«ከታሪክ የማይማሩ ደግመው፣ ደጋግመው ለመሣሣት ይጋለጣሉ፤» የሚለው ብሂል ለዚህ ብሔራዊ በዓል መደብዘዝ አብይ ማጣቀሻ ነው። በደርግ የአገዛዝ ዘመን ይህ ዕለት ከብሔራዊ በዓልነት ደረጃ ወርዶ በመታሠቢያ ቀን ደረጃ እንዲከበር መደረጉ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነበር። በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ይብስ ስህተቱ ወደማይታረምበት ደረጃ ደርሷል። ይህንን ለማለት የሚያስደፍረው የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ፋሽስት ኢጣሊያን ሲፋለሙ በሠማዕትነት ያለፉትን የአቡነ ጴጥሮስን፣ የደጃዝማጅ አፈወርቅ ወልደሰማዕትን እና ከሁሉም በላይ የማይጨው አርበኞቻችንን የመታሠቢያ ኃውልቶች አፍርሷል፣ ሌሎችንም ታሪካዊ ኃውልቶች አፍርሶ ድራሻቸውን ለማጥፋት እንቅስቃሴውን ቀጥሏል። ችግሩ የሰማዕታቱ መታሠቢያ የሆኑት ኃውልቶችን በማፍረስ ብቻ የሚገደብ አልሆነም፣ እንዲያውም ታሪካዊቱን አገር ኢትዮጵያን እስከመበታተን የሚደርስ ታላቅ ብሔራዊ ክህደት የሚፈጸመበት የታሪክ ወቅት ላይ እንገኛለን። ይህ ታሪካዊ ክህደት ከአሁኑ ትውልድ ተሻግሮ የተተኪው ትውልድም ማፈሪያ እንዳይሆን ጊዜው ሣይመሽ ዛሬውኑ ለተግባራዊ እርምጃ መነሣት ይኖርብናል።
ኢትዮጵያ እና ዜጎቿ በዚህ የታሪክ ማጥ ውስጥ ሲዳክሩ፣ በፋሽስት ኢጣሊያ ለተጨፈጨፉት ሠማዕታት ቋሚ ጠበቃ ሆኖ የቆመው “Global Alliance for Justice: The Ethiopian Cause” በመባል የሚታወቀው ተቋም ነው። ይህ ተቋም ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ለሠማዕቶቻችን ቀዳሚ ጠበቃ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም። ሆኖም የሌሎቻችን ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያጋጠመንን ብሔራዊ ፈተና በአሸናፊነት ለመወጣት፣ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ስም እስከከተደራጁት ሁሉም ዓይነት ድርጅቶች እና ተቋሞች ከፍተኛ የሆነ ብሔራዊ አስተዋፅዖ ይጠበቃል። ስለሆነም ሠማዕቶቻችንን ከመዘከር ባሻገር ብሔራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ሁላችንም በያለንበት የድርሻችንን መወጣት ይገባናል። የሺህ ኪሎሜትሮች ጉዞ የሚጀመረው በአንድ እርምጃ ነውና ይህንን ታሪካዊ ዕለት ኢትዮጵያውያን በያለንበት ከብሔራዊ በዓሎቻችን አንዱ አድርገን እንድናከብረው ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የአደራ ጥሪውን ያቀርባል።
ለሠማዕታት ተገቢውን ክብር እንስጥ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
<!–
–>