የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ወይም ልሂቃኖች ብዙ ጊዜ በስሚ ስሚ ላይ ብቻ ተንተርሰው፣ ወይንም ተጽፎም ከሆነ ምን ያህል እውነትነት አለው ሳይሉና ሳያጣሩ፣ ለጊዜያዊ ፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ብቻ ፣ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ጋር የማያገናኙ ሀሳቦችን እንደሚያራምዱ ካለፉት 50 እና 60 ዓመታት የአገሪቱ ፖለቲካ የተጓዘበት ጉዞና ውጤቱ አሳይቶናል። ለምሳሌ አፄ ምኒሊክ የጅምላ መጨረሻ ኬሚካል መሳሪያ ወይንም ኒኩለር ቦምብ ያላቸው ይመስል « 5 ሚሊዮን ኦሮሞ ጨረሱ» ብለው፣ ራሳቸው ተሳስተው ትውልድን የሚያሳስቱ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን መኖራቸውን አስተውለናል። ይህ አባባል ዕውነት ብሎ ለማመን በቅድሚያ፣ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ስንት ነበር? ከዚህስ ውስጥ ኦሮሞው ምንያህል ነበር? ብሎ በመጠየቅ ዕውነታውን መረዳት ተገቢ ነበር። ለነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ከተገኘ በኋላ ምኒልክ ያን ያህል ሕዝብ ለመግደል የተጠቀሙበት መሣሪያ ምን ዓይነት ነው? ጭፍጨፋው ለስንት ጊዜ ቆዬ? በወቅቱ ይህን ያህል ሰው ለመግደል ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ነበረበት። ለነዚህና መሰል ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ቀርቶ ሳይጠይቁ «ጠላት ይቀባል ጥላት» እንዲሉ የምኒልክን ስም ለማጥፋት የፈለጉ ሰዎች የተናገሩትን እንደ ደረቅ ሐቅ ቆጥረው እንደ በቀቀን ደጋግሞ ማውራት ልሂቃኖቻችን ለሳይንሳዊ መርህ የማይገዙና ለርሱም ባዕድ መሆናቸውን ያሳያል። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ከዚህ አባባል ተያያዥነት ያለው ዶ/ር መሳይ ከበደ “TPLF in Disarray and the Remaking of National Unity” በሚለው ጽሁፋቸው የሚከተለውን አባባል የያዘ ሀሳብ ማግኘቴ አባባላቸው ከማሳዘን አልፎ ስላስገረመኝ፣ ወይም «በምኒልክ ጊዜ የደነቆረ በምኒልክ አምላክ ሲል ይኖራል» እንዲሉ ሆኖብኝ፣ ለዚህ ጽሑፌ መነሻ ስለሆነኝ ነው። እንዲህ ይላል “But when unrests multiply, especially when they come from the Oromo who are supposed to have most benefited from the liquidation of Amhara hegemony and the establishment of federal system of self-rule, they reveal a deep crack in the very foundation of the regime”.
እግዚአብሔር ያሳያችሁ! እንግዲህ እኚህ ሰው በምንም ይሁን ምን ጥናት አድርገው የፒኤችዲ ዲግሪ ያላቸው ሰው ናቸው። በነገራችን ላይ ማንም ሰው የትምህርት ደረጃው ምንም ይሁን ምን ጥፋት ካየሁ ጥፋቱን ከመናገር ወደኋላ አልልም። አንድ ሰው «ዶክተር» ወይንም «ፕሮፌሰር» ስለተባለ ብቻ ሁሉን ነገር ያውቃል፣ ይረዳል ማለት አይደለም። ዕውቀቱ በሰለጠነበት የሙያዘርፍ ነው። ያም ጎበዝና ተከታታይ ጥናትን ምርምር የሚያደርግ ከሆነ ነው። በሌላ በኩል ፣አይደለም ዩንቨርስቲ የገባ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ያጠናቀቀ ሳይንስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃል። ሳይንስ በጥናትና ምርምር ዘዴዎች ተጠቅሞ በቋሚ ሕግ የሚገዛ ፣የሰው ልጅ በአምስቱ የሕዋሳት ስሜቶቹ ሊረዳው የሚችል ዕውቀት፣ ግኝት፣ ወዘተ ነው። ለአንድ ነገር ስያሜ ወይም መጠሪያ ከመስጠቱ በፊት፣ ሊያሟላቸው ይገባል የሚላቸውን መስፈርቶች ይዘረዝራል። “Definition or criterias” ይሉታል። አንድ ነገር ይሄ ነው፣ ወይንም ይህ አለው ለመባል የሚይዛቸው ከ atoms ጀምሮ ሁሉ ነገር ግልፅ የሆነ ሊያምዋሉት የሚገባ መስፈርት ያስፈልጋል። ግልፅ የሆነ ነገር እንክዋን ባይኖር ቢያንስ ይሄንን ይሄንን ካላምዋላ እንዲህ ሊባል አይገባውም ይባላል። ወደ ዋናው ጉዳዬ ወደ ገደለው ልግባ፤
አንድ ልሂቅ ወይንም የፖለቲካ ሰው ድሮ አማራ ገዛ ወይንም በዶ/ር መሳይ አገላለጽ Amhara hegemony ነበር ለማለት ምን Definition/criteria ይዘው ነው። ወይንስ በጥላቻ የተሞሉትን እነ ኦነግ፤ ትህነግ (ወያኔ)፣ ግንቦት 7፣ ሲነአ፣ ኦብነግ፣ ወዘተ የመሳሰሉት እና ምዕራባውያን የድሮ መሪዎች አማርኛ ስለሚናገሩ ብቻ አማራ ድሮ ገዛ የሚለውን ሀሳብ ተቀብለው ነው። በግልጽ የተፃፈ በመረጃ ላይ የተንተራሰ መስፈርት ባይኖርም፣ ኮንፈረንስ ተካሂዶ አንድ ብሄር ገዛ ለማለት ሊካተቱ የሚገባቸው መስፈርቶች ላይ እስከምንስማማ እኔ በግሌ አማራ ድሮ ገዛ ከማለታችን በፊት፣ ከዚህ በታች የገልጽኳቸው 5ቱ ነጥቦች ተገቢ መልስ ማግኘት አለባቸው ባይ ነኝ። በዚህ አጋጣሚ ዛሬ አገሪቱን እያገዛ ያለው ትግሬ ወይስ ጥቂት ትህነግ (ወያኔ) አባላት ናቸው? ለማለት ይቻላል ወይም አይቻል እንደሁ ባስቀመጥኩት ንድፈ ሀሳብ መሰረት እንድትወስኑ ለናንተ ትቼዋለው።
- የሥርዓቱ ወሣኝ የሥልጣን ቦታዎች የተያዙት በየትኛው ብሔር አባላት ነው?
እዚህ ጋር ሁለት ነገሮች መታሰብ አለባቸው። አንደኛ የሀገሪቱ መሪ አማርኛ ስለተናገረ ብቻ አማራ ነው ማለት አይቻልም። አፄ ኃይለሥላሴ ምንም በአማርኛ ቢገዙም የእሳቸውን ማንነት፣ ወርደን የብሄር ደም እንቁጠር ካልን ኦሮሞነታቸው ይበዛል፤ የመኮንን ጉዲሳ ልጅ ናቸው። መንግሥቱ ኃይለማሪያምም እንዲሁ የወልዴ አያና የልጅ ልጅ ናቸው። እራሳቸው ኦሮሞ እና አማራ መሆናቸውን ነግረውናል። ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ኦሮሞ ናቸው። ለገሠ ዜናዊ አማርኛ አቀላጥፎ የሚናገር ትግሬ ነው። ለገሠ ዜናዊ አማራን ከምድረ ገጽ የማጥፋት እቅድ ነድፎ እስከ ሕይዎቱ መጨረሻ የሠራው በአማርኛ አገሪቱን እያስተዳደረ ነው። እዚህ ጋር እንደ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ዓይነቶች አሻንጉሊት መሪዎችን አይጨምርም። ብሄርን ቆጥረን ወላይታ ሥልጣን ላይ ሆነ ለማለት የሚደፍር ሰው እንደማይኖር አምናለሁ። አማርኛ አቀላጥፎ በመናገሩ ብቻ፣ አማራ ነው ሥልጣን ላይ ያለው እንደማትሉም አምናለው። ስለዚህ ብሔር ቆጥረን ከሄድን፣ ወደኃላ ብዙ ካልሄድን ከቅርቦቹ በብሄር ሲቆጠር አማራ የሆነ የለም። ከመለስ እና ከኃይለማሪያም ውጪ የድሮዎቹ ራሳቸውን በኢትዮጵያዊነት እንጂ፣ በብሔራቸው ራሳቸውን ለይተው አያውቁም። 0/1 አትሉም ለአማራው ወይንም ለኦሮሞው መሪዎቹን ብቻ ካሰብን። ለትግሬ 1/1። እንቀጥል…
- ሥልጣን ላይ አለ የተባለው መሪ አማራ ከተባለ ለአማራ፣ ትግሬ ከተባለ ለትግሬ ፣ኦሮሞ ከተባለ ለኦሮሞ ወዘተ ለብሔሩ ምን አደረገ? ብለን እንጠይቅ።
አፄ ምኒሊክም፤ አፄ ኃይለሥላሴም፤ ወይንም መንግሥቱ ጠብታ አማራ ደማቸውን ቆጥረው ራሳቸውን እንደ አማራ ቆጥረዋል እንበል። እነሱ ራሳቸውን በኢትዮጵያዊነት ብቻ እንደቆጠሩ ብናውቅም። እንግዲህ ለአማራነት ከሠሩ መሆን ያለበት፣ የአማራ ለሚሉት ሕዝብ ከሌላው በተለየ ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግ አለባቸው። አማራው በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች የትምህርት፣ የጤና፣ የመንግድ፣ የንፁሕ ውኃ አቅርቦት፣ የመብራት፣ የመንገድ ወዘተ አገልግሎቶች ሊገነቡ ይገባል። እነዚህን ስናገናዝብ በሦስቱም በአማራነት በሚከሰሱት መሪዎች የአማራ ሕዝብ ይኖርባቸዋል በተባሉት አካባቢዎች ከሌሎች ክልልሎች በተለየ ሁኔታ የተሠራ አድልዖ የለም። እውነታው የሚያሳየው ሶስቱም የሥልጣናቸው መቀመጫ ያለበት መሃል ሃገር ላይ አተኩረው ብዙ ነገር በአዲስ አበባ ዙሪያ የተሠራ እንደሆን እናያለን። አፄ ኃይለሥላሴ የትውልድ ሀገራቸው ሐረር አካባቢ የተወሰኑ የልማት ሥራዎች እንዲሰሩ ተጽዕኖ አሳድረው ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህ ግን አመድ አፋሽ የሆነ ውጤት ነው የሚታየው። «የሚያለቅስ ልጅ የወላጆቹን እንክብካቤ ያገኛል» የሚሉት ዕውነት ሆኖ፣ ኤርትራውያኖች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያለቅሱ ስለነበር ቀኃሥ ለኤርትራ ብዙ የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ማድረጋቸው ዕውነት ነው። መንግሥቱ ኃይለማርያምም አንድ ሰሞን የአገሪቱ በጄት ተጠቅሎ ኤርትራ ላይ እንዲፈስ ማድረጉ ይታወቃል። ሁለቱም ይህን ያደረጉት፣ የማይጠግቡ የጠላት ቅጥረኞችንና የባንዳ ልጆችን ለማባበል ነበር። ከዚህ በተረፈ አማራ በብቸኝነት ይኖርባቸዋል የሚባሉ ቦታዎች መካከል ጎጃምን፤ ላኮመልዛ (አሁን ወሎ)ን፤ ጎንደርን ወዘተ አመፀ እያሉ ሲወጉት ሲያስወርሩት እንጂ፣ ኑሮው ይሻሻል እያሉ ከሌላው የተለየ ልማት ሲያለሙለት አልታዩም። ለመንግሥቱ ኃይለማሪያም ሌላውን ትተን የጎንደር ሕዝብ እንዲህ በማለት ነው ብሦቱን የገለጸው።
« መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም፣
ያሁኑን ማርልኝ ሁለተኛ አልወልድም፤»
ላኮመልዛ/አንጎት በሁሉም ዘመን በረሃብ አለንጋ ተገርፏል። ለገሠ ዜናዊ ግን ከአጋሮቹ ጋር ሆኖ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍለ-ሀገሮች ተመሳሳይ ዕድገት የነበራትን ትግራይን በመጀመሪያ የሌሎችን ክፍለ አገሮች አካል የነበሩ አውራጃና ወረዳዎችን ወደ ትግራይ በመጠቅለል የትግራ ገበሬ ለም መሬት ላይ እንዲሠፍር አድርጓል። በሁለተኛ ደረጃ ከቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች እየተዘረፈ ትግራይ ብለው ወደከለሉት ውስጥ የገነቡትን ፋብሪካዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የአውሮፕላን ጣቢያዎች፣ ድልድዮች፣ መንገዶች ወዘተ ምን እንደሠሩ ፀሐይ የሞቀው፣ ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው። የሚገርመው የቀደሙት 3 መሪዎችን አማራ ናቸው፣ ለአማራ ነው፣ የሠሩት ቢሉንም እነኚህ መሪዎች መሀል ኢትዮጵያ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረጉባቸውን ቦታዎች የአሮሞ ክልል ነው ብለው ከለሉት። ለአማራ ሠሩ ብለው የቀደሙ መሪዎችን እነሱ የሠሩበትን ቦታ የኦሮሞ ነው የሚሉን ከሆነ ታዲያ ተደብቀው ለኦሮሞ ነበር ሢሠሩ የነበረው አይሉንም? ለማንኛውም ለአማራ አሁንም 0/1 ስጡ፤ ለትግሬ 1/1 እና ለኦሮሞ 0.5/1 ስጡልኝ። እነ ኦነግ፤ የቀደሙት የአማራ መሪዎች ለአማራ ብቻ ነው የሰሩት ተበድለናል ብለው መልሰው ይሄንንው ቦታ የኦሮሞ ብቻ ነው ለኛ ብቻ ይገባናል ይሉናል። አንድም የቀደሙት መሪዎች ከለገሠ በፊት ያሉት ማለት ነው፣ አንድን ብሄር አደራጅተው ሌላ ብሄርን ጠላት አድርገው አጥቅተው አያውቁም፤ ነገር ግን ከተለያየ ብሄር ደጋፊዎቻቸውን አደራጅተው ተዋግተዋል። ትህነግ ግን ትግሬን አደራጅታ ዓላማዬ ብለው አማራን ለማጥፋት እየሠሩ ነው፣ ይህንንም አማራን እናጠፋዋለን አላማ በድብቅ ሳይሆን ባደባባይ የተናገሩት ነው።
- የሀገሪቱ ቁልፍ ሥልጣኖች (መከላከያ/ደህንነት/ውጭ ጉዳይ ወዘተ) በማን ነው የተያዘው?
የቅርብ መሪዎችን ብንመለከት አማርኛ ከመናገራቸው ውጪ፣ ብዙዎቹ የተቀላቀሉ እንደሆኑ ልብ ብለናል፤ ለገሠን ሳይጨምር ምክንያቱም ለገሰ አማርኛ ቢናገርም፣ ባደባባይ እንኳን ከዚህ ወርቅ ሕዝብ ተወለድኩ እንኳንም ከሌላው ተወልጄ በቅናት የማይ ባልሆንኩ ብሎ ብሄሩን ስላወጀ። በመንግስቱም፤ በዐፄ ኃይለሥላሴም ይሁን በዐፄ ምኒሊክ ጊዜ የነበረውን የሥልጣን ክፍፍል ብንመለከት አማራም ኦሮሞም ትግሬም ብዙ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው እናያለን። ያውም እንዳሁኑ የአሻንጉሊትነት ሥልጣን ሳይሆን፣ ባለ ሙሉ ሥልጣን በመሆን ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት ሠርተዋል። አሁን በትህነግ (ወያኔ) ያለውን ተመልከቱ፤ ሁሉም ሥልጣን በትግሬ ነው የተያዘው። ለይስሙላ ሥልጣን የተሰጣቸው እንኳን ከሥራቸው ትግሬ እንደታኮ አላቸው። ታዲያ በምን ስሌት ተሰልቶ ነው፣ ድሮ ሥልጣን በአማራ ነበር የተያዘው የሚባለው? እንዳልኩት እኔም ትክክለኛው የሥልጣን ክፍፍሉ ስብጥር ቁጥር ስለሌለኝ በደፈናው ጥቂት ሰዎችን ምሳሌ ጠቅሼ አልከራከርም። በደፈናው አማራ ሥልጣን ላይ ነበረ የሚሉትም እንዲሁ ልክ አይደሉም፤ ምክንያቱም መረጃ ሳያቀርቡ መናገር ከዕውነቱ ሊያደርሰን ስለማይችል። እውነታው፣ ቢያንስ በግልጽ የሚታወቁትን ካየን ግን ፣አማራ ድሮ ሥልጣን ላይ እንዳልነበረ ያሳያል። አሁንም ለትግሬ 1/1 ስጡልኝ። አማራውም ኦሮሞውም 0.5/1 ሊሰጠው ይገባል ትሉ ይሆናል። ሥልጣን ውስጥ ስላሉበት ነገር ግን በግሌ አማርኛ የተናገረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አማራ ስለማይሆን 0.5/1 ለአማራ አልሰጥም ቢያንስ አማራ ናቸው የተባሉት አማራ መሆናቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ።
- የሀገሪቱ ንግድ፤ ትምህርት፤ የጤና ግልጋሎት በማን ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት?
ስለድሮው የሀብት ክፍፍል፣ የትምህርት መስፋፋት፣ የጤና ሽፋን ወዘተ ብንመለከት ምናልባትም በጣም ተበደልን የሚሉት ትግሬዎች ተጠቃሚዎች ሆነው እናገኛቸዋለን። ኦሮሞው ከአማራው የተሻለ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት አለው። ብቸኛው አማራው እና ትግሬው መጀመሪያ የተጠቀመው ሊባል የሚችለው ትምህርት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ስለሆነ መጀመሪያ የተስፋፋው እና ብዙ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ወደ ሰሜን ስላሉ ያኔ ተጠቃሚ ሆነው ይሆናል። ዘመናዊው ትምህርት ከተስፋፋ በኃላ ግን ዩኒቨርስቲ የሚገባውን በፐርሰንት ማስላት ነው። አሁን በዩኒቨርስቲ ወይንም በጤና ያለውን አስተዋጽኦ አስቀምጡና ከድሮው ጋር አወዳድሩና ፍረዱ። ወያኔ ምናልባት አማራ እንዳይዋለድ ሕዝቡን መሃን የማድረግ፣ ከሥራ የማባረር፣ በሽተኛና ታማሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ከመሥራቱ በቀር፣ ለአማራው ሕይዎት መደላደል የሚጠቅም ምንም ዓይነት ሥራ አልሠራም። የመጣው አማራን በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት ነውና! እዚህ ጋር አማርኛ የሚናገረውን ሁሉ እና ብሄሩን ቅድሚያ የማይሰጥ ስለኢትዮጵያዊነቱ ብቻ የሚያተኩር ሁሉ አማራ እየተባለ ፣አማራ ተጠቃሚ ነበር የሚለው የተሳሳተ እሳቤ ነው። እስቲ ልብ በሉ ፣ባሕርዳር ዙሪያ ጣና ዳር የመብራት እና ውሃ አገልግሎት እንደልብ አይገኝም። ሌላው ስንት የረቀቀ ዘመናዊ ሕክምና ሲያገኝ፣ የአማራ ሕዝብ በትራኮማና በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ በሚችሉ ተላላፊ በሽታዎች አካሉንና ሕይዎቱን ያጣል። ትህነግ (ወያኔን) ብትመለከቱ ደግሞ፣ አሁን ከጥበቃ ኃላፊ፤ ከቀበሌ ሊቀመንበር እስከ መከላከያ እና የመጨረሻውን የመሪነት ሥልጣን፣ ሁሉን ነገር ተቆጣጥረውታል። አሁንም ትግሬ ገዛ ሲባል የሚደረገውን እዩትና አማራ ገዛ በሚሉበት ሰዓት፣ ያለውን ልዩነት አወዳድሩ፤ አማራ ምን ያህል ስልጣን ላይ እንደነበረ እና ምን ያህል አማራ ለሚለው ሊጠቅም እንደሞከረ አስቡት። በፍፁም፣ አማራ ለአማራ ብቻ ብሎ በታሪክ ሠርቶ አያውቅም። አሁንም ለትግሬ 1/1 ለአማራው 0/1 ስጡልኝ። ለኦሮሞ 0.5/1 ይሰጥ። ምክንያቱም ቢያንስ የኦሮሞ ክልል ብሎ የከለለው ውስጥ ትንሽ ስልጣን አላቸው በትህነግ (ወያኔ) መልካም ፍቃድ ቢሆንም። የአማራ ብሎ የከለሉት ውስጥ ግን ኤርትራዊ ነን ከሚሉት ጨምሮ አብዛኛው ስልጣን በትግሬ ነው የተያዘው።
- የሀገሪቱ የመግባቢ ቋንቋ ምን ሲሆን ነው አንድ ብሄር ገዛ የሚባለው?
እንግዲህ አማራው ሚሊዮን ጊዜ ገዛ የሚባለው አማርኛ ለብዙ መቶ አመታት የመንግሥታት ቋንቋ ስለሆነ ብቻ ይመስለኛል። በዚህም ምክንያት አማርኛ የአማራ ከመሆን አልፎ የኢትዮጵያ ሆኗል። የአማራ ጠላቶች እነ ለገሠ እና አጋሮቹ እንኳን፣ አማርኛ እየተናገሩ ነው አማራን ለማጥፋት የሠሩት። ዛሬም ድረስ አማርኛ እንዳይነገር የተባለበት ቦታ ሁሉ፣ በከፍተኛ ደረጃ አማርኛ እየተነገረ ነው። ስለዚህ አማርኛ ስለተነገረ ብቻ፣ ዛሬም ድረስ አማራ እየገዛ ነው ሊባል ነው? ትህነጎች (ወያኔዎች) ቁጥራቸው አነስተኛ ስለሆነ ነው መሰል፣ ይቺን ነገር ብቻ አልደፈሩም። ትግርኛ ብሄራዊ ቋንቋ ይሁን አላሉም። ሆኖም፣ አማርኛን ቢናገሩትም፣ ስለሚጠሉት ሊያዳክሙትና ሊያጠፉት ብዙ ሲለፉ ይታያሉ። ግን አልቻሉም ። ይልቁንም እየተስፋፋ መጣ ። አረብኛ በብዙ አገራት ይነገራል። ከእስልምና ጋር አብሮ እየተስፋፋ በዓለም ዙሪያ ይነገራል። ፊደል ያለው አማርኛ/ግእዝ ስለሆነ እና የመንግሥት ቋንቋ አማርኛ ስለነበረ፣ ለዘመናት አማርኛ እየተስፋፋ መሄድ ማለት ግን፣ አማራ የበላይነት ነበረው ማለት አይደለም። በቃ! አማርኛ አሁን የሀገሪቱ ሀብት ነው እንጂ፣ የአንድድ አማራ የተሰኘ ነገድ ብቸኛ ሀብት ወይም መገናኛ መሣሪያ አይደለም። እንግዲህ ተማሩ፣ ተመራመሩ የተባሉ ይህ ሁኔታ ይጠፋቸዋል ተብሎ ለማመን ያስቸግራል። ስለዚህ አንድ ቋንቋ በሀገሪቱ ውስጥ በብዛት መነገር ማለት የዛ ብሔር የግድ የበላይነትን ማሳያ ወይም መገለጫ ሊሆን አይችልም። የሚያሳየው የቋንቋውን እድገት ነው። ስዋሂሊ ቋንቋ ምሥራቅ አፍሪካ በብዛት ይነገራል። ግን የዛ ቋንቋ መጀመሪያ ተናጋሪዎች እስካሁን የበላይ ስለሆኑ ወይንም ድሮ ገዢ ስለነበሩ አይደለም። ቋንቋው በዚያ አካባቢ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ በማደጉና ብዙ ሕዝብ ለግብይት ስለሚጠቀምበት ነው። ስለዚህ እዚህ መስፈርት ላይ ለሁሉም 0/1 ነው የምሰጠው። ሲደመር ትግሬ 4/5 ሲያገኝ አማራ 0.5/5 እና ኦሮሞ 5 ነው በኔ መስፈርት ያገኙት። የሚገርመው ሁሉም ግን አማራ ገዢ ነበር የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ያስፋፋሉ። አሁን አሁንማ አማራውን ምን እንዳስነኩት አይታወቅም፣ ሳይበድል በዳይ ነበርኩ ብሎ እንዲያምንና እንዲቀበል ያስማሉት ይመስላል። ይህ በውሸት ሕዝብን መወንጀል ሊወገዝ ይገባዋል። አማራ ዝም በማለቱ እነ ቢቢሲ ሳይቀር አማራ ከትግሬ ጋር ሆኖ ኦሮሞን እንደሚበድል አድርገው አቀረቡ አማራው በሁለቱም ወገኖች የጥቃት ሰለባ መሆኑ እየታወቀ። በተለይ ተማርን የሚሉ ወገኖች እንዲህ ዓይነቱን «በቅሎ ወለደች፣ ሸንበቆ አፈራ፣ ንብ ማር ጋገረች» እያሉ የሚያወሩትን፣ የሚጽፉትን እየተከታተሉ አወቅንባችሁ ሊባሉ ይገባል።
እንግዲህ እነ ዶ/ር መሳይ ከበደ አማርኛ በመላው ኢትዮጵያ ሥራ ላይ ከመዋል ይልቅ የተወሰኑ የሀገሪቱ በባንቱስታን ስታይል በተከፋፈሉ የሀገሪቱ ክልሎች ላይ ብቻ አማርኛ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን ካልሆነ በስተቀር እና ሀገሪቱ የጋራ የሆነ ብሄራዊ ቋንቋ እንዳይኖራት መደረጉን እሰየው ለማለት ካልሆነ በስተቀር፣ የአማራ የበላይነት ቀርቶ ኦሮሞች መብታቸው የተከበረበት ዘመን ነው ያሉበት ምክንያት አልገባኝም። በምን መስፈርት ተንተርሰው ነው ድሮ አማራ የበላይ ነበር ያሉን? ከላይ እንዳስቀመጥኩት በያንዳንዱ ዘርዝረን አማራ የበላይ እንደነበር እሳቸውም ይሁን ሌላ ሊያስረዱኝ የሚችሉበት ተጨባጭ ነገር ሊያመጡ ግድ ይላቸዋል። ከላይ እንዳነሳሁት ድሮም አማራ ተጠቂና ከርታታ ነበረ ፤ አሁን ደግሞ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖበታል። ያም ሆኑ ድሮ ገዢ ነበር እየተባለ «የወደቀ ግንድ ምስማር ይበዛበታል » እንዲሉ ሁሉም በእርዳ ተራዳ እያጠቃው ነው። አማራው ደግሞ ለዚህ ያለው መልስ ዝምታ ሆነ። ልብ በሉ «ዝምታ ለበግም አልበጃት»። መጨረሻዋ መበላት ነው። ተማርን የምንል ሰዎችም በመረጃ ላይ፣ በመስፈርት ላይ ተንተርሰን እንናገር፣ እንጻፍ እንጂ፣ ከተራውና ከማይሙ ባልተለየ ሁኔታ ተባለ ብለን መጻፉና መናገሩ የሚያስንቀን ብቻ ሳይሆን፣ ያስጠላናል። አማራ ገዢ ነበር ወይንም ትግሬ ነው ለማለት፣ ምን ምን ነገሮች በዚያ ብሄር አባላት ሲካሄዱና ከብሄራቸው ጋር ሆነው ምን ሲያደርጉ ነው የሚለውን በግልጽ ማስቀመጥ አለብን። እኔ በግሌ ቢያንስ ዝርዝር መረጃ ለእያንዳንዱ ባላስቀምጥም፣ ምን ምን ተንተርሼ አሁን አንዳንዶች እንደሚሉት ሳይሆን፣ ትግሬ ሌላውን እየገዛ ነው፣ አማራ ድሮ አልገዛም፣ አሁንም ድሮም አማራው ተጨቋኝ ነው ያልኩበትን አስረድቻለሁ ብየ አስባለሁ። ሌላው ሕዝብ አማርኛ መናገሩ፣ አማራን ጨቋኝ ያስብለዋል ልትሉ ካልደፈራቹ በስተቀር።
ልብ ያለው ልብ ይበል!
አበበ ተድላ
ጥር 2008