መፈጠር ለመኖር እንደሆነ ስናስበው አንዳችን ከአንዳችን ጋር በአንድም በሌላም መልኩ ተዋህደን መኖራችን ተፈጥሮ በሯሷ ያስተማረችን እውነት ነው።ይሁንና በአብሮነታችን ታሪካችን ፤ባህላችን፤ሐይማኖታችን ወዘተ፤የመሳሰሉት ሁነቶች የጋራ የሆነ ነገር እየፈጠርን አንደኛው ለሌላኛው በቅብሎሽ እየተዋረሰ እንዲኖር አስችሎት አመቱን እንደ እለት እንዲኖር ውበት አድረጎ ታጋርቶታል።በዚህ ባህሉ የነገሮችን መፈጠር በሚመስለው ነገር ሲተረጉም እና የመመራቱ ሄደት ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር አለ።ለዚህ ነው በርዕሴ ዶሮ ጮኸ ለማለት የወደደኩት;;
ነገሩ እንዲህ ነው። በሐገራችን አውራ ዶሮ ንጊቱን ለማብሰር የሚጮህበት ሰዐት አለው ።የሁሉም እምነት አንድ ነው ።በተለይ እንደ ኢትዮጲያ በብዙ የባህል ድርብርቦሽ የምትኖር ሃገር ሁሉንም ብሄር ፤ሐይማኖት አንድ ሊያደርግ የሚችል ብዙ የመሃል ነገር ያላቸው ህዝቦች ከውበታቸው አንዱ እንዲህ ያለው መተሳሰር ነውና ፤ አውራ ዶሮ የሚጮኸው ንጊቱን ለማብሰር መሆኑን ከዳር አስከዳር ይስማሙበታል።ይብሰን ብሎ አማርኛው በስነ ቃል ያስረዋል።”ዶሮ ከጮኸ የለም ለሊት ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት”። እና ታዲያ አውራ ዶሮ ያለግዜው የጮኸ እንደው “አሁንስ ይህ መንግስት በቃለት አውራ ዶሮ ያለ ግዜው ጮኸ “ይባላል።ታዲያ በአውራ ዶሮ ጩኸት የትኛው መንግስት እንደወረደ ባላውቅም ሰሞኑን የተነሳው ሰደድ እሳት የአውራ ዶሮን ጩኸት እንዳስታውስ አድርጎኛል።አሁን የምፈራው መንግስታችን ይህን ሚስጥር ካወቀ አውራ ዶሮች ሁሉ ባሉበት ተይዘው ይታረዱልኝ ያለ እንደው ነው። ግን ቀኑ ከደረሰ ሴቷም ቢሆን ትጮሃለች ።
አውራ ዶሮን ሁሉ መግደል ጩኸቱን ማሳነስ እንጂ ሊሆን ያለውን መመለስ አይቻልም።ኢትዮጲያዊ ተስፋውን ከእምነቱ ጋር ያዋደደ ብልህ ፍጡር ነው ።ማንነቱ ካመነበት ፈቀቅ የሚያደርገው ቢመስል የሚደገፍበት የቀን ጀግና ዋስ እስከሚሆነው እንጂ ጨርሶ አንቀላፍቶ አልነበረም።ሁሉን በነገ የተሻለ ቀን እያሰበ ላለመደው ስርዐት በማያውቀው ነገር የሚያውቀው የትላንቱ እየተሰበረና እየጠፋ ቢበዛበት እንኳን ፤ስለሚወዳት ሃገሩና ህዝቡ ፤ስለ ሃይማኖቱና አንድነቱ መታገስን ገንዘብ አድርጎ ከስፍር የፈሰሰ ትግስት አድርጎ ሲኖር ማየት ከምንም በላይ ነበር።እስቲ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በትረ ስልጣኑን ከያዘ እንኳን ምን ተሰፈረለት።ዘረኝነት፤ርሃብ፤ስደት፤ውርደት፤የማያውቀው ባህል ባለቤት፤የራሱ የሆኑት ሁሉ አሴቶች አራግፎ የምዕራብዊያን ባህልና ውራጅ ናፋቂ እንዲሆን ማድረግ ፤ሃገር እንዳለው ማስረሳትና የጥቂቶች የበላይነት እያመሰገነ እንዲኖር ማድረግ፤ ሙሰኝነት፤ግብረ ሰዶማዊነት……አረ ስንቱን ።ይህ ሁሉ አነሰና መንግስት እና ህዝብ አብሮ መኖር ቀረና ማን እንደሚመራው እንኳን በውል የማያውቀው ህዝብ ከማንትህ አባረንሃል ከቄየህም እናባርህ ቢሉት ተቆጣ ።በዛ አለ።ምላሹ ግን ልክ ነህ አልነበረም ።ያው እንደተለመደውና እንደሚታወቀው ሆነ።እሺ እሱም ይሁን እግዚአብሔር የወደደውን አደረገ እንበል ፤ ግንሳ መንግስት ያላት ሀገር መተዳደር ያለባት በአግባቡ ሆኖ ሳለ አዘዥና ነዛዡ ሳይታወቅ በስልጣን ላይ ያሉት ከህዝብ ጋር ፤ከፓርቲ ጋር ፤ከሐገር ጋር ሁሌም ጥል ናቸው ።ሁሌም መደባደብ ሁሌ መግደል ሁሌ ማሰር ብቻ ሁሌ የሆነ ነገር አለ።ይህ ከምን በመነሳት እንደሆነ ግራ ያጋባል ።እውቀት ቢጠፋ የተፈጥሮ ክህሎትን በመጠቀም ማስተዳደር ይቻላል። ዘጠና ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ አለ እና ዘጠና ሁለት ሚሊዮን ሐሳብ ሊኖር ይችላል።
ይህን ሁሉ መንግስት አደለም እራሱ የሐሳቡ ባለቤት እራሱን ማስተናገድ የማይችልበት ሁኔታ አለ።ግን መንግስት የሐገሩ አሳዳሪ ከሆነ ለራሴ ያለውን እንኳን ተጠቅሞ ማስተዳደር የአባት ነበር።ግዴለም እውቀት ይጥፋ ፤ ጠዋት በቴለቪዥን መስኮት ወጥቶ በሰላም ያሳደረ በሰላም ያውለን የኢትዮጲያ ህዝብ ሆይ በፀሎትህ አስበን ከዚህ ያለፈ እውቀት የለንም ቢባል ፤ የሐገሩ ባህል ነውና ሁሉም የበኩሉን ለማድረግ ይሯሯጥ ነበር።ያ እንዳይሆን እናውቅልሃለን ተባለ ።በምታውቁት ልክ አሳድሩን ፤አስተዳድሩን ሲባለ ፤ልጅ አዋቂ ወንድ ሴት ሳይባል ፤አንድ ሲባል ድብደባ አለፈ ሲባል እስር ፤ጨመረ ሲባል ግድያ፤ የእለት ከእለት ተግባር ሆነና አረፈው።ሁሉን ማድረግ ይቻል ይሆናል ሐሳብን ግን አስቀድመን ከጠቀስናቸው አንዱንም ማድረግ አይቻልም።የሚቻለው ነገር ቢኖር በጋራ እኩል ሆኖ አስቦ የእኩል ሐገር ማድረግ ነው።እሱም ብቻ አደለም ፤ መንግስት እኮ የህዝብ ወላጅ ማለት ነው።ትልቁን እንደ ትልቅ ትንሹንም እንደ ትንሽ ይዞ ሲያበቃ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ የሚያልፍ ሆደ ሰፊ ወላጅ ነው።ይህ ካልሆነ ማነው ባለቤቱ? መቼ ነው እፎይታው? ማነው እሱ እፎይታ ሰጭው? ሁሉም መልስ የሚያሻቸው ጥያቄዎች ናቸው።
የህዝብ ቁጥር ላይ በስልጣን ከመኖር በየ አንዳንዱ ልብ ውስጥአብሮ መኖር የብልህነት አንዱ አካል ነው ።ወደ ሕዝብ ሐሳብ መሄድ እንጅ ሕዝብን ወደራስ ሐሳብ መጎትት ትከሻን ከማድከም ያለፈ ድካም አይዘልም። ብሔራዊ እርቅም ለመነጋገር መፈለግም የሚወልዱትን አውቆ እንደ ማሳደግ ነው ።ይህ ሁሉ ሳይሆን በመቅረቱ እና የሞኝ አስተዳደር በብልሆች ሃሳብ ማደርም መክረምም አልሆነለትም።ብትናገር ልክ እናስገባሃለን ፤አጋንት ጠንቋይ የሚሉ የመንደረኛ ገፊ ቃላት ባደባባይ መነገር መጀመራቸው የዚሁ የደካማ አመለካከት ፍሬ ሃሳቦች ናቸው።በጦር መሳሪያ ብዛት መታመን በየአንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ስንት ጦር እንዳለ አለማወቅ ኋላቀር አመለካከትን ስድስተኛ የስሜት ህዋስ ሆኗአል ማለት ነው።መቼም ልብ ያለው ልብ ይላል።ከዚህ በኋላም እንደ ትላንቱ የሚታሰብ ከሆነ ህዝቡን ብቻ ሳይሆን የምትጠሉት ሮጠው የማያመልጡ ውላጆቻችሁንም(የተዋለዷችሁንም) መሆኑን ማመን ይገባል ባይ ነኝ።ለሁሉም መልስ ሊሆን የሚችል ብሔራዊ እርቅ አደርጉና ሁሉንም የሚወክል ህዝባዊ መንግስት መመስረት ዋነኛና ብቸና አማራጫችሁ መሆኑን የአቅሜን ማስታወስ እወዳለሁ።በዚህ አጋጣሚ ሳዳምን፡ጋዳፊንም እጣቸውን እናንተም ባታወጡ ምኞቴ ነው ።
በጥቅሉ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይም ሆነ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ የህዝብ የበላይነትን በማክበር የወጡበትን ማህበረስ ከራስ እኩል አድርጎ ማየት ውሎ አድሮ አክባሪውን ያከብር እንደሁ ነው እንጂ አያዋርድም ።ይህ በታሳቢነት ቢያዝ ከመጥን በላይ ከመተኛትም ሆነ እንቅልፍን ሳይጠግቡ ከመንቃት ያድናል።ሁለቱም የጤና አደሉምና።
ቸር እንሰንብት !
The post አውራ ዶሮ ጮኸ – ከመኳንንት ታዬ appeared first on Medrek.