ከዞን ዘጠኝ አንዱ ነው። ባላጠፋው ጥፋት ባልሰራው ስራ፣ አገሩን እና ህዝቡን በመዉደዱ “ሽብርተኛ” ተብሎ ከአምስት መቶ ቀናት በላይ ከጓደኞቹ ጋር በወህኒ ተሰቃይቷል። ማእከላዊ በምትባል ቦታ ኢሰብአዊ ቶርቸር ተፈጸሞበታል። አላማቸው የርሱን ሞራሉን ለመስበር፣ አንገቱን ለማስደፋት፣ ለመሰባበር ነበር። አዎን በአካሉ ላይ ጉዳት አደረሱበት። ግን መንፈሱን ሊነኩት አልቻሉም። አልተሳካላቸውም።
ብዙዎች ምንም ሳይደርስብን፣ ከአሁን ለአሁን አንድ ነገር እንሆናለን ብለን በፍርሃት ተተብትበት ፣ አንገታችንን ደፍተን ዝምታን መርጠን ፣ ግፍና ጭቆናን አሜን ብለን ተቀብለን እንደ ባሪያ እና እንደ እንሣ እንኖራለን። ዝም በሉ ስንባል ዝም እያልን ፣ ተነሱ ስንባል እየተነሳን፣ ቁጭ በሉ ስንባል እየተቀመጠን ፣ ክብራችንን እና ስብእናችንን ጥለን እየታዘዘ እንደሚንቀሳቀስ ሮቦት ሌሎች ለኛ እየወሰኑልን ኖረናል።
ይህ ወጣት ግን “ስለሚያገባኝ እጦምራለሁ” ብሎ እግዜር የሰጠውን ነጻነት አሳልፎ መስጠት አልፈለገም። ደበደቡት፣ አሰሩት፣ አሰቃዩት እርሱ ግን አልፈራም። አሁንም ስለሚያገባኝ እጦምራለሁ ይላል።
ናትናኤል ፈለቀ ነው። እርሱን እና ጓደኞቹ ፍርድ ቤት ነጻ ብሏቸዋል። ሆኖ አቃቢ ሕግ ይግባኝ በማለቱ ፍርድ ቤት ይቅርባሉ። ተመለሰውም ወደ ወህኒ ሊወርዱ ይችላሉ። ሆኖም “የነፃነት ትግላችን ዋነኛ ምሰሶ ለነፃነታችን በፈቃደኝነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችን ነው” ሲል ለነጻነት መከፈል ያለበትን ለመክፈል እንደተዘጋጀ ይነግረናል።
ናትናኤል የጦሞረዉን ለማንበብ ከዚህ በታች ይመልከቱ፡
==============================
በናትናሄል ፈለቀ (Zone9)
ማዲባ “Long walk to Freedom”
አንዳንዴ “ተስፋ” ጠላታችን ይሆናል። ነገሮች እንደሚሻሻሉ ወይንም ከዚህ የባሰ እንዳይከፉ እያልን በተስፋ እየተታለልን ማድረግ የሚገባንን ሳናደርግ ወደን ሳይሆን ተገደን እንከፍላለን። ነፃነታችንን የሚያጎናፅፈን መክፈል ብቻ ሳይሆን የምንከፍለው ለነፃነት የሚገባውን መሆኑን አምነን በፈቃደኝነት ወደን ስንከፍል ነው።
አምባገነኖች በሚያስተዳድሯት ሀገር ተራ በተራ እያንዳንዳችን ላይ የጭቆና በትር ማረፉ አይቀርም። ጥያቄው እየሸሸንም ቢሆን ተራችንን ጠብቀን ዋጋ ከፍለን ጭቆናን እናራዝማለን ወይንስ በፈቃደኝነት ዋጋ ከፍለን ነፃነታችንን እንጎናፀፋለን? ነው።
ከዕስር ከመውጣታችን በፊት ለነፃነቴ መከፈል ከሚገባው ዋጋ ላይ እየቀነስኩኝ ነበር። እያንዳንዷ በዕስር የማሳልፋት ቀን ለነፃነቴ እያቀረበችኝ እንደሆነ ነበር የሚሰማኝ። ከዕስር ከወጣሁ በኋላ ለነፃነቴ ለመክፈል ያለኝ ፈቃደኝነት በብዙ “ምክንያቶች” አብሮኝ የለም።
ወዳጄ የሺዋስ አሰፋ “ፍርሃት በብዙ ምክንያቶች ተሽሞንሙና ትደበቃለች” ይለኝ ነበር። ምናልባት ማረሚያ ቤት ካገኘሁት ዓይኑን እንዴት እንደማይ አላውቅም።
ይህች ጽሑፍ ምናልባት በራሴ የፌስቡክ ግርግዳ ላይ የማሰፍራት የመጨረሻ ልትሆን ትችላለች። የፊታችን ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ላይ የሚሰጠውን ውሳኔ ለመስማት ዳኞች ፊት ከጓደኞቼ ጋር እቆማለሁ። ተራዬ ደርሶ (ሁለተኛ?) የጭቆና በትር ይሰነዘርብኝ ይሆናል። ወይንም እንደገና <<ተስፋ>> ለማድረግ እቀጠር ይሆናል።
ለክፉም ለደጉም እስር ቤት ያስተዋወቀኝን አንድ ምርጥ ጸሐፊ ልጥቀስ እና የኔ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ ሰዎች ማልቀሻ ልተውላችሁ:–
“…And if it is a despot you would dethrone, see first that his throne erected within you is destroyed. For how can a tyrant rule the free and the proud, but for a tyranny in their own freedom and a shame in their own pride? And if it is a care you would cast off, that care has been chosen by you rather than imposed upon you. And if it is a fear you would dispel, the seat of that fear is in your heart and not in the hand of the feared.”