* “የሟቾች ቁጥር እስከ መቶ ሊደርስ ይችላል” ነዋሪዎች
* “የሞቱት 14 ሰዎች ናቸው” ኢህአዴግ
ሰሞኑን በጋምቤላ በደረሰው የእርስበርስ ፍልሚያ እስከመቶ የሚጠጉ መሞታቸውን የክልሉ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ የሞቱት 14 ብቻ ናቸው ይላል፡፡ ዘረኝነትንና ጠባብ ጎሰኝነትን ለኢትዮጵያ እንደ “ገጸ በረከት” ያመጡት መለስ በየቦታው የጫሩት እሣት ለፍርድ ሳያቀርባቸው ሾልከዋል፡፡ እሣቱ ግን አሁንም እየነደደ ነው፡፡
ጎልጉል ከአካባቢው ነዋሪዎችና ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ ባገኘው መረጃ መሠረት በግጭቱ የሞቱት እስከ መቶ እንደሚደርስ ይነገራል፡፡ ግጭቱ ከመነሻው በቀላሉ የተነሣ ቢሆንም ወዲያውኑ ወደከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ሥር የሰደደ ፖለቲካዊ ምክንያት እንዳለው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ይህንኑ ዜና ኢሳት ሲዘግብ የሟቾቹ ቁጥር ከመቶ እንደሚያልፍ ምንጮቹን ጥቅሶ አስታውቋል፡፡
ጸረ ቁጥር የሆነው ኢህአዴግ ወራትን ባስቆጠረው የተማሪዎች ዓመጽ ከሁለት መቶ በላይ ሞተው ሟቾች ከአስር ያልበለጡ ናቸው ከማለቱ በፊት መጀመሪያ ምንም የሞተ የለም፤ ቀጥሎም የሞቱት አምስት ናቸው ማለቱ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ የኢህአዴግ አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ በጋምቤላው ግጭት የሞቱት ቁጥሩን እርግጠኛ ለማስመሰል ይመስላል 14 ናቸው ብለዋል፡፡
አቶ መለስ በአዛዥነት ከሌሎች የህወሃት ሹማምንት ጋር በመሆን በሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ 424 የአኙዋክ ጎሣ አባላት በግፍ መጨፍጨፋቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የጭፍጨፋው አስፈጻሚ የነበሩት እና ኢህአዴግን ከድተው በውጪ አገር የሚገኙት የቀድሞው የክልሉ ኃላፊ ኦሞት ኦባንግ ኦሉም ከህወሃት ጋር ሆነው የተከሉት መርዝ ለሰሞኑ ግጭት መባባስ ምክንያት እንደሆነ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ፡፡
በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) የዘር ጭፍጨፋ ከተካሄደባቸው በኋላ መሬታቸውን በግፍ ከተነጠቁት አኙዋክ ወገኖች መካከል ከዘር ማጥፋቱ ያመለጡት በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩት አገር ለቅቀው ተሰደዋል፡፡ በዓለምአቀፍ ድርጅቶች ዘንድ በቁጥር ደረጃ ለመጥፋት የተቃረቡ ከሚባሉት አኙዋኮች በህይወት የቀሩት ደግሞ አሁን ለዘር እንዳይቀሩ ሆነው እየተጨፈጨፉ ይገኛሉ፡፡ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ግጭቱ እርስበርስ መሆኑ ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ህወሃት ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ያለው “የጫጉላ ጊዜ” በማብቃቱ ለተቀናቃኛቸው ሬክ መቻር ግልጽ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ የኑዌር ተወላጅ የሆኑት ሬክ መቻር ወደ ጋምቤላ እንደፈለጉ ሲወጡና ሲገቡ መክረማቸውን ጎልጉል ከዚህ በፊት ዘግቦ ነበር፡፡ የመቻርን ኃይል ለመደገፍ ከጋምቤላ በርካታ ኑዌሮች ወደ ደቡብ ሱዳን ገብተው ከሳልቫ ኪር የዴንቃ አባላት ጋር ጦርነት መጋጠማቸውና ከሞቱት መካከልም “የመከላከያ ሠራዊት” አባላት ለመሆናቸው ማስረጃ ስለመገኘቱ ጉልጉል በተደጋጋሚ መረጃ ደርሶታል፡፡
አሁን በተከሰተው ግጭት ቀድሞውኑም የታጠቁት የኑዌር አባላት አሁን ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ግጭት ጋር በተያያዘ የመቻር ኃይል ያስታጠቃቸው ድንበር እያለፉ በመዝለቅ በአኙዋኮች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት አሁንም አልቆመም፡፡ የአኙዋክ ጎሣ አባላትም ራስን ከመከላከል ጀምሮ መልሶ እስከ ማጥቃት በሚያደርጉት ምት በገጠር ቀበሌዎች የሚገደሉት ንጹሃን ቁጥር እጅግ እየጨመረ መሄዱ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ለጎልጉል አስታውቀዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያንን እንደ እህል በዘር ከረጢት እየሠፈረ ለዚህ ሁሉ ዓይነት ስቃይና መከራ እንዲሁም ለማያባራ የዘር ግጭት የዳረገው መለስ ነው፤ ወደ ህይወት ማምጣት ብችል አስመጥቼ ፍትህ እንዲበየን ማስደረግ እፈልግ ነበር፤ ሙት አይወቀስም ይባላል፤ ልክ ሊሆን ይችላል አባባሉ ግን ለመለስ አይሠራም፤ እኔ ፍትህ የጠማኝ ነኝ” በማለት የመረረ አስተያየቱን ለጎልጉል በውስጥ መስመር የሰጠው ወጣት ይናገራል፡፡
ህወሃትና መለስ በኢትዮጵያ የተከሉት የዘር ፖለቲካ በአገሪቱ በበርካታ ቦታዎች የማንነት ጥያቄ ከማስነሳት አልፎ የህይወት መስዋዕትነት እያስከፈለ ነው፡፡ እምቢባዮችን “ልክ እናስገባለን” በማለት እየፎከረ አገር በነጻ አውጪ ስም የሚገዛው ህወሃት፤ የህይወት ዑደቱን እስኪያጠናቅቅ “ባለ ራዕዩ መለስ” ያስቀመጡለትን “ራዕይ” በትጋት እያስፈጸመ ይገኛል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
<!–
–>