Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

“የልጄን ነገር አደራ…” እናት ሎሚ

$
0
0

የእናትን መሪር ሐዘን ሰምቸ ሆዴ ተላውሷል፣ የእናትን ጥልቅ ጭንቀቷ፣ ያለ አባት በአሳር በመከራ ያሳደገቻት የእናትን ሎሜ መሪር ሐዘን ተረድቸ ህመም መታመሜ እውነት ሳለ በዝምታ እየቆሰልኩ ማስረጃ መረጃ ፍለጋ መዋተቴ ህመሜን አክብዶታል፡፡  ከጉያዋ ወሽቃ፣ በትንፋሿ አሙቃ፣ ስታገኝ በደስታ፣ ስታጣ ተከፍታ ድሃ አደግ ቤቷን አሟሙቃ ነገን ልጆቿን ለወግ ለማዕረግ የማድረስ ምኞት ተስፋን ሰንቃ ተስፋዋን የተነጠቀች እናት እንባ ውስጤን አድምቶ አቃጥሎታል። እናት ዛሬ ማለዳ በላኩልኝ መልዕክት እንዲህ ይላል “የልጀን ነገር አደራ እባክህ ነፍሴን አሳርፋት” …

ሰው ሆዬ ሲጨንቀው እኔ መረጃን ከምንጩ ከማሰራጨት ባለፈ ሁሉን ማድረግ የሚቻለኝ አድርጎ ይስለኛል፤ እኔ ግን አቅሙ የለኝም! መረጃዎችን ለወገናቸው ጥቅም ቅድሚያ ከሚሰጡ የመንግስትና የድርጅት አባላት በሚስጥር፤ ከቀሩት ወገኖች በአደባባይ የሚደርሰኝ መረጃ የተጣሰው የስደተኛ መብት ይከበር ዘንድ ሁሌም የመረጃ ጉልበቴ ነው! ያገኘኋቸውን መረጃዎች እያጣራሁ ሰሚ ቢገኝ አቀርባቸዋለሁ! ከዚህ ባለፈ ጉልበት የመርዳት አቅሙ እንደሚገመት  የለኝም!

በተለያዩ አቅጣጫዎች መረጃን ፈላፍየ የማግኘቴን ያህል ግን ለመብት ማስከበሩና ለመፍትሔው የመንግስት ተወካይ የቆንስልና ኢንባሲ ሰዎች እንጅ እኔ አቅም ስልጣኑ የለኝም … በመንግስት ተወካዮቻችን በኩልማ መረጃን ለማግኘት እንኳ ከአንድ ተራ ዜጋ ያነሰ መብት እንዳለኝ ስንቶች እንደሚረዱ አላውቅም! መረጃ በማቀበሌ ብቻ “መንግስትን አትወድም፤ ተቃዋሚ ነህ” የሚሉኝ ካድሬዎች አንድ መረጃ ሳቀርብ በአካልና በዋትሳፕ በቡድን ተሰባስበው “በነቢዩ ጽሁፍ ላይ እንዝመት፤ መልስ እንስጠው!” እኔ የማነሳቸውን ጉዳዮች እንኳ መርምረው ስለሰብዐና ብለው፣ ፈጣሪን ፈርተው በስደት የተጨነቀ ወገናቸውን አይደግፉም፣ ስለሰብዕና የቆመው፣ ወገኑን የደገፈውን በስውር ያሳድዱታል፣ ለእነሱ ሁሉም ነገር ድርጅታቻው ነው! እነሱ እንዲህ ናቸው…!

እኔ የሆነና የተጨበጠ ግልጽ ያለ መረጃ  ሳቀርብ እነሱ የተንሸዋረረ ስም ማጥፋቱ ልማድ አድርገውታል! … በዚህ መካከል የተገፋው ወገን ድምጽ ከፍ ብሎ ይሰማኛል! የእናት ሎሜ ረጋስ የአደራ መልዕክት ደግሞ የእኔን የጨካኙን ልብ አርዶታል፤ ሆዴን ያላውሶታል … እኒህን እናት ምን ላድርጋቸው? ከሰሞኑ በውስጤ እየተብላላ ሰላም የነሳኝ እንደ እናት ሎሜ ረጋስ እዚህ ደረጃ ያልደረሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቻቸውን በኮንትራት ልከው ደብዛው የጠፋባቸውን በገጠር ያሉ እናቶችን አስብኳቸው … ታምሜ ሰንበትኩ፤ በቤቴ ውስጥ ሳይቀር ሰላም አጣኝ፤ ህመሜን ተረድቶ የሚያክመኝ ባጣም ችየው የእናት ሎሜን አደራ ለመወጣት የቤዛን ታሪክ በጨርፍታ አሳውቃችኋለሁ!

እህት ቤዛን ሳውዲ ያደረሳት መንገድ …!

በሃያዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኘው እህት ቤዛ አሸናፊ እንግዳ ከአሰላ ተነስታ በቦሌ አየር መንገድ በኩል ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ሳውዲ አረቢያ ያቀናችው ከሶስት አመት በፊት ነበር ። ከዚያ ወዲህ ብዙ ጊዜ ከቤተሰቧ ጋር ትገናኝ ነበር፤ መስከረም 18 ቀን 2008 ዓም ከእህቷ ጋር ከተገናኘች ወዲህ ግን ድምጿ ጠፍቷል። ቤተሰቦችዋ ከወሰዳት ኤጀንሲ እስከ ሳውዲ አሰሪዋ  ድረስ በየአቅጣጫው ሲያፈላልጓት ሰንብተው ለመጨረሻ ያገኘኋት በአሰሪዋ በኩል መረጃ ተገኘ። አሰሪዋ የቤዛን ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን አስረድተው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሞቷን እንዲያረጋግጡ አሳወቋቸው፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ስለ አሟሟቷ ምንም ማስረጃ ሳያቀርብ  ቤዛ ራሷን ሰቅላ መግደሏን ለቤዛ ቤተሰቦች አረዷቸው። እናትና የቀሩት ቤተሰቦች ከሀዘኑ በላይ ሞተች የተባለበት መንገድና ስለመሞቷ የፎቶም ሆነ የሰነድ መረጃ አለመቅረቡ ሓዘናቸውን መሪር አደረገው። የቤዛ ቤተሰቦች በዚህ ሁኔታ የሚይዙ የሚጨብጡት አጥተው “ሬሳዋ ይላክልን አስመጡልን” ብለው ሲጠይቁ የቤዛ አስከሬን ተቀብሯል “የሚል መልስ ተሰጣቸው። ሞተች የሚለውን ማመን የገደዳቸው እናት ሎሜ ረጋስ መላው ቤተሰብ በቤዛ ዙሪያ የሆነውን በጥርጣሬ ማየት ጀመሩ፡፡ ወላጅ ቤተሰብ ሳይጠየቅና ሳይፈቅድ ምን ሲባል የቤዛ አስከሬን ሳውዲ ላይ ተቀበረ?ለምን?እንዴት? ይህን የቤተሰብ ውል ያለው ጥያቄ ነው፤ ቤተሰብም እኛም ወላጅ ቤተሰብ ሳይጠየቅና ሳይፈቅድ ምን ሲባል የቤዛ አስከሬን ሳውዲ ላይ ተቀበረ? ለምን? እንዴት? እንጠይቃለን!

የቤዛ ቤተሰቦች በተለይም እናት ሎሜ እርማቸውን ሊያወጡ በማይችሉበት መንገድ ከሀዘን ላይ ሐዘን ተደራረበ፤ ተጫነባቸው፡፡ ቤዛ ራሷንና ድሃ አደግ ቤተሰቧን ለመደገፍ ሕጋዊ በተባለው ኤጀንሲ ቪዛ ይዛ ለስራ ወደ ሳውዲ መላኳ እውነት ነው ። በተላከችበት ሃገር በስራ ላይ እንዳለች ስለመሞቷ ቤተሰብ ፈለገው ባይጠይቁ የተገኘው መረጃም ላይገኝ ይችል እንደነበር ቤተሰቦችዋ ያስረዳሉ። ሞታለች የሚለው መርዶም ድፍንፍን ያለ መሆኑ ቤተሰቡን ግራ አጋብቶታል። የተነገራቸው መረጃ የተዛባ ነው እስከ ማለት ደረሰዋል። በዚህ የመከራ አጣብቂኝ ለወደቁ ቤተሰቦች ከቀናት በፊት የለቀቅኩት የአሚናት መረጃ ተስፋን አጭሮባቸው እኔኑ ማፈላለግ ጀመሩ። በእርግጥም ሞታለች ተብሎ ተነግሯቸው በሐዘን ተቀምጠው እርማቸውን ባወጡ በሁለት ዓመታት አሚናት መዲና በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተገኝታለች። በውል የማይታወቅ የመኪና ግጭት አካሏ ጉዳት ከደረሰባት ከሁለት ዓመት በኋላ አሚናት በአብሮ አደጓ በእህት ሀድያና በቀሩት ወገኖቿ ትብብር ሐገር ቤት ገብታለች፣  ለሀገሯ ምድር በቅታለች። ከእናቷና ቤተሰቦቿን ተቀላቅላለች። የአሚናት እውነት የቤዛን ቤተሰቦች ልጃቸው በተመሳሳይ መንገድ እንደ አሚናት ትመጣ ይሆናል የሚል ተስፋን አጭሮላቸዋል፡፡ እናትና እህት የአሚናትን ታሪክ ከሰሙ በኋላ ቤዛ አለች ብለው ተሰፋ አድርገዋል፡፡ “ራሷን ሰቅላ ሞተች” ተብሎ የተነገራቸው አላምን በለው ትተውታል፤ በአንጻሩ ያችን የደስ ደስ ያለት የሚያውቋት ቤዛ “ትመጣለች” ብለው ዓይናቸው በተስፋ ይዋትት ይዟል፡፡ … የቤዛ ነገር ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ የቤዛ ቤተሰቦች እንደ አሚናት ሁሉ ቤዛ  የፈለገውን ጉዳት ደርሶባትም ይሁን በሕይወት ትቀላቀላቸው ዘንድ ጓጉተዋል … የልጃቸውን ጉዳይ አጣርቸ እንዳሳውቃቸው  ደግሞ እኔኑ ፍለጋ ይዘዋል …

ስለ እህት ቤዛ ዝርዝር መረጃ!

ከተባበሩት ኢምሬት አድራሻየን አግኝታ ልብ ሰባሪውን የቤዛ ታሪክ ያጫዎተችኝ እህት motherየቤዛን እናት እና የመላ ቤተሰቡን ሐዘን ጫፍ ጫፉን  ነበር። ስለሆነው ሁሉ ሙሉ መረጃን አደንደሚያስፈልገኝ ገልጨላት ብዙም ሳይቆይ ከቤዛ እህት እህት ከመአዛ አሸናፊ ጋር አገናኘችኝ፡፡ ከመአዛ በዋትሳፕ ተገናኝተን ስለ ቤዛ ብዙ አጫዎተችኝ ፤ መአዛና ቤዛ መስከረም ሲጠባ በፊስ ቡክ ይገናኙና ያወሩ እንደነበር ፣ ቤዛ ወደ ሃገር ለመምጣት ዝግጅት ላይ እንደነበረች እህት መአዛ ገላልጣ አወጋችኝ ፡፡ የእናቷን መከራና ቤተሰቡ የገባበትን የሐዘን ማጥ ስትናገረው ደግሞ ልብ ይሰብራል፡፡ የቤዛ እናት ወ/ሮ ሎሚ የልጃቸውን መሞት በመረጃ አስረግጦ  የነገረቸው ስለሌለ እንደ አሚናት እናት ወ/ሮ ወርቅነሽ ልጃቸው አደጋ ደርሶባት ተደብቀው እንጅ “ሞተች” ብለው ለማመን ገዷቸዋል። እናም ሌት ተቀን “እህህ” እያሉ እንባቸውን በማዝራት በር በሩን በማየት ቤዛን ይጠብቃሉ … የእናት አንጀት! ምስኪኗ እናት የወ/ሮ ሎሜ ረጋስ ከዓመታት በፊት ወደ ሳውዲ የመጣች አንድ ፍሬ ልጃቸውን በመላከ ሞት የመነጠቃቸው መርዶ እንደ ቀላል፣ እንዳአልባሌ ነገር “ልጅሽ ቤዛ ራሷን ሰቅላ ሞታለች” ተብለው ጎረቤት፡ ዘመድ አዝማድ፤ እድርተኛ ተሰብስቦ፣ ደረት ተመቶ ፣ ሙሾ ተደርድሮ ሀዘን  ቢቀመጡም “ቤዛ ሞታለች” ብለው አላመኑም፡፡ በሐዘን ላይ መሪር ሐዘን ተደራርቦባቸዋል፣ ቅስማቸው ተሰብሯል፡፡

የቤዛ ቤተሰቦች ቤዛ ሞተች በተባለበት የጅዳ ከተማ የምገኘው ለእኔ አፋልገን ብለውኝ ፈቃደኛ መሆኔን አሳውቄያቸዋለሁና በእኔ ላይ ተስፋ ጥለዋል፤ እንዲህ አሉኝ “ነቢዩ ቤዛ ጤነኛ ነች፣ ራሷን ስታ አትታነቅም፣ ግን ሞታም እንደሁ ስለአሟሟቷ መረጃ ሰባስበህ ሞተች በለን ! ካለችም አለች ብለህ የደስታ ብስራት አሰማን፤ እኛ የምንፈልገው በልጃችን ላይ የሆነውን ማወቅ ብቻ ነው፤ እባክህ ተባበረን፡ እባክህ እርዳን” የሚለው መልዕክት ደጋግመው አድርሰውኝ ነበርና ተጨናንቄያለሁ፡፡ ወላጅ ቤተሰብ በውጭ ጉዳይ በኩል የመቅበሪያ ውክልናና ካልላኩ ማስቀበር እንደማይቻል አሳምሬ ባውቅም ፡የቤዛ ከቤተሰብ እውቅና ውጭ መቀበር በእርግጥም አሳሳቢ ነው፡፡ የቤዛ ቤተሰቦች ቤዛ የሆነችውን አፈላልገህ፤ አጣርተህ አሳውቀን ቢሉኝም ፤ “ሞተች” ተብሎ ፎቶም ሆነ ተዛማጅ መረጃ አልቀረበላቸውምና “ቤዛም ትመጣልናለች” ብለው በተስፋ እየተጠባበቁ መሆኑ ደግሞ ከብዶኛል፡፡ የከበደኝ ያለ ነገር አይደለም፣  ወላጅ ዘመድ ሳይሰማ፣ ማንነታቸው ሳይረጋገጥ እንደወጡ የቀሩ ብዙ የስደት ታሪኮችን መስማት ሳይሆን አይቻለሁና የወላጅ  ህመሙ ዘልቆ ያማል !

የቤዛ ቤተሰቦች ”እባክህ ቤዛን  አፋልገን!” እናት ተማጽኖ ካቀረቡልኝ ሳምንት አለፈው፤ ሰምቸው እንዳልሰማሁ ተረጋግቸ ጉዳዩን ውስጥ ውስጡን ማጣራት ይዣለሁ ፤ የቤዛን እህት በተደጋጋሚ ፎቶ እንድትልክልኝ አድርጌ እያቀረብኩና እያራቅኩ በመጠለያው በር ላይ በተደጋጋሚ ወድቀው ካነሳኋቸው እህቶቸ ፎቶዎች ጋር ባመሳስለውም ቤዛን አላገኝኋትም። ቤዛ አዕምሮዋ ታውኮ ራሷን መሰቀሏን በሰበር መረጃ አቅርቤው ነበርና እሱንም ተመለከትኩት፤ ራሷን ሰቀለች የተባለችው እህት ደግሞ የልጆች እናት መሆኗን ከመጠለያው በወቅቱ ያገኘሁት ያስረዳል። ይህም ከቤዛ ጋር አልገናኝ አለኝ … ሌላ መረጃ አስታወስኩ፤ ራሷን ሰቀለች የተባለችው እህት ከመሞቷ ከቀናት በፊት በጀዳ ቆንስል የቅርብ ርቀት ግቢ አትግቢ በሚል የነበረውን ግርግር የሚያሳይ በሚስጥር የተነሳ ተንቀሳቃሽ ምስል በእጀ ይገኛልና እሱኑ እያቀረብኩና እያራቅኩ ማየቴን ቀጠልኩ … ጩኸት ግርግሩ ይታያል!የዚያች እህት ምስል ግን ብዙም ግልጽ አይደለም፤ ከቪዲዮው ፎቶ አንስቸ ለቤዛ ቤተሰቦች ላኩላቸው። ለመለየት ተቸገሩ … እንዲህ እንዲህ እያልኩ ሳምንት ገፋሁት … ተደጋግሞ የሚደርሰኝ የቤዛ ቤተሰቦች ጭንቀትና ተማጽኖ አላስቀምጥ አለኝ! ሰምቸው ጉዳዩን እስካጣራ ብየ ለጊዜው የዘለልኩት ፣ ግን  ሰላም የነሳኝን የቤዛን እናት ጭንቀት የቤዛ ቤተሰቦች የሚያስረዳውን ከእህቷ ከቤዛ የደረሰኝ አንዱን የድምጽ መልዕክት ከፍቼ መስማቴን ቀጠልኩ… እንዲህ ይላል !

“እባክህን ነብዩ ከጎናችን ሁን፣ ይህን የመጣብንን ነገር ተባብረህን የሆነ ነገር ላይ  እንድንደርስ እፈልጋለሁ፣ እባክህን! በቃ ከምነግርህ በላይ ነው፡፡ በተለይም እናቴ በጣም እየተጎዳች ነው:: ምን ማድረግ እንዴት ማድረግ እንዳለብኝ እንኳን ግራ እስኪገባኝ ድረስ በጣም ተጎድታለች፡፡ እሷ ነች ያሳደገችን ፣ አባታችን ልጅ ሆነን ነው የሞተው ፡፡ በመጨረሻም የእሷ ክፍያ ይሄ ሆነ፡፡ እና የሚሰጡን መረጃ እንዳልኩህ በጣም የተለያየ ነው፣ እ …ጓደኛዋን ሳናግራት ነበር ፤ እዛው ዘመድ  ቤት የምትሰራ ልጅ ነችና ሰውየየ የነገረኝ ከመዲና፣ የሚኖሩበት መዲና ነው፣ ወደ ጅዳ ስትጠፋ ነው፣ እ …ዱርየዎች አግኝተዋት ተጫውተውባት ከዚያ ውጭ  ላይ የጣሏት፣ ዓይነት ነገር ነው የነገረኝ የእኔ ሰውየ፣ ሰውየ አይዋሽም ብላ ነው የነገረችኝ፡፡ ከኢንባሲ (ከጅዳ ቆንስል ለማለት ነው) በኩል ደግሞ የምትሰማው ያው እንደነገርንህ ራሷን እንዳጠፋች ነው የሚናገሩት፡፡ በጣም እኔ እንጃ ዝብርቅርቅ ነው ያለብኝ፣ በምትችለው ነገር ተባብረህ  የሆነ ነገር ላይ እንድትደርስልን እለምንሃለሁ ! በቃ በምትችለው ነገር!! የሆነ ብቻ ትክክለኛውን ነገር ቢያንስ ቢያውቅ ሰው አዕምሮው ያርፋል፡፡ ሁለተኛ ነገር የአስከሬኑ ጉዳይ ራሱ እንዴት?  ማን? መጠየቅ እንዳለብኝ አላውቅም ነብዩ፡፡ ከሥራህ በተጨማሪ እንደወንደምነት ነው የምጠይቅህ፣ እንዴት ማድረግ እንዳለብን አላውቅምና ካንተ ራሱ ምክር እፈልጋለሁ በቃ፡፡ ማንም የለም ከጎናችን ፣ እንዳልኩህ እናታችን ነው ያሳደገችን ሌላ ከጎናችን ሆኖ የሚረዳን የሚያግዘን እንደዚህ እንደዚያ አድርጉ ብሎ የሚነግረን የለም!  እዚህ ካሳንችስ ሄደን ነበረ፣ ምንም ዓይነት መረጃ የለም፣ እንዲጠየቅላችሁ የምትፈልጉት ካለ ፎርም ሙሉ ብሎ ነግሮኛል ሰኞ ሒጀ እሞላለሁ፣ እስኪ የሚያመጡትን ነገር ከዚያ ካለ አያለሁ ! እኛጋ ወረቀት ተቀብሎ ቁጭ ማድረግ ነው፣ እኔ “እህቴ ድምጿ ጠፍቶ ወር ከ15 ቀን ሳይሞላ ነበር ለሄደችበት ኤጀንሲ ያሳወቅኩት፣ ጠፍታብኛለችና እናንተ መጠየቅ በሚገባችሁ በኩል ጠይቁልኝ ”ብየ ሰጠሁት፣ ግን ምንም ዓይነት መልስ አልሰጠኝም፡፡ በእኛም ጥረት ላይ  ነው እዚህ ላይ ያለው፡፡ ግን እየተሰጠን ያለው ኢንፎርሜሽን ደግሞ የተለያየ የተዘበራረቀ  ነው፣ እባክህን  እ ባ ክ ህ ን  አንተ አንድ እንድታደርግ እፈልጋለሁ፣ በቃ ! እግዚአብሔር ይርዳህ አንተንም፡፡ ምንድነው ማድረግ ያለብን ነገር? ከዚህ ውጭ ደግሞ የራስህ የሆነ ስለሠራህበት ስለምታውቅ ስለሠራህበት የተወሰነ ምክር እንድትሰጠኝ !”  ይላል ሙሉ መልዕክቱ…

እናም የቤዛን ቤተሰብ አቤቱታና የጭንቀት የድረሱልን ጥሪያቸውን ይድረሳችሁ፤ ስለ እህት ቤዛ አሸናፊ እንግዳ መኖርና መዳረሻ ዙሪያ የተጨበጠ መረጃ ያላችሁ ወገኖች ታሳውቁን ዘንድ አደራየ የጠበቀ ነው!  “እህት ቤዛን አፋልገን ” በማለት አደራ የሰጡኝ  የሚማጸኑኝ የእናትና የቤተሰቡን ጭንቅ ተረድታችሁ ያላችሁን መረጃ ታቀብሉን ዘንድ በትህትና እንማጸናልን !

ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓም

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles