Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የተቃዋሚዎች ትብብር የሚያንገበግባቸው የሽፍንፍን ኢህአዴጎች መፍጨርጨር ሲጋለጥ

$
0
0


ታህሳስ 27 ቀን 2008 (ከበጽናቱ አሸናፊ ለመድረክ ጽ/ቤት የተላከ)
እ. ኤ. አ. ጃንዌሪ 3 ቀን 2016 ዓ ም “የመድረክ መሪው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለአንድነት ትግሉ እንቅፋት ከመሆናቸውም በላይ የኦሮሞ ሕዝብን ተቃውሞ ለመሸፋፈን እየሞከሩ ሲሉ የመድረክ አባላት ወነጀሉ” በሚል ርዕስ የመድረክንና የሰማያዊ ፓርቲን ግንኙነት፣ የኦሮሞ ሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴና የኢማዴ-ደህአፓና የአረና ትግራይን የውሕደት እንቅስቃሴ አስመልክቶ በምኒሊክ ሳልሳዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ ሰሞኑን አነበብኩት፡፡ ጽሑፉን አንብቤ የተረዳሁት እውነት ቢኖር የተቃዋሚ ፓርቲዎች የትብብር ጥረት ምን ያህል የኢህአድጎችን ሰፈር እንደሚረብሽና እንደሚያስጨንቃቸው ነው፡፡ ጽሑፉ ሽፍንፍን የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዲስቶች የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የትብብር ዜና ሲሰሙ የእግር እሳት ሆኖባቸው እያቃጠላቸውና እያንገበገባቸው፣ እንደ እሬትም እየመረራቸው ይህንኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀና ጥረት በተልካሻ አሉባልታቸው ለማደናቀፍ የሚችሉ መስሎአቸው እያደረጉ ያሉት መፍጨርጨር እንደሆነምይዘቱን በጥሞና ለገመገመ ሰው ሁሉ ግልጽ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡


ይህ የአሉባታ ጽሑፍ ላይ ላዩን ሲታይ መድረክንና የወቅቱን የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን ለማጥላላት የተነሱ ሰዎች ያዘጋጁት ቢመስልም ከጽሑፉ ማጠቃለያ ለመረዳት እንደሚቻለው ዋና ዓላማው በአሁኑ ወቅት ሰማያዊ ፓርቲ ከመድረክ ጋር ተባብሮ አብሮ ለመሥራት የያዘው አቋም እንዳስጨነቃቸውና እንዳንገበገባቸው፣ ስለሆነም ይህንኑ ለማደናቀፍ የተነሱ መሆኑን የሚያጋልጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው ካለአንዳች አፍረት ሰማያዊ ፓርቲ በአንጻራዊነት ጠንካር ድርጅታዊ አቋም ያላቸውንና በአቋማቸው ጽናት በተግባር የተፈተኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ካሰባሰበው መድረክ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት ትቶ ከተለያዩ ፓርቲዎች ከተበታተኑ ሰዎች ጋር ብቻ እንዲሠራ መሰሪ ምክራቸውን መለገስ የጀመሩት፡፡ ጸሐፊው በጽሑፉ የመጀመሪያ ፓራግራፍ ላይ “ትግሉ የነፃነት፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ ሆኖ ባለበት በተናጥል የሚደረግ ትግል ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ለጥቃት እየዳረገን ባለበት” በማለት የወቅቱን የትግል ትብብር አስፈላጊነት ከገለጸ በኋላ “በአንድ አፍ ሁለት ምላስ” እንደሚባለው ይህንን በሚቃረን መልኩ በማጠቃለያው ባስቀመጠው የመፍትሔ ሀሳብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚከፋፍል ፀረ-ትብብር አቋም ማንጸባረቁ ብቻ የተሸፋፈነ የኢህአዴጎች ሥራ መሆኑን በሚገባ ይነግረናል፡፡
በበኩሌ የመድረክም ሆነ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ይህንን የመሰሪዎችን መልዕክት

በቀላሉ በመረዳት የኢህአዴግ መልዕክተኞች እነዚህን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመከፋፈል እያደረጉ ያሉትን ደካማና ከንቱ መፍጨርጨር ዋጋ አሳጥተው ሥራቸውን በመልካም ግንኙነትና ትብብር እንደሚቀጥሉና ሌሎች ሐቀኛ ተቃዋሚዎችም የትብብራቸው አካል በመሆን ትግሉን ለማጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንዲያበረክቱ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ሙሉ እምነቴ ነው፡፡በጽሑፉ የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ለአንድነት ትግሉ እንቅፋት እንደሆኑና የወቅቱን የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ ለመሸፋፈን እየሞከሩ እንደሆነ በማስመሰል የቀረበው ሀሳብም በተጨባጭ ካለው የሊቀመንበሩ ተግባራዊ ሥራዎች ጋር በፍጽም የሚቃረንና ከከፋፋዮቹ ከንቱ የመከፋፈል ምኞት የመነጨ ባዶ አሉባልታ እንጂ የመድረክ አባላት አቋም እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁኝ፡፡ ለዚሁም ተጨባጩ ማስረጃ ፕሮፌሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተባበረ የጋራ አቋም አምባገነኑን ሥርዓት እንዲፋለሙ በማስተባበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፆ ሲያበረክቱ የቆዩ በመሆናቸው በተደጋጋሚ የኢህአዴግ ሽፍንፍን ፕሮፓጋንዲስቶች ኢላማ ሆነው መቆየታቸው ነው፡፡ ፕ/ሩ ተቃዋሚዎችን ለማስተባበር በተንቀሳቀሱ ቁጥር ይሄው ሥራቸው ለኢህአዴጎች የእግር እሳት ሆኖ እያንገበገባቸው አምባገነን ገዥዎቻችን መሰሪ ፕሮፓጋንድስቶችን በማሰማራት የትብብር እንቅስቃሴዎችን ባለ በሌለ ኃይላቸው ለማክሸፍ ስንቀሳቀሱ እንደኖሩም በሚገባ የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም የእነዚህ የተሸፋፈኑ የኢህአዴግ ጄሌዎች አሉባልታ በፕሮፌሰሩ ላይ ቢያተኩርባቸው ነገሩ የሚያስደንቅም አዲስም አይደለም፡፡ ፕ/ሩ በሕዝቦቹዋ እኩልነት ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያ አንድነትና ትክክለኛ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲሰፍን ባላቸው ጽኑ አቋም ለዚሁም ትክክለኛ ዓላማ ጊዜአቸውንና ጉልበታቸውን በመሰዋት የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ለኢህአዴጎችና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለማይሹ ኃይሎች የእራስ ምትሀትና የእግር እሳት ስለሆነባቸው ባለፉት 25 ዓመታት እንደዚህ ዓይነት አንዳችም ጭብጥ የሌላቸውን አሉባልታዎች ሲያሰራጩ እያየን ሲንታዘብ የቆየነው ጉዳይ ስለሆነ የአሁኖቹ የምኒሊክ ሳልሳዊ ፌስቡክ ጸሐፊዎችም የማን መልዕክተኞች እንደሆኑ ለመረዳት የሚያስቸግር ጉዳይ አይደለም፡፡


የኦሮሞ ሕዝብን ፍትሐዊና ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሚመለከትም የመድረክ ሊቀመንበርም ሆኑ ሌሎች የመድረክ አመራር አባላት የኦሮሞ ሕዝብ ሕጋዊና ፍትሐዊ ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ እንዲያገኝ ከኦፌኮ ጋር የጋራ አቋም በመያዝና ወቅታዊ መረጃዎችንም በመለዋወጥ በጋራ መግለጫዎችን በማውጣትና ሰላማዊ ሰልፍንም ለማደራጀት ጥረት በማድረግ (በገዥው ፓርቲ ቢከለከሉም) እጅ ለእጅ ተያይዘው በመታገል ላይ ናቸው፡፡ ለማንኛውም የኦሮሞ ሕዝብ የፍትሐዊ፣ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉ እውነተኛ ወዳጅና አጋር ማን እንደሆነና ትግሉን ከፍላጎቱና ዓላማው ውጭ ለመጎተትና ለማሰናከል እየተፍጨረጨሩ ያሉ አፈጮሌ መሰሪዎች እነማን እንደሆኑ በሚገባ ለይቶና ጠንቅቆ የሚያውቅ ስለሆነ ለከፋፋዮች ወሬና አሉባልታ ጆሮውን ይሰጣል ብዬ አልገምትምና ሙከራቸው ከንቱ ሆኖ እንደሚቀር አልጠራጠርም፡፡ ኦፌኮና ሌሎች የመድረክ አባል ድርጅቶችም በመሰሪዎቹ ደካማ አሉባልታ የሚከፋፈሉ ሳይሆኑ በስትራቴጂያዊ የጋራ ዓላማና የትግል አጋርነት ላይ የተመሠረተና በትግልም የተፈተነ ግንኙነት ያዳበሩ ስለሆኑ የከፋፋቹ ርካሽ አሉባልታ በጭራሽ ሊከፋፍለቸው አይችልም ብዬ አምናለሁ፡፡


በአሁኑ ወቅት የተቃዋሚዎች አንድነት የሚያስደነብራቸውን ኢህአዴጎች እያስጨነቃቸው ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ የኢማዴ- ደህአፓና የአረና ትግራይ የውሕደት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስለዚህም ነው እነዚህ ሽፍንፍን የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዲስቶች በተቃዋሚ ጎራ ያሉ ሰዎች መስለው በሁለቱ ፓርቲዎች የውሕደት እንቅስቃሴ ላይ ርካሽ ማጥላላት የተያያዙት፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የሕዝቦች እኩልነት በተግባር እንዲረጋገጥ፣ የዜግነት መብት በትክክል ተግባራዊ እንዲሆንና በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲሰፍንና የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ተወግዶ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲሰፍን ለማድረግ በያዙት ጠንካራ የጋራ አቋም ላይ ተመሥርተው የጀመሩት የውሕደት እንቅስቃሴ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይወሰን ተመሳሳይ አላማ አንግበው የተነሱትን ሁሉ በማቀፍ ጠንካራ ሕብረብሔራዊ፣ ሀገርአቀፍና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሚያስገኝ የተረዱት ኢህአዴጎችና ሌሎች ፀረ-አንድነት ኃይሎች ያሰኛቸውን አሉባልታ ቢነዙም ፓርቲዎቹና አባላቶቻቸው የጀመሩትን ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ዓላማ በቆራጥነት ተግባራዊ ያደርጋሉ እንጂ በወረኞቹ ርካሽ አሉባልታ ከትክክለኛ አቋማቸው ዝንፍ እንደማይሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡

The post የተቃዋሚዎች ትብብር የሚያንገበግባቸው የሽፍንፍን ኢህአዴጎች መፍጨርጨር ሲጋለጥ appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles