Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

አዲስ አበባ … “አዲስም” – “አበባም” የማያደርጓት 12 ነገሮች – ከደምስ ሰይፉ

$
0
0

ከደምስ ሰይፉ

1) (የመኪና ጋጠ ወጥ ጥሩንባ) …

በተለይ ሃይገር፣ ሲኖ ትራክና ቅጥቅጥ አይሱዙ … ክላክስ መንገደኛን ማስጠንቀቂያና ከፊት ያለን መኪና ማንቂያ የመሆኑ ፋሽን ድሮ ቀረ… ምንም በሌለበት ሁሉም እየተነሳ ያንባርቅብሃል… ሰፈር ውስጥ ነኝ፣ ት/ቤት ሊኖር ይችላል፣ የሕክምና ማዕከል በአቅራቢያዬ አለ፣ እንስሳ ላስደነብር እችላለሁ… ወዘተ የፍንዳታ ሹፌሮች አዕምሮ ላይ በስህተት የማይከሰት ቁምነገር ነው… መንገድ ተዘጋግቶባቸው ተሰልፈው በቆሙና ወዴትም ሊሄዱ እንደማይችሉ በሚታወቅ መኪኖች ላይ የጥሩንባ እሩምታ መልቀቅ ምን ይባላል?…

addis ababa

2) (ንጽሕና) …

ሰፈር ለይታ ያጸዳችውን ሰፈር ለይታ ታከማቸዋለች… አንዱ መንደር የቆሻሻ ጥዩፍ፣ ሌላው ቀዬ የቆሻሻ እቅፍ ነው የሚመስለው… ሰውም የንጽሕና ጉዳይ ጉዳዩ አይደለም… ታክሲ ውስጥ የጫማ ሽታ ይሰነፍጥሃል፣ መንገድ ላይ የመጸዳጃ ቅርናት ያፍንሃል… ሁሉም የየቤቱን ጉድ በየጥጋጥጉ መድፋት አይጎረብጠውም… በጠራራ ጸሐይ አጥርና የቆመ መኪና ተጠግቶ ሲያንፎለፉለው የማያፍር እልፍ ነው…

3) (ጩኸት) …

ያረጁ ተሽከርካሪዎች ድምጽ የነዋሪው የኑረት ሳውንድ ትራክ ነው… ከአገልግሎት ሰጪዎች የሚለቀቁ ድምጾች ጸጥታን በሲዲ የሚሸጥ አሳታሚን ያስመኛሉ… የሚያንገሸግሽህን ዘፈን ራስ ምታት ከሚለቅ ድምጽ ጋር ትሰማለህ… ዝግ ብለው ስክነት የሚቸሩህን ዜማዎች የምትሰማው ባለታክሲውና ባሬስታው ዝግ ያሉ ሲሆኑ ነው… ሙዚቃው ይፈጥናል… መኪናው ይፈጥናል… አደጋውን አስበው… የትም ሂድ ማጫወቻውን የያዘው ሰው የሚመርጥልህን ጩኸት እንጂ አንተ የምትሻውን ጸጥታ ማጣጣም ዘበት ነው… ነዋሪው ቲአትር እያየ ያወራል፣ እየበላ ያወራል፣ አብሮህ ቁጭ ያለ ሰው ካንተ ጀርባ እርቆ ከተቀመጠ ሌላ ሰው ጋር የሚነጋገር ይመስል እየጮኸ ያወራል… እሪ ብሎ የሚጮህ የስልክ ጥሪ አሰምቶህ እሪ ብሎ እየጮኸ ስልክ ያናግራል… የሐይማኖት ተቋማት ከግቢው ምዕመን በሚተርፈው ድምፃቸው ሰላም ይነሱሃል…

Public transport, Addis Ababa, Ethiopia, Africa

4) (ችኮላ) …

ለመዝናናት የወጡ ጥንዶች ሳይቀር ይቸኩላሉ፣ ታክሲው ይቸኩላል፣ መንገደኛው ይቸኩላል… ለአንድ እንግዳ ሰው ‘ዝናብ መጣ እንዴ?’ የሚያስብል ችኮላ… በችኮላ ይወራል፣ በችኮላ ይበላል፣ በችኮላ ይሰራል፣ በችኮላ ይፈርሳል፣ በችኮላ ቃል ይገባል፣ በችኮላ ቃል ይበላል…

5) (በረሃማነት) …

ጸሐይ መታኝ ልጠለል ብትል ዛፍ የሚባል ታሪክ የለም… አረፍ ብዬ ልተንፍስ ብትል መቀመጫውም መተንፈሻውም የለም… ከፍለህ የምትቀመጥበት እንጂ ደክሞህ የምታርፍበት አንዲትም ታዛ የለችም…

6) (ግለኝነት) …

እንኳንና የሩቅ ሰው ቤተሰብም እርስ በርስ አይፈላለግም፣ ጉርብትና የቤቶች መቀራረብ ስያሜ እንጂ የሰዎች መተሳሰብ መጠሪያነቱ አክትሟል… እንኳን ፊትህን አይቶ ማዘን ችግርህን ነግረኸው መረዳዳት ቀርቷል…

ethiopia 3

7) (ስግብግብነት) …

ባለሃብቱ በሰበሰበው አይረካም… መካከለኛው ባለው አይደሰትም… ያለው ለሌለው አያዝንም… አከራይ በየሩብ ዓመቱ ኪራይ ይቆልልብሃል፣ ነጋዴው በብዙ እጥፍ ያተርፍብሃል፣ ሬስቶራንቶች የሚያቀርቡልህን ምግብ መጠን በመቀነስና የሚጠይቁህን ዋጋ በመጨመር የሚስተካከላቸው የለም… ነግ በኔ ተረት ነው፣ ለሕሊና መኖር ወሬ ነው…

8) (ዘረፋ) …

በጠራራ ጸሐይ ጉንጭህን ለቡጢ፣ ጎንህን ለሴንጢ የሚዳርጉ እልፍ ናቸው… ሞባይልና ላፕቶፕ ይዘህ ማን አለብኝ ብሎ መጓዝ – ‘ባክህ ናልኝ መዘዝ’ የማለት ያህል ነው… የሕዝብ የምትለው ተቋም ውስጥ ‘በእጅህ ካልሄድክ’ ጉዳይህ ዳር አይደርስም… ብዙ ካላስጨበጥክ ጥቂት አታገኝም… አስተናጋጅ ባንተ ሳንቲም ለራሱ ቲፕ ይቆርጣል… ረታክሲ ዳት መልስ ስትጠይቀው ይገላመጣል… ሱሰኛው ልክ ወስኖ ብር ይጠይቅሃል…

drink

 

9) (መሸተኝነት) …

ከልጅ እስከ አዋቂ የቢራ አንገት ጨባጭ ነው… መዝናኛው ቢራ ነው፣ መተከዣው ቢራ ነው፣ ግብዣ – ድግስና መሰባሰቦች ሁሉ ቢራ ናቸው… ታክሲ ውስጥ ሬዲዮው ‘ጠጣ’ ይልሃል፣ እቤትህ ቲቪው ‘ጠጣ’ ይልሃል፣ መ/ቤትህ ጋዜጣው ‘ጠጣ’ ይልሃል፣ መዝናኛ ቦታህ ወዳጅህ ‘ጠጣ’ ይልሃል… መንገዱ ሁሉ ‘ጠጣ’ ‘ጠጣ’ ‘ጠጣ’ ብሎ እንዳዛጋ ነው…

10) (እምነት ማጉደል) …

ብዙ ባሎች ለሚስቶቻቸው አይታመኑም፣ ብዙ ሚስቶችም ለባሎቻቸው እንዲሁ… ወዳጆች አይተማመኑም፣ መንግስት ለሕዝብ አይታመንም… ሻጭና ገዥ አይተማመኑም…

merkato-addis-ababa-copy

11) (ልመና) …

ልመና የሥራ መስክ እንጂ የችግረኞች መደጎሚያ መሆኑ እየቀረ ነው… በተስኪያን ሄዶ ስለ ገብርኤል ያለህ መስኪድ ተሰልፎ በአላህ ይልሃል… አካል ጉዳተኛውን ከጤነኛው መለየት ፈጽሞ አትችልም… ፊትን መገጣጠብና እጅ እግርን ማቆሳሰል እድሜ ለግራሶ እንጂ ቀላል ነው… አንጀት ይበላሉ እየተባሉ የሚፈበረኩት ትርክቶች እየቸኩ መጥተዋል… ምግብ እየበላህ እፊትህ መጥቶ ግትር ይልብሃል… አንዳንድ ነውረኛ የጀመርከውን ትተህ ብትሄድ ግድ አይሰጠውም… ይሉኝታ ማጣት የቢዝነሱ ሰዎች ተቀዳሚ ተግባር ነው…

File Photo

File Photo

12) (ግድ አልባነት) …

እግርህ በደረሰበት ሁሉ የግድየለሾች ተግባር ጮክ ብሎ ይጠራሃል… ታክሲ ውስጥ የተተፋ ማስቲካ ጫማህን ሲያጣብቀው፣ የመንገድ ምልክቶችን ተሸከርካሪ ሲድጠው፣ የእምዬን ስም አንዳንድ መደዴ ሲያራክሰው፣ ባለ ጥምባሆው በተዝናኖት ክብህ ጭሱን ሲያንቦለቡለው፣ አጥር ምሰሶና ግንባታን በማስታወቂያ ድሪቶ ሲያስጠይፈው፣ የቤቱን ፍሳሽ ከወንዞችና ከጎርፍ ጋር ሲቀይጠው፣ አሽከርካሪው በበጋ አቧራ በክረምት ጭቃውን መንገደኛ ላይ ሲያዘንበው፣ በታክሲ ጥቅስ ሰበብ ክብርህን ሲነካው፣ በግንባታ ሰበብ መንገድህን ሲዘጋው… ወዘተረፈ…
————————–
ይህ ሃሳብ አዋሳ፣ ድሬ፣ ባሕርዳርና ሸገር በሚኖሩ ጓደኛሞች ክርክር ላይ ተመስርቶ የተፈተለ ነው… ውይይቱ ሁሉንም አዲስ አበቤ የሚጠቀልል ፍረጃ እንዳልሆነ ልብ ይሏል… የተባለውን ካለማድረግ አልፈው ለችግሩ የመፍትሔ አካል በመሆን የተጠመዱ ብዙ ናቸውና… እናንተ ግን ምን አላችሁ?…

The post አዲስ አበባ … “አዲስም” – “አበባም” የማያደርጓት 12 ነገሮች – ከደምስ ሰይፉ appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles