Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ወቅታዊው የሀገራችን ፖለቲካና የአርበኛ ታጋዩ ትዝብት ከኤርትራ ( ክፍል ሁለት)

$
0
0

በኦሮሞውም ላይ ሆነ በሌላው ወገናችን ላይ በአማራ ስም ለደረሱ በደሎች በይፋ ይቅርታ የሚጠይቅና የሞራል ካሳን ከፍሎ ሰላምና እርቅ የሚያወርድ ሕዝብ የመረጠው መንግስታዊ ኣካል በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ይህንን ሃላፊነት ስለምን እኛው በኛው ስለኛው አናደርገውም? ብሄራዊ ዕርቅና መግባባትስ ላይ ለመድረስ ምን አዳገተን? ሌላስ ከኛ የቀረበና ሊያስታርቀን የሚችል ምን ሃይል ይኖራል ስል ጠየቅኩ።

ይህን ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩ ሰዎች ወይ ዝምታን መርጠዋል አሊያም የችግሩ አካል ሆነዋል ብዬ አስባለሁ።የብሄር ማንነት ስሜትን ገርተው፣ በወሬ እንጂ በተግባር ሊተረጉሙት ያልቻሉትን የትልቋን ዘመናዊና ውስብስብ ኢትዮጲያ ስዕል በአዕምሮአቸው መገንባት ላልቻሉ የመንፈስ ድኩማኖች እንዲህ ያለ የትልቅነት ሃላፊነትና አደራ ይከብዳቸው ይመስለኛል።

በአዕምሮአቸው የምትለዋን ቃል ያዙልኝ። ሁሉም ነገር የሚጠነሰሰው አዕምሮ ውስጥ ነውና።ፊዮዶር ዶስቶየቭስኪ ” በጎጆዎቹ ጣሪያ ላይ ያለውን እሳት ስለምን ለማጥፋት ትሞክራላችሁ። ሲጀመርም እሳቱ እኮ ያለው በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ነው’ ይላል። ክፉም ሆነ በጎ ነገር መጠንሰሻው የሰው አዕምሮ ውስጥ ነውና። የሰው አዕምሮ ደግሞ ትዝታዎችን የመንቀስ፣ የመምረጥ፣ አንዱን የማፈን አንዱን የመግለጥ ልዩ ችሎታ አለው። እስቲ ተወልደን ስናድግ ያሳለፍነውን መልካሙን ትዝታ ስለህዝብና አገር ስንል ከተደበቀበት ጓዳ ፈልፍለን አውጥተን እንመርምረው። ዕውነትን አንካዳት።”አገርን ጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ህብረተሰቡ ያለፈባቸውን የተወሰኑ ክፉ የጋራ ትዝታዎችንና ልምዶችን መርሳትና መቅበር ያስፈልገዋል” ይላል አንድ ማንነቱን የዘነጋሁት ሰው። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ አንድነትንና መከባበርን የሚሰብኩ ጠንካራ ትዝታዎቻችንን አጉልቶ ማሳየትና መስበክ ያስፈልጋል። እንኳንስ ስለመልካም አላማና ስለኢትዮጲያ ፍቅር ሲባል ይቅርና እነ አቶ መለስና ግብረአበሮቹ ጥላቻንና ልዩነትን የሚያበረታቱ የፈጠራ ታሪኮች ላይ ምን ያህል እንደሰሩ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። መጨረሻቸው ግን አላማረም። ትልቁን የትግራይ ሕዝብ ትንሽ አደረጉት፣ በገዛ አገሩ አሸማቀቁት፣ አሀዱ ብሎ ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር በደምና በአጥንቱ በፈጠራት ምድር ላይ ባይተዋር አስደረጉት! ልማቱና ዕድገቱ በጥርጣሬና በቅናት እንዲታይ ሆነ።(ትግራይ አድጋለች ወይንስ አላደገችም ወደሚለው ክርክር መግባት አልፈልግም። ካደገችም እሰየው እንኳንም አደገች!ወያኔ ሲወገድልን የትግራይ እድገት የሌላውም ዕድገት ነው ተብሎ እንደሚታይ አልጠራጠርም። ትግራይ የኢትዮጲያ፣ ኢትዮጲያም የትግራይ ናቸውና)። በጦርነት አውድማ ጀግንነታቸው ገዝፎ ተራራን አንቀጠቀጡ የተባሉት የሕወሃት ልጆች በምርጫ ካርድ ሲንቀጠቀጡ ታዩ። የስልጣን ማጣት ፍርሃታቸውም የለየለት አውሬ አድርጎአቸው ሕጻናትንና አዛውንትን ያለምንም ርሕራሄ በየአደባባዩ መዘረር ጀመሩ። ይህ ቁሻሻ ታሪክም ለዚህ እየሰፋና እየከፋ ላለ የትግራይ ሕዝብ ጥላቻ ተጨማሪ ቤንዚን ሆነ።  ግን ይህን ያደረገ የትግራይ ሕዝብ ነው ወይንስ ሕወሃት? እኔ ሕወሃት ነው ባይ ነኝ። የትግራይን ሕዝብ ከለላ አድርጎ የሚፈጽመው እኩይ ተግባር ነው ብዬ ከልቤ አምናለሁ። ሕዝብ እንደሕዝብ በተቀደደለት ቦይ መፍሰስ እንጂ የኑሮን ፍሬን ይዞ የሚፈላሰፍበት ጊዜውም ጉልበቱም የለውም። ፖለቲካውና ፍልስፍናው የልሂቃኖቹ ስራ ነው። እንደነ መለሰ ዜናዊ ወደ ክፉ መንገድ የሚወስዱ ወይንም እንደ ፕሮፍፌሰር ብርሃኑ ነጋ አይነቶቹ  ወደመልካሙና ወደተቀደሰው የሰላም መንገድ የሚያደርሱ ልሂቃኖቹ ናቸው። ለዚህም ነው “ሕዝብ የመሳሳት መብት አለው” ከሚለው የፕሮፌሰር መስፍን መልደማሪያምን አነጋገር የምጋራው። ልሂቃን ቢሳሳቱ ግን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላቸዋል።

ህወሃት በኢትዮጲያ ሕዝብ ላይ ይህን ያህል ግፍ እየሰራ እንዴት ለ25 ዓመት ቆየ? ያልሰማነው፣ ያላየነው፣ ባንድም ሆነ በሌላ ያልደረሰብን መከራ የለም እንደ ሕዝብ። ታዲያ እንዴት ታገስነው? ዕንቆቅልሹ ምን ላይ ነው? ነፍሳቸውን ይማረውና ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ በአንድ ወቅት የወያኔ/ሕወሃትን ስርአት የሚደግፉ ሶስት አይነት የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ ይላሉ። አንደኛ ዘረኛ የሆኑ ሰዎች( ዘመኑ የትግሬ ነው በሚል ልባቸው በትዕቢት ያበጠ የትግራይ ተወላጆች )፣ ሁለተኛ ጥቅመኞች ( የተለያየ ብሄር አባላት ቢሆኑም ሕወሃት/ወያኔ ለሚጥልላቸው ፍርፋሪ የተገዙ ሆድ አደሮች) እና በሶስተኛነት ደግሞ ምን እየተሰራ እንደሆነ ምንም ያልገባቸው ምስኪኖች ሲሉ ይከፍሏቸዋል።

የመጀመሪያዎቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ብዙም አያነጋግሩንም። በቅርቡ ዶ/ር ደብረጺዮን የትግራይ የበላይነት ብሎ ነገር የለም ሲል የቧለተውን ቧልት ወደጎን አድርገን፡ አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ፣ መከላከያ፣ የስለላና ደህንነት ተቋማት፣ የመሬት ቅርምትና የመሳሰለውን ማን እንደተቆጣጠረው እናውቃለን። ሁለተኛዎቹ ፍርፋሪ ለቃሚዎች አዲሱ ለገሰን፣ አባዱላ ገመዳን፣ ሽፈራው ሽጉጤን፣ አለምነህ መኮንንና የመሳሰሉትን ጥንብ አንሳዎች ያካትታል። የኔ ጥያቄ ሶስተኞቹ ላይ ነው። ወያኔ ሆን ብሎ በተለያዩ መንገዶች የሚሰራብን የልዩነት ፖለቲካና መዘዙ  እንደተጠበቀ ሆኖ( በፌስ ቡክና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ በደንብ ሰልጥነው ስማቸውን  እየቀያየሩ እርስ በርስ የሚያባሉንን መሰሪዎች ማለቴ ነው) አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የወያኔ/ሕወሃትን ድብቅና ግልጽ አጀንዳ የሚያራምዱ ብዙ ምስኪኖች እንዳሉ ታዝበናል። እነኚህ ሰዎች ደግሞ ትግላችንን በጣም እየጎዱትና እያጓተቱት ነው ብዬ አምናለሁ። ስለ ዕዉነት ለመናገር ብዙዎቹ ኢትዮጲያዊነት በሚለው ጉዳይ ላይ ችግር የለባቸውም። ግን ይህንን ኢትዮጲያዊነት የሚያዩበት መነጽር የተንሸዋረረ ይመስለኛል። ዐይን ሲደክም መነጽር መቀየር እንዳለበት ሁሉ እነኚህም ወገኖቼ መነጥራቸውን የመቀየሪያ ጊዜአቸው የደረሰ ይመስለኛል።። ምክንያቱም ወያኔ በቀደደልን የልዩነት ቦይ መፍሰስ ብቻ ሳይሆን ጭራሹን ቦዩን አስፍተንና አጥልቀን በዛው የጥፋት መንገድ መንጎድ ከጀመርን የኢትዮጲያ ሕዝብ “አረ ወያኔ ይማረኝ” የሚልበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ እፈራለሁ። የዚህ የዚህ የለመድነውን ወያኔን ይዘን እንጓዝ የሚል የተሸናፊነት፣ የባርነት አስተሳሰብ ማለት ነው።

አዕምሮ ማለት የሕይወት ልምድንና ትዝታን በስርአት ማቀናጀት  ይመስለኛል። ሚዛናዊ ወይንም የተዛባ አዕምሮ የዚህ ቅንጅት ስኬትና ድክመት ዉጤት ይሆናል ማለት ነው። እዚህ ላይ አንድ የራሴን የልጅነት ተሞክሮ እንዳካፍል ፈቀድኩ።

በደርግ ዘመን አባታችን በፖለቲካ ሰበብ ለሁለት አመት ታስሮ ነበር። አምስት ለአቅመ አዳም ያልደረስን የጨርቆስ ሕጻናትን የማሳደግ ሃላፊነት በብቸኛዋ እናታችን ትከሻ ላይ ወደቀ። ለክፉ ቀን ተብሎ የሚቀመጥ የቁጠባ ባህል በሌለበት ቤተሰብና ማህበረሰብ ውስጥ የአባታችን ድንገት መታሰር ወዲያዉኑ ለረሀብ አጋለጠን። ምስኪኗ እናታችን ምኑን ከምን እንደምታደርገው ግራ ገባት። አንድ ጉሊት ገበያ ውስጥ እህልና ጥራጥሬ በመሸጥ የሚተዳደሩ አቦይ ገብረሕይወት የሚባሉ ነጋዴ ነበሩ። የትግራይ ተወላጅ መሆናቸውን በኋላ ላይ ነው ያወቅነው። እናም እናታችን ለብዙ ጊዜ እህል የምትሸምተው ከኚህ ሰው ላይ ነበርና የሷ ድንገት ከገበያቸው መጥፋት አሳስቧቸው ለምን እንደጠፋች ይጠይቋታል። እሷም ባለቤቷ (አባታችን) መታሰሩንና እህል ለመሸመትም እንደዱሮው አቅሙ እንደሌላት ታስረዳቸዋለች። አቦይ ገብረሕይወት በጣም በመበሳጨት ” ምነው ገነት እንዲህ ታደርጊያለሽ? ነውር አይደለም? ይሄ መንግስት እኮ በሁላችንም ላይ እኩል የመጣብን ጠላት ነው። ላንቺ ብቻ አይምሰልሽ። ከዚህ ወር ጀምሮ እንደዱሮሽ በየወሩ የሚያስፈልግሽን እህል ውሰጂ። ገንዘብ ስታገኚ ወደፊት ትከፍይኛለሽ” ነበር ያሉት እኚህ አባት። ዛሬ ወያኔ እንዲጠሉ ያደረጋቸው የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጲያዊ አባት። አለምንም ማጋነን ለአምስት ሕጻናት ወንድም እህቶቼና ለእናታችን ሕይወት መቆየት አቦይ ገብረሕይወት የተጫወቱት ሚና ትልቅ ነበር።

 

ከረዥም ዘመን በኋላ ወደኢትዮጲያ ለዕረፍት በሄድኩበት ጊዜ ምስጋና ላቀርብላቸው ባጠያይቅ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ሰማሁ። እግዜብሄር ነፍሳቸውን ይማር! ይህ ፍቅርና መተሳሰብ አሁን አለን? ከሌለስ እንዴት ብለን ነው ከቀበርንበት ጓዳ ፈልገን አውጥተን ዳግም የሕይወታችን መርህ፣ የማህበረሰባችን እሴት የምናደርገው?

 

እንግዲህ እኔ ያሳለፍኩትና ላስታውሰውም የምፈልገው ትዝታዬ እንዲህ ያለውን የደግነትና የመተሳሰብ ባህላችንን እንጂ ዛሬ አንዱን የወርቅ ፍልቃቂ አንዱን ርካሽ እያደረጉ የጥላቻ መርዛቸውን ስለሚተፉብን የእፉኝት ልጆች አይደለም። የአቦይ ገብረሕይወትን ታሪክ እንደምሳሌ አነሳሁት እንጂ ብዙዎቻችን ይህን የመሳሰሉ ጥሩ ትዝታዎች በልባችን ጓዳ እንዳሉ አውቃለሁ። ሳንፈራና ሳናፍርበት ዳግመኛ አደባባይ እናውጣቸውና እንኑራቸው!

 

ሀገራችን ለተዘፈቀችበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጠያቂዎቹ  እነ እገሌ እነ እገሌ ናቸው ብሎ የመፍረድ ሃሳቡም ሆነ ፍላጎቱ የለኝም። ሁላችንም ብንሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃችን አለበት። ማንም ከተጠያቂነት የሚድን የለም። እኔ ንጹህ ነኝ የሚል ቢኖር እንኳ እሱ ያንቀላፋ ነው። ስለዚህም ይመስለኛል አሁንም ባለቅኔው ጸጋዬ እንመርመር ሲል ደጋግሞ ሲሞግተን የኖረው።

መርገምት አለ በደማችን ዉስጥ

መመርመር አለብን በግልጥ።

ኢትዮጲያዊ የምንባል ዘር

ሳንተላለቅ ባስቸኳይ፣ ተይዘን ቶሎ እንመርመር።

ከሶማሊያም ከዩጎዝላቪያም

ይብሳል የኛዉ አሲዳም!……

እንመርመር

መቅሰፍት አለ ደማችን ዉስጥ

ቃል የሚያስክድ ልሣነ-ብልጥ

መሃላ የሚያስገለብጥ

ሽምጥጥ የሚያስደርግ ባንዴ

የደም ጦስ የስልጣን ዉርዴ!……..( ሀሁ ወይስ ፐፑ)

 

 

የብሄር ፖለቲካው ተጧጡፏል። እጅግ የሚገርመው ከነኚህ የብሄር ጦረኞች ውስጥ የተወሰኑት አዛውንቶች መሆናቸው ናቸው። እርግጥ አንዳንድ በተለይ ኦሮሞንና አማራን እንወአክላለን የሚሉ “መሃላ ገልባጭ፣ ልሳነ ብልጥ አሲዳም ብላቴኖች” እዚህም እዚያም ባይጠፉም። አዛዉንቶቹ ግን በኔ እይታ የአቦይ ስብሃት የመንፈስና የስጋ መንትያዎች ይመስሉኛል። “የሃሰት ከንፈር፣ የተጣመመ አንደበት የነርሱ መገለጫዎች ናቸው፣ ክፉ ካላደረጉ አይተኙም፣ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳል” እንዲል መጽሃፉ። ከፍቅር ይልቅ ለጥላቻ፣ ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት፣ከትዕግስት ይልቅ ለስም ማጥፋት፣  ከሕይወት ይልቅ ለመቃብር የቀረቡ። ከዚህ አለም ይልቅ የቀጣዩ አለም አፉን ከፍቶ የሚጠብቃቸው ። ይህ ዕውነት ግን የሚረብሻቸው አይመስልም። እቺን ምድር ለዘላለሙ ተለይተዋት ሲሄዱም በነሱ ጦስ ከዘመን ዘመን የሚሻገረው የጥላቻና የቂም በቀል ድግስ ብዙም አያስፈራቸውም። እንደ ሮማው ቄሳር ኔሮ ኢትዮጲያ ስትነድና ስትቃጠል ኮረብታ ላይ ቁጭ ብለው ክራር እየመቱ ይዝናናሉ። ” ኑና የስራችንን ውጤት ተመልከቱ። አርበኞች ግንቦት 7ን አንኮታኮትነው፣ መሪዎቻቸውንም እንዲሁ አሰናክለናቸዋል። አማሮች ደስ ይበላችሁ! ኦሮሞም እልል በል!” እያሉ ያሽካካሉ። ወያኔ የተካነበትን የዘረኝነት እስክስታ አሻሽለው ያስነኩታል። ወጣት ተተኪዎቻቸውንም ያለመታከት ያሰለጥናሉ። መተካካት ይሏል ይህ ነው።

 

ይህ ሊሆን የቻለው ግን በነዚህ ሰዎች ፍላጎትና ጥረት ብቻ ነው ብዬ አላስብም። ኢትዮጲያንና ኢትዮጲያዊያንን በእኩል አይን አይቼ፣ በእኩል ሚዛን አስቀምጬ ማንም በማንም ላይ የማይሰለጥንባት፣ የበላይና የበታችነት በሽታ አካቶ የጠፋባትን ሀገርና ህዝብ ለማየት እመኛለሁ የሚለው ምሁር ድምጹን በማጥፋቱና ከጨዋታው ራሱን በማግለሉ ብቻ ይመስለኛል። በተለይም በአማራ ልሂቃን ላይ ይህ ችግር ይበልጥ ይስተዋላል። በቅርቡ በናትናኤል መኮንን ፌስ ቡክ ላይ ያነበብኩት ነገር ሃሳቤን ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። “ከፍተኝ የሆነ የኤሊት ክፍተት ያለበት የወል ስብስብ አማራ ብቻ ነው”ይላል ጸሃፊው። በትምህርት የበሰሉ፣ ቀላል የማይባል የሕይወት ተሞክሮ በሀገርና በውጪው አለም ያካበቱ፣ ታሪክን ያነበቡ፣ ክፉና ደጉን ዉሸትና ዕውነቱን የለዩና ያለፈ የታሪክ ጠባሳን እየገሸለጡ ከሚያስላዝኑንና ከሚያሸማቅቁን መንደረኞች ይልቅ የተሻለ የወደፊት ተስፋና ራዕይ ሊያመላክቱን ይችሉ የነበሩ  የዘመናችን ሙሴዎች ከነአሮኖቻቸው መሰወር ዋነኛው ምክንያት ነው ብዬ አስባለህ። እንደ ኢትዮጲያ በምሁሮቿ የተካደች አገር በዚህ አለም ላይ የለችም ይላል ፕሮፌሰር ብርሃኑ። እውነት ነው።ይህ የጠንካራና አገር ወዳድ ምሁራን ክፍተት በመፈጠሩም ይመስለኛል ” የጋለሞታን ቤት ማንም ይዘዝበት” እንዲሉ ኢትዮጲያን ባል መሳይ ደላላዎች ብቻዋን አገኟትና እንዳሻቸው ይባልጉባት ገቡ። ኢትዮጲያ የጎረምሶችና የወሲብ ደላላዎች መጫወቻ ሆነች። ይህ መቀየር አለበት። የሸሹትም መመለስ አለባቸው። ልመና ሳይሆን ጥሪ ነው። የሕሊና ትዕዛዝም ጭምር። የውዴታ ግዴታ እንዲሉ!

 

ካላሰለቸዋችሁ በቀር አንድ ሌላ የመጨረሻ ልምዴንም ላካፍላችሁ። ማየት ማመን ነው። አንዳንዶች የኤርትራን መንግስት (ሻዕቢያን) ክፉኛ ያብጠለጥሉታል። የድሮ ታሪክና ቁስልም አንስተው መታመን የሌለበት ለኢትዮጲያ መፍረስ የማይተኛ ጠላት ነው ይላሉ። ማየት ማመን ነው። ይህንን የነዚህን ሰዎች ውንጀላና ጥርጣሬ እኔ አልጋራውም። በፖለቲካ አለም ውስጥ ቋሚ ወዳጅ ወይንም ቋሚ ጠላት የለም ከሚለው የተለመደ አመለካከት ባሻገር የሰው ልጅ ከዕድሜና ከሕይወት ተሞክሮ መቀየር  መቻሉ ይመስለኛል ከእንስሳት የሚለየው። ከብዙ ኤርትራዊያን ጋር ባደረግኩት የግልም ሆነ የቡድን ውይይት ዋናው ምኞታቸው ከኢትዮጲያ ህዝብ ጋር በሰላምና በእኩልነት ላይ የተቃኘ መልካም ጉርብትና ብቻና ብቻ እንደሆነ እመሰክራለሁ። ሁሉንም የፖለቲካ ልዩነት በታንክና በጠመንጃ የመፍታቱ የሞኝነት ዘመን አስተሳሰብ ጊዜው አልፎበታል። ያንን ለነጄኔራል ጻድቃንና ለነሱ የገደል ማሚቶ ለሆነው ሃይለማሪያም ደሳለኝ እንተውላቸው። በኤርትራ መንግስትና ወደፊት በትግላችን በምትመሰረተው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጲያ መካከል የሰላም ጉርብትናና የጋራ ብልጽግና ዋናው መታወቂያችን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ።

 

ትግላችንን በተመለከተም የኤርትራ መንግስትም ሆነ ህዝብ በነሱ ምድር ውስጥ ላለ ተቃዋሚ ሃይል በሙሉ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሁሉም የራሱን ትግል በነጻነት እንዲያራምድ ፈቃዳቸው እንደሆነ ታዝቤአለሁ። ከዚያም አልፎ ያሉበት የኢኮኖሚ ውስንነት ሳያግዳቸው በተለያይ መንገድ ድጋፋቸውን እየሰጡም እንዳለ መመስከር እችላለሁ። ለከፍተኛ ህክምናም ሆነ ለደህንነታቸው አስጊ ናቸው ለተባሉ የተቃዋሚ አመራሮችም ወደሌላ ሃገር ለህክምናም ሆነ ለህይወት ዋስትና አስፈላጊውን ትብብር አድርገው በሰላም ሲሸኟቸውም አይቻለሁ።( ዘመነ ካሴ የቅርብ ምስክር መሆኑን ልብ ይሏል)። በእርግጥ የኤርትራ መንግስት እንደመንግስት የራሱ የሆነ የጥቅም ፍላጎትና የደህንነት ስጋቶች ይኖሩበታል። ከወያኔ ወዲያ ምን አይነት ኢትዮጲያ ትመጣለች? ምን አይነት ምስራቅ አፍሪካ? በሁለታችን አገሮች መካከልስ ምን አይነት ግንኙነትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሊያሳስበው እንደሚችል ይታወቃል። ከዚህ ተፈጥሮአዊ ከሆነ የፖለቲካና የደህንነት ስሌት ውጪ ኤርትራ ለኛ ክፉ ሆናብናለች ማለት በዕውነት ላይ እንደመሸፈጥ፣ በጓደኛህ ላይ ክህደትን እንደመፈጸም፣ እህል ላበደረ ጠጠር መመለስ እንደማለት ነው። በክፉ ቀን የደረሰችልን አገር ናት።  እናከብራታለን፣ እንወዳታለን። ታዲያ በምን ተአምር ነው ምንም ስላላየው ነገር በወሬና አሉባልታ ብቻ ራሱን እየነዳና እየተነዳ ይሄንን መንግስትና ህዝብ በጠላትነት የሚፈርጀው?  በክፋት የሚያብጠለጥለው? በርግጥ ይሄ የጤና ነው? እባካችሁ ስለኛ ክብርና የአዕምሮ ሰላም ስትሉ ከእንደዚህ አይነት የሰይጣን ድርጊት ተቆጠቡልን!

 

አንባቢ ሆይ አደራህን በከንቱ ወሬ እንዳትወናበድ! እንዳትሸበር! እኔ አርበኛ ታጋይ ዕዝራ ዘለቀ እዚህ ኤርትራ ውስጥ ስላለው ነገር የምናገር በህይወት ያለሁ እስካሁንም ያልሞትኩ ምስክር ነኝ።

 

 

ትናትናም ዛሬም ነገም ለዘለአለሙ ኢትዮጲያዊ

 

አርበኛ ታጋይ ዕዝራ አስቻለው ዘለቀ

 

ከኤርትራ

 

The post ወቅታዊው የሀገራችን ፖለቲካና የአርበኛ ታጋዩ ትዝብት ከኤርትራ ( ክፍል ሁለት) appeared first on ሳተናው: Ethiopian Amharic News | Breaking News: Your right to know!.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles