(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ ሰኔ ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)
ሐራ ዘተዋሕዶ
- ቅዱስ ሲኖዶሱ ለአዊ ዞን ሀገረ ስብከት በከፍተኛ ድጋፍ መርጧቸው ነበር
- 27 ዓመታት ባስቆጠሩበት የኢየሩሳሌም ገዳማት፣ በማገልገል ላይ ይገኛሉ
- “የአበውን አሠረ ፍኖት የተከለተ አቋምና ምላሽ ነው”/አስተያየት ሰጭዎች/
- የሐምሌ ተሿሚዎችን ቁጥር በአንድ ይቀንሰዋል፤ በጥቅምቱ ጉባኤ ይታያል
- ቋሚ ሲኖዶስ፣ የዶ/ር አባ ኃይለ ማርያምን ምደባ ደቡብ ጎንደረር አደረገ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ እንዲሾሙ በቅርቡ ከመረጣቸው ቆሞሳት አንዱ፣ “የጀመርኩት ሥራ አለብኝ” በሚል ዕጩነቱን እንዳልተቀበሉት፣ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች አስታወቁ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ግንቦት 10 ቀን ባካሔደው ምርጫ ተወዳድረው ካለፉት ዕጩ ቆሞሳት አንዱ የኾኑት፣ አባ ገብረ ሥላሴ ተስፋ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት አገልጋይ እንደኾኑና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በደብዳቤና በስልክ ለተላለፈላቸው ጥሪ፣ የጀመሩት ሥራ እንዳለ በመጥቀስ፣ ዕጩነቱን እንደማይቀበሉትና በሹመቱም ለመገኘት እንደማይችሉ ማስታወቃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
በዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት የምርጫ ሥርዓት ደንብ መሠረት፣ በአ/አበባ ሀገረ ስብከት፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ከኾኑት መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ጋራ ለአዊ ዞን ሀገረ ስብከት ለውድድር የቀረቡት አባ ገብረ ሥላሴ፣ ድምፅ ከሰጡት 38 አጠቃላይ የምልአተ ጉባኤው አባላት 31ዱን በማግኘት በከፍተኛ ድጋፍ ተመርጠው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ለሌሎች ተሿሚዎች እንደተደረገው ኹሉ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ፥ በተመረጡበት የአዊ ዞን ሀገረ ስብከት ዕጩ ቆሞስ አድርጎ መድቦ በመንበረ ፓትርያርኩ ማረፊያ ቤት ቁጥር 60 በመስጠት ጥሪ ቢያደርግላቸውም፣ እስከ አኹን በገዳማቱ ካላቸው ሓላፊነት በላይ ሌላ ለመጨመር እንደማይችሉ በመግለጽ ዕጩነቱን እንዳልተቀበሉት ለቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ዘግይተው በሰጡት ምላሽ አስታውቀዋል፡፡
“ከዚኽ በላይ ሓላፊነት ለመጨመር በቁ አይደለኹም፤ በተሰጠኝ የክህነት ሥልጣን ከሠራኹበት ይበቃል፤” የሚል የአበውን አሠረ ፍኖት የተከለተ አቋምና ምላሽ እንዳላቸው ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡
በቦታቸው ስለሚተኩት ዕጩ፣ ለጊዜው የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት በቀጣይነት ይካሔዳል ከተባለው ምደባ ጋራ ጉዳዩ አብሮ እንደሚታይ ተነግሯል፡፡ የአዊ ዞን ሀገረ ስብከትን በአኹኑ ወቅት ደርበው እየመሩ ያሉት፣ የባሕር ዳር፣ መተከልና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተጠቁመው፣ ለኤጲስ ቆጶስነት የታጩት አባ ገብረ ሥላሴ ተስፋ ዘኢየሩሳሌም፣ በሞያቸው የቅኔ መምህር ናቸው፤ በወንበር አስተምረዋል፤ ትርጓሜም መጻሕፍትም ያውቃሉ፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤትም ተምረዋል፡፡
ወደ ኢየሩሳሌም ገዳማት በ1982 ዓ.ም. አምርተው በዚያ 27 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በዴር ሡልጣን ገዳም እና በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት፥ ቄሰ ገበዝ፣ መጋቤ(ከ1998 እስከ 2000 ዓ.ም.)፣ ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም ኾነው አገልግለዋል፤ ዐረብኛ፣ ዕብራይስጥ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው በመናገራቸው ከእስራኤል መንግሥትና ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋራ የሚደረጉ የገዳማቱንና የማኅበሩን ጉዳዮች እንደ ፕሮቶኮልና የውጭ ግንኙነት ኾነው በማስፈጸም ሠርተዋል፤ አኹንም በተለይ በዚኹ ተግባር እየረዱ ይገኛሉ፡፡
ለገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት ባላቸው ቅንነትና ታዛዥነት ይታወቃሉ፤ “በማንኛውም ሥራ ሲመደቡ እሺታን እንጂ እምቢን አያውቁትም” ይሏቸዋል፡፡ በማኅበር ካልኾነ በቀር በቤታቸው አንድም የመመገቢያ ዕቃ እንኳ የሌላቸው መኾኑ ለሥርዓተ ገዳሙ ያላቸውን ታማኝነት ያሳያል፡፡ በስብከተ ወንጌልና በሰንበት ት/ቤት አገልግሎቶች አዘውትረው ይገኛሉ፡፡ ማኅበረ ምእመናንን በእጅጉ ያከብራሉ፡፡ በጸሎተ ቅዳሴና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በማስፈጸም የተጉ ናቸው፡፡ መጻሕፍትን መመልከት ያዘወትራሉ፤ ለወቅታዊ መረጃዎችም ቅርብ ናቸው፡፡
ሊቃነ ጰጳሳት በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት ምደባ ለማካሔድ፣ ከሀገር ውስጥና ውጭ የተጠቆሙና በቅዱስ ሲኖዶሱ በተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት፥ ዕውቀታቸው፣ የቆየ ታሪካቸውና ሥነ ምግባራቸው ተገምግሞና ተመዝኖ ብልጫ ያገኙ 16 ዕጩ ቆሞሳት በቅዱስ ሲኖዶሱ እንደተመረጡ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባለፈው ግንቦት 14 ቀን ለብዙኃን መገናኛ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ኤጲስ ቆጶሳት ለሌሉባቸው የውጭ አህጉረ ስብከትም ተጨማሪ ጳጳሳት እንደሚመደቡ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በርክበ ካህናት ስብሰባው እንደተስማማ፣ ፓትርያርኩ በመግለጫቸው የጠቀሱ ሲኾን፤ ጉዳዩም በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ምልአተ ጉባኤው እንደሚጠና ጠቁመዋል፡፡
የፊታችን ሐምሌ 9 ቀን ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾሙት ዕጩ ቆሞሳት፣ ከመጪው ኹለት ሳምንት በኋላ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና፣ ትምህርተ ኖሎት፣ ሕግና ታሪክ፣ አስተዳደር፣ የቅርስ አያያዝ፣ ማኅበራዊ ኑሮና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሴሚናሮች እንደሚሰጣቸውና እስከ ሰኔ 15 ቀን ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ተጠቃለው በመግባት ሪፖርት እንዲያደርጉ በቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት መታዘዛቸው ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ቋሚ ሲኖዶስ፣ በትላንት፣ ሰኔ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ የዶ/ር አባ ኃይለ ማርያምን ምደባ፣ ወደ ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በማድረግ ማስተካከሉ ተገለጸ፡፡ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት፣ ካለፈው ዓመት ግንቦት 2008 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እየተመራ የሚገኝ ሲኾን፣ በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫው፣ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም እንዲመደቡበት በምልአተ ጉባኤው ተወስኗል፡፡
ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት መመደባቸውን በመግለጽ ጽ/ቤቱ የመንበረ ፓትርያርክ ማረፊያቸውን ዕቃ ቤት እንዲያሟላ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መታዘዙ፣ ከብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ተቃውሞ እንደቀረበበትና በምልአተ ጉባኤው በጸደቀው መሠረት እንዲስተካከል መጠየቃቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
The post ኤጲስ ቆጶስነት የተመረጡት አባት፣ “ሓላፊነት ለመጨመር አልበቃኹም” በሚል ዕጩነቱን ሳይቀበሉ ቀሩ፤ ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም ደቡብ ጎንደር ተመደቡ appeared first on ሳተናው: Ethiopian Amharic News | Breaking News: Your right to know!.