ላለፉት ተከታታይ አመታት ሰርክ ስለእናቴ አስባለሁ፤ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ስለሷ መንፈሰ ጠንካራነት ለመመስከር አንደበቴ ይደነቃቀፋል። ብእሬ ይዝላል! እንደው ባጭሩ እማዋይሽ የኔ፣ የምንግዜም ጀግና፣ ልጆቿን የሀገር ፍቅርን እና ከህዝብ. የመወገንን ፅናት፤ በአግባቡ ያስተማረች እና ምሳሌ እንደሆነች እኔ ልጇ ህያው ምስክር ነኝ።
እስርንና መከራን ለመቀበል መዘጋጀት፣ ሞትን ከመጋፈጥ በላይ እንደሚከብድ ብትረዳም ቅሉ መከራውን ለመቀበል ያልሰነፈች ብርቱ፤ የእናትነት ፍቅሯን ብቻ ሳይሆን ፅኑ የሀገር ፍቅሯን ያጋባችብኝ፤ ዘመኗን ሙሉ ከበዳዮች ያልወገነች ብርቅ ናት እናቴ።
እማዋይሽ! በዚህ ጨቋኝ ስርዓት ስር ለመኖር ማንነቷ የበቀለችበት ጀግና አብቃይ ምድር በጅ አይላትም፡፡ እንደ ማንም እናት ሰቆቃን መቀበል ምርጫዋም አይደለም፤ በተመቸ ቤትና በሞቀ አልጋ ላይ ከልጆቿ ጋር ማሳለፍንም ከቶ አትጠላም፤ ከዚህ በላይ ግን የታመነችለት የእውነት እዳ በእጅጉ ያስጨንቃታል። ከሴትነቷ በላይ የገዘፈው ልበ-ሙሉነቷ ጭቆናን ለመቀበል አሻፈረኝ እንድትል አድርጓታል፡፡
እናቴ ሆይ ዛሬ በጉልበተኞች እጅ ብትገኝም፤ ነገ ዘመን ሲፈቅድ አዋቂዎችና አስተዋዮች ወደ አደባባዩ ሲመጡ ተገቢውን ክብር ማግኘትሽ አይቀርም፤ በእውነተኞቹ ዘንድ አንቺም በፅናትሽ ትወደሻለሽ።
እናቴ ሆይ በጣም ናፍቀሽኛል! በጣም!!! ግን ምን ማድረግ እችላለሁ?
ስቃይሽ፣ እየከፈልሽ ያለውን መከራ ሳስበው…! ለሴት ክብር ባለው ማህበረሰብ ውስጥ እንደመብቀላችን፤ በእናትና በሴት ላይ ፈፅሞ ይደረጋል ተብሎ የማይታመን በደል ተፈፅሞብሻል፤ ከሁሉም ከሁሉም ልጅነቴን የምናፍቅባቸው ያለስስት የጠባሁት ጡቶችሽ በዱላ ተደብድበዋል! እስካሁንም ህመሙ እያሰቃየሽ ነው። ህመምሽ ያለጥርጥር የኔም ነው። ለኔ ከሌላው ስቃይሽ ሁሉ ይልቅ ይህንን ሳስብ ሆድ ይብሰኛል! አቅም አልባነቴ ጎልቶ ይሰማኛል። ይህን ስቃይ ያቀመሱሽ ከምን ተፈጠሩ? ብዬ እንድጠይቅ ያደርገኛል።
መልካም መጥፎን ድል እንዲነሳና ያዘኑ ልቦች እንደሚፅናኑ በእጅጉ ኣምናለሁ! እናም ከጥንካሬሽ ተለቅቼ በመንገድሽ እፀናለሁ… መልካም ነገን በማሰብ እፅናናለሁ
The post እናቴ ሆይ ናፍቀሽኛል! appeared first on ሳተናው: Ethiopian Amharic News | Breaking News: Your right to know!.