በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደሚታመነዉ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ከእስር ቤት የተፈታ አንድ ከባድ ወንጀለኛ ነበር ይህ ወንጀለኛ በርባን በመባል ይታወቃል። በወቅቱ ህዝቡ አይሁድን ሲገዛ ለነበረው ለሮማዊው ንጉሥ ጴላጦስ፣ “ይህንን ወንጀለኛ ፍታልንና በምትኩ ኢየሱስን ሥቀለው!” ብለዉ በለቅሶና በታላቅ ጩሀት ልመና ሰላቀረቡ ነበር በርባን ነፃ አዉጥቶ እየሱስን ለመስቀል የወሰነዉ።
ይህንን ታሪክ ወደኋላ ተመልሼ ያሰብኩት ባሳለፍነዉ ግንቦት ወር አጋማሽ ገደማ የዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ በተመረጠበት ቅፅበት ነበር። ሆኖም ግን ያ ፃድቅ ለዚህች ዓለም ይዞት የመጣዉ በረከት አሁን ላለንበት የመልካምነትና የሰብዓዊ እሳቤ ፅንፍ መነሻዉ የሆነልን መሆኑ ነዉ:: የሀገራችንም ሁኔታ ከዚህ አይለይም እዉነትን፣ ፍትህን፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲን የሚሻ ሰዉ ለዘመኑ ጴላጦሶች የሚያሰሙት የጩህትና ለቅሶ አንዲሁም ዋይታ እዉነት አንዲፈታና ፍትህ እንዲነግስ በአንፃሩ ያለንስሐ ወደመድረክ የመጡ የሲኦል ተምሳሌቶች በፍትህ መድረክ እንዲዳኙና ወደ ጤና መሪነት ሳይሆን ወደ ማገገሚያ እንዲሄዱ መንገዱን ለመጥረግ ነበረ:: ሆኖም ይህ የዓለም መደረክ ነው፤ የፖለቲካ ቁማር ያየለበት፤ ከሰብአዊና አለማቀፋዊ መፍትሄዎች ዙርያ ከመስራት ይልቅ እራስን በክልልና በፖለቲካ የለየበት ጊዜ… ከሰውነት አስተሳሰብ የወጣበት ዘመን። በርግጥ የሶርያን ሕፃናት መታደግ ያልቻለ የዓለም ፖለቲካ፣ የፍልስጤማዉያንን የነፃነት ጥማት መመልከቻ ፍላጎት ያጣ የድርጅት ስብስብ፣ የሩዋንዳን የዘር አልቂት ያቀነባበረ ስልጣኔ፣ የሱማልያን ጤና መመለስ ያልቻለ የዉቀት ክምችት በዓለም የጤና ድርጅት መድረክ እዉነትን ዳግም ሊሰቅላት ቢፈቅድ አይደንቅም አይገርምም ወደ አህጉራችንም ዞር ብለን ብንመለከትም ጉዳዩ ብዙም የራቀ አይደለም የአፍሪካዉያን መሪዎች በተለያየ በዲፕሎማሲ ክታብ የታሰሩበት፣ ታሪካዊ እሴትን ለማስጠበቅ በሚል የተሸነገሉበት አንዲሁም በጓሮ በኩል የሚገኙ ጥቅማጥቅምች የሁዋልዮሽ የፊጥኝ ይዘዋቸዉ ያሉበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ:: ለነገሩ የማን ዘር ነሽና በድንግል ትዳሪ ከነ ዘር ማንዘርሽ አይደል የሚባለዉ:: ሆኖም ከዉጤቱ በላይ የዚህን ሰዉ አስነዋሪ ሥራ አደባባይ ላይ በማዉጣት የዓለም ሕዝብ የመጀመሪያ መወያያ ርዕስ በማድረግ ረገድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያኖች አንባገንነትንና ፀያፍ ስራዎችን አርቆ ቆፍሮ ለመቅበር ያሳዩት የትብብር መንፈስ፣ ፅናት፣ እልህና ቁርጠኝነት አጅግ የሚያኮራና በቀጣይ ስራዎች ላይ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ይህ የትብብር መንፈስ ማደግ መጠናከር መደራጀትና መቀጠል ከቻለ ከፍተኛ ለዉጥ ማምጣት የሚችል አቅም ምንጭ መሆኑ ለሀገራችን አዲስ የብስራት ዜና ይህሆናል።
ዶክተር ቴዎድሮስ ይህንን ቦታ ለመያዝ በግል ፍላጎታቸዉ ብቻ ሳይሆን የደም ዝዉውራቸዉን የሚለካዉና የሚቆጣጠረዉ ሰዉየዉም በዉሳኔ መስጠት ሂደት የሚሳተፉበት ሕወሐት(ሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ) አሽከርካሪዎች ጥናትና ዝግጅት በተለይም በሞት የተገላገልናቸዉ ሟች አቶ መለሰ ዜናዊ ብሂል ቀደም ብሎ የተቀመረ ዛሬ ሳይሆን የአንድ የልጅ እግር ወጣት እድሜን የፈጀ ጉዞ ማድረጋቸዉ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰነባብቷል:: ሰዉየው ገና በጠዋቱ ስንት የጤና ሙሁር በስራቸዉ አንቱ የተባሉና ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም መስጠት የሚችሉ ፕሮፌሽናል የሆኑ ዜጎች በሞሉባት ሀገር እዚህ ግባ የማይባል አቅምና የስራ ልምድ ይዞ ከትግራይ የጤና ቢሮ ሽቅብ ወደ የጤና ሚንስቴርነት ሲምዘገዘጉ ብሎም ያለምንም ትምህርት ብቃት መለኪያና ጥናት እንዲሁም እዚህ ግባ በማይባል የዉጭ ዲፕሎማሲ ልምድ የሀገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር በመሆን (ያዉ ጉልቻ ቢለዋወጥ ነገር) ስዩም መስፍንን የተካበት ሲቀጥል በግሎባል ፈንድ እንዲሰሩ በማድረግ ከዛም የአፍሪካ ዙር ሲደርስ ተጠብቆ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል እንዲወዳደሩ በማድረግ ለዛ ሥራ ማኪሃጃ የሚሆን ዳጎስ ያለ በጀት በመመደብ በዓለም ላይ ስመ ጥር የሆኑትን አፈ ቀላጤዎችንና አማካሪዎችን በመቅጠር ከዛም በካቢኔ ሹም ሽር ሽፋን ወትሮም በብቃት ያላመጣቸዉ ስርዓት የረዥም ዓመት ፈቃድ ሰቶ አሰናብቷቸዋል:: ይሁንና የእባብ ልጅ እባብ እንዲሉ ሰዉየዉ በሀገር ዉስጥ በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን እንደ ዘመድ አዝማዶቻቸዉ የአድዋ ጉዶች የነበሩበትን የስልጣን መንበር ሽፋን በማድረግ የሀገሪቱን አንጡረሃብት ያለአግባብ ዘርፈዋል፣ ከተለያዩ አለማት በእርዳታ መልክ የተገኙ ገንዘቦችን ያለሕግ አግባብ አባክነዋል፣ ለግል ጥቅም አዉለዋል፣ ቀናቸዉ ያለፈባቸዉ መድኃኒቶች ወደሀገር ዉስጥ ለማስገባት በሚስጥር በተደጋጋሚ ዉል ፈፅመዋል፣ በተለያዩ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ላይ በዉሳኔ ሰጭነት ተሳትፈዋል:: እንዲያው በደረቁ ከሚሆን ለአንባብያን ግልፅ ለማድረግ ሰዉየዉ በተለያዩ ስልጣን ቦታዎች ላይ በነበሩበት ዘመን በዉሳኔ ሰጭነትና ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከሆኑባቸዉና ከተሳተፉባቸዉ በመረጃ ከተረጋገጡባቸዉ ወንጀሎች ዉስጥ ደግመን በጥቂቱ ብናነሳ
- በሶማልያ ክልል የደረሰዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል
- በአማራ ክልል ነዋሪዎች ላይ የተደረገዉ የዘር ማምከን ወንጀል
- በጋምቤላ ክልል የደረሰዉ ግድያና ጭፍጨፋ
- በሐገራቸዉ የፖለቲካ መድረክ እንዲሁም በጋዘጠኝነት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የአንባገነኑን ድሪቶና ነዉር አደባባይ ያወጡ ታጋዮችን በግፍ በማሳሰር የማሰቃያ እርምጃ በመስጠት በማስገደል ወንጀል
- በሚሊኒየም ዴቨሎፕመንት ጎል ፕሮጀክት የተገኙ ጥቅሞችን ለግል ፍላጎት በማዋል ያልተሰሩ ስራዎችን ተሰርቷል በማለት ለማህበረሰቡ ተቀደዉ የተሰፉ የዉሸት ወሬዎችን በማስነገር
- የኮለራ ወረሽኝ በሽታን በተደጋጋሚ ከዓለምአቀፍ ዜና አዉታሮች በመደበቅ ዜጎች በተገቢዉ ሰዓት ተገቢዉን እርዳታ ሳያገኙ ቀርተዉ እንዲሞቱ ምክንያት በመሆን. . .
ዕኒህንና ሌሎች ተዘርዝረዉ የማያልቁ ግፍና መከራን የፈፀመ የዘመኑ በርባን በዓለም መድረክ ኢትዮጵያ የሚል የጨዋና የክብር ካባ ለብሶ በዓለም መድረክ አይንን በጨዉ አጥቦ ብቅ ማለት ያስቆጣዉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊን ከጥግ እስከ ጥግ ከአራቱም ማዕዘን ቀፎዉ እንደተነካ ንብ በቁጣ ያንቀሳቀሰ ጉዳይ ሆኗል በቁጣም አልቀረ የአለምን የዜና አዉታሮን ትኩረት በመሳብ በትክኖሎጂ በመታገዝ የማጋለጥ ተሰርቷል ይህ የማጋለጥ ዘመቻም የተቃዉሞ ፊርማ ከማሰባሰብ አስከ ትዊተር ዘመቻ ከተካዉሞ ሰልፍ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዉስጥ በመግባት ቀጥተኛ ተቃዉሞ እስቀማቅረብ የደረሱ ነበሩ ወደፊትም የሚቀጥሉ ናቸዉ የሚል እምነት አለኝ። በተለይም በሰዉየዉ ቀጥተኛ በደልና ግፍ የተፈፀመባቸዉ የምስክርነት ቃላቸዉን በፅሁፍ በመተየብ በተለያዩ መረጃ ማሰራጫ ጣቢያዎች ለተነባቢ ማብቃታቸዉ የሰዉየዉን መሰሪና አስነዋሪ ማንነት አደባባይ አርቃኑን ያስቀረ ነበረ።
በአንፃሩ ኢትዮጵያ በሚለዉ ትልቅ የክብር መጋርጃ ተሸፍነዉ የሀገርን ክብር የሚያረክሱ የዘር ኮማሪዎች የሰዉየዉን ግፍ አደባባይ በማዉጣት በዓለም ሕዝብ ፊት ራቁቱን ያስቀሩትን እየተከተሉ የኢትዮጵያችንን ክበር አወረዳችሁ ጥቅሙ ለሀገር ነዉ በማለት አዛኝ ቅቤ አንጓች በመሆን ተቃዋሚን በማሸማቀቅ ሥራ ላይ ተጠምደዉ የከረሙ ሆድ አደሮች በስተመጨረሻም ከያሉበት ተለቃቅመዉ የአዉሮፕላን ትኬት ተቆርጦላቸዉ የዉሎ አበል ታስቦላቸዉ አልጋና ሌላም ጥቅማጥቅም ያገሬ ሕዝብ ሳይሞላላት በሚከፍለዉ ግብር የሚተዳደሩ ኤምባሲዎች አስተባባሪነት ሰዉየዉን ለመደገፍና ኢትዮጵያውነትን ለመሸቀጥ አደባባይ የወጡም አልታጡም ይሁንና አቶ በቀለ ገለታ በተባበሩት መንግሥታት የአለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ዋና ዳይሬክተርነት ፣ አቶ ጌታቸዉ እንግዳ በተባበሩት መንግሥታት ቅርስና ምርምር ተቋም (UN-UNESKO) ምክትል ዳይሬክተርነት ፣ እንዲሁም እነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በዓለም ባንክ የቦርድ አባል ሁነዉ በኃላም በ ተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ የአስተዳደር ቦታ ላይ በኩራት ሰርተዋል!! እየሰሩም ነዉ ግን አንድም ቀን ኢትዮጵያዊነታቸዉን አንደክብር ካባ ሲደርቡት እንጂ ለገበያ ሲያቀርቡት አልታዩም፡፡
ይሁንና የሰዉየዉ በዓለም የጤና ድርጅት ለመምረጥ ያደረጉት የአንድ ወጣት አድሜ ጉዞ ዉጤት የህዉሃት ደቀመዛሙርት ለሆኑት የዳቢሎስ ግብር አዉጪ ሆድ አደሮች ከህዝብ በደል፣ ከወገን መራብ መቸገርና መራቆት፣ ፍትህን አቶ በአደባባይ ደሙ ሲፈስ ከማዘንና ከመቆጨት ይልቅ ከግፈኞች የሚወረወርላቸዉ ምፅዋት ነብሳቸዉን አስቷቸው ስጋቸዉን አደልቦት ስቡ አይምሮዋቸዉን ለደፈነባቸዉ የዘመኑ ፈሪሳውያኖች የሰሞኑ ዉስኪ መጨለጫ ቤታቸው ማድመቂያ ምክንያት ሲሆን ለዛኛዉ መንደር ደግሞ በስጋት የከረሙት የወርቅ ዘር ነን ባዮች የህዉሃትን ትርጉም አልባ የዘር መለዮ ያደረጋትን ባንዲራ በማዉለብለብ በእምበር ተጋዳላይ ዘፈን አስረሽ ምችዉ ዳንኪራ ሲረግጡ ከርመዉበታል:: ለነገሩ በነዚህ ደናቁርት አይምሮ ከዚ የዘለለ ትልቅ ሃሳብ መጠበቁ ሞኝነት ነዉ:: በዚሁ አጋጣሚ እንዳዉ ለሀገር ፋይዳ አለዉ ብላችሁ ስትሞግቱ ለቀረማችሁ መሃል ሰፋሪዎች በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጭብጥ ማስያዝ ወደድሁ ሰዉየዉ መመረጥም ሆነ አለመመረጥ ለሀገራችን የሚጠቅም በተለየ ሁኔታ የምናየዉ ፋይዳ የለውም። ይሄ ተቋም እንጂ ኢህአዴግ ወይም ህወሓት የዘረጋው የፓርቲ ሲስተም አይደለም። ኢትዮጵያን ለብቻ ወይም አፍሪካን ተጠቃሚ የሚያደርግ ምንም ነገር “አይኖርም:: ኖሮም አያውቅም!
ወደዋናዉ ነጥቤ ስመለስ “በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ” እንዲሉ አበዉ የሰዉየዉ “ጤና ለሁሉም” የሚል ጭምብላቸዉን ለብሰዉ የክፋት ጎራደያቸዉን ለመምዘዝ ብቅ ያሉበት የዓለም መድረክ የሰዉየዉን ብሎም በሀገራችን እየተፈፀመ ያለዉን ጭቆና በደል አንባገነንነትና ከልክ ያለፈ ግፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲሁም የመሳሰሉትን ዘርዝሮ ለዓለም ሕዝብ በግልፅ ለማሳየት የሚያስችል አዲስ ምእራፍ የከፈት ሆኗል በተለይም በሐገራቸዉ ፍትህ እንዲነግስ ቀን ከሌት ሳይታክቱ በፅኑ ለሚታገሉ ትንታግ ሀገር ወዳድ ሕዝብ አክባሪ ኢትዮጵያኖች አዲስ የትግል ምእራፍ ከፋች መልካም ዜና ነዉ ለማለት ያስደፍራል:: በዚህ አጋጣሚም ለሀገር ወዳድ ፍትህ ናፋቂ ሀገር አልባ ባላገር ወገኖቼ እንኳን ለአዲሱ የትግል መድረክ አበቃን ለማለት እወዳለሁ መጪዉ ዘመንም እንደ ከዚህ ቀደሙ የዓለም ጤና ድርጅት የፈጠረልንን አዲስ መደረክ በመጠቀም የሰዉየዉን ዱካ በማነፍነፍ በሀገራችን እይተፈፅመ ያለዉን ፀያፍ ሥራና ግድያ፣ ዝርፊያና ሽብር፣ እስራትና እንግልት በማጋለጡ ረገድ ጠንክረን በአንድነት በመከናጀትና በመስራት ለአንባገነኑ ስርዓት የእግር እሳት በመሆን ታሪካዊ አደራችንን መወጣት ይጠበቅብናል እላለሁ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ነዉ ነገሩ።
ሰላምና ፍትህ ለሀገራቺን!!
/መብራቱ
ከስቶክሆልም ስዊድን