Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ሌ/ኮ ፍሥሐ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” በተሰኘው መፅሐፋቸው ስለ መ ኢ ሶን በተረኩት ላይ በጥቂቱ – መርድ ከበደ

$
0
0

ሌ/ኮ ፍሥሐ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” ብለው በኅዳር ወር 2008 ዓ/ም አንድ መጸሐፍ አሳትመው ለንባብ አቅርበዋል፡፡ ለዚህ አስተዋፆዋቸው ምሥጋናዬ እጅግ ከፍ ያለ ነው ፡፡ ምንም እንኳን ስለመኢሶን እዚህና እዝያ የከታተቱት ውሀ የመይቁዋጥር ቢሆንም ቅሉ፣ ከመጸሐፉ ጠቃሚ መረጃዎችን አግኝቸበታለሁ፡፡


መጸሐፋቸው በ5 ክፍሎችና በ15 ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን ፤ አቀራረቡ እጅግ አስበውበት ያዘጋጁት መጸሐፍ እንደሆነ ያስታውቃል ፡፡ በነዚህ ክፍሎችና ምዕራፎች ውስጥ ፣ ስለ  አብዮቱ ወቅት ሁኔታ ያልዳሰሱት አርዕስተ ነገር ጥቂት ነው ማለት ይቻላል ፡፡ በክፍል 1 ውስጥ ፣ ከቅድመ 1966 ዓ/ም እንቅስቃሴ አንስተው እስከ የገጠር መሬት አዋጅ ድረስ ፤ በክፍል 2 ውስጥ ደግሞ ፣ ከሚያዚያ 1968 ዓ/ም “ከብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም” አዋጅ እስከ ነጭና “ቀይ ሽብር” ድረስ ፤ በክፍል 3 ፣ የሱማሊያ ወረራን ፣  የአሜሪካ ሴራን ፣ የድርጅቶች ሽኩቻና የኢሠፓኮ መቋቋምን ፤ በክፍል 4 ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ “ሠራተኞች ፓርቲ” ምስረታ ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መቋቋምና የደርግ የውድቀት ዋዜማን ከአስቃኙን በኋላ ፤ በመጨረውና በክፍል 5 ላይ ደግሞ ፣ ተሞክሮ ስለነበረው መፈንቅለ መንግሥትና “መሠሪ” ብለው ገጽ 124 ላይ በሚጠሯቸው ግለሰብ በሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ስለተደረገላቸው የመጨረሻዋ ራት ግብዣ ያትታሉ ፡፡ በነዚህ ክፍሎችና ምዕራፎች ውስጥ ስለ መላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) በተለያዩ ጥያቄዎች ላይ ስለነበረው አቋም አኮስሰውም ቢሆን ለመጠቃቀስ ሞክረዋል ፡፡ ለምሣሌ ፣ መኢሶንና የሥልጣን ጥያቄ ፣ መኢሶንና “ቀይ ሽብር” ፣ መኢሶንና የኤርትራ ጥያቄና ፣ መኢሶንና በራስ የመተማመን ፖሊሲ ጥያቄ ፣ ወዘተ . ላይ ጽፈዋል ፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ዕውነታውን የሚገልፁ ትረካዎችን እንዳካተቱ እገነዘባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ለምሣሌ በገጽ 316 ላይ ፤ “በደርግ ቁጥጥር ስር የነበሩት መገደል ነበረባቸው ወይ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ” እያሉ ሲሉ፤ ግድያውን እሳቸው ይቀበሉት ያወግዙት ግልፅ አለማድረጋቸው ጥያቆዎችን ጭሮብኛል፡፡ አንዳንዱን ደግሞ፣ ከደራሲው በማይጠበቁ የወሬ ማጣፈጫ ሀረጎች የተመላ ሆኑ አግኝቼዋለሁ፡፡ለምሣሌ ገጽ 89 ላይ ዶ/ር እሸቱ ጮሌን ጠቁመው ያሳሰሩት መኢሶኖች ናቸው ያሉትና ፣ ገጽ 225 ላይ ደግሞ የጥር 26ን የነዓለማየሁ ኃይሌን ግድያ ተከትሎም ፣ መኢሶኖች በደስታ ፈጥዘው ሊቀመንበሩን ይስሟቸው ነበር ይላሉ ፡፡ ዶ/ር እሸቱ ጮሌን ጠቁመው ያሳሰሩት በዕውነት መኢሶኖች ነበሩን ? ማስረጃቸው ምንድን ነው? የመኢሶን አመራር ልዩነት አፈታት ይታወቃል ግልፅ የሆነ ውይይት ነው ፡፡ ጥቆማም ሆኖ አያውቅም ፡፡ መኢሶኖች የነዓለማየሁ ኃይሌን ግድያን በዕውነት እንደ ታላቅ ድል ቆጥረውትና ፈንጥዘው ነበርን ? የጥር 26 ቀን ፣ 1969ዓ/ም ግድያ ለነኮ/ል መንግሥቱ ትልቅ ድል ሆኖ ይቆጠር እንጂ ፣ ለመኢሶን ግን አልነበረም ፡፡ ስለዚህም ነው የካቲት 20 ቀን ፣ 1969 ዓ/ም መኢሶን በልሳኑ “በሠፊው ሕዝብ ድምፅ” ቁጥር 52 ላይ “ አብዮቱን ማፋፋም ፣ ለመጨረሻው ፍልሚያ መዘጋጀት “ በሚል አርዕስት ሥር ፤ “ ማንም ሰው በቀላሉ ሊገነዘበው እንደሚችል ሁሉ ፣ በደርግ ውስጥ በነበሩት ቀንደኛ የቀልባሽ ኃይሎች ወኪሎች ላይ በጥር 26/1969 የተወሰደው ቆራጥ አብዮታዊ እርምጃ ፣ የኢትዮጵያን አብዮት ለዘለቄታው ከቅልበሳ አደጋ አድኖታል ማለት አይደለም ፡፡ ለአብዮቱ የጥቂት ጊዜ ፋታን ገዝቷል ማለት ግን ይቻላል ፡፡ ከዚህ በፊት መኢሶን በየጋዜጣ ቁጥሩ ደጋግሞ እንደገለጸውና እስከ መጨረሻውም ሳይሰለች እንደሚገልጸው ሁሉ ፣ የኢትዮጵያን አብዮት ከቅልበሳ ለዘለቄታው ሊያድንና በአድሀሪ ኃይሎች ላይ ሁሉ ድልን አስገኝቶ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚችለው ኃይል የነቃ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል ብቻ ነው  “ በማለት ፣ ገና ቀሪ ትግል እንዳለ ነው ያስታወቀው ፡፡

fiseha-desta - satenaw 2ይኸንን ካልኩ ዘንዳ ወደ ተነሳሁባቸው ነጥቦቼ ልመለስ ፡፡

l.መኢሶን ለምን በኋላ ላይ ከደርግ ጋር ሕብረት ፈጠረ ? ደርግ ፣ የየካቲት 1966 ዓ/ም ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የፈጠረው የመለዮ ለባሾች ስብስብ ነው ፡፡ መኢሶን ደግሞ ከሐምሌ 30 ቀን ፣ 1960 ዓ/ም አንስቶ ፣ ለሀገር ይበጃል ያለውን የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፎ ለመጭው ትግል ሲደራጅ የነበረ የምሁራን ስብስብ ነበር ፡፡ መኢሶን መጀመሪያ ላይ የደርጉ ተቃዋሚ እንደ ነበር ይታወቃል ፡፡ ሆኖም ግን በትግሉ ሒደት ወቅት መኢሶን አቋሙን ቀየር፡፡ መኢሶን በትግሉ ሒደት ውስጥ አቋሙን ለምን ከሙሉ ተቃዋሚነት ወደ ሂሳዊ ድጋፍ ለመለወጥ በቃ ? ብለን ብንጠይቅ ፤ መኢሶን ደርግን በተመለከተ አቋሙን የለወጠው ፣ ደርግ በተለይ የገጠር መሬትንስላወጀ መሆኑን መረዳት አያዳግትም ፡፡ በዚህ ላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ አድሀሪ የዐረብ መንግሥታትና አጎራባቾቻችን የሱማሌና የሱዳን መንግሥታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ይፈታተኑ እንደነበር ይታወቃል ፡፡ በአብዮቱ ወቅት ደግሞ ከነእርሱ በተጨማሪ በሥር ነቀል አብዮታችን የተነሣ ጥቅማቸው የተነካው ዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም በአንድ ወገንና የሀገር ውስጥ የአድህሮት ኃይሎች በሌላ ወገን እጅና ጓንት በመሆን ደርግን ለመጣል የሚያደርጉትን እርብርብ አጧጧፉት ፡፡ በዚህ ላይ ይኸ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ (COMPASS) እንደሌለው መርከብ ከወዲያ ወዲህ ሲዋዥቅ የነበረው አብዮታችን ፣ ወዴት መጓዝ እንዳለበት አቅጣጫ ጠቋሚ ፕሮግራም ያስፈልገው ነበር ፡፡ የደርጉ “ ኢትዮጵያ ትቅደምና ” “የኢትዮጵያ ሕብረተሰባዊነት “ ለለውጡ አቅጣጫ ጠቋሚ ሊሆኑ አልቻሉም ፡፡ ስለዚህም ነው መኢሶን ይኸንኑ በተመለከተ “ የኢትዮጵያ ሕብረተሰባዊነት “ሲታወጅ ፤ በሰሕድ ቁጥር 29 (ሐምሌ 11ቀን 1967 ) ላይ ፤ “…ሕብረተሰብአዊነት መታወጁ ወይም የመንግሥት መመሪያ ሆኖ መውጣቱ ምንም ያህል ሊለውጠው የማይችል ኢትዮጵያ የደረሰችበትና ያለችበት የታሪክ ደረጃ አለ ፡፡ በዛሬይቱ ዓለምም ግማሽ-ፊውዳልና ግማሽ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሥርዐት በነገሠባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገሮች ሶሻሊስት አብዮት ለማድረግ አይቻልም ፡፡ የዚህ ዐይነቱ ሕብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ፤ ፖለቲካዊና ማኀበራዊ አቋም ሁሉ ይህንን አይፈቅድም ፡፡ እዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ሊከናወን የሚችለው ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ነው ፡፡ “ ሲል የተቸው (ሠረዝ የራሴ) ፡፡የመኢሶን የአመራር አባላት ደርጉ ግራ ተጋብቶ ሥልጣኑን ለሲቪሉ ማኀበረሰብ አስረክቦ ወደ ጦር ካምፑ ለመመለስ እንዳሰበ ሲነግራቸውና የፖለቲካ ፓርቲ አስኳል አቋቁመው ሥልጣኑን እንዲረከቧቸው በጠየቋቸው ጊዜ ፣ ይህ ጉዳይ የሕዝቡ የራሱ ጉዳይ ስለሆነ ሕዝቡ ነቅቶና ተደራጅቶ የራሱን ፓርቲዎች እንዲያቋቁም ለማብቃት ድጋፍ መስጠት እንደሚችሉና ለዚሁም ይረዳ ዘንድ አንድ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት እንዲቋቋም ያደርጋሉ ፡፡ ተራማጆቹ ለለውጡ ሕዝባዊ መሠረት ለመስጠት ያመቻቸው ዘንድ ለደርጉ ድጋፍ ባያደርጉ ኖሮ የውስጥና የውጭ ፀረ-አብዮትና ፀረ-አንድነት ኃይሎቹ ደርጉን ይጥሉት እንደነበር ጥርጥር የለውም ፡፡ እነሌኮ/መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መኢሶን ተዳክመዋል ብሎ ጥሎን ፈረጠጠ ይላሉ እንጂ መኢሶን ለአብዮቱ መሳካት ሲል ከደርጉ ጋር ያደረገው የፖለቲካ ትብብር ደርጉ ደካማ በነበረበት ወቅት መሆኑ መዘንጋት የለበትም ፡፡መኢሶን በሕጋዊ መድረኩ ተጠቅሞ የሕጋዊ መድረኩን ትግል በመቀላቀሉ የአብዮቱ ጎራ በአፋጣኝ ለመሰባሰብ ከመቻሉም በተጨማሪ ትግሉም ሕዝባዊ መሠረት ሊያገኝ በቃ ፡፡ አልፎ ተርፎም የውጭ ተራማጅ ሀገሮች ለአብዮታችን ዕውቅና በመስጠት ከኛ ጋር መተባበር ጀመሩ ፡፡ አንዳንዶቹ መኢሶን ከደርግ ጋር አብሮ በመሥራቱ ደርግን አጠናከረው ይላሉ፡፡ዕውነቱን ለመናገር የተጠናከረው ደርጉ ሳይሆን የአብዮቱ ጎራ ነበር ፡፡ ደርጉ በዚህን የነፍስ ውጭ ፣ የነፍስ ግቢ ትንቅንቅ ወቅት እንኳን ሊጠናከር ይቅርና እርስ በራሱ እየተጠፋፋ ስለነበር ቁጥሩ እያነሰ በመሔድ ላይ ነበር ፡፡ ስለዚህ መኢሶንን ከደርጉ ጋር ያገናኘውም ሆነ ያለያየው፣ የአብዮቱ ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ፡፡መኢሶን ከመጀመሪያውም ቢሆን ፣ ደርጉ አብዮቱን እስከ ተወሰነ ደረጃ እንደሚሸኝ ተጓዥ እንጂ ፣ እንደ ዘላቂ ተጓዥ ተመልክቶት አያውቅም ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ መኢሶን በወቅቱ የፖለቲካ አካሔዱ በመደቦች ባህሪ ትንታኔና በቅራኔዎች አፈታት ቅደም ተከተል ሕግጋት መሠረት የሚመራ እንደነበር አመላካች ነበር ፡፡ ከዚህ ከመደባዊ ትንታኔ በመነሣትም መኢሶን ወታደራዊው ደርግ የመጀመሪያውን የአብዮት ደረጃ ማለትም የዲሞክራቲክ አብዮቱን ደረጃ ከሠፊው ሕዝብ ጋር አብሮ ለመጓዝ ይቻል እንጂ ፣ ደርጉ የንዑስ ከበርቴ ስብስብ እንደመሆኑ መጠን አብዮቱን ወደ ሁለተኛው ደረጃ (ወደ ሶሻሊስቱ) እንደማያሸጋግረው ጠንቅቆ ያውቅ ነበር ፡፡ ከደርግ ጋር የተባበረውም ከዛሬ ወዳጄ ጋር ሆኘ የአብዮቱን የውስጥና የውጭ ተፃራሪዎች ልዋጋቸው ከሚል እሳቤ ነበር ፡፡ ይኸ ደግሞ በአብዮቱ ወቅት አማራጭ የሌለው ብቸኛ ጎዳና ነበር ፡፡ እነ ሌነንም ቢሆኑ በታላቋ ራሻ የጥቅምት አብዮት ጊዜ ከነክረንስኪ ጋርና ፣ እነ ማኦ ደግሞ የሀን ሥርዎ መንግሥትን ለመጣልና የጃፓን ኢምፔሪያሊዝምን ወራሪ ኃይል ለመመከት ከነ ጀነራል ሻንጋይሸክ ጋር ጊዜያዊ ትብብር ያደረጉት ለዚሁ ነበረ ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሕብረት በመፍጠር መታገል በታሪክ መኢሶን ብቸኛ ተደርጎ ባይወሰድ መልካም  ነው ፡፡

ll.መኢሶንና የሥልጣን ጥያቄ 

እነ ሌ/ኮ ፍሥሐ ደስታ ሌላ መኢሶንን የሚከሱት የሥልጣን ጥመኛ ነው በማለት ነው ፡፡ ይኸም የራሣቸውን የሥልጣን ጥማት ለመሸፋፈን ሲሉ መኢሶን ላይ የሚያናፍሱት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው ፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ አቶ ተስፋዬ መኮንን “ይድረስ ለባለታሪኩ” ብለው ጥቅምት 1985 ዓ/ም ባሳተሙት መጸሐፋቸው ገጽ 243 ላይ ስለዚሁ ጉዳይ ሲያወሱ ፤ “… በዚህም ሕብረቱ በአስቸኳይ መዋሀድና አመራሩን መሸከም ካልቻለ በቀር የደርግ አመራር ሊቋቋመው የማይችለው አስፈሪ የሆነ የተቀነባበረ የወረራና የመገንጠል ጦርነት እየመጣ እንደሆነ ጭንቀት በተሞላበት ሁኔታ በኮ/ል መንግሥቱ መገለፁን ዛሬ በአቋም ስለተለያየን መካድ አይቻልም ፡፡ ለዚህ ግን አለመሳካት ምክንያቱ የመኢሶን ወደኋላ ማፈግፈግ ነበር “ ብለው መኢሶንን ሥልጣን ለመካፈል ባለመስማማቱ ይወቅሱታል(ሠረዝ የራሴ)  ፡፡ ገሥጥ ተጫኔም “ነበር” ብለው በጻፉት በመጀመሪያው መጸሐፋቸው ገጽ 270 ላይ ፤ “ በዚያን ወቅት ኢማሌድህን “አመራሩን ተረከብ” አሉት ፡፡“ አልችልም እንደገባህበት አንተው ተወጣው “ እንደማለት አፈገፈገ ፡፡ “ ብለው አስፍረውታል ፡፡

እንግዲህ ሀቁ ይኸ ሆኖ እያለ በምን ተዐምር ነው የመኢሶን ሰዎች የሥልጣን ጥመኞች ሊባሉ የሚችሉት ? የመኢሶን አመራር አባሎች የሱማሌውን የዚያድ ባሬን ዐይነት የይስሙላ ሶሻሊስት መንግሥትና ፓርቲ ከኮለኔል መንግሠቱ ሰደድ ጋር ሆነው ለመመሥረት  አልፈለጉም ፡፡ ይኸንን ደግሞ እርስዎ እራስዎ በመጸሐፎ በገጽ 229 ላይ ግሩም አድርገው እንዲህ ሲሉ ፤“ …ኮ/ል መንግሥቱም ጦሩን ፣ ደህንነቱንና መስተዳድሩን በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ ያለማንም ተቀናቃኝ የመጨረሻው ወሳኝ ሰው ሆኑ ፡፡ እኛም በሳቸው የምንሾምና የምንሻር ፣ የምንታሰርና የምንገደል ፣ ፊታቸው ሲከፋ እየተከፋን ፣ ሲስቁ የምንስቅ ሁነን አረፍነው ፡፡ “ በማለት የፓርቲው አባሎቹም ሆኑ ባለሥልጣኖቹ በድርጅቱና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ፋይዳቢስ እንደነበሩ ግሩም አድርገው ገልጸውታል ፡፡

መኢሶን አዝማሚያው ስላላማረው እራሱን ከኢማሌዴኅ በይፋ ካገለለ በኋላ ፣ እነ ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም ስላቋቋሙት “የወዝ አደር ፓርቲ” ሌ/ኮ ፍሥሐ በገጽ 553 ላይ ሲገልጹም ፤ “  በአጭሩ ኢሠፓ ከመጀመሪያው ጀምሮ በጓድ መንግሥቱ ማዕከልነት ይመሰረታል እንደተባለው ታጋይ ማርክሲስቶችን አሰባስቦ ለትግሉ አመራር ይሰጣል የተባለው ድርጅት ወደ አንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ተለወጠ ፡፡ በውጭና በመፈክር ኮሚኒስቶች ፣ በተግባር አስመሳዮች ተሞልቶ የማታ ማታ የተጠበቀውን አመራር ሳይሰጥና ኃላፊነቱንም ሳይወጣ ወደ ውድቀት አመራ ፡፡ “ በማለት ነው ፡፡ ግን ሌኮ/ፍሥሐ ይህ እርስዎንም እንደሚያጠቃልል ይገነዘባሉ ?

የሚገርመው ሌ/ፍሥሐ ደስታ ይኸንን ሁሉ ከነገሩን በኋላ የመኢሶን አመራር አባሎች ለምን የዚህ አሳፋሪ ድርጊት አካል አልሆኑም ? ለምን በጊዜ ጥለውን ፈረጠጡ ማለታቸው ነው ፡፡ ሌ/ኮ ፍሥሐ ደስታ ስላቋቋሙት ፓርቲና መንግሥት አይረቤነት የነገሩን በኅዳር ወር 2008 ዓ/ም ላይ ሲሆን ፣ መኢሶን ግን እነ ሌ/ኮ መንግሥቱ የሚመሠርቱት ፓርቲያቸው እንዲህ ዐይነት ሊሆን እንደሚችል “ሀገር ከዳ ፣ ከአብዮቱ ፈረጠጠ” ካሉትም በኋላ ፣ መኢሶን በልሣኑ “በሰፊው ሕዝብ ድምፅ” ቁጥር 65 ጥር 21 ቀን ፣ 1970 ዓ/ም ከሕዝብ መሀል ሆኖ የሚከተለውን ነግሯቸው ነበር ፤ “ ሩቅ ሳንሄድ የሱማሌ ወዝአደርና ሰፊ ሕዝብ የደረሰበትን ውድቀት እንመልከት ፡፡ በሱማሊያ እንደምንም ተውተፍትፎ “ የወዝአደር ፓርቲ ባስቸኳይ ተመሠረተ ” መሐመድ ዚያድ ባሬ የሰፊውን ሕዝብ ወገኖች የመደራጀት መብትና ዲሞክራሲን አፍኖ ይዞ በጨለማና በግርግር “የወዝአደር ፓርቲ” አቋቋመ ፡፡ …በዚህ መልክ ተውተፍትፎ የተቋቋመ ፓርቲ ውሎ ሲያድር ምን ዓይነት ፋሽስታዊና እብሪተኛ መልክ እንደሚይዝ የዚህን ዕብሪት ገፈት በመቅመስ ላይ ያለው የሱማሊያ ወዝአደርና ሰፊ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለአብዮታዊት እናት አገራችን ክብርና ሕልውና በመዋደቅ ላይ ያለው መደበኛና ህዝባዊ ሠራዊት የተገነዘበው ሀቅ ነው ፡፡ “ እንግዲህ ሌ/ኮ ፍሥሐ ደስታም ይኸንኑ ነው አደረግን ብለው አሁን ላይ የሚነግሩን ፡፡ የሚገርመው ግን መኢሶን እነርሱ ስለሚያቋቁሙት ፓርቲ ምንነት ከ6 ዓመት በፊት ነግሯቸው ነበር ፡፡ እንዲህ ዕይነቱን የለውጥ ፋና ወጊ ድርጅት ምን አደረገን ብለው እንደሚወነጅሉት አይገባኝም ፡፡

መኢሶን ስለ ሥልጣን ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት አቋሙን ገልጾ ነበር ፡፡ ለዚሁም የሠፊው ሕዝብ ድምፅን ቁጥር 42 ፣ ሰኔ 17 ቀን ፣ 1968 ዓ/ም የተጻፈውንና ፣ ቁጥር 45 ፣ ነሐሴ 10 ቀን ፣ 1968 የተጻፈውን መመልከት ይበቃል ፡፡ ይኸን ሁሉ ስል ግን ፣ መኢሶን የሥልጣን ፍላጎት አልነበረውም ለማለት አለመሆኑን ይታወቅልኝ ፡፡ መኢሶን በሚያዚያ 13 ቀን ፣ 1968 ዓ/በታወጀው አዋጅ መሠረት በሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን ቢይዝ ኖሮ ደስታውን አይችለውም ፡፡ ሀገራችንም እስካሁን ያልታደለችው ለእንደዚህ ዐይነቱ የሥልጣን ሽግግር ነው ፡፡ መኢሶን የሚቃወመው ሥልጣን መያዝን ሳይሆን ከሕዝብ ይሁንታ ውጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ሩጫ ነው ፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ሲታወጅ ፤ የሥልጣን ሽግግርን በተመለከተ አዋጁ የሚለው ፤ “ የሰፊው ሕዝብ ትግል ተደራጅቶና ገፍቶ አብዮታዊ ሕዝባዊ ግንባሩ እንደተቋቋመ በትግሉ ውስጥ የተሳተፉት የግንባሩ አባል ፓርቲዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚያቀርቧቸው ምልምሎች መሀከል ሕዝቡ በሙሉ ነፃና ምስጢራዊ በሆነ ምርጫ እንደራሴዎቹን መርጦ የመንግሥቱን ከፍተኛ ሥልጣን ወደሚይዘው አብዮታዊ ሕዝባዊ ሸንጎ ይልካል ፡፡ የሕዝቡ ወኪሎች አጥንተው ባጸደቁት ሕገ-መንግሥት መሠረት የመንግሥቱ መዋቅሮች ፣ ዘርፎችና የሥልጣን ክፍፍሎች ተወስነው በወዝ-አደሩ ፓርቲ መሪነት ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ይቋቋማል ፡፡ ”

ደርጎችም ለዚህ አዋጅ ተግባራዊነት ከተራማጁ ጎን ሆነው ሊታገሉና ፣ አላደረጉትም እንጂ በአዋጁ መግቢያ ላይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል በገቡት መሠረት ሥልጣኑን ለሰፊው ሕዝብ አስረክበው ወደ ጦር ካምፓቸው ሊመለሱ ነበር ፡፡ ይኸ እንግዲህ በይፋ ለሕዝብ በአዋጅ የተገባ ቃል ኪዳን ነበር ፣ ከሳሾቻችን አሌ እንደማይሉት እርግጠኛ ነኝ ፡፡ እንግዲህ በይፋ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ቃል ኪዳን ከገባን በኋላ ነው በቤተመንግሥት ዱለታ ሥልጣን እንጋራ ያላችሁን ፡፡ መኢሶን እንዲህ ዐይነት ቅሌት ውስጥ አይገባም ፡፡ ሥልጣን አጓጉቶትም አልገባምም ፡፡ ኮሎኔል ፣ የሥልጣን ጥያቄን በተመለከተ ዕውነታው ይኸው ነው እንግዲህ ፡፡ አንድ የረሳሁትን ነገር አሁን አስታወስኩ ፣ ያኔ አባሎቻችሁ እኛን ባዩ ቁጥር ጮሆ ላሞራ ስትሉ እሰማ ነበር ፡፡ ለምን እንደዚያ እንደምትሉ ግን አልገባኝም ነበር ፡፡

lll.መኢሶንና ቀይ ሽብር

በመጀመሪያ ደረጃ ቀይ ሽብር ማለት ምን ማለት ነው ? ለምንስ አስፈለገ ? ማርክሲስቶች ቀይ ሽብር የሚሉት በአንድ የርስ በርስ ጦርነት (አብዮት) ወቅት ጣምራ ሥልጣን ተፈጥሮ አብዮተኞችም ሆኑ ወይም ደግሞ ፀረ-አብዮተኞች የመንግሥቱን መዋቅር ተጠቅመው ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ በማይችሉበት ወቅት ተራማጆችየሚጠቀሙበት የትግል ዘዴ ነው ፡፡ በተለይ ፀረ- አብዮተኞች ሥልጣናቸውን በሠላም ላለመልቀቅ ሲሉ አብዮተኞቹ ላይ ግድያ መፈጸም ስለሚጀምሩ ፣ አብዮተኞቹም ቀንደኛ ፀረ-አብዮተኞቹ የአብዮቱን ሒደት እንዳይገቱት ለማድረግ ፀረ-አብዮተኞች ላይ የሚወስዱት እርምጃ ነው እንጂ ፣ እንደነ ኮ/ል መንግሥቱ ሮጠው ያልጠገቡ ልጆችን ከቤታቸው በገፍ እያወጡ መረሸን አይደለም ፡፡ አቶ አንዳርጋቸው የሚያወራው ቀይ ሽብር እስከ ነሐሴ 14 ቀን 1969 በቀንደኛ ፀረ- አብዮተኞች ላይ ስለተወሰደው ቀይ ሽብር ሽብር እንጂ ፣ ደርጉ ነሐሴ 21 ቀን ፣ 1969 ዓ/ም አዋጅ ቁጥር 129/69 ብሎ ካወጀ በኋላ ስለተካሔደው ዐይነት የመንግሥት ሽበርና ጭፍጨፋ አይደለም ፡፡

እርስዎ ቀደም ሲልም ኅዳር 1 ቀን ፣ 1997 ዓ/ም በወጣውም አዲስ ዘመን ላይ ለፍርድ ቤት ቃሎን ሲሠጡ ፤ “መኢሶን ቀይ ሽብርን  ከመንግሥት ተደብቆ አካሔደው” ፣ “ሊቀመንበር መንግሥቱ ደግሞ አስቆሙት” ብለዋል  ፡፡ አሁንም በመጸሐፎ ገጽ 247 ላይ ይኸንኑ ነው የሚደግሙልን ፡፡ እንደው ለመሆኑ በሬዲዮን ፣ በጋዜጣና በቴሌቪዥን እየተለፈፈ በ “ቀይ ሽብር” ስም የተካሔደ የመንግሥት ሽበርና ጭፍጨፋ “ድብቅ” ሊባል ይችላልን? እረስተውት ነው እንጂ፣ ሊቀመንበር መንግሥቱ “ቀይ ሽብርን” አስቆሙ እንጂ አላካሔዱም ካሉን በኋላ ፣ እንደገና ደግሞ ገጽ 255 ላይ ፤ “ የደርግ መንግሥት በየግንባሩ የተከፈተበትን ጦርነትና የሱማሊያን ወረራ ለመከላከል በቅድሚያ በመሀል አገር ነጭ ሽብር አውጆ ይንቀሳቀስ የነበረውን ኢሕአፓን በቀይ ሽብር በመደምሰስ በአሸናፊነት መውጣት ነበረበት ፡፡ “ ብለው ቀደም ሲል የተናገሩትን ይቃረኑታል ፡፡

ለምንድን ነው መኢሶን “የፈረጠጠበትን” እና “ ቀይ ሽብር ” ያካሔዳችሁበትን አዋጅ ዓመተ ምህረቱን ሲጽፉ ቀኑን   ያልጻፉት ? ቀኑን ካልገለጹልን መኢሶን መሳተፍ አለመሳተፉን ለማወቅ አይቻልም ፡፡ ስለዚህ አንባቢን ለማስረዳት ስል ቀኖቹን እኔው ልጥቀስሎት ፡፡  “ቀይ ሽብሩን” ያካሔዳችሁበትን አዋጅ ያወጃችሁት ነሐሴ 21 ቀን ፣1969 ዓ/ም ነበር ፣ መኢሶን ደግሞ ኅቡዕ የገባው ነሐሴ 14 ቀን ፣1969ዓ/ም ነው ፡፡ ስለዚህ በቀይ ሽብር ተብየው ጊዜ መኢሶን አልነበረም ፡፡              እስቲ ስለ “ ቀይ ሽብር ” አንድ ከፍተኛ የደህንነት ባልደረባ የነበሩ ሰውዬ ለሊቀ መንበር መንግሥቱ በ1994ዓ/ም የጻፉትን ላስነብቦት ፤መቸም እኝህን ሰውዬ እርስዎም ሳያውቋቸው የሚቀሩ አይመስለኝም ፡፡ ለማንኛውም “ቀይ ሽብርን” ኮሎኔል መንግሥቱ እርስዎ እንደሚሉት ያስቆሙት ግለሰብ ሳይሆኑ ፣ በመአከልነት ሲያካሒዱት እንደ ነበር ሠይፉ ታምራት የሚባሉ ግለሰብ ፣ ሐምሌ 1994 ዓ/ም “ጦቢያ መጽሔት” ላይ ያቀረቡትን ትዝብታቸውን ቀንጨብ አድርጌ ላቅርብሎት፡፡

1.”ብርሃኑ ከበደን በደርግ ምርመራ ሾመው ሀገር ሲፈጅ ፣ ካሣሁን ታፈሰ ወይም ፍፁም ገብረሃና ብቻ የሚያውቁት ሳይሆን ፣ ኮ/ል መንግሥቱም በሚገባ ያውቁታል ፡፡ ዘጠና የሚሆኑ ምርጥ ወታደሮች ያሉበት የልዩ ጥበቃ ኮማንዶ በአሥራተ ካሳ ግቢ ተቋቁሞ የሰው ልጅ እንደሰው ያይደለ አገዳደል እየታነቀ ሲጣል ፣ በቦታው ተገኝተው የገመዱን ሸምቀቆ ባያጠብቁም ዝርዝሩን ለተስፋዬ ወልደ ሥላሴና ለዘሪሁን አጋፋሪ ትተው ቤትዎ የተቀመጡ አልነበሩም፡፡ ዛሬ የመድሀኒት ግምጃ ቤት እያሉ የሚያሾፉበት ግቢ ከኩባው ካስትሮ ልምድ የመነጨ ፣ በኩባዊያንና በምሥራቅ ጀርመን ባለሞያዎች የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍለቂያ ግቢ ሆኖ እግረ መንገዱን የአብዮታዊ ሠደድ ልዩ ስኳድ መፈልፈያ ሲያደርግ የሚያውቁት ለገሠ በላይነህ ብቻ ሳይሆኑ እርስዎም የጉዳዩ ዋናው ባለቤት ጭምር ነዎት፡፡

2.“… ዛሬ እኔ ቀይ ሽብርን የአቆምኩም ነኝ ፣ እንደ እርስዎው የጲላጦስ እጥበት ሊታጠቡ የሚሞክሩት ግለሰብ የአዲስ አበባ ቀበሌዎችንና ካድሬዎችን በቀድሞው ፓርለማ አዳራሽ ሰብስበው ሲያነጋግሩ ቀበሌዎች ፣ “እኛ ፀረ-አብዮተኞችን እየያዝን ለፖሊስ ስንሠጥ ፣ ፖሊስ እያደራጀ ይለቅብናል ፡፡ ከነሚለጥፈው ወረቀቱ እየሠጠን ተደራጅቶ ይወጣብናል ፡፡” ብለው አቤት ሲሉ ፣ “ሲለጥፍ ያገኘኸውን እዚያው ግድግዳው ላይ በጥይት አትለጥፈውም ?” በሚል መመሪያ መጠነ ሠፊ ግድያ እንዲጀመር በማስደረጋቸው ኮ/ል ተካ ቱሉና ካሣሁን ታፈሰ ቢሮ መጥተው ሲያነጋግሩዎት የሠጡት ምላሽ ምን እንደነበረ ማስታወስ ይችላሉ ?”

  1. “የከፍተኛ ዘጠኙ ቀልቤሳ ነገዎ ከከፍተኛ 12ቱ ሠለሞን ይመስገንና ከከፍተኛ ሁለቱ በድሩ መሐመድ ጋር ሆነው የብሔራዊ ትጥቅ ኮሚቴ በነበረው ሰለሞን ይመስገን በኩል የተወሰዱትን መሣሪያዎች ለወዝ አደር ሊግ ልዩ ስኳድ ሰጥተው በብርሃኑ ከበደ የጎን ትዕዛዝ በየቀበሌው ግድያ ስለሚፈጽሙ ሰዎች በዝርዝር ሪፖርት ከቀረበሎት በኋላ ለገሠ አስፋውን ጠርተው ቀበሌዎችን በሚመለከት የሠጡትን መመሪያ (ትዕዛዝ) የሚያስታውስዎት ሰው ይፈልጋሉ? ወይስ በደህንነት መዋቅር በሪፖርት መልክ ከ001 እስከ 009 ባሉ ኮዶች ይቀርቡ የነበሩ ዘገባዎችን አልተመለከትኩም ቢሉ ፣ ከኮ/ል ተካ ቱሉ ሌላ የሚያውቅ የሌለ ይመስሎታል?”
  2. “የከፍተኛ 25 ማዕከላዊ እስር ቤትን የመሳሰሉ ተቋማት ተፈጥረው ሲያድጉ እርስዎም በሚገባ ያውቃሉ ፡፡ የተመደቡ ወታደሮችን ለመለወጥ መመሪያ ሠጥተው እንደነበር ያስታውሳሉ ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከፍተኛ የኢሕአፓ አመራር በከፍተኛ 25 በቁጥጥር ሥር ውሎ የአንድ አስኳል ገንዘብ ካጋለጠ በኋላ ገንዘቡ ከጎንደር ባንክ ወጭ ተደርጎ ግለሰቡ በብርሃኑ ከበደ አማካይነት ወዲያውኑ ሲረሸን ፣ ሙሉ ሪፖርቱ ቀርቦልዎት ውሳኔ ሲሠጡ ተጨማሪ ወታደሮች ከደህንነትና ከፖሊስ እንዲሁም ከልዩ ጥበቃና ከወታደራዊ ፖለቲካ መምሪያ በየቦታው ተበትነው በመኖሪያ ቀበሌያቸው ተሰማርተው በቀይ ሽብር ሒደት ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለተካ ቱሉ መመሪያ አልሠጡም ?”

ትንኝ ገድዬ አላውቅም እያሉ የሚቀጥፉትን መንግሥቱ ኃይለማርያምን አቶ ሠይፉ ታምራት የ”ቀይ ሽብር” ቁንጮ ተዋናይ እንደነበሩ ያጋልጣሉ ፡፡ እኝህ ውስጥ አዋቂ ሰው ፣ ሰደድንና ወዝ-ሊግን ከቀይ ሽብር ጋር ስማቸውን አያይዘው ሲጠቅሱ ፣ መኢሶንን አንድም ቦታ ላይ አልጠቀሱትም ፡፡ ለምን ይመስሎታል ? ያልጠቀሱበት ምክንያት ፣ መኢሶን “ቀይ ሽብር” ከመካሔዱ በፊት ነሐሴ 14 ቀን ፣ 1969 ዓ/ም የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ እራሱን ከኢማሌዴህ አባልነት አግልሎ ሕቡዕ ገብቶ ስለነበር ነው ፡፡

ማንም በቀላሉ ለማረጋገጥ እንደሚችለው የመኢሶን መፈክር ፤ “የነቃ ተደራጀና የታጠቀ ሠፊ ሕዝብ ያሸንፋል !!!” የሚል ነበር ፡፡ ያልነቃና ያልተደራጀ ሕዝብ ቢታጠቅም አብዮቱን ከግቡ ሊያደርሰው እንደማይችል በፅኑ ያምናል ፡፡ ስለዚህ በትግሉ ወቅት አተኩሮ ይንቀሳቀስ የነበረው ሕዝብን በማንቃትና በማደራጀት ላይ ነበር ፡፡ መኢሶን ኃይልን የሚጠቀመው ባስፈላጊ ጊዜ ብቻ ነበር ፡፡ አለበለዚያ ልዩነትን ለመፍታት የሚጠቀመው በውይይት ነው ፡፡ የድርጅቱ አመራር ፣ ልዩነት እንዴት መፈታት እንዳለበት ሲመክር ጥር 10 ቀን ፣ 1968 ዓ/ም ፤ “ የሠፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 36 ላይ ፤ “ ዕውነተኛዎቹ ተራማጆች የሚያምኑት በፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ብቻ በመከራከርና በመወያየት የፖለቲካ መስመርን ማጥራት በሚለው አብዮታዊ መመሪያ እንጂ ፤ በሃሜት ፤ በፈጠራ ወሬ ፤ በስም ማጥፋትና በጥቆማ ዘመቻ ወይንም ደግሞ ከናካቴው በበትር መዘዛ አይደለም “ ብሎ ነበር ፡፡

መኢሶን ከሕጋዊው መድረክ እራሱን እስካገለለበት እስከ ነሐሴ 14 ቀን ፣ 1969 ዓ/ም ድረስ ሦስት የመሣሪያ አሰሳዎች ተደርገው እንደነበር ይታወቃል ፡፡ አንደኛው አሠሳ በኅዳር ወር 1969 ዓ/ም የተደረገው ሲሆን ፣ ሁለተኛው ፣ ከመጋቢት 14 ቀን ፣ 1969 ዓ/ም እስከ 18 ቀን ፣ የተደረገው ነው ፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ፣ በሰኔ 1969 ዓ/ም የተደረገው ነበር ፡፡ በኅዳር ወር 1969 ዓ/ም በተካሔደው አሰሳ ላይ ፣ “የዘመቻው ትኩረት የጦር መሣሪያ በመሰብሰብ ላይ ስለነበር ኢሕአፓ የደረሰበት ጉዳት ጥቂት ነበር ለማለት ይቻላል” ሲሉ የኢሕአፓ የፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሠ ይገልጹታል ፡፡ ለዚህ የታኅሣሥ 5 ቀን ፣ 1997 ዓ/ም “አስኳል” ጋዜጣን ገጽ 7ትን መመልከት ይቻላል ፡፡

በሰኔ 1969 ዓ/ም የተካሔደውንም አሰሳ አስመልክተው ፣ “ከዚህ በተረፈ በሰኔ 1969 ዓ/ም አንድ ሌላ አሰሳና የትጥቅ ማስፈታት እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ተካሒዶ ነበር ፡፡ ይሁንና መኢሶን በዚህኛው እንቅስቃሴ ውስጥ አልተሳተፈም ፡፡ አሰሳውን ያንቀሳቀሱትና የመሩት ሰደድ ፣ ወዝ አደር ሊግ ፣ ማሌሪድና የደርግ የፀጥታ የዘመቻ ክፍሎች ነበሩ ፡፡ ” ሲሉ መኢሶን በዚህኛው አሰሳ እንዳልተሳተፈ ይመሰክራሉ ፡፡ግርማ ከበደንም ከመኢሶን ጋር ለማያያዝ የምትሞክሩት ከወንጀሉ ለመሸሽ ነው እንጂ ፣ የመኢሶን አባል አለመሆኑን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ ፡፡ መኢሶን ግርማን እንዳታስታጥቁ ቢነግራችሁም ፣ መኢሶን ከተቃወመው የእኛ ሰው እናድርገው ብላችሁ ፣ ማንም የቀበሌ ተመራጭ አውቶማቲክ መሣሪያ ከመታጠቁ በፊት እናንተው አስታጠቃችሁት ፡፡ የሊቀ መንበር መንግሥቱን አጎት ስለተተናኮለ ብቻ ይዛችሁ ገደላችሁት ፡፡ እነዳሮን ባሰቃቂ ሁኔታ በገደለበት ወቅት ግን ዝንቡን እሽ ያለው ሰው አልነበረም ፡፡ በግርማም አስታካችሁ የሕዝቡን መሠረታዊ ድርጅቶች (ቀበሌዎችን) በአሉታዊ ፕሮፓጋንዳ ዘመታችሁባቸው ፡፡ መኢሶን በወቅቱ የተቃወማችሁ ይኸንን የፀረ-አብዮተኛ አካሔዳችሁን እንጂ ግርማ ለምን ተገደለ ብሎ አልነበረም ፡፡ እናንተ ግን መኢሶን የግርማን መገደል ተቃወመ ብላችሁ ተንጫጫችሁ ፡፡

መኢሶን በፊትም ቢሆን ኅዳር 14 ቀን ፣ 1967 ዓ/ም ላይ የቀድሞ ባለሥልጣኖችንም ያለ ሕግ አግባብ ስትረሽኑ ፤ ይኸንን ግድያ አስመልክቶ ታኅሣሥ 4 ቀን ፣ 1967 ዓ/ም ባወጣው “የሠፊው ሕዝብ ድምፅ” ጋዜጣው ላይ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር ፤ “በአሁኑ ጊዜ የማናችንም ደህንነት ህልውን ህይወት አንዳችም ዋስትና የለውም ፣ በፋሽዝም ወይን ጠጅ ሰክሮ የጠነበዘ የዕብደት ዳንኪራ ይደለቃል ፡፡ እርግጠኛ አለመሆን አለመተማመን የመኖር ዋስትና ማጣት ወረርሽኝ በሀገሪትዋና በሕዝቦቿ ላይ ሠፍኗል ፡፡ ኅዳር 14/67 ሳይታሰብ ሳይጠረጠር ስድሳ ሰዎች በድንገት ተረሽነው በአንድ ጉድባ ውስጥ ዓለምበቃኝ አጥር ሥር ተቀበሩ ፡፡” ካለ በኋላ ፣ “የቀድሞዎቹ ባለሥልጣኖች ለአስቸኳይ ፍርድ ቀርበው ጥፋታቸው ተዘርዝሮ እንደየ ጥፋታቸው ወዲያውኑ መቀጣት ሲገባቸው ሰባትና ስምንት ወር አስቀምጦ በድንገት መረሸን ምን ትምህርት ይሠጣል ነው ፡፡ “ (የሠፊው ሕዝብ ድምፅ ፣ ቁጥር 16 ፣ 04/04/67 ዓ/ም እትምን ይመለከቷል)፡፡

እንግዲህ ኮሎኔል ፣ መኢሶን ይህንን ስላለ የቀድሞ ባለሥልጣኖች ለምን ተገደሉ ብሎ ተቃወመ ለማለት ይቻላል ? መኢሶን ያኔም ቢሆን የተቃወመው ባለሥልጣኖቹ ለምን ያለ ሕግ አግባብ ይገደላሉ ብሎ ነው ፡፡ ስለ ግርማ ከበደ እኔ የምለውን ካላመኑ ፣ አቶ ሠይፉ ታምራት በጦቢያ መጽሔት ቀጽ 9 ቁጥር 12 1994 ላይ ፤ “ካነሱና ከነካኩ ዘንዳ አንዳንድ ነገር ላስታውስዎት ፡፡ የአራት ኪሎው ግርማ ከበደ ከአጀማመሩ ወዴት እየተራመደ እንደሆነ በዝርዝር ከተነገሮት በኋላ ግርማ ከበደን አስጠርተው ኡዚ አስታጥቀው ከወኔ ወኔ አላብሰው አልሸኙትም ? እውን የአሥራት ወልዴ ጉዳይ ባይሆን ኖሮ ተካ ቱሉ ባሉት ብቻ ግርማ ከበደን ያስረሽኑ ነበር ?” ብለው ሊቀመንበር መንግሥቱን ይጠይቋቸዋል ፡፡ ኮሎኔል ፣ ድርጊቱ የቅርብ ጊዜ ስለሆነ መዋሸት አያዋጣም ፤ ምክንያቱም ሀቁን የምንመሰክር ሌሎች ሰለባ ከመሆን በሕይወት የተረፍን ሰዎች አለንና ነው ፡፡

 

 

lV.የሱማሌ ጦርነትና የመኢሶን አቋም

መኢሶን ዋናው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ፣ የሱማሌ መንግሥት የምዕራብ ሱማሊያ ነፃ አውጭ ፣ የሱማሊ አቦ ነፅ አውጭ እያለ እያስታጠቀ ሰርጎ ገቦችን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ማስገባት እንደጀመረ ፣ መንግሥት የአካባቢውን ሕዝብ እንዲያስታጥቅና ሕዝቡ እራሱድንበሩን እንዲጠብቅ ቢጠይቅ ሰሚ ጠፍቶ ፣ የሱማሌ ጦር ያለአንዳች ተከላካይ ድሬዳዋ ድረስ ሰተት ብሎ እንዲመጣ አደረጋችሁት ፡፡ መኢሶንም በኋላ ላይ መንግሥት ለጦርነት ሲዘጋጅ ፣ ሕዝባዊ ሠራዊቱን መልምሎ ማምጣት ብቻ ሳይሆን ፣ ካድሬዎቹ ይዘውት ከመጡት ምልምል ሠራዊቱ ጋር ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው አብረው እንዲዘምቱ አቶ ኃይሌ ፊዳ ፈቃድ መጠየቁ ይታወቃል ፡፡ መኢሶን ይህንን የጠየቀው ዘማቹ ሠራዊት ስለጦርነቱ ባህሪ ተገንዝቦ በፀረ-አብዮተኞች ፕሮፓጋንዳ ሳይወናበድ ቆርጦ በአንድ ልብ እንዲዋጋ ነበር ፡፡

እናንተ ግን የመኢሶንን መሳተፍ በመፍራት ፍቃድ ከለከላችሁ ፡፡ ይግረማችሁ ስትሉም በጦሩ ካምፕ ውስጥ የነበሩትንም የመኢሶን አባላት ከጦር ካምፑ እንዲወጡ አደረጋችኋቸው ፡፡ ይኸ እራሱ መኢሶንን ነጥሎ ከዘመቻው ማግለላችሁን አሳብቆባችኋል ፡፡ ይህን ማድረጋችሁን ደግሞ ገሥጥ ተጫኔ ፣ ሻምበል ፍቅረሥለሰሴም ሆኑ እርስዎም እራስዎ በጻፋችሁት መጸሐፍ ውስጥ ይህንን ለማድረጋችሁ በግልጽ መስክራችኋል ፡፡ መኢሶን ካድሬዎቹ ከዘማቹ ጦር ጋር አብረው ይዝመቱ ያለው ፣ ጦሩን ከአድሀሪያን ውዥንብር ለመታደግ ነበር እንጂ የናንተን ሥልጣን በመከጀል አልነበረም ፡፡ ሆኖም ግን እናንተ መኢሶንን ነጥላችሁ ከዘማቹ ጦር ጋር እንዳይዘምት በመከልከላችሁ ፣ መኢሶን እንደፈራውም ዘማቹ ሠራዊት ጦር ግንባር እንደደረሰ በአድሃሪያን ፕሮፓጋንዳ ተወናብዶ ከጦር ግንባር መሸሽ ይጀምራል ፡፡ ሀገር ወዳድ የሆኑ አዝማቾችም በፀረ-ሕዝቦች ጥይት ከጀርባቸው እየተመቱ ወደቁ ፡፡ ይኸ ሁሉ ጥፋት የማንም ሳይሆን የእነ መንግሥቱ ኃይለማርያም ለሥልጣን መስገብገብ ያመጣው ችግር ነበር ፡፡ መኢሶን የጠየቀው ተቀባይነት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ጥቃት ባልደረሰ ነበር ፡፡ ለነገሩ እናንተ ስለ ሀገር ጉዳይ ደንታቢስ ናችሁ ፡፡ የሠሜኑ ጦር ግንባር ዋና የሀገሪቱ ችግር ሆኖ እያለ ፣ በመጸሐፎ ገጽ 452 ላይ ምንድን ነው አደረግን ያሉት ? “  ለትግራይ ራስ ገዝ ግን በዚህ መስክ ማለትም በአስተዳደርም ሆነ በውትድርና ሞያ ልምድ ያልነበረው ሻምበል ለገሰ አስፋው እንዲጠቆም የፖለቲካ ቢሮ አባላቱ ውስጥ ውስጡን ቅስቀሳ ጀመሩ ፡፡ ይህም በበጎና በቅንነት አስበውበት ሳይሆን ከፕሬዘዳንቱና ከአካባቢው ለማራቅ ነበር ፡፡ “ አይደለም እንዴ ያሉት ? ይኸ የተንኮል ሥራችሁ ሀገር ይጎዳል ፣ ሠራዊቱን ያስጨርሳል ፣ የከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ሞራል ይነካል ብላችሁ እንዴት ማሰብ አቃታችሁ ? ይህን ሁሉ የምትሠሩት ስለሀገሪቷ መፃኢ ዕድል ደንታቢስ ስለነበራችሁ ነው ፡፡ መኢሶንንም ያገለላችሁት በዚሁ የተንኮል አስተሳሰባችሁ ነበር ፡፡                                                                                         ደርጉ መኢሶንን ከማግለልም አልፎ ፣ የመኢሶንን ካድሬዎች ማሰርና መግደል ይጀምራል ፡፡ ይኸንንም ታደርጉ እንደነበር እርስዎም በመጸሐፎ ገጽ 249 ላይ ፤“ ደርግም ቢሆን ኢሕአፓ ገደላቸው በማለት በነጭ ሽብር ሽፋን ተቃዋሚዎቼ ናቸው ያላቸውን አስወግዷል ፡፡ ብለው መስክረዋል ፡፡ ሁላችሁንም ልቅም አድርገን እስክንጨርሳችሁ ለምን አልጠበቃችሁንም እንደማይሉኝ ተስፋ አለኝ ፡፡ ስለዚህ ነው መኢሶን የዚህን ጊዜ ካድሬዎቹን ከተጨማሪ ጥቃት ለመታደግ ሲል ነሐሴ 14 ቀን ፣ 1969 ዓ/ም ላይ እነ አቶ ኃይሌ ፊዳን ኅቡዕ እንዲገቡ ያደረገው ፡፡   መኢሶን ቀደም ሲልም ደርጉ ከአብዮቱ በሚያፈገፍግበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ እንደሚወስድ በልሳኑ በሰሕድ ቁጥር 39 ሚያዚያ 30 ቀን ፣ 1968 ዓ/ም ኅቡዕ ከመግባቱ ከዓመት በፊት እንዲህ ሲል በግልጽ አስታውቆ ነበር ፤ “ መኢሶን በፕሮግራሙ መግቢያ ላይ እንደገለጸው ፤ ለነዚህ አበይት ዓላማዎቹና በጠቅላላው ለፕሮግራሙ ሥራ ላይ መዋል … ያለአንዳች ማወላወል ፤ በሚሥጢርና በይፋ በሕጋዊ መንገድና በሕገ-ወጥነት በሠላማዊ መንገድና በአመፅ እንደ ጊዜውና እንደሁኔታው በሚለወጥ ታክቲክ ምንም ጌዜና ምንም ሁኔታ በማይለውጠው ቆራጥነትና ታታሪነት የሚታገሉ አብዮታዊያንን አስተባብሮ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ነፃነትና አንድነት አሰልፏል ፡፡ የኢትዮጵያ ጭቁኖች የሚያደርጉትን ትግል ዳር እስከ ዳር አስተባብሮ ፤ የተጣራ አብዮታዊ አመራር ለመስጠት በጭቁን ሕዝቦችና በታሪክ ፊት የተቀበለውን አደራ እስከ መጨረሻው ይጠብቃል ፡፡ ጭቁኖች በትግላቸው እንደሚገፉ ፤ በትግል እሳት የተፈተኑ አባሎቹ አብዮታዊ ግዴታቸውን ለመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ ሙሉ ዕምነት አለው ፡፡” ብሎ ነበር (ሠረዝ የራሴ) ፡፡ ይኸንንም የመኢሶን አመራር አባሎች ኅቡዕ ሲገቡ ከደርግ  የሚደርስባቸውን አደጋ ሳይፈሩ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ በዓላማቸው በመፅናት በቁርጠኝነት በመቆም የዕምነት ፅናታቸውን አሳይተዋል ፡፡  በነኮ/ል ፍሥሐ የሚነገረውን “ደርግ ተዳክሟል ብሎ መኢሶን ጥሎን ፈረጠጠ” የሚለውን ቅጥፈት እዚሁ ላይ ላቁምና ፣ ወደ ሌሎች ወደ ተነሱ ነጥቦች ልሸጋገር ፡፡ “ ሌባ  እናት ልጇን አታምንም “ የሚባል አባባል አለ ፡፡ ስለዚህ ሌ/ኮ መንግሥቱም ፣ ሌ/ኮ ፍሥሐምተገቢውን  ሆኑ ሻምበል ፍቅረሥላሴም እነርሱ እራሣቸው እንደነገሩን ፈሪዎች ስለነበሩ የመኢሶን አመራሮችንም በነእርሱው ዐይን ነው የሚያይዋቸው ፡፡ መኢሶኖች ግን ፊሪዎች አልነበሩም ፡፡ እነርሱ ቀና ብለው ለማየት የሚፈሯቸውን ሌኮ/ል መንግሥቱን ሳይፈሩ መልስ ይሠጧቸው ነበር ፡፡ ለዚህም ነው ገሥጥ ተጫኔ “ነበር” ብለው በጻፉት የመጀመሪያ መጸሐፋቸው ፣ መኢሶን ኅቡዕ ገባ ብለው በነገሯቸው ጊዜ ፤ ከእንግዲህ የጓድ ሊቀ መንበር አመራርን የሚፈታተን ማነው የሚል ጥያቄ መጣብኝ “ በማለት እራሳቸውን የጠየቁት ፡፡ ገጽ 273ትን ይመለከቷል(ሠረዝ የራሴ)

V . መኢሶንና የኤርትራ ጥያቄ         

ሌላው መኢሶን በደርጉ የሚከሰስበት ጉዳይ የኤርትራ ጉዳይ ነው ፡፡ መኢሶን የኤርትራ ጉዳይ በሠላማዊ መንገድ የፖለቲካ መፍትሄ ይፈለግለት እንጂ ፣ ወታደራዊ መፍትሄ የለውም ብሎ ደጋግሞ ደርግን ወትውቷል ፡፡ በዚህ ጥያቄ ዙሪያም መፍትሄ ይሆናሉ ካላቸው ሀሣቦች ጭምር ብዙ ጽፏል ፡፡ እናንተ ግን መኢሶን የመከራችሁን ትታችሁ ፣ ለችግሩ መፍትሔ ያመጣል ያላችሁትን ፣ “የቀይ ኮከብ” ዘመቻን በአወጃችሁ ጊዜ  ፣ የኤርትራ ጥያቄ እስካሁን መፍትሔ ያላገኘው መኢሶን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ይፈታ ስለሚል ነበር” ብላችሁ ለሕዝብ ልታሳጡን ሞከራችሁ ፡፡ ተዉ የተባላችሁትንም ጦርነት አካሒዳችሁ በአሳፋሪ ሁኔታ ተሸነፋችሁ ፡፡ ኤርትራንም በዚሁ ጥፋታችሁ አስገነጠላችሁ ፡፡ እናንተ ከአፍንጫችሁ አርቃችሁ ስለማታስቡ መኢሶን አብሯችሁ በሚታገልበት ጊዜ ብዙ ችግሮች ይገጥሙት እንደ ነበር  አውቃለሁ ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ መኢሶን ምንም ሳይላችሁ እናንተው ተመልሳችሁ የ——- ተቆጢታ እንደሚባለው ፣ መኢሶንን ከሳሾችመሆናችሁ  ነው፡፡

Vl . መኢሶንና በራስ የመተማመን ጥያቄ                                                                               

መኢሶን ደርጉ በራስ በመተማመን ፖሊሲ መሠረት እንዲመራ ለማድረግ ሳያሰልስ ጥረት አድርጓል ፡፡ በዚህ መርህ የማይመራ ኃይል ደግሞ ዞሮ ዞሮ የሀገሩን ሉዑሏዊነት ለባዕድ አሳልፎ መስጠቱ አይቀርም ፡፡ ይህም እንዳይሆን መኢሶን ጥረት አድርጎ ነበር ፡፡ እናንተ ግን ከሥልጣናችሁ አስበልጣችሁ የሚታያችሁ ነገር ስላልነበር የመኢሶንን ምክር ልትሰሙ ፍቃደኛ አልነበራችሁም ፡፡ ሌ/ኮ ፍሥሐ ፣ ለመሆኑ መኢሶን  የሀገሪቷን ሉዐሏዊነት እንድታስከብሩ ገና ከጠዋቱ ምን ነበር የመከራችሁ ?

የካቲት 20 ቀን ፣ 1969 ዓ/ምላይ ባወጣው  ልሣኑ “የሠፊው ሕዝብ ድምፅ” ቁጥር 52 ላይ ፣ ” ከአብዮቱ ፊት የተደቀኑት ችግሮች የትኞቹ ናቸው ? “ ብሎ ከጠየቀ በኋላ ፣በሦስተኛ ደረጃ የሚያቀርበው የሱማሌን ችግር ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ ሱማሊያ ሰርጎ ገቦችን እያስታጠቀች በኦጋዴን ፣ በባሌና በሲዳሞ በኩል አሰርጋ ወደ ኢትዮጵያ እንደምታስገባ አስታውቆ ፣ ሐ- በሚለው ሆሄ ሥር የሚከተለውን ምክር ሰንዝሮላችሁ ነበር ፤ “በአብዮቱ ፕሮግራም በተጠቀሰው መሰረት ፣ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ክብሯንና ነፃነትዋን በምንም  መንገድ ሳታስነካ ፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረቱ ግንኙነቶችን ከውጭው ዓለም ጋር መፍጠር ይኖርባታል ፡፡ አብዮቱ ስለተከበበና በብዙ ችግሮች ውስጥ ስለገባን የአገራችንን ክብርና ነፃነት ለምንም አይነት ጊዜያዊ ጥቅም መሸጥ የለብንም “ ብሎ መክሮ አልነበረም ?

እናንተ ግን ለምክሩ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላችሁ ኢትዮጵያ ሶቭየት ሕብረትን ሳታስታውቅ ከሌላ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳታደርግ የሚያግድና የሀገሪቷን ሉዐላዊነት የሚፃረር የውጫሌን ውል የሚመስልከሶቪዬት ሕብረት ጋራ ለ20 ዓመት ፀንቶ የሚቆይ ውል በኅዳር ወር 1971 ዓ/ላይ ተዋውላችሁ አረፋችሁት ፡፡ይኸም ብቻ አይደለም ፤ ሀገሪቷ በዓለም አንቱ በተባሉ የጦር ትምህርት አካዳሚዮች ያሠለጠነቻቸው ፣ ማለትም በእንግሊዙ ሳንድህረስት ፣ በፈረንሣዩ ሳንሲር ፣ በአሜሪካኑ ዌስት ፖይንት ወዘተ. ያሰለጠነቻቸው የራስዋ የጦር መኮንኖች እያሏት፣ እናንተግን ሠራዊታችን የራሱ የጦር መኮንኖች የሌለው ይመስል በሶቭዬትና በኩባ የጦር መኮንኖች እንዲመራ አላደረጋችሁም ? ይኸ የሀገር ክዳታችሁ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን የጦር ልምድ ያላቸውንና የሀገራቸውን መልካምድር ጠንቅቀው የሚያውቁትን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ሞራል አልገደለም ይላሉ ? የኩባና ሶቪዬት ሕብረት ጦር አዛዦች ባልነበሩበት ወቅት አይደለም እንዴ የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች የኤርትራ ግንባሮችን ገትረው ሲከላከሉ የነበሩት ? መኢሶን በራስ የመተማመንን አስፈላጊነት አብዝቶ የወተወታችሁ ይኸ ሁሉ እንዳይደርስ በማሰብ ነበር ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ምክሩ ሰሚ ጆሮ አላገኘም ፡፡ አሁንም ድረስ የመኢሶን ምክር የገባችሁም አይመስለኝም ፡፡ ምክንያቱም አሁንም መኢሶን ይቅር በለን ስትሉ ሳይሆን የምሰማው ፣ ስትወነጅሉት ነው የማየው ፡፡

Vll .መደምደሚያ

መኢሶን መቸም ለሀገሩ ታላቅ ራዕይ የነበረው አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት ነበር ፡፡ ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች  የተሻለ የተማረ የሰው ኃይል ያሰባሰበ ድርጅት እንደነበረ የሚጠሉት እንኳን ሳይቀሩ መመስከር ተገደዋል ፡፡ ሌ/ኮ ፍሥሐ ፣ እርስዎ እንደሚሉት መኢሶን በዚያን በክፉ ቀን አብዮቱን ጥሎ አልፈረጠጠም ፣ ሀገርንም አልከዳም ፡፡ መኢሶን ከናንተ ከተለየ በኋላም በሂሳዊ ድጋፉ ትግሉንከሠፊው ሕዝብ መሀል ሆኖ ቀጥሏል ፡፡ ለዚህም ሕያው ምስክሩ በ1970ዎቹ ከናንተ ጥቃት እራሱን እየተከላከለ በልሣኑ ያወጣቸው የነበሩት ጽሁፎች ናቸው ፡፡ ዕውነቱን ለመናገር ከአብዮቱ የፈረጠጣችሁት እናንተው እራሣችሁ ነበራችሁ ፡፡ ሀገርም የከዳችሁ እናንተው እራሣችሁ እንጂ መኢሶን አልነበረም ፡፡ ከአብዮቱ ፈረጠጣችሁ የምላችሁ ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሥልጣን አስረክባችሁ ወደ ጦር ካምፓችሁ ልትመለሱ ሚያዚያ 13 ቀን ፣ 1968 ዓ/ም ቃል ኪዳን በአዋጅ የገባችሁበትን “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን” አሽቀንጥራችሁ ጥላችሁ ፣ የሲቪልና ወታደራዊ ቢሮክራቶችን አቅፋችሁ ሥልጣን ላይ ጉብ በማለታችሁ ነው ፡፡ ሀገር ከዳችሁ የምላችሁ ደግሞ ፣ መኢሶን ፣ለመናኛ ጥቅም ብላችሁ የሀገሪቷን ሉዐሏዊነት አደጋ ላይ እንዳትጥሉ ብሎ ቢመክራችሁም ፣ እናንተ ግን አሻፈረኝ ብላችሁ ኢትዮጵያን ለ 20 ዓመት የሶቭዬት ሕብረት ጥገኛ በማድረጋችሁ ነው ፡፡

የሚገርመው ደግሞ በጠራራ ፀሐይ ሀገር ከድተው ፣ በጦር ግንባር ያሰማሩትን ሠራዊት በትነው ፈርጥጠው ዚምባብዌ የገቡትን ግለሰብ ፣ በመጸሐፎ ውስጥ “ፕሬዝዳንቱ ወደ ስደት አመሩ” ሲሉ ፣ ከሀገር ያልወጣውንና እራሱን ከእናንተ እንጂ ከትግሉ ያላገለለውን መኢሶንን እኛን ጥሎ ወደ ገበሬው ዘንድ ሔደ ብለው በመቆጨት ፣ “ ሀገር የከዳና ከአብዮቱ የሸሸ “ ማለትዎ ነው፡፡ ይህ በመኢሶን ላይ ያለዎትን ክፍተኛ ጥላቻ እንዳሎት ከሚያንፀባርቅ በቀር ምንም ዕውነትነት የለውም ፡፡

ሌላው የገረመኝ ነገር በመጸሐፎ በገጽ 220 ላይ ፣ የመኢሶን ሰዎች  “ እያለከለኩ መጡ “ ያሉት ነው ፡፡ ጥላቻዎን ለመግለጽ ካልሆነ በቀር አለከለከ የሚለው ቃል ለውሻ እንጂ ለስው ልጅ መገለጫ አይሆንም ፡፡ የመኢሶን አመራሮች በሩጫው መድከማቸውን ለመግለጽ ፈልገው ከሆነ ፣ ቁና ቁና እየተነፈሱ መጡ ለማለት ይችሉ ነበር ፡፡ ጥላቻዎ ግን ይህንን ለማለት አላስቻሎትም ፡፡ ይህም እንግዲህ የትረካዎ ማጣፈጫ እንጂ ሀሳዊ መሆኑን ወደ ጎን ትቼ ነው፡፡

የመኢሶን አመራር አባሎችን እስከማውቃቸው ድረስ ከእናንተ በሁሉም እረገድ እጅግ ይገዝፉብኛል ፡፡ የመኢሶን ሰዎች እንደ እናንተ አብዮቱ ከየጦር ክፍላችሁ አግበስብሶ  እንዳገናኛችሁ የተገናኙ ግለሰቦች ሳይሆኑ በዓላማ ዙሪያ ተሰባስበው ለሀገር ይበጃል ያሉትን ፕሮግራም ነድፈው ለረጅም ዓመታት ለመጪው የኢትዮጵያ አብዮት ጥርጊያ ጎዳና በማዘጋጀት ሥራ ላይ የተጠመዱና አንቱ የተባሉ ምሁራን ነበሩ ፡፡ የመኢሶን አመራር አባሎች ፣ በኢትዮጵያ የየካቲት ሕዝባዊ አመጽ ከመጀመሩ ከእረጅም አመታት በፊት ጀምረው አብዮቱ የደከሙበት ጉዳይ ስለነበረ ፣ ለሥልጣን ጓጉተው እንደ እናንተ አብዮቱን ለማኮላሽት ፍቃደኛ አልነበሩም ፡፡ ይህም አቋማቸው ሊያስገርመን አይገባም ፡፡ አቶ ኃይሌ ፊዳ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዐት ተቃዋሚ ነው ተብሎ ፓስፖርቱን ሲነጠቅ ዶ/ከበደ መንገሻ ደግሞ አንቱ የተባለ ምሁር ቢሆንም ቅሉ የግል ሕይወቱን ወደ ጎን በማድረግ ሲቸግረው ዘበኝነት እየተቀጠረ ፣ “ትግላችንና ታጠቅ” የተባሉትን በአውሮፓ የኢትዮጵያ የተማሪው ማኀበር መጽሔቶችን ያለአንዳች ክፍያ ጣቶቹ በፊደላት ስለት እየተተፈተፉ ለመጭው የኢትዮጵያ አብዮት ጥርጊያ ጎዳና በማዘጋጀት ላይ የተጠምደ ምሁር ነበር ፡፡ በዚህ ስብእናቸውም ብዙ ወጣቶችን ለሀገር ተቋርቋሪ አድርገው ኮትኩተው አሳድገዋል ፡፡ ከነዚህም ወጣቶች መሀል አንዱም እኔ በመሆኔ እኮራለሁ ፡፡

የመኢሶን አመራር አባሎች ለአብዮቱ ቅድመ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ሌ/ኮ መንግሥቱም ሆኑ ፣ ወይም ደግሞ ሻምበል ፍቅረሥላሴና ሌ/ኮ ፍሥሐ ደስታ ፣ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዐት እንዳይወድቅ ተንከባካቢዎች ነበሩ ፡፡ ደርጎቹን የፖለቲካ ስው ያደረጋቸው የኢትዮጵያ አብዮት እንደነበረ መዘንጋት የለበትም ፡፡ የእናንተ ጉድ ተጽፎ ስለማያልቅ ገበሬ ነው የፈጃቸው እኛ አልነካናቸውም የምትሉትን ቅጥፈት በተመለከተ ዕውነቱን ልንገሮትና ልሰናበት ፡፡ ኮሎኔል ፣ ለምን እጃችሁ ላይ ያለውን የንፁሀን ደም ገበሬው ላይ ለመለቅለቅ ትፈልጋላችሁ ? ገበሬው ፣ የመኢሶንን የአመራር አባሎች ፣ እናንተ እጅ እንዳይወድቁ ጎጆው ውስጥ ደብቆ የሚበላውን እያበላ ፣ የሚጠጣውን እያጠጣ አስቀመጣቸው እንጂ እናንተ እንደምትሉት አልገደላቸውም ፡፡ ጫንጮም ሆነ አምቦ የነበሩትን የመኢሶን ሰዎች ተወርዋሪ ጦር ልካችሁ የፈጃችኋቸው እናንተው ናችሁ ፡፡ ከንባታና ሀድያም የነበሩትን ከእስር ቤት እያወጣችሁ ነው የገደላችኋቸው፡፡ በሌሎች አካባቢ የነበሩትንም እናንተው ናችሁ እንጂ የዘመታችሁባቸው ፣ ገበሬው ዝንባቸውን እንኳን እሽ አላለም ፡፡ ለዚህ ሕያው ምሥክሮች የሆንን አሁንም በሕይወት የተረፍን አለን ፡፡ ምሥክር የለም ብለው አይዋሹ ፡፡

ገበሬውማ ሜዳ ላይ ጥላችሁት የሔዳችሁትን አስከሬናችንን ሰብስቦ በሥርዐቱ ቀበረ ፡፡ በመኢሶን ጦስ ገበሬው ተባባሪ ተብሎ ከመኢሶኖች ጋር አብሮ በስር ቤት ፍዳውን በልቷል ፡፡ ይኸንን ሀቅ የስር ቤታችሁ መዝገብ አስፍሮት ይገኛል ፡፡ እረስተውት ነው እንጂ ፣ በ1970 ዓ/ም መኢሶኖች እንደወጡ የአዲስ አበባ የቀበሌ ማኀበራትና የአዲስ አበባ ዙሪያ የገበሬ ማኀበራት በአዲስ አበባ ተሰብስበው መኢሶንን በመደገፍ ውሳኔም አሳልፈው ነበር ፡፡ እርስዎ ግን ይኸንን ሁሉ “እረስተው” መኢሶኖችን ገበሬው ፈጃቸው ይላሉ ፡፡ አለቃዎም ኃይሌ ፊዳን ገበሬው ነው የገደለው ብለዋል ፡፡

ኮሎኔል ፣ ለጥፋቱ ይቅርታ የሚጠይቅ ሰው መዋሸት አለበት ይላሉ ? ወይንስ እርስዎም እንደ አለቃዎ ኃይሌን ገበሬው ነው የገደለው ባይ ኖት ? እስቲ አምቦ የነበሩትን የመኢሶን አባሎች እንዴት እንደገደላችኋቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና “ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች ከተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ “ ብለው ባሳተሙት መጸሐፋቸው ገጽ 87 ላይ ያሰፈሩትን ላስነብቦት ፤ ”

እራሱን ስቶ የነበረውን ወንድሜንና ረዳቱን ይዘው የዛኑ ሌሊት ጉዴላ የምትባለውን የቶኬ አካባቢ ከተማ የዘመቻ ማዕከል አድርገው ተንቀሳቀሱ ፡፡ ይህ ካሳየ አራጋው በተባለው የደርግ አባል የተመራው ዘመቻ ፣ አንድ የኮማንዶ ቡድን እነዶ/ር ተረፈ ወዳረፉበት የአጎታችን ቤት ይልካል ፡፡ እነ ዶ/ር ተረፈ ባልጠበቁት ሠዐት መከበባቸውንና ማንገራገር ቢመክሩም ከኮማንዶ ጋር ለመዋጋት የሚያሥችላቸው አቅም ስላልነበራቸው እጃቸውን ይሠጣሉ ፡፡ ከተያዙበት ቦታ አንድ ኪሎ ሜትር እንደሔዱ የተኩስ እሩምታ ተከፍቶባቸው ተጨፈጨፉ ፡፡ መንገድ የመራቸው የወንድሜ ረዳት መገደላቸውን አይቶ በመጮሁ እሱንም እዛው ጨመሩት ፡፡ በዚህ ፋሽሽታዊ ጭካኔ በዕለቱ የተጨፈጨፉት፤

1.ዶ/ር ተረፈ ወልደፃዲቅ የትምህርት ሚኒስቴር

  1. ከበደ ዲሪባ ፣ የሸዋ ክ/ሀገር የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ

3.ኢዮብ ታደሰ

4.ለማ ፊዳ

5.ሽመልስ ኦላና                                                                                                                                                          6.መራዕድ ከበደ

7.አሰፋ ነመራ

8.ዲማ ጉዲና ፣ ታላቅ ወንድሜ

9.ኩመላ ከሮርሣ

10.አጥናፍ ይማም ፣ የዶ/ር ተረፈ ባለቤት ነበሩ ፡፡

አጥናፍ ጥይት ብቻ ነው የሚለየኝ ብላ ወደከተማ ልንመልሳት ያደረግነውን ጥረት እምቢ ብላ ያለችንና በመጨረሻም ጥይት ሊለያት ያልቻለ ተጋይ ሴት ነበረች ፡፡ አጥናፍ አራስ ልጅዋን ጭምር ትታ ጫካ የገባች ሴትም ነበረች ፡፡

ኮሎኔል ፣ ሻለቃ ካሳዬ አራጋው የሚባል ገበሬ የደርግ አባል ነበር ነው የሚሉኝ ? በከምባታና ሀዲያስ የነበሩት የመኢሶን አባሎች ፣ ማለትም ዶ/ር ንግሥት አዳነ ፣ አቶ ደስታ ታደሠ (የዶ/ር ንግሥት ባለቤት ) ፣ አቶ ኤፍሬም ዳኜ ፣ አቶ ኃይለሥላሴ ወ/ገሪማ ፣ አቶ በለጠ ሙቱሮና አቶ ለገሠ የተባለውን ገበሬ ጨምሮ ፣ አዲስ አበባ ድረስ አምጥታችሁ አይደለም እንዴ ፣ ዶ/ር ንግሥት አዳነንና ባለቤቷን አቶ ደስታ ታደሠን ከስር ቤት አውጥታችሁ የገደላችኋቸው ፡፡ ጫንጮስ የነበሩትን የመኢሶን አባሎች ዶ/ር ከበደ መንገሻን ፣ አቶ ዳንኤል ታደሰን ፣ አቶ ምትኩ ተርፋሳን ፣ አቶ ደንቢ ዲሣሣንና አቶ ዳንኤል (የትግል ሥም ነው) የተባሉትን ከአዲስ አበባ የተላከው የኮማንዶ ቡድናችሁ አይደለም እንዴ ሜዳ ላይ የፈጃቸው ?

እነ አቶ ኃይሌ ፊዳን ፣ ገበሬው ከአዲስ አበባ ጦር መላኩን ነግሯቸው ስለነበር በሌላ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ኬላ ላይ በጥርጣሪ ይያዛሉ ፡፡  በተያዙበት ወቅትም ብዙ ሕዝብ አይቷቸው ስለ ነበር ፣ እንደነ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ሊረሽኗቸው አላመቻቸውም ፡፡ የደርጉ የዘመቻ ቢሮ እነ ኃይሌን ሊረሽናቸው ፈልጎ ፣ ቁጥጥር ሥር አውሏቸው ለነበረው አካል ፣ “ ሲያዙ ሰው አይቷቸዋል ወይ ? “ ብሎ ሲጠይቅ ፣ ከአሳሪው ክፍል የተሠጠው መልስ ፣ አዎን ብዙ ሰው አይቷቸዋል የሚል በመሆኑ ከመረሸን ተረፉ ፡፡

ኮሎኔል ፣ ይኸንን ሁሉ የምነግርዎት በወቅቱ ያደረጋችሁትን ያጡታል ብዬ ሳይሆን ፣ እኛም የፈጸማችሁትን ወንጀል እናውቅ እንደነበረ ለማሳወቅ ብዬ ነው ፡፡ ከኢሉ አባቦራ (ኤሉባቦር) የያዛችኋቸውን የመኢሶን ካድሬዎች ፣ አዲስ አበባ አምጥታችሁ እስር ቤት ስታጉሯቸው ፣ ዶ/ር ከድር መሐመድን ግን መልሳችሁ መንገድ ላይ ገደላችሁት ፡፡ ወለጋ ይገኙ የነበሩትን የመኢሶን ካድሬዎችም እንዳለ አዲስ አበባ እስር ቤት ነው አምጥታችሁ ያጎራችኋቸው ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ኃይሉ ገርባባን አውጥታችሁ ገደላችሁት ፡፡ ሲዳሞ ይገኙ ከነበሩት ደግሞ ግርማ ሥዩምና ጋሻው ታደሠ እጃቸውን ቀደም ብለው ለመንግሥት ሲሠጡ ፣ አንዳርጋቸው አሰግድ ፣ አበራ የማነአብ ፣ ዳዊት አሰፋና ሌሎቹ ሲተርፉ ፣ መስፍን ካሱን ይዛችሁ አዲስ አበባ በማምጣት እንደምትገሉት እያወቃችሁዐይኑን አጥፍታችሁ ካሰቃያችሁት በኋላ ገደላችሁት ፡፡

እንግዲህ አለቆቾም እርስዎም ገበሬ ፈጃቸው የምትሏቸው ምሁራን እነዚሁ ናቸው ፡፡ ለመሆኑ ኮሎኔል ፣ ከልቡ አጥፍቻለሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ የሚል ሰው መዋሸት አለበትን ? ለማንኛውም እንደናንተው ለወሬ ነጋሪ ከመኢሶንም ወገን በሕይወት የተረፍን እንዳለን ፣ ወደፊት ስትጽፉ አትዘንጉ ፡፡ በመሣሪያ ገድላችሁናል ፣ በብዕር ግን አትገድሉንም ፡፡ እናንተ ያኔ እኛን ስትፈጁ የሚታያችሁ የነበረው የተማረውን ክፍል አስወግዳችሁ ሥልጣን ያለ ተቀናቃኝ መጨበጣችሁን ብቻ ነው እንጂ፣ ሀገሪቷንና አብዮቱን ይዛችሁ ገደል መግባታችሁ አልታያችሁም ፡፡ሌላው የገረመኝ ነገር ደግሞ መኢሶንን በሥልጣን ጥመኝነት የምትከሱ ሰዎች ፣ ሥልጣን ሊቀናቀነን ይችላል ብላችሁ የገመታችሁትን ኃይል ሁሉ ካጠገባችሁ በመግደልና በማሰር ካገለላችሁ በኋላ ፤ በእናንተው መሀል የሥልጣን ሽኩቻው መቀጠሉ ነው ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እርስዎ በመጸሐፎ ገጽ 322 ላይ ፤ “የሥራ አስፈጻሚው አንድ የፖለቲካ ቢሮ ሆኖ የሚሠራና ሰባት አባላት ብቻ ያቀፈ እንደሚሆን ጥናቱ በሂደት ላይ እያለ በመታወቁ ከአስራ ሶስቱ የደርጉ ቋሚ ኮሚቴ አባላት መካከል እነማን ይመረጡ ይሆን በሚል በቋሚ ኮሚቴ አባላት መካከል የሥልጣን ሽኩቻ ተፈጠረ ” አይደለም እንዴ ያሉን ፡፡

እንግዲህ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ፣ የሥልጣን ጥመኛው ማን ነው ይላሉ ? መኢሶን ወይስ እናንተ ? በኋላስ ላይ መድበለ ፓርቲ ልታቋቁሙ ሚያዚያ 13 ቀን ፣ 1968 ዓ/ም ለሕዝብ ቃል የገባችሁበትን ፕሮግራም ትታችሁ ፣ ብቸኛውን ፓርቲያችሁን  መሥርታችሁ ካበቃችሁ በኋላ ዝሆን ፣ አንበሳና ጎሽ ነን ተባብላችሁ ለምርጫ “ስትወዳደሩ” ምንድን ነበር የሠራችሁት ? ሕዝቡ ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ እያለ የምርጫ ቀኑን ቢጠብቅም ፣ እናንተ ግን ይኸንንም ዕድል ሕዝቡን በመንፈግ ዝሆን ብቻ ነው መመረጥ ያለበት ብላችሁ አረፋችሁት ፡፡

እስቲ ልጠይቆት ፤ ገጽ 348 ላይ ፤ “ የኢትዮጵያ መንግሥት የደህንነት ሚኒስትሩ ኮ/ል ተስፋዬ ወ/ሥላሴ የአሜሪካን መንግሥት የደህንነት ሠራተኛ ነበሩ ብለውናል ፤ ይህንኑም ለሌኮ/ል መንግሥቱ አስታውቄም ነበር ብለዋል ፡፡ መንግሥቱ ግን ጉዳዩን ቀደም አድርገውም ያውቁ ነበርና ዝም አሉኝ ብለዋል ፡፡ “ ኮሎኔል ፣ሊቀመንበር መንግሥቱስ ዝም በማለት ከአሜሪካንና ከኮ/ተስፋዬ ጋር ሆነው የዚምባብዌ መኖሪያቸውን አመቻቹበት እንበል? እርስዎ ግን የኢትዮጵያን ደህንነት ለአሜሪካን አሳልፎ የሚሠጥ ቁልፍ ባለሥልጣን መሀላችሁ መኖሩን ካወቁ በኋላ ፣ ሌላ እንኳን ማድረግ ባይደፍሩ ከሀገር ወጥተው ሲያበቁ ለምን ሚሥጥሩን ይፋ አላወጡም ? ይኸም ይቅር እንበል ፣ ለምን የ1981ዱን መፈንቅለ መንግሥት ተግተው ለማክሸፍ ተንቀሳቀሱ ? ይኸንን ዕውነታ ካወቁ በኋላ ሊቀመንበር መንግሥቱ በአብዮቱ ወደፊት ሳይሆን የሚሔዱት ወደ ኋላ እየተመለሱ እንደሆነ እልታይዎትም ? የሀገሪቷን የደህንነት ቢሮ ለአሜሪካኖች ክፍት አድርጋችሁ አይደለም እንዴ ሠራዊቱን ስታስጨፈጭፉት የነበራችሁት ? በዚች ሀገርና ሕዝብ ላይ የፈጸማችሁት ወንጀል ከ – እስከ አይባልም ፡፡ እናንተ ግራ እጃችሁን እየሠቀላችሁ ፣ ከጓድ ሊቀመንበር አመራር ጋር ወደፊት በምትሉበት ወቅት ፣ መሪያችሁ ልትከተሏቸው ወደማትችሉበት ሀገር ጉዟቸውን ያዘጋጁ እንደ ነበር አልተገነዘቡም ፡፡ ለአሜሪካን እምፔሪያሊዝም የሀገሪቷን ሚስጥር ክፍት ያደረጋችሁ ፍጡሮች በምን የሞራል ብቃት ነው መኢሶንን ከአብዮት የሸሸና ሀገር የከዳ ለማለት የምትችሉት ?                                                                    ሌ/ኮ ፍሥሐ ፣ እንግዲህ መኢሶን አስቀድሞ መደረግ ያለበትን ነገር ከመምከር ባለፈ ምን ሊያደርግ ይችላል ይላሉ ? ለማንኛውም ጽሑፌን የናንተው የሞያም ሆነ የፓርቲ ባልደረባ በነበረው በገሥጥ ተጫኔ “ነበር” ብሎ በሰየመው መጸሐፉ ገጽ 275 ላይ ስለ መኢሶን በሠጠው የምስክርነት ቃል ልዝጋው ፤ “ መኢሶን በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ / ቤት መቋቋም ሰበብ ከደርግ ጋር ከተወዳጀበት ጊዜ አንስቶ ከሞላ ጎደል ለሁለት ዓመት ያህል ለአብዮቱ ሂደት መቃናት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን አውቃለሁ ፡፡ ለምሣሌ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም እንዲወጣ ፤ የአብዮቱ ወገኖች ነቅተው በየፈርጃቸው ተደራጅተውና ታጥቀው እንዲታገሉ ፣ የኤርትራ ጉዳይ በውይይት መድረክ እንዲፈታ ጥረት ካደረገባቸው ብሔራዊና አብዮታዊ ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ እንደነበሩ አስታውሳለሁ “ ነው ያሉት ፡፡ አዩት ኮሎኔል ፣ ገሥጥ ከኛ ጋር የአቋም ልዩነት ቢኖራቸውም ቅሉ ፣ ቀና ሰው በመሆናቸው የተነሣ ዕውነቱን ለመመሥከር በቅተዋል !!! ለእናንተም የእርሳቸውን ልቦና እንዲሠጣችሁ ነው ምኞቴ ፡፡ በተረፈ “ ከመጠምጠም መማር ይቅደም “ ያሏት አባባል ተስማምታኛለች ፡፡ ምክንያቱም አባባሏ በእናንተና በመኢሶን አመራር መካከል የነበረውን ልዩነት ፍንትው አድርጋ ታሳየኛለች ፡፡ የመኢሶን ሰዎች ተምረው የጠመጠሙ ሲሆኑ ፣ እናንተ ደግሞ ሳትማሩ የጠመጠማችሁ እንደነበራችሁ ግልጽ ነውና ፡፡ ኮሎኔል ፣ በመጸሐፎ ገጽ 5 ላይ ፤ “ ከሰው ስህተት አይጠፋምና መጽሐፉን በሚገባ አንብበው በጭፍን ሳይሆን በገንቢ መልኩ የሚሰጡትን ማንኛውንም አስተያየትና ሂስ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ፡፡ “ ያሉትን ሳነብ ፣ በጥላቻ የተነሣ ስሜታዊ ሳይሆኑ ለአንባቢ አሁን ካቀረቡልን የተሻለ መረጃ ያቀርቡልናል ብዬ ገምቼ ነበር ፡፡  መኢሶንን በተመለከተ ከመጸሐፎ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ፣ ስህተት ሳይሆን የፈፀሙት ሆን ብለው ከጥላቻ ተነስተው የሥም ማጥፋት ዘመቻ ነው ያካሔዱበት ፡፡ በተረፈ “ ከመጠምጠም መማር ይቅደም “ ያሏት አባባል ተስማምታኛለች ፡፡ ምክንያቱም አባባሏ በእናንተና በመኢሶን አመራር መካከል የነበረውን ልዩነት ፍንትው አድርጋ ስለምታሳይ ፡፡ በዚሁ ልሰናበት ፡፡

 መርድ  ከበደ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles