Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የክቡር ሚኒስትሩ ከብስጩ ሚስታቸው ከዲያስፖራው ከሹፌራቸው እና ከአማካሪያቸው ጋር ተወያዩ::

$
0
0

የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ተበሳጭተዋል  

Birhane Gebrechristos
ብርሃነ ገብረክርስቶስ

– ምን ሆነሻል?
– ምን ሆንኩ?
– ፊትሽ የጠቋቆረው::
– ለምን አይጠቁር?
– እኮ ምን ሆነሻል?
– ተያዘ::
– ያ ሱቅ?
– ክፈል ክፈል ብዬ ስንቴ ነው የነገርኩህ?
– እና ሱቁ ተያዘ?
– ሱቁማ ቢሆን የተሻለ ነበር::
– እና ሱቁ አልተያዘም?
– እኔ ስለሱቁ አይደለም የማወራህ::
– እና ምኑ ነው ተያዘ የምትይው?
– አዳራሹ ነዋ::
– የምን አዳራሽ?
– የእህቴ ልጅ ሠርግ መድረሱን ረሳኸው?
– ደረሰ እንዴ?
– አንተ ምን ሐሳብ አለብህ?
– የማላስበውን ብጠይቂኝ ይሻላል?
– እኮ ምን ታስባለህ?
– ስለዚች አገር ነዋ::
– ይቺን አገር ስለመቦጥቦጥ?
– ይህቺን አገር ስለማልማት ነው እንጂ::
– ራሴን ስለማልማት ነው ያልከኝ?
– እውነትም ተናደሻል ማለት ነው?
– እንዴት አልናደድ?
– አታስቢ::
– ጤንነትህን ግን መጠራጠር ጀምሬያለሁ::
– ለምንድን ነው የምትጠራጠሪው?
– የሠርጉ ወረቀት እኮ ተበትኗል::
– ይበተና ምን ችግር አለው?
– ወረቀቱ ላይ የተጻፈው አዳራሽ ለሌላ ተከራየ እያልኩህ እኮ ነው::
– ያ ሆቴል አይደል እንዴ?
– አዎን ነው::
– ባለሆቴሉ እኮ ልማታዊ ነው::
– ቢሆንስ ታዲያ?
– በአንድ ስልክ ነዋ የምጨርሰው::
– ምኑን?
– የእኛ ሠርግ እዛ እንዲሆን::
– እኛ እኮ ስላልከፈልን ነው ለሌላ ሠርግ ያከራዩት::
– አንድ ነገር አትርሺ::
– ምን?
– የእኛ ሠርግ ልማታዊ ነው::
– እ…
– እኛ የተከራየነውን አዳራሽ ለመከራየት የፈለጉት ደግሞ…
– ምን?
– ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው::
– እኛ እኮ ስላልከፈለን ነው እነሱ የከፈሉት::
– አየሽ ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆናቸውን የምታውቂው ቀድመው ሒሳብ በመክፈላቸው ነው::
– አንተ እውነትም ለይቶልሃል::
– ለማንኛውም አታስቢ::
– ለምን አላስብ?
– እኔ እጨርሰዋለሁ::
– እኮ እንዴት?
– ሆቴሉን ተቆጣጥሬዋለሁ::
– እ…
– 100 ፐርሰንት:: [አንድ ዳያስፖራ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለ]
– ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እንዴት ናት?
– እየተመነደገች ነው::
– ኧረ የምሰማው ነገር አሳስቦኛል::
– ምን ሰማህ?
– ይኸው ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ
ተከስቷል::
– እኛ ምን እናድርግ ታዲያ?
– ሐዋሳ ላይም መሬት መንቀጥቀጥ እንደነበር ሰምቻለሁ::
– ይህ እንግዲህ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው::
– ሰሞኑን ደግሞ በማኅበራዊ ድረ ገጽ የምሰማው ጉድ ነው::
– በየማኅበር ቤቱ አለመሄድ ነዋ::
– ኧረ እኔ ፌስቡክን ማለቴ ነው::
– ፌስቡክ እኮ የወሬኞችና የሥራ ፈቶች ነው::
– አይ ክቡር ሚኒስትር አሁን አሁን እኮ ጥሩ የመረጃ ምንጭ ሆኗል::
– ለመሆኑ ምን ሰምተህ ነው?
– ይኸው ድሬዳዋ ዓሳ ዘነበ እየተባለ ነው::
– ለምን ይመስልሃል የዓሳ ሚኒስቴር ያቋቋምነው?
– እ…
– ይኼ እንደሚመጣ ቀድመን አውቀን ነበር::
– እየቀለዱ ነው?
– የምን ቀልድ ነው? በዕድገት ቀልድ የለም::
– የምን ዕድገት?
– ይኼ የህዳሴያችንና የዕድገታችን ውጤት ነው::
– እንዴት ሆኖ?
– ገና ወርቅ ይዘንባል::
– ወርቃችንማ ተጠርጐ እየተወሰደ ነው::
– ምን አልክ አንተ?
– ሰምተዋል::
– ለማንኛውም ይኼ ዜና ሊያስደስትህ ይገባ ነበር::
– የእግዚአብሔር ቁጣ ነው እኮ ይኼ::
– ይኼማ ቁጣ ሳይሆን ደስታ ነው እንጂ::
– እንዴት ሆኖ?
– መጽሐፍ ቅዱስ አታነብም እንዴ?
– አነባለሁ ኧረ::
– ታዲያ እግዚአብሔር ለእስራኤሎች በየቀኑ መና ያዘንብላቸው ነበር እኮ::
– አዎን እሱን አውቃለሁ::
– መና የሚያዘንብላቸው ስለሚወዳቸው ነበር::
– ልክ ነው::
– ይኸው በእኛም ዕድገት በጣም በመገረሙ ዓሳ ማዝነብ ጀመረ::
– እና እግዚአብሔር ዓሳ ያዘነበው በዕድገቱ ተገርሞ ነው::
– በእኛ ዕድገት ብዙ ነገር ይዘንባል::
– ብዙ ነገር መዝነቡንማ አውቃለሁ::
– ማለት?
– የወጣቶች ሊግ፣ የሴቶች ሊግ…
– እ…
– የወጣቶች ፎረም፣ የሴቶች ፎረም፣ የባለሀብቶች ፎረም…
– እያሽሟጠጥክ ነው::
– በእናንተ ጊዜ ያዘነባችኋቸውን ነገሮች እየነገርኩዎት ነው እንጂ::
– ወሬኛ ነገር ነህ::
– ይኸው ሰሞኑን ደግሞ ሌላ ነገር ማዝነቡን ተያይዛችሁታል::
– ምን?
– ደላላ! [ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]
– ስብሰባው አለቀ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
– የምኑ ስብሰባ?
– የመሪዎቹ ስብሰባ::
– ተሸኙ እኮ ወደ አገራቸው::
– መቼም ጥሩ መዝናኛ ነው::
– ምኑ ነው መዝናኛው?
– ስብሰባው ነዋ::
– እንዴት ማለት?
– ያው በዓመት አንዴ ለሳምንት በደንብ
ተዝናንተው ይሄዳሉ::
– አትሳሳት::
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– ሲጀመር ስብሰባው በዓመት አንዴ ሳይሆን ሁለቴ ነው::
– ያው ሁሌ በዚህ ሰሞን ነው የሚመጡት ብዬ ነው::
– ሁለተኛው ደግሞ አንዱ የአፍሪካ አገር ነዋ የሚካሄደው::
– እናንተም በተራችሁ እንድትዝናኑ?
– ምን ይላል ይኼ? መዝናናት ሳይሆን ሥራ ነው::
– እሱን እንኳን ተውት::
– እንዴት ማለት?
– ሰሞኑን አይደል እንዴ ጉዱን ያወቅኩት?
– አልገባኝም::
– ለሳምንት ዕረፍት የወጣሁት የአንዱ ዲፕሎማት ሾፌር ለመሆን ነበር::
– እሺ::
– በቃ የአዲስ አበባ ጭፈራ ቤት አንድ አልቀረኝም::
– እ…
– ክቡር ሚኒስትር አዲስ አበባን አውቃታለሁ ብለው ያስባሉ አይደል?
– በሚገባ እንጂ::
– እኔ ግን እንደማያውቋት እነግርዎታለሁ::
– እንዴት ማለት?
– ክቡር ሚኒስትሩ ማሳጅ ቤቱ ቢሉ፣ ሺሻ ቤቱ ቢሉ፣ ገስት ሃውሱ ቢሉ ኧረ ስንቱ::
– ምንድን ነው የምታወራው?
– ብቻ ይኼ የስብሰባ ተሳታፊ ነኝ የሚል ሁሉ የሚገኘው እኮ እዛ ነው::
– እ…
– እንዲያውም አንዳንዴ የስብሰባው ቦታ የተቀየረ ነው የሚመስለው::
– ማለት?
– በቃ ሁሉም ተሳታፊዎች ያሉት በየማሳጅ ቤቱ፣ በየሺሻ ቤቱና በየጭፈራ ቤቱ ነዋ::
– ወይ ጣጣ::
– ለማንኛውም እርስዎም ሲሄዱ ይዘውኝ ቢሄዱ ደስ ይለኛል::
– የት?
– ስብሰባ ሲሄዱ::
– ሞላጫ! [ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– መቼም የሙጋቤን ንግግር ተከታትለኸዋል?
– አዎን ክቡር ሚኒስትር::
– ልክ ልካቸውን እኮ ነው የነገረልኝ::
– እነ ማንን?
– ኒዮሊብራሎቹን ነዋ::
– እሱ እኮ ሁሌም ነው የሚናገረው::
– ከእንግዲህ ግን ቀልድ የለም ብሏል::
– የምን ቀልድ?
– የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤቱ ውስጥ መግባት አለብን::
– እንዲህ በቀላሉ::
– እኮ አሁን መዘጋጀት አለብን::
– ለምኑ?
– ምክር ቤቱ እኛ እንድንገባ ኒዮሊብራሎቹ አይፈልጉም::
– እሱማ የታወቀ ነው::
– ስለዚህ በራሳችን እናቋቁማለን::
– ምንድን ነው የምናቋቁመው?
– የራሳችንን የተባበሩት መንግሥታት::
– እየቀለዱ ነው?
– በዚህ ቀልድ የለም::
– እና ምን ይደረግ?
– ኮሚቴ ይቋቋም::
– የምን ኮሚቴ?
– የራሳችንን የተባበሩት መንግሥታት የሚያቋቁም ኮሚቴ::
– ኮሚቴ ግን አልበዛም?
– አየህ ኮሚቴ ሲኖር ግልጽነትና ተጠያቂነት ይኖራል::
– ስለዚህ ኮሚቴው እንዴት ይዋቀር?
– ያው እንደተለመደው ከሴቶች ፎረም፣ ከወጣቶች ፎረም፣ ከነጋዴዎች ፎረም
… የተውጣጡ ይሁኑ::
– የብሔር ተዋፅኦስ?
– እሱማ ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ነው::
– የኮሚቴው ሥራ ምንድን ነው የሚሆነው?
– ኮሚቴው በአዲሰ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶችን የማሳመን ሥራ ይሠራል::
– እሺ ክቡር ሚኒስትር::
– ይህን ለማድረግ ደግሞ ዲፕሎማቶችን እናደራጃቸዋለን::
– በምን?
– በአንድ ለአምስት!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles