* “ማንም ከሕግ በላይ መሆን አይችልም” ታሳሪው ጠ/ሚ/ር
የቀድሞ የእስራኤል ጠ/ሚ/ር ኤሁድ ኦልመርት ወደ እስር ቤት ወረዱ፡፡ በሃይማኖቱ ዓለም ታላቅ ዝነኝነትን የተጎናጸፉት ራባይ (ረቢ) ዮሺያሁ ፒንቶም ወደዚያው አምርተዋል፡፡ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች የህወሃት/ኢህአዴግ “ሻኮችን” ማን ይንካቸው ሲሉ ጠይቀዋል?
እስራኤልን ለሦስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት የሰባ ዓመቱ ኤሁድ ኦልመርት ከሙስና ጋር በተያያዘ የ19 ወራት እስር ተበይኖባቸው እስርቤት ወርደዋል፡፡
በአስተዳደር ዘመናቸው ከፍልስጤማውያን ጋር ስምምነት ለማድረግ ከፍተኛ እርምጃዎች ሲወስዱ የነበሩት ኦልመርት ወደ ወሳኝ ደረጃ ላይ ሲደርሱ በሥልጣን ላይ እንዳሉ በሙስና፣ ጉቦ፣ እና ሌሎች ገንዘብ ነክ ወንጀሎች መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡ በተለይም የአናፖሊስ ኮንፍራንስ በተባለው ስብሰባ በርካታ ውሳኔዎችን ለድርድር በማምጣት ከፍልስጤማውያን ጋር ለመስማማት መሞከራቸው በአክራሪዎች ዘንድ ለሙስናው ክስ እንዳጋለጣቸው ይነገራል፡፡
እስራኤል ሙሉ በሙሉ ከምዕራብ ዳርቻዎች የመልቀቋን እንዲሁም የየሩሳሌምን ጥንታዊ ከተማ እስራኤልና ፍልስጤም በእኩል የሚጠቀሙባት ለማድረግ በዓለምአቀፍ ቁጥጥር ሥር እንድትውል የሚያደርግና የመሳሰሉ ያልታሰቡ አጀንዳዎችን ወደ ጠረጴዛ ማምጣታቸው እና ለስምምነት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
የየሩሳሌም ከንቲባና የገንዘብ ሚ/ር በነበሩበት ጊዜ ከምርጫና የቤቶች ግንባታ ጋር በተያየዘ የወሰዱት ጉቦና መማለጃ አለ በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ከፍልስጤማውያን ጋር ወደ ስምምነት ለመድረስ ከፍተኛ ሙከራ ባደረጉበት ወቅት መሆኑ ክሱ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ደጋፊዎቻቸው ይናገራሉ፡፡
ኦልመርት ከሥልጣናቸው እንደለቀቁ በእግራቸው የተተኩት የአሁኑ ጠ/ሚ/ር ቢኒያም ኔታኒያሁ ሲሆኑ ከፍልስጤማውያን ጋር የሚደረገው ድርድርም በዚያኑ መልክ አቅጣጫውን ቀይሯል፡፡
“በኔ ላይ የተመሰረተውን የጉቦ ክስ ፈጽሞ የማልቀበለው ነው” ያሉት ወደ እስርቤት በመሄድ የመጀመሪያው የእስራኤል ጠ/ሚ/ር የሆኑት ኦልመርት “ውሳኔው ቢከብድብኝም፤ እቀበለዋለሁ፤ ማንም ሰው ከህግ በላይ መሆን አይችልም” በማለት ከመታሰራቸው በፊት ባሰራጩት የቪዲዮ መልዕክት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በእስራኤል አክራሪ ኦርቶዶክስ አይሁድ የሆኑትና የራሳቸውን የሃይማኖት መስመር የከፈቱት ራባይ (ረቢ) ዮሺያሁ ፒንቶ በሙስና እና ጉቦ ተከስሰው የተበየነባቸውን የአንድ ዓመት እስር ለመፈጸም ወደ እስር ቤት አምርተዋል፡፡ ከጉቦ ጋር በማያያዝም በሚመሯቸው ድርጅቶች ውስጥ በደረሰ ብክነት ክስ ተመስርቶባቸው ተፈርዶባቸዋል፡፡
ራሳቸውን “እኛ” እያሉ የሚጠሩት የ42ቱ የሃይማኖት መሪ በእስኤልና በአሜሪካ በተለይ በኒውዮርክ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ባለጸጋዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ … የአስተምህሮታቸው ደቀመዛሙርት በመሆናቸው እና ከግለሰቦቹ ጋር ባላቸው የጠበቀ ግንኙነት “አይነኬ” እንደሆኑ ይነገርላቸው ነበር፡፡
በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ሲሉ በመታመማቸው ምክንያት የፍርዱን አካሄድ የሚያስተጓጉሉ ቢመስሉም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ወደ እስር ቤት ከመወሰዳቸው በፊትም “እኛ ታምመን ነበር፤ ሆኖም ለአንዲትም ደቂቃ አልፈራንም” በማለት ተናግረዋል፡፡ ህምመማቸውን ምክንያት በማድረግ ወደ እስር ቤት እንዳይወሰዱ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
በሙስና እና ግልጽነት ዓለምአቀፍ መለኪያ መሠረት እስራኤል 37ኛ ደረጃ አካባቢ ስትገኝ ኢትዮጵያ 110ኛ አካባቢ በሙስና ከተዘፈቁ አገራት መካከል አንዷ በመሆን ትጠቀሳለች፡፡
ሰሞኑን በእስራኤል የተከሰተውን የሚከታተሉ ወገኖች ሙስና የዕለት ተለዕት ክስተት በሆነባት የህወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የሚገኙን “የሙስና ሻርኮች” ማን ይደርስባቸው ይሆን በማለት ለጎልጉል ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “እስከ እንጥላችን ገምተናል” በማለት በራሱ በመሪው የተተቸውና ከአናት ጀምሮ የሙስና ባህር ውስጥ የሚዋኘው ኢህአዴግ በተለይ በ“አይነኬው” ህወሃትና ግብረአበሮቹ የሚፈጸመው ዓይን ያወጣ ሙስና እና ግፍ ከሥሩ እስካልተነቀለ ድረስ አሁን የሚታየው “የመልካም አስተዳደር” ነጠላ ዜማ ከቀናት በኋላ መሰልቸቱ አይቀርም ብለዋል፡፡
ጥርስ አልባው የጸረ ሙስና ኮሚሽንም የፖለቲካ ሥራ ለመተግበር የተፈጠረና የተቀመጠ እንጂ በእርግጥ ሥልጣንና ኃይል የተጎናጸፈ በራሱ የሚወስን ድርጅት እንዳልሆነ እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡
የሙስናውን “ሻርኮች” በተመለከተ ጉልጉል “ሙስናን በስንጥር” በሚል የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ባቀረበው ዘገባ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ “በቀረጥ፣ በሙስናና ባለስልጣናትን የንግድ ሸሪክ በማድረግ ኢትዮጵያን እየጋለቡዋት ያሉ “ባለሃብቶችና አሽከሮቻቸው” እስካልተነኩ ድረስ ኢህአዴግ በሙስና ላይ የጀመረውን ትግል ሙሉ ሊያደርገው አይችልም። ጅማሮው የችግሩ ቁልፍና እምብርት በሆነው ተቋም ላይ መሆኑ ይበል የሚያስብል ቢሆንም የሙስናው ድር ያልተበተበው የለምና የመጨረሻው አካሄድ ወዴት እንደሚያመራ ለመገመት ቢቻልም ጅምሩ ይገፋል የሚል ጥርጣሬ በስፋት አለ።…
“የባለስልጣናት ሚስቶችን፣ ዘመዶችና ወዳጆችን በተቋሞቻቸው ውስጥ በማይመጥኑት ሃላፊነት በመመደብ፣ ከተለያዩ የማማለያ ሽልማቶች ጋር ከፍተኛ ደሞዝ በመክፈል፣ አንዳንዴም ውጪ አገር ድረስ የህክምና ወጪ በመሸፈን ሰበብ የአገሪቱን የአመራር በትር ጨብጠው አገሪቱን እያለቡ ያሉት ሙሰኞች በይፋ እንደሚታወቁ የሚገልጹ ክፍሎች “አሁን ተጀመረ የተባለውና ይፋ የተደረገው የሙስና ትግል ህወሃት/ኢህአዴግ እነዚህን ክፍሎች ብብቱ ስር ይዞ የሚቀጥል ከሆነ ከቀልድ አይዘልም” ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ። ራሱ ህወሃት የሙስናው ንጉሥ ሆኖ “ሙስናን እዋጋለሁ” ማለቱ ከንቱ ፕሮፓጋንዳ ነው …
“አትራፊ የሆኑ የህዝብና የአገር ተቋማትን ወደ ግላቸው ያለ ክፍያ፣ ያለ ተመጣጣኝ ዋጋ፣ በተጭበረበረ ጨረታና አሰራር ወደ ግላቸው በማዞር አቶ መለስ “ተራው ህዝብ” በማለት በሚጠሩት ህዝብ ትከሻ ላይ እንዳሻቸው የሚዘሉትን “የሙስና አባቶችን” መታገል የማይችል የጸረ ሙስና ቀረርቶ ከተራ የፖለቲካ ልዩነት የዘለለ መነሻና መድረሻ ሊኖረው አይችልም። ለዚህም ነው የጸረ ሙስና ኮሚሽን በርካታ መረጃዎች እየደረሱት አፉን እንደተለጎመ የጋማ እንስሳ እንደ ስሙ መሆን ያልቻለው፤ ምክንያቱም ፈጣሪው ለሆነው መስገድ የግዱ ነውና፡፡”
ስለዚህ አሁንም ጥያቄው “ዋናቹን ሌቦችና የሙስና ሻርኮች ማን ይነካቸዋል?” ነው!
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
<!–
–>