የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያም ኔታኒያሁ አዛን “መታገስ የማይቻል ጩኸት” እየሆነ መጥቷል በማለት ተናገሩ፡፡ ጉዳዩ ያስቆጣቸው የሙስሊም መሪዎች ንግግሩ በሃይማኖታችን ላይ ማዕቀብ ለመጣል የተቃጣ ነው ብለውታል፡፡
ባለፈው አርብ በእስራኤል ሸንጎ የሊኩድ ፓርቲ አባላት በተገኙበት ኔታኒያሁ ባደረጉት ንግግር በእስራኤል የሚገኙ የአረብ ከተሞች ለአገሪቷ ሕግ መገዛት አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህንንም በማድረግ ለአገሪቷና ለማኅበረሰቡ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው በማለት አስታውቀዋል፡፡
“በአብዛኛዎቹ የአረብ ከተሞች ሕግ አይከበርም፤ ይህም አዛን እና ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት ተጠቃሽ ናቸው” በማለት ቢኒያም ኔታኒያሁ የተናገሩ ሲሆን ከዚህ አኳያ ከበርካታ መስጊዶች የሚሰማው አዛን “መታገስ የማይቻል ጩኸት እያስከተለ” ስለሆነ መንግሥታቸው ሕግ ሊያወጣ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
አዛን (አድሃን) ለጸሎትና ለስግደት ሙስሊሙ እንዲሰበሰብ የሚደረግ ጥሪ ነው፡፡ ድምጸ መረዋ በሆኑ የሚሰማው ይህ ጥሪ በበርካታ ቦታዎች በድምጽ ማጉያ የሚደረግ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ያለ ድምጽ ማጉያም የሚከናወን ነው፡፡
“ይህንን (ጩኸት) መቀበል በጭራሽ አይቻልም” ያሉት ኔታኒያሁ በአረብም ሆነ በአውሮጳ አገራት እንዲህ ያለ ጩኸት በድምጽ ማጉያ እንዲሰማና ሰዎች እንዲረበሹ የሚፈቅድ ሃይማኖታዊ ፅሁፍ የለም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ገደብ ሊደረግበት ይገባል፤ እንዲያውም ጩኸትን የሚከለክል ሕግ አለን እርሱን ተግባራዊ እናድርገው ብለዋል፡፡
በእስራኤል በሚገኙ የአረብ ከተሞች የሚታየው ከአንድ በላይ ሚስት የማግባት ሁኔታን በተመለከተም “ይህንን ክስተት በተመለከተ የሴቶች (መብት ተሟጋች) ድርጅቶች እንደ ሙታን ዝምታን” መምረጣቸውን የወቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩ የተወሳሰበ መሆኑን ከመናገር ግን አልተቆጠቡም፡፡ ሲያጠቃልሉም “ሕግ የምንከተል አገር መሆን አለብን ወይም የለብንም” በማለት ቃላት በተግባር መተርጎም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በየሩሳሌምና በፍልስጤም ግዛቶች ጠቅላይ ሙፍቲ የሆኑት ሼክ መሐመድ ሁሴን ጉዳዩን በመስጊዶቻችን ላይ የተሰጠ “ማስጠንቀቂያ”፤ በሃይማኖቱ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያነጣጠረ ነው ብለውታል፡፡ በእስራኤል ሸንጎ አረባውያኑ እንደራሴዎች ጉዳዩ የዘረኝነት መንፈስ የተጠናወተው በማለት የጠቀሱት ሲሆን ኔታኒያሁ የአረብ ጥላቻ በመቀስቀስ ርካሽ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት በመደጋገም የሚሞክሩት አደገኛ አካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“ኔታኒያሁ እንደ አገር አስተዳዳሪ ጉዳዮችን መመልከት ይገባቸዋል እንጂ እንደ አምባገነን ወታደራዊ መሪ መሆን የለባቸውም” በማለት ሌላኛው እንደራሴ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወቅሰዋል፡፡
የእስራኤል ሸንጎ አባላትና አይሁዳዊ ሰፋሪዎች በወታደሮችና በፖሊሶች በመታገዝ ባለፈው መስከረም ወር የአል-አቅሳን መስጊድ ከወረሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከ2400 በላይ ፍልስጤማውያን ታስረዋል፤ 30 ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ጨምሮ 158 ተገድለዋል፤ 10ሺህ የሚጠጉ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ የየሩሳሌም ኢንቲፋዳ የሚባለውን ተቃውሞ ቀስቅሷል የሚባልለት ይህ ድርጊት ለእስራኤል በየሩሳሌም አካባቢ በሚገኙ የአረብ ሰፈሮች ላይ የከረሩ ሕግጋትን እንደትተገብር ነጻነት እንደሰጣት በሰፊው ይነገራል፡፡ (ለዜናው ጥንቅር የተለያዩ የዜና ምንጮችን ተጠቅመናል፤ የመግቢያ ፎቶ ሲያሳት ዴይሊ)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
<!–
–>