(ሰንደቅ) በመጽሔት፣በቴሌቭዥን፣በሬዲዩና በፊልም አዘጋጅነትና ደራሲነት የሚታወቀው ብርሃኔ ንጉሴ ከፍተኛ ወጪ፣የባለሞያዎች ድካምና ከፍተኛ ዝግጅት ተደረገበት ያለውን የአዲሱን ፊልሙን ጨረፍታ በማህበራዊ ድረ ገጾች ከለቀቀበት ቅጽበት አንስቶ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ድረ ገጾች ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ፊልሙን እንደማይመለከቱ በመግለጽ ሌሎችም ይህንኑ በማድረግ እንዲተባበሯቸው እየጠየቁ ነው፡፡
በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ደጋፊነቱ የሚታወቀውና ደጋፊነቱንም ከህዝብ በሚሰበሰብ ግብር በሚተዳደር ራዲዩ የገለጸው ብርሃኔ ንጉሴ ለአዲሱ ፊልሙ ‹‹ቤዛ ››የሚል ስያሜ ያወጣለት ሲሆን በፊልሙ የቀድሞውን የህወሓት ጄነራል ሓየሎም አርአያን ታሪክ ይዞ ለመቅረብ መሞከሩን አስታውቋል፡፡
በሆቴል ውስጥ በተነሳ ረብሻ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ ከተቀጠፈች 20 ዓመት የሞላውን ሓየሎምን ታሪክ በፊልም ለመቅረጽ ያነሳሳውን ምክንያት በፌስ ቡክ ገጹ ያሰፈረው ብርሃኔ ‹‹ርህራሄው፣ደግነቱና ለደርግ ጀነራሎች ጭምር የነበረው ወዳጅነት የማረከኝ በመሆኑ››ብሏል፡፡
በፊልሙ ላይ በዋና ገጸባህሪነት የምትታየው ‹‹ቤዛ››ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ሐየሎም ሊያገኛት ወደ አርሲ ፍለጋ የወጣላት መሆኑን የገለጸው ደራሲው ከህወሓት የትጥቅ ትግል ጋር በተያያዘ ፊልም ሲሰራ የአሁኑ ሁለተኛው ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የሰራው ሙሴ ፊልም ከህወሓት ከፍተኛ ገንዘብ ተበርክቶለትና በመንግስት ቁሳቁስ ጭምር እየተደገፈ ለእይታ ያበቃው መሆኑን የሚያስታውሱ ሰዎች ቤዛንም ሕወሓቶች ስፖንሰር ማድረጋቸውን የፊልሙ ቀረጻ ትግራይ ላይ ሲከናወንም የክልሉ መንግስት የትራንስፖርት መኪኖችን በማዘጋጀት፣ጠባቂዎችን በመመደብና ያረፉባቸውን ሆቴሎችና የተጠቀሟቸውን አገልግሎቶች ክፍያ መሸፈኑን ይገልጻሉ፡፡
ብርሃኔ ቤዛን በማህበራዊ ድረ ገጾ ች ባስተዋወቀበት ወቅትም የፌስ ቡክና የትዊተር ተጠቃሚዎች እነሓየሎም ደርግን በመጣል ያቆሙት ስርዓት ከደርግ ባልተለየ ሁኔታ እየገደለና እያሰረ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት የስርዓቱን ባለሟሎች ማዳነቅ ከስርዓቱ ጋር መተባበር ነው በማለት ፊልሙን ማንም ሰው ባለማየት ለመንግስትና ለስርዓቱ ደጋፊዎች ያለውን ተቃውሞ እንዲያሳይ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡
ዜጎች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲገልጹ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ የስርዓቱ ደጋፊዎች የሚያቀርቧቸውን ማናቸውም አይነት ነገሮችን አለመጠቀም በመሆኑም የብርሃኔ ፊልም ለስርዓቱ የሌለ ምስል የሚሰጥ ተደርጎ በመወሰዱ ተቃውሞ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ በፊልሙ ላይ በማህበራዊ ገጾች እየቀረበ የሚገኘው ተቃውሞ እየጨመረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ደራሲው የሰጠው አስተያየት የለም፡፡