Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

አደጋውና ማስጠንቀቂያው – ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

$
0
0
daniel-kibret.jpg satenaw
ዳንኤል ክብረት
ጅብ ልጁን እየላጨ ነበር አሉ፡፡ ሰማ፡፡ ግን የድምጹን አቅጣጫ ለማወቅ አልቻለም፡፡ አህያም ብትጠብቅ ብትጠብቅ የመጣ ጅብ የለም፡፡ ውሻውንም ‹ባክህ ዝም ብለህ ሽብር ስትነዛ ነው እንጂ፤ ጅቡ ወይ ሞቷል፣ ወይ የለም፣ ወይ ተኝቷል› አለቺው፡፡ ‹አይደለም› አለ ውሻ፡፡ ‹አይደለም፤ ጅቡ ሰምቷል፡፡ አንቺ ግን መስማቱን ማወቅ አልቻልሽም፡፡ አሁንም በዚህ ቢበቃሽ ጥሩ ነው› አላት፡

፡ ‹ጥጋበኛ ሰው ሦስት ነገሩ ይወፍራል – ጆሮው፣ ዓይኑና ልቡ› ይላል መዝገበ ጠቢባን፡፡ ጆሮው ከራሱ በቀር እንዳይሰማ ሆኖ፣ ዓይኑም ከራሱ በቀር እንዳያይ ሆኖ፣ ልቡም ቢያይም ቢሰማም እንዳያስተውል ሆኖ ጥጋብ ይደፍነዋል፡፡ እነዚህ በጥጋብ ሲደፈኑ ደግሞ ‹ኩራትና ትዕቢት› ዓይንና ጆሮ ይሆናሉ፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሆድ ዕቃ የመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ አየር መንገዱ ያስመረቀውን ዘመናዊ ኮሌጅ በማስመልከት የአየር መንገዱን ነገረ ሥራ እንድንጎበኝ ተጋብዘን ነበር፡፡ የጥገና ቦታውን፣ የካርጎ ማዕከሉን፣ አዳዲስ እያስፋፋቸው የሚገኙ የካርጎና የጥገና ቦታዎችን አይተናል፡፡ የአየር መንገዱን የሆድ ዕቃ ለሚመለከት ሰው ከጥንት ጀምሮ እየካበተ፣ እየተሳለጠና እየሠለጠነ የመጣውን ይህን ታላቅ ሀገራዊ ድርጅት፤ እስከ ጀርባ አጥንቱ ድረስ ለመረዳት ያስችለዋል፡፡ እንዲያውም እኛ ሀገር እንደ አበሻ መድኃኒት ሁሉም ነገር ምሥጢር ስለሚሆን ነው እንጂ ልጆቻችን በጉብኝት ፕሮግራሞች የአየር መንገዱን የሆድ ዕቃ የማየት ዕድሉ ቢኖራቸው ኖሮ አየር መንገዱንም እንዲወዱ፣ የፈጠራ ፍላጎታቸውም እንዲጨምር ያደርገው ነበር፡፡

በጥገና ክፍሉ የጀመረው ጉብኝት፣ በካርጎ ክፍሉ በኩል አድርጎ በአዳዲስ የማስፋፋያ ፕሮጀክቶቹ በኩል ሲጠናቀቅ ዓይኔ አንድ ነገር ላይ ዐረፈ፡፡ ነገሩ የተጻፈው በአየር መንገዱ የጥገና ክፍል ግድግዳ ላይ ነው፡፡ ለእኔ ከጥገና መሣሪያዎች፣ ከጠጋኞቹ ብቃትና ከጥገና ብቃቱ … የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ከሰጡት ዕውቅና ባልተናነሰ የሳበኝ በየግድግዳው የተለጠፉት የደኅንነት ማሳሰቢያዎቹ ናቸው፡፡
‹አደጋውን ሪፖርት ከማድረግህ በፊት ምልክቱን ቀድመህ ተናገር – “report a hazard before you have to report an accidents” ይላል፡፡ በዚያ ፈረስ በሚያስጋልብ የጥገና አዳራሽ ውስጥ የተለያዩ አደጋዎችን ሊጠቁሙ የሚችሉ ምልክቶች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ምልክቶች በመብራት አማካኝነት ማስጠንቀቂያ እንዲያስተላልፉ ተደርገዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የማስጠንቀቂያ እሪታ (ሳይረን) ያሰማሉ፡፡ እነዚህን የአደጋ ምልክቶች ቀድሞ ማወቅና ለእነዚህ ምልክቶችም ተገቢውን ምላሽ መስጠት በኋላ ለአደጋው ምላሽ ከመስጠት ያድናል፡፡ ጎበዝ ባለሞያም የደረሰውን አደጋ ሳይሆን አደጋ እንደሚመጣ የሚገልጠውን ማስጠንቀቂያ ቀድሞ ይናገራል፡፡ ይኼ ነው የጥገና ክፍሉ ግድግዳ ላይ በትልቁ የተሰቀለው፡፡

በሀገራችን ‹በዕንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ›፣ ‹ጢሱን አይተህ እሳቱን፣ ቀንዱን አይተህ ከብቱን ተጠንቀቅ›፣ ‹በቅርቡ ያልመለሰ እረኛ፣ በሩቁ ሲባዝን ይኖራል›፣ ‹ውሻውን አይተህ ካልተደበቅክ አዳኙ አይቶ ይገድልሃል›፣ ‹አውው ሲል ዝም ካልክ ‹አሙሙ ብሎ ይገምጥሃል› የሚሉ የዚህ ምክር ጓደኞች ሞልተዋል፡፡ ውሻ ለአህያ ‹የመጀመሪያው መጥሪያ፣ ሁለተኛው መቅረቢያ፣ ሦስተኛውም መበያ ነው› ብሎ የመከረው ምክር የዚህ ማስጠንቀቂያ አንድምታ ትርጓሜ ውስጥ ‹ታሪክ አንደ አህያ ነው› ተብሎ ተካትቷል፡፡ ታሪኩስ እንደምን ነው ቢሉ፣ አህያና ውሻ መንገድ ዘመቱ አሉ፡፡ ከዘመቻ ሲመለሱ መሸባቸውና ውሻ የሚበላ አጥቶ ተኮራምቶ ሲተኛ፣ አህያ ግን መስኩ ላይ ያገኘቺውን ሣር ግጣ ሆዷ ተነፋ፡፡ ‹ከተራበ ይልቅ ለጠገበ አዝናለሁ› እንዲል ሕዝቡ፡፡ ይህስ ስለምን ነው ቢሉ? የጠገበ ሰው ረሐብ ያለ አይመስለውም፡፡ የተራበ ተጠቅልሎ ሲተኛ፣ የጠገበ ግን የተጠቀለለውን እየፈታ እንደ አጤ ልብነ ድንግል ጦር አውርድ ይላል፡፡

እናም አህያ ከጥጋቧ ብዛት ‹ልጩህ› አለች፡፡ ውሻ ‹ለምን› ቢላት ‹ፎረሸኝ› አለች፡፡ ‹ፎረሸኝ ማለትስ ምን ማለት ነው ቢሉ፤ ጥጋቤ ቅጥ አሳጣኝ፤ ከትዕቢት አላግቶ ምን ይመጣል አስባለኝ፣ የጠገበ ሲጮኽ የተራበ እንደሚበላው እንዳላውቅ አደረገኝ› ማለት ነው፡፡ እናም አህያዋ ልትጮህ ስትል፤ ‹ተይ ይቅርብሽ ጅብ ይሰማሻል› አላት ውሻ፡፡ ከጠገቡ አያስቡ፣ ከወፈሩ ሰው አይፈሩ፣ ከተበቱ አይታይ ሥጋቱ፣ እንዲል መጽሐፈ ባልቴት፡፡ ‹ተው ባክህ፤ የት አግኝቶ ይሰማኛል› አለቺው፡፡ ‹እንዴ ይኼኮ የጅብ አገር ነው፡፡ የተራበ ጅብ የጠገበ አህያ መስማት እንዴት ያቅተዋል› አላት፡፡ ‹ባክህ ቢሰማስ ምን ያመጣል› አለቺና አናፋች፡፡ ‹ምን ያመጣል ብሎ ገብቶ፣ ማን ያወጣል ብሎ ጮኸ› እንዲል ነገረ ሕዝብ፡፡

ጅብ ልጁን እየላጨ ነበር አሉ፡፡ ሰማ፡፡ ግን የድምጹን አቅጣጫ ለማወቅ አልቻለም፡፡ አህያም ብትጠብቅ ብትጠብቅ የመጣ ጅብ የለም፡፡ ውሻውንም ‹ባክህ ዝም ብለህ ሽብር ስትነዛ ነው እንጂ፤ ጅቡ ወይ ሞቷል፣ ወይ የለም፣ ወይ ተኝቷል› አለቺው፡፡ ‹አይደለም› አለ ውሻ፡፡ ‹አይደለም፤ ጅቡ ሰምቷል፡፡ አንቺ ግን መስማቱን ማወቅ አልቻልሽም፡፡ አሁንም በዚህ ቢበቃሽ  ጥሩ ነው› አላት፡፡ ‹ጥጋበኛ ሰው ሦስት ነገሩ ይወፍራል – ጆሮው፣ ዓይኑና ልቡ› ይላል መዝገበ ጠቢባን፡፡ ጆሮው ከራሱ በቀር እንዳይሰማ ሆኖ፣ ዓይኑም ከራሱ በቀር እንዳያይ ሆኖ፣ ልቡም ቢያይም ቢሰማም እንዳያስተውል ሆኖ ጥጋብ ይደፍነዋል፡፡ እነዚህ በጥጋብ ሲደፈኑ ደግሞ ‹ኩራትና ትዕቢት› ዓይንና ጆሮ ይሆናሉ፡፡ ከዚያም
ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
ከመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ፡፡ የሚለው ትንቢታዊ ግጥም እስኪደርስባቸው ድረስ እንደ ኤድስ ማስታወቂያ ‹አላይም፣ አልሰማም እያሉ መኖር ነው፡፡

አህያ አሁንም መስኩን ብቻዋን ይዛ ትገሸልጠው ጀመር፡፡ መስክ ብቻን መያዝ ጥጋብ ያመጣልና ልቧ ተነፋ፡፡ ልቡ የተነፋ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መጮኽ ይወዳልና ‹ልጩህ› አለች፡፡ ውሻ ‹ተይ ይቅርብሽ ቅድም የታገሰሺን ጅብ ትእግሥቱን አታስጨርሺው› አላት፡፡ ‹ባክህ ምንም አያመጣም› አለቺና አናፋች፡፡ ‹አናፋች› ማለትስ ምንድን ነው ቢሉ፤ ‹እንዳመጣላት ጮኸች፣ ደነፋች፣ ያዙኝ ልቀቁኝ አለቺ› ማለት ነው፡፡ ልጁን ሲላጭ የነበረው ጅብ፤ አሁን አቅጣጫውን ለየና ወደ አህያዋ ዘንድ መምጣት ጀመረ፡፡ ነገር ግን አቅጣጫውን እንጂ ቦታውን አላገኘውም፡፡ ‹አቅጣጫውን እንጂ ቦታውን አላገኘውም› ሲል ምንድን ነው? ቢሉ፤ ‹ሆዱ ግም ግም ብሏል፣ ልቡ ቱግ ቱግ ብሏል፣ መፍትሔው ጠፍቶበት እንጂ ችግሩን ለይቷል› ማለት ነው፡፡

አህያም እንደለመደቺው ብቻዋን በመስኩ ላይ ተለቀቀቺበት፡፡ ውሻ ግን ምንም አብሮ ቢዘምት እንደ አህያ የሚበላ አላገኘም፡፡ የተረፈው የዘመቻው እንጉርጉሮ ነው፡፡ ያንን እያንጎራጎረ ተኛ፡፡ ምንም ባዶ ሆድ ባያስተኛ፡፡ አህያ ግን ድጋሚ ፎረሻት፡፡ ‹ልጮህ ነው› አለቺው፡፡ ‹ይቅርብሽ፣ አሁን ሲሆን ልብ፣ ካልሆነም አደብ ግዢ፤ የመጀመሪያው መጥሪያ፣ ሁለተኛው መቅረቢያ፣ ሦስተኛውም መበያ ነው› አላት፡፡ ሲጠግቡ እንጀራ ወደ ሆድ እንጂ ነገር ወደ ልቡና አይገባምና አልሰማቺውም፡፡ ‹ሰሚ ስታገኝ ተናገር፣ ዳኛ ስታገኝ መስክር› ነውና ዝም አላት፡፡ አህያም ጥጋብ አህያ መሆንዋን አስረስቷት ነበርና ለሦስተኛ ጊዜ አናፋች፡፡ ያን ጊዜ ቦታው ጠፍቶት ሲያደፍጥ የነበረው የተራበ ጅብ፤ ከኋላዋ ቦትርፎ፣ አህያ መሆንዋን እንድታውቀው አደረጋት፡፡ ችግሩ አህያነቷን ያወቀቺው ከተበላች በኋላ ሆነ፡፡

ያን የአየር መንገዱን የጥንቃቄ ማስታወቂያ እዚያ መስክ ላይ በአህያኛ የለጠፈላት ቢኖር፣ እርሷም የመስሚያ ጆሮና የመስማሚያ ልብ ቢኖራት ኖሮ በተረፈች ነበር፡፡ ከእርሷ በፊት እንደ እርሷ የመሰለ ነገር የገጠማት ቀበሮ ከአደጋው በፊት በማስጠንቀቂያው ተርፋለች ተብሎ በእንስሳት ታሪከ ነገሥት ውስጥ እንዲህ ተመዝግቧል፡፡ አንበሳ ታምሜያለሁ ብሎ በተኩላ በኩል እያስነገረ እንስሳቱ ሁሉ ሊጠይቁት ሲሄዱ በክርኑ ደቁሶ ይበላ ጀመር፡፡ በኋላ መተኛት ሰልችቶት ከአልጋው ተነሣና ምስጢሩን እንዳታወጣ ተኩላን አንገቷን ይቀነጥሳታል፡፡ አንበሳ ጫካ ውስጥ ሲመላለስ ቀበሮን ያገኛታል፡፡ ‹እፈልግሻለሁ› እያለ ይቀጥራታል፡፡ ትጠፋበታለች፡፡ ይቀጥራታል፤ ትጠፋበታለች፡፡ አንድ ቀን አሳቻ ቦታ አገኛትና ‹ለመሆኑ ለምን እንደምፈልግሽ በምን ዐውቀሽ ነው የምትጠፊው› ይላታል፡፡ ‹እኔማ በምን ዐውቃለሁ፤ ከተኩላ ጭንቅላት ተምሬ ነው እንጂ› አለቺው አሉ፡፡ ካለፉት ስሕተት የማይማር፣ ያን ስሕተት ለመድገም የተረገመ ይሆናል፡፡ የታሪክ አንዱ ጥቅሙ ከአደጋው በፊት በምልክቱ እንድንነቃ ለማድረግ ነውና፡፡ ያለፉንን ሰዎች ስንወቅስ ከመኖር የተወቀሱበትን መረዳቱ ይበልጥ ይጠቅም ነበር፡፡

ቅሬታዎችን ማዳመጥ፣ ችግሮችን በጊዜ መፍታት፣ ለጥቃቅኑ ጉዳዮች ቀድሞ ትኩረት መስጠት፣ ጢሱን ሲያዩ እሳቱ እንደሚከተል መገመት፣ ከአደጋው በፊት በማስጠንቀቂያው ለመንቃት ያስችላል፡፡ የተናቀ ባቄላ ሆድ ይጎጥራል፡፡ ቻይኖች ጠብታ ውኃ እድሜዋ ከረዘመ ዐለት ትሰብራለች ይላሉ፡፡ ዝሆን አደን ሲሄድ ትንኞች የተሰበሰቡበት ሥፍራ ደረሰ፡፡ ሚስቱ ‹እኔ ይሄ ነገር አላማረኝም እንመለስ› አለቺው፡፡ ዝሆኑም ‹ለትንኝ ብለን› ይላትና ዝም ብሎ ይሄዳል፡፡ አንዷ ትንኝ ጆሮው ውስጥ ትገባና ትጮህበት ጀመር፡፡ ያ እንደ ሰፌድ የሰፋ ጆሮው መልሶ ድምጽዋን ሲያስተጋባለት የትንኟ ጩኸት እንደ ፈንጅ ድምጽ እየተሰማው ያስሮጠው ጀመር፡፡ ሚስቱ ተው ስትለው አልሰማ ብሎ የነበረው ዝሆን፣ ትንኝ እያስጮኸች መንደሩ ደረሰ፡፡ ለደግነት እንጂ ለክፋት የሚያንስ የለም፡፡

የመሪዎች፣ የመንግሥታትና የድርጅቶች ታላቅነት የሚለካው ከአደጋው በፊት ለማስጠንቀቂያው በሚኖራቸው ዝግጅት ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን የመጀመሪያው መስሚያ፣ ሁለተኛው መቅረቢያ፣ ሦስተኛውም መበያ ይሆናል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles