመጣ ይሆናል የሚል ተስፋን አጭሮላቸዋል።

እናትና እህት የአሚናትን ታሪክ ከሰሙ በኋላ ቤዛ አለች ብለው ተሰፋ አድርገዋል። “ራሷን ሰቅላ ሞተች” ተብሎ የተነገራቸውን አላምን ብለው ትተውታል፤ በአንጻሩ ያችን የደስ ደስ ያላት የሚያውቋት ቤዛ “ትመጣለች” ብለው ዓይናቸው በተስፋ ይዋትት ይዟል። … የቤዛ ነገር ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። የቤዛ ቤተሰቦች እንደ አሚናት ሁሉ ቤዛ የፈለገውን ጉዳት ደርሶባትም ይሁን በሕይወት ትቀላቀላቸው ዘንድ ጓጉተዋል … የልጃቸውን ጉዳይ አጣርቼ እንዳሳውቃቸው ደግሞ እኔኑ ፍለጋ ይዘዋል …

ስለእህት ቤዛ ዝርዝር መረጃ

ከተባበሩት ኢምሬት አድራሻየን አግኝታ ልብ ሰባሪውን የቤዛ ታሪክ ያጫወተችኝ እህት የቤዛን እናት እና የመላ ቤተሰቡን ኀዘን ጫፍ ጫፉን ነበር። ስለሆነው ሁሉ ሙሉ መረጃን እንደሚያስፈልገኝ ገልጨላት ብዙም ሳይቆይ ከቤዛ እህት ከመዓዛ አሸናፊ ጋር አገናኘችኝ። ከመዓዛ በዋትሳፕ ተገናኝተን ስለቤዛ ብዙ አጫወተችኝ፤ መዓዛና ቤዛ መስከረም ሲጠባ በፌስ ቡክ ይገናኙና ያወሩ እንደነበር፣ ቤዛ ወደ ሀገር ለመምጣት ዝግጅት ላይ እንደነበረች እህት መዓዛ ገላልጣ አወጋችኝ። የእናቷን መከራና ቤተሰቡ የገባበትን የኀዘን ማጥ ስትናገረው ደግሞ ልብ ይሰብራል። የቤዛ እናት ወ/ሮ ሎሜ የልጃቸውን መሞት በመረጃ አስረግጦ የነገረችው ስለሌለ እንደ አሚናት እናት ወ/ሮ ወርቅነሽ ልጃቸው አደጋ ደርሶባት ተደብቀው እንጅ “ሞተች” ብለው ለማመን ገዷቸዋል። እናም ሌት ተቀን “እህህ” እያሉ እንባቸውን በማዝራት በር በሩን በማየት ቤዛን ይጠብቃሉ … የእናት አንጀት! ምስኪኗ እናት የወ/ሮ ሎሜ ረጋስ ከዓመታት በፊት ወደ ሳውዲ የመጣች አንድ ፍሬ ልጃቸውን በመላከ ሞት የመነጠቃቸው መርዶ እንደ ቀላል፣ እንደአልባሌ ነገር “ልጅሽ ቤዛ ራሷን ሰቅላ ሞታለች” ተብለው ጎረቤት፡ ዘመድ አዝማድ፤ እድርተኛ ተሰብስቦ፣ ደረት ተመትቶ፣ ሙሾ ተደርድሮ ኀዘን ቢቀመጡም “ቤዛ ሞታለች” ብለው አላመኑም። በኀዘን ላይ መሪር ኀዘን ተደራርቦባቸዋል፣ ቅስማቸው ተሰብሯል።

የቤዛ ቤተሰቦች፤ ቤዛ ሞተች በተባለበት የጅዳ ከተማ የምገኘው ለእኔ አፋልገን ብለውኝ ፈቃደኛ መሆኔን አሳውቄያቸዋለሁና በእኔ ላይ ተስፋ ጥለዋል፤ እንዲህ አሉኝ “ነቢዩ ቤዛ ጤነኛ ነች፣ ራሷን ስታ አትታነቅም፣ ግን ሞታም እንደኹ ስለአሟሟቷ መረጃ ሰባስበህ ሞተች በለን! ካለችም አለች ብለህ የደስታ ብስራት አሰማን፤ እኛ የምንፈልገው በልጃችን ላይ የሆነውን ማወቅ ብቻ ነው፤ እባክህ ተባበረን፡ እባክህ እርዳን” የሚለው መልዕክት ደጋግመው አድርሰውኝ ነበርና ተጨናንቄያለሁ። ወላጅ ቤተሰብ በውጭ ጉዳይ በኩል የመቅበሪያ ውክልና ካልላኩ ማስቀበር እንደማይቻል አሳምሬ ባውቅም፤ የቤዛ ከቤተሰብ እውቅና ውጭ መቀበር በእርግጥም አሳሳቢ ነው። የቤዛ ቤተሰቦች ቤዛ የሆነችውን አፈላልገህ፤ አጣርተህ አሳውቀን ቢሉኝም፤ ”ሞተች“ ተብሎ ፎቶም ሆነ ተዛማጅ መረጃ አልቀረበላቸውምና ”ቤዛም ትመጣልናለች“ ብለው በተስፋ እየተጠባበቁ መሆኑ ደግሞ ከብዶኛል። የከበደኝ ያለ ነገር አይደለም፣ ወላጅ ዘመድ ሳይሰማ፣ ማንነታቸው ሳይረጋገጥ እንደወጡ የቀሩ ብዙ የስደት ታሪኮችን መስማት ሳይሆን አይቻለሁና የወላጅ ሕመሙ ዘልቆ ያማል።

የቤዛ ቤተሰቦች ”እባክህ ቤዛን አፋልገን!” እናት ተማጽኖ ካቀረቡልኝ ሣምንት አለፈው፤ ሰምቸው እንዳልሰማሁ ተረጋግቼ ጉዳዩን ውስጥ ውስጡን ማጣራት ይዣለሁ፤ የቤዛን እህት በተደጋጋሚ ፎቶ እንድትልክልኝ አድርጌ እያቀረብኩና እያራቅኩ በመጠለያው በር ላይ በተደጋጋሚ ወድቀው ካነሳኋቸው እህቶቸ ፎቶዎች ጋር ባመሳስለውም ቤዛን አላገኘኋትም። ቤዛ አዕምሮዋ ታውኮ ራሷን መሰቀሏን በሰበር መረጃ አቅርቤው ነበርና እሱንም ተመለከትኩት፤ ራሷን ሰቀለች የተባለችው እህት ደግሞ የልጆች እናት መሆኗን ከመጠለያው በወቅቱ ያገኘሁት ያስረዳል። ይህም ከቤዛ ጋር አልገናኝ አለኝ … ሌላ መረጃ አስታወስኩ፤ ራሷን ሰቀለች የተባለችው እህት ከመሞቷ ከቀናት በፊት በጅዳ ቆንስል የቅርብ ርቀት ግቢ አትግቢ በሚል የነበረውን ግርግር የሚያሳይ በሚስጥር የተነሳ ተንቀሳቃሽ ምስል በእጄ ይገኛልና እሱኑ እያቀረብኩና እያራቅኩ ማየቴን ቀጠልኩ … ጩኸት ግርግሩ ይታያል! የዚያች እህት ምስል ግን ብዙም ግልጽ አይደለም፤ ከቪዲዮው ፎቶ አንስቼ ለቤዛ ቤተሰቦች ላኩላቸው። ለመለየት ተቸገሩ … እንዲህ እንዲህ እያልኩ ሣምንት ገፋሁት … ተደጋግሞ የሚደርሰኝ የቤዛ ቤተሰቦች ጭንቀትና ተማጽኖ አላስቀምጥ አለኝ! ሰምቼው ጉዳዩን እስካጣራ ብዬ ለጊዜው የዘለልኩት፣ ግን ሠላም የነሳኝን የቤዛን እናት ጭንቀት የቤዛ ቤተሰቦች የሚያስረዳውን ከእህቷ ከቤዛ የደረሰኝ አንዱን የድምጽ መልዕክት ከፍቼ መስማቴን ቀጠልኩ … እንዲህ ይላልለ፡-

“እባክህን ነብዩ ከጎናችን ሁን፣ ይህን የመጣብንን ነገር ተባብረኸን የሆነ ነገር ላይ እንድንደርስ እፈልጋለሁ፣ እባክህን! በቃ ከምነግርህ በላይ ነው። በተለይም እናቴ በጣም እየተጎዳች ነው። ምን ማድረግ እንዴት ማድረግ እንዳለብኝ እንኳን ግራ እስኪገባኝ ድረስ በጣም ተጎድታለች። እሷ ነች ያሳደገችን፣ አባታችን ልጅ ሆነን ነው የሞተው። በመጨረሻም የእሷ ክፍያ ይሄ ሆነ። እና የሚሰጡን መረጃ እንዳልኩህ በጣም የተለያየ ነው፣ እ … ጓደኛዋን ሳናግራት ነበር፤ እዛው ዘመድ ቤት የምትሠራ ልጅ ነችና ሰውየየ የነገረኝ ከመዲና፣ የሚኖሩበት መዲና ነው፣ ወደ ጅዳ ስትጠፋ ነው፣ እ … ዱርየዎች አግኝተዋት ተጫውተውባት ከዚያ ውጭ ላይ የጣሏት፣ ዓይነት ነገር ነው የነገረኝ የእኔ ሰውየ፣ ሰውየየ አይዋሽም ብላ ነው የነገረችኝ። ከኤምባሲ (ከጅዳ ቆንስል ለማለት ነው) በኩል ደግሞ የምትሰማው ያው እንደነገርንህ ራሷን እንዳጠፋች ነው የሚናገሩት። በጣም እኔ እንጃ ዝብርቅርቅ ነው ያለብኝ፣ በምትችለው ነገር ተባብረህ የሆነ ነገር ላይ እንድትደርስልን እለምንሃለሁ! በቃ በምትችለው ነገር!! የሆነ ብቻ ትክክለኛውን ነገር ቢያንስ ቢያውቅ ሰው አዕምሮው ያርፋል። ሁለተኛ ነገር የአስከሬኑ ጉዳይ ራሱ እንዴት? ማን? መጠየቅ እንዳለብኝ አላውቅም ነብዩ። ከሥራህ በተጨማሪ እንደወንድም ነው የምጠይቅህ፣ እንዴት ማድረግ እንዳለብን አላውቅምና ካንተ ራሱ ምክር እፈልጋለሁ በቃ። ማንም የለም ከጎናችን፣ እንዳልኩህ እናታችን ነው ያሳደገችን፤ ሌላ ከጎናችን ሆኖ የሚረዳን የሚያግዘን እንደዚህ እንደዚያ አድርጉ ብሎ የሚነግረን የለም! እዚህ ካሳንችስ ሄደን ነበረ፣ ምንም ዓይነት መረጃ የለም፣ እንዲጠየቅላችሁ የምትፈልጉት ካለ ፎርም ሙሉ ብሎ ነግሮኛል፤ ሰኞ ኺጄ እሞላለሁ፣ እስኪ የሚያመጡትን ነገር ከዚያ ካለ አያለሁ! እኛጋ ወረቀት ተቀብሎ ቁጭ ማድረግ ነው፣ እኔ “እህቴ ድምጿ ጠፍቶ ወር ከ15 ቀን ሳይሞላ ነበር ለሄደችበት ኤጀንሲ ያሳወቅኩት፣ ጠፍታብኛለችና እናንተ መጠየቅ በሚገባችሁ በኩል ጠይቁልኝ ”ብየ ሰጠሁት፣ ግን ምንም ዓይነት መልስ አልሰጠኝም። በእኛም ጥረት ላይ ነው እዚህ ላይ ያለው። ግን እየተሰጠን ያለው ኢንፎርሜሽን ደግሞ የተለያየ የተዘበራረቀ ነው፣ እባክህን እ – ባ – ክ – ህ – ን አንተ አንድ እንድታደርግ እፈልጋለሁ፣ በቃ! እግዚአብሔር ይርዳህ አንተንም። ምንድነው ማድረግ ያለብን ነገር? ከዚህ ውጭ ደግሞ የራስህ የሆነ ስለሠራህበት ስለምታውቅ ስለሠራህበት የተወሰነ ምክር እንድትሰጠኝ!” ይላል ሙሉ መልዕክቱ …

እናም የቤዛን ቤተሰብ አቤቱታና የጭንቀት የድረሱልን ጥሪያቸውን ይድረሳችሁ፤ ስለእህት ቤዛ አሸናፊ እንግዳ መኖርና መዳረሻ ዙሪያ የተጨበጠ መረጃ ያላችሁ ወገኖች ታሳውቁን ዘንድ አደራዬ የጠበቀ ነው! “እህት ቤዛን አፋልገን” በማለት አደራ የሰጡኝ የሚማጸኑኝ የእናትና የቤተሰቡን ጭንቅ ተረድታችሁ ያላችሁን መረጃ ታቀብሉን ዘንድ በትህትና እንማጸናልን!

ቸር ያሰማን!

ነቢዩ ሲራክ

መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles