ዛሬ በአሳዛኝ ሁኔታ ወገኖቻችን ከቆሻሻ ስር ተቀብረው አዘንን፣ በሊቢያ ወንድሞቻችን ሲታረዱ አዘንን፣ በባሕር ሲወድቁ፣ በየአገሩ ብዙ ክፉ ነግር ሲደርስባቸው፣ ሕዝባችን በረሐብ ሲቀጣ፣ በጥይት ሲገደል ብዙ ብዙ…. አያልቀም፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ለሴረኞች ራሳችንን አሳልፈን በመስጠታችን ነው፡፡ ደጋግ አባቶቻችን በተፈጥሮ ጥበባቸው አገርን መሥርተውና ከጠላት ጠብቀው ሰጡን፡፡ እኛ ግን ዛሬ ከሴረኞች ጋር ተባብረን እነሱ የሰሩትን ታሪክ አቃለልን፡፡ እነሱንም ሰደብን፡፡ እውነትን በውሸት ለውጠን ታሪክ ብለን ተነሳን፡፡ በአይናችን የምናየውን የምናውቀውንም ሁሉ ካድን፡፡ በውሸት ስለምንኖር የምንጮሕላት ፍትህ የምጽዐት ያህል ራቀችን፡፡ ከኢትዮጵያ ክፉም ደግም ታሪኮች ውስጥ ኢትዩጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ እንዲሁም የመላው የዓለም ሕዝቦች ታላቅ ጉልበት የሆነው የታላቁ የሚኒሊክ ታሪክ በሴረኛ የሕዝብ ጠላቶች በልዩ ሁኔታ የተዘመተበት ሚስጥር እስካሁንም ለብዙዎቻችን ግልጽ አልሆነልንም፡፡ ደግሜ ለጠቅሰው እፈልጋለሁ፡፡ የሚኒሊክ ታሪክ ለኢትዩጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ሁሉ ብሎም ነጻነትንና ፍትህን ለሚሹ ሁሉ ልዩ ማስታወሻ ሆኖ በልዩ አክብሮት ሊዘከር የሚገባው ታሪክ ነው፡፡ እውነታው ግልጽ አድርጎ የሚያሳየው ይሄንን ሆኖ ሳለ የሕዝብ ጠላት በሆኑ ዛሬ በተነሱ ሴረኞች ይህን ታሪክ ለማጉደፍ ያልተጻፈ፣ያልተደረገ፣ ያልታሰበ ሁሉ ኮተት እያመጡ ሲያወሩና ሲሰብኩ ይሄው 26 ዓመት ሊሆነን ነው፡፡ የዛሬ 26 ዓመት የተወለደ የዛሬው ጎልማሳ በሉት ስለሚኒሊክ ቢጠየቅ የሚያውቀው ሴረኞቹ የነገሩትን እንጂ እውነተኛውን ታሪክ አደለም፡፡ ሴረኞቹ ውሸቱን ደጋግመው እንደልባቸው ሲያወሩ ተሳስታችኋል የሚል ጠፋ፡፡ ጭራሽ ሴረኞቹ የፈጠሩትን ውሸት እውነት እንደሆነ አምኖ ከሴረኞቹ ጋር የሚደራደረው በዛ፡፡ ሴረኞቹም 26 አመት የዋሹን ሳይበቃቸው አሁንም እየዋሹ የሚነግሩንን ሁሉ አምነን አሜን ብለን እስካልተቀበልን ድረስ ፍጹም መደራደር እንደማይፈልጉ እየነገሩን አቅም አግኝተው ሊያስፈራሩን ሞከሩ አሁንም እያደረጉት ያለው ይሄንኑ ነው፡፡ የልብ ልብ ስለተሰማቸው አሁን እነሱ ከሚያወሩት ታሪክ በቀር ሌላ ታሪክ ማውራት እንደማይቻል ያስጠነቅቁናል፡፡ 26 ዓመት ውሸት ሲናገሩ ከልካይ አልነበራቸውም፡፡ ብዙውን በውሸት ታሪክ እንዳጠመቁትና በዚህም እንደተሳካላቸው አውቀዋል፡፡ ጥቂተ ጉዳዮችን በነጥብ በነጥም ላንሳ፡፡
እውን ሚኒሊክ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ናቸው;
ለዚህ ጥያቄ አብዛኛው ዛሬ ያለው የኦሮሞ ትውልድ መልሱ አዎ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ምክነያቱም የሚኒሊክን ታሪክ የሚያውቀው በአኖሌው የውሸት ሀርካ ሙራና ሐርማ ሙራ ነውና፡፡ ዛሬ አንዳንዶች እረ ይሄ ታሪክ ከእውነት የራቀ ነው ብለው ሲሉ ይሄንን ካልተቀበላችሁ ጠላቶች ናችሁ የሚል ማስፈራሪያ ይቀበላሉ፡፡ የሚኒሊክ በአርሲ የነበረው ጦርነት ሚኒሊክ ራሳቸው ከአዘኑባቸው ብዙ ሕዝብ የሞተባቸው ጦርነቶች አንዱ እንደነበር አሳምረን እናውቃለን፡፡ ጡትና እጅ ከተቆረጠም በጦርነት ሂደት እንደማንኛውም አደጋ ተከስቶ ይሆናል፡፡ ውጊያ እንደመሆኑም ጡትና እጅ ሳይሆን አንገትም እንደሚቆረጥ እናውቃለን፡፡ ይሄ ደግሞ ከሁለቱም ወገን ሊሆን የሚችል ነው፡፡ በእርግጥ ሴቶችና ሕጻናት በውጊያው ሰለባ የመሆን እድል ይገጥማቸዋል፡፡ ሆን ተብሎ ሳይሆን በጦርነት ሂደት ውስጥ በሚፈጠር ስህተት፡፡ ሴረኞቹ የሚሉት ታሪክ ግን ከጦርነት ውጭ በሆነ ሠላማዊውን ሕዝብ ሰብስበው ቆረጡት ነው፡፡ አዎ ዛሬ አኖሌ ላይ ሀውልት የተከሉትም ያንን በሚል ነው! ይህ ነበር ሴረኞቹ ለዛሬው ትውልድ ከአበረከቱት የውሸት ታሪክ አንዱና ለእነሱም እንደስኬት የሆነላቸውና የበለጠ በመዋሸት ሌላም ስኬት ማስመዝገብ ይቻላል ብለው እንዲያምኑ ያበረታታቸው፡፡ አኖሌም በሉት ሌሎች ጦርነቶች ግን በውጊያ ከነበሩ የሰው ሕይወት መጎዳት ውጭ ሴረኞቹ የሚሰብኩን አይነት ታሪክ አንድም ቦታ አልተመዘገበላቸውም፡፡
ሌላው ሴረኞቹ ይሄው የአርሲ ጦርነት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተደረገን ጦርነት አድርገው ይሰብካሉ፡፡ ምኒሊክ ግን አንድን ሕዝብ ለማጥቃት በሚል ያካሄዱት አንድም ጦርነት የለም፡፡ ሴረኞቹ ሸዋን የሚኒሊክ ተላላኪ አድርገው ስለፈረጁት የሸዋ ኦሮሞ እኮ ዋነኞቹ የሚኒሊክ ተዋጊዎች ነበሩ የሚለውን አይቀበሉም፡፡ እውነታው ግን ከዚህም የዘለለ ነው፡፡ ከአርሲ ጋር የነበረው ጦርነት የኦሮሞን ሕዝብ ኢላማ ያደረገ ሳይሆን አገርን አንድ ለማድረግ በነበረ ሂደት እንደነበር ሴረኞቹ ሳይረዱት ቀርተው አደለም፡፡ ይልቁንም ከማንም በላይ እነሱ ይሄንን እውነት ያውቁታል፡፡ የማያውቀው የእነሱን ስብክት የሚያደምጠውና ከእውነተኛው ታሪክ እንዲገለል የተደረገው ነው፡፡ ልብ በሉ ሸዋን ጠቅሻለሁ፡፡ ጅማም፣ ወለጋም፣ ኢሉ አባቦራም ከአርሲ በቀር ሌላው የኦሮሞ ሕዝብ ጋር እኮ ምኒሊክ አልተዋጉም፡፡ በተቃራኒው ከእነዚህ ሁሉ ሕዝቦች ጋር ልዩ የወዳጅነት ትስስር ነበራቸው፡፡ በጦራቸውም ይሁን በስልጣን መዋቅሮቻቸው ትልልቁን የሚኒሊክን ሥርዓት የመሩትም በአብዛኛው የእነዚሁ የኦሮሞ ሕዝብ ተወላጆች ናቸው፡፡ ዛሬ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ በሚኒሊክ ላይ ያለው እይታ ከዚህ ይለያል፡፡ አርሲ ሊያውም የተወሰነ አካባቢ በሆነ ጦርነት ነው ዛሬ ላለው ትውልድ ሚኒሊክ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ክተት እንዳወጁ እየተሰበከው ያለው፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ሚኒሊክ በአርሲው ጦርነት ብዙ ሕዝብ እንደተጎዳና አዝነውም እንደነበር የሚኒሊክ የራሳቸው ታሪክ የሚናገረው ነው፡፡ ዛሬ ከጦርነት ውጭ ጡትና እጅ ተቆረጠ እንደሚሉት ሳይሆን ይልቁንም በወቅቱ ከጦርነት በኋላ ሕዝቡ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይሆንበት ሚኒሊክ ወታደሮቻቸውን የሕዝቡን ንብረትና መሬት እንዳይነካ አዋጅ አውጥተውበት እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ አለ፡፡ ለሚኒሊክ የአርሲ ሕዝብ እንደማንኛውም አልገብርም ብሎ እምቢ እንዳለ ሕዝብ ተዋጉት እንጂ ኦሮሞ ስለሆነ አልነበረም፡፡ ይሄው አይነት ጦርነት በወላይታ ከንጉስ ጦና ጋር ተደርጓል፡፡ ጦናም ተሸንፈው ከተማረኩ በኋላ ሚኒሊክ ዓላማቸውን አስረድተው መልሰው በወላይታ በነበሩበት ንግስና ሕዝቡን እንዲመሩ ነው ያደረጉት፡፡ ጦናም የሚኒሊክ ዓላማ አገርን አንድ አድርጎ በበለጠ ስኬት ሕዝብን ማስተዳደር እንጂ እሳቸውን (ጦናን) አስወግዶ አገሩን መቆጣጠር እንዳልሆነ ስለተረዱት ከዚያ በኋላ በወዳጅነት እንደቀጠሉ በአደዋው ጦርነትም ለሚኒሊክ የአገርህን አድን ጥሪ ብዙ ወታደሮችን በመላክ የወላይታ ሕዝብ የታሪካውዊ አደዋ ድል ሆኖ ዛሬም እንዘክረዋለን፡፡ ዛሬ ላይ ያለው የወላይታ ሕዝብ በሚኒሊክ ላይ ቂም የለውምም፡፡ ይልቁንም ሚኒሊክ ለገነቧት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተሟጋች ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ በሚኒሊክ ዋና ዋና በሚባሉት የስልጣን እርከኖችና የጦርነት መስኮች ዋነኛውን ድርሻ የነበረው የኦሮሞ ሕዝብ ዛሬ ላይ የሚኒሊክን ታሪክ እንደ ጠላት ታሪክ ሲያየው እንታዘባለን፡፡ ዛሬ ያለው የኦሮሞ ትውልድ በውሸት ታሪክ የተሞላ በመሆኑ እንደዚያ ቢያስብ አንፈርድም፡፡ የምናዝነው እውነተኛውን ታሪክ እያወቁ ከሴረኞች ጋር እንወደድ በሚል ተባባሪ በመሆን ሕዝቡ የራሱ የሆነውን የምኒሊክን ታሪክ እንዲጠላ አስተዋጾ እያደረጉ ባሉ ምሁራን ነን ባዮች ነው፡፡ በቅርቡ ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ የዛን ዘመን ታሪክ እውነታ በጨረፍታ ሊነኩት በመሞከራቸው ሴረኞቹ ኃይሌ የተጠቀሙት አንዳንድ ቃላት እንደ ስህተት በማጉላት ተነቃብን በሚል ይመስላል በፕሮፌሰሩ ላይ እንዴት እንደዘመቱ እናውቃለን፡፡
ከሁሉም የአገሪቱ የታሪክ ሂደቶች ይልቅ የኦሮሞ ሕዝብ በአገሪቱ የበላይነት ድርሻ የነበረው በሚኒሊክ መንግስት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናትና የቆዩም አባቶቻችን በማያሻማ ሁኔታ ይነግሩናል፡፡ የታሪክ ድርሳናቶቹን ለማንበብ የአባቶቻችንንም ቃል ለመስማት ፍቃደኞች አልሆንም፡፡ የሴረኞቹን የውሸት ታሪክ ግን ደጋግመን አነብንበናል፡፡ እራሳችን ሴረኞች በአጠመቁን የውሸት ታሪክ ዋና የዚህ የውሸት ታሪክ አዛማች ሆነናል፡፡ ንግስቲቱን ጣይቱን ጨምሮ ታላላቁን የሚኒሊክን የስልጣን እርከን የያዙት እኮ ኦሮሞዎች ነበሩ ሲባል ሊያደምጥ የወደደ የዛሬ ኦሮሞ እምብዛም ጠፋ በምትኩ የአኖሌን የውሸት ታሪክ ድግምት ደግመውበት የፈዘዘው በዛ፡፡ ጣይቱ ብጡል (ንግስት)፣ ራስ መኮንን ኃ/መስቀል ጉዲና (የሚኒሊክ አጎትና ቀኝ እጅ)፣ ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ(ከሚኒሊክ ቀጥሎ የስርዓቱ ዋና፡፡ እንደዛሬው በአሻንጉሊትነት ሳይሆን ሙሉ የመወሰን ሥልጣን ያለው) በሚኒሊክ አስተዳደር ወሳኝ ሚና ከነበራቸው ኦሮሞዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በጦር ውሎው ከአየን ከጀግናው ራስ ጎበና ዳጬ (ሥሙ የዛሬውን ኦሮሞ ትውልድ የሚያስበረግገው) እንጀምር፣ ጀግናው ገበየሁ ጎራ፣ ባልቻ ሳፎ፣ … በጥቂቱ ናቸው፡፡ ከሌላ ሕዝብ ግን እንቁጠር ቢባል በሚኒሊክ ሥርዓት ምን ዓልባት በፍለጋ ሁለት ሶስት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በመጨረሻም ሚኒሊክ ንግስናቸውን የሰጡት ለልጅ ልጃቸው የጁ ኦሮሞው ራስ አሊ ለሚወለዱት ኢያሱ ነበር፡፡ ይህ ነው እውነታው፡፡ ሴረኞቹ የእኛን ታሪክ ካልተቀበላችሁ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላቶች ናችሁ ብለው እውነተኛ ታሪክ የሚናገረውን ሁሉ ይዘምቱበታል፡፡ በውሸት ታሪክ እንድ ትውልድ እንዳተረፉ ስላወቁት የልብልብ ተሰምቷቸዋል፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ወኔና ጉልበት ከሚሆነው ከእውነተኛው የአባቶቹ ታሪክ ከሆነው ከሚኒሊክ ታሪክ በመነጠል ዛሬ አቅመቢስ ሆኖ እነሱ (ሴረኞቹ) እንደፈለጉት የሚዘውሩት ሆኗል፡፡ ሚኒሊክ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ነገስታት ለኦሮሞ ሕዝብ ያደላ አስተዳደር እንደነበራቸው ግን ታሪክ ሊክድ አልቻለም፡፡ እውነት ነውና!! ይህን ያላመነ ኦሮሞ ነው ዛሬ አቅመቢስ ሆኖ ለሌሎች መጫወቻ የሆነው፡፡ ይህን የአባቶቹን ታሪክ ያጣጣለ ትውልድ ነው ዛሬ በሴረኞች ፍላጎት እጁን እያጣመረ አደባባይ እየወጣ የሚሞተው፡፡ ሴረኞቹ የእነሱን ታሪክ ካልተቀበልን የኦሮሞ ጠላቶች አድርገውናል፡፡ እኛም ጠላት ላለመባል የውሸት ታሪክ እየተቀበልን ማስተጋባቱን መርጠናል፡፡ እነዚህን በአባቶቻችን የክብር ታሪክ ላይ የዘመቱ ጠላቶቹን የዛሬው የኦሮሞ ትውልድ ነቅቶባቸው የአባቶቹ የሆነውን የሚኒሊክን ታሪክ ይቅርታ እስከሚጠይቅ ድረስ በባርነት መኖሩ ይቀጥላል፡፡ ሴረኞቹም ተጨማሪ ድል ሆኖላቸው በሕዝብ መከራ እነሱ ይኖራሉ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብና የነጻነት ትግሉ ቡድኖች
አብዛኞቹን የኦሮሞ ሕዝብ የነጻነት ትግል እስከዛሬ የመሩት ከላይ የጠቀስኳቸው በኦሮሞ ሕዝብ ሥም የሚነግዱ ሴረኞች በመሆናቸው ዛሬ 70 ዓመት ተቆጠረለት ቢባልም ጭራሽ እንኳን ነጻነትንና ፍትህን ሊያመጣ ሕዝቡን ራሱን ወዳጣ የመከነ ነው ያደረገው፡፡ ይልቁንም ከኦሮሞ ሕዝብም አልፎ የነዚህ ነጻነት ታጋይ ነን የሚሉ የኦሮሞ ቡድኖች ለሌሎች ሕዝቦችም ከፍተኛ ሸክም ሆነው እናያለን፡፡ የኦሮሞ የነጻነት ታጋይ ነን በሚሉ በአብዛኛው ከሕዝብ ይልቅ ልዩ ሴራን ያዘሉ ግለሰቦች እንዲመሯቸው በመደረጉ በታሪክ ዕዳ እስከመሆን የደረሱ ጥፋቶች ጠፍተዋል፡፡ ኦነግ የተባለው ዋነኛው ቡድን ለዘመናት ዋና አላማ አድርጎ የተነሳው የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መለየት ነበር፡፡ ይህ ቡድን ከኦሮሞ ሕዝብም አልፎ ሌሎች እሱ በጥቅሉ የደቡብ የሚላቸውንም ሕዝቦች በተሳሳተ የታሪክ ምዕራፍ እንዲጓዙና ዛሬ ለገቡበት ውድቀት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የዛሬ 26 ዓመት አካባቢ ከመሰሉ ሕወሐት ጋር ዋነኛው ሥራው አድርጎ ቋንቋን መጠቀም በሚል የኦሮሞ ሕዝብ የፊደል መጠቀሚያውን ከግዕዝ ወደ ላቲን እንዲቀይር አደረጎ ተንቀሳቀሰ ሌሎችንም በአጫፋሪነት ሰበሰበ፡፡ ሁሉም በዘመቻ ፊደል ቀየረ፡፡ ይህ የታሪካዊው መምከን መጀመሪያው ነበር፡፡ ነፍጠኛ በሚል ሥም አማራ የተባለ ሁሉ አንደም እድል እንዳይኖረው ማድረግ ሌላው ዋና ተግባሩ ሆነ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ሌሎችን በተለይም አማራ የተባለውን ሕዝብ እንዲጠላ ቀን ከሌሊት መስበክ ቀጣዩ ሥራው ሆነ፡፡ ሁሉንም አደረገ፡፡ እየቆየም ዛሬ ላይ የኦሮሞን ሕዝብ በዙሪያው ያሉት ሁሉ በጥርጣሬና በክፉ እንዲያዩት ያበቃቸውን ድርጊቶች በተለያዩ ቦታዎች በማከናውን በሕዝቦች መካከል ታሪካዊ መቃቃርን አዳበረ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በአለፉት 26 ዓመታት ከአጎራባቹቹ ብዙዎቹ ጋር ደም ያፋሰሰ ጦርነት አደረገ፡፡ ከዛም አልፎ እርስበእርስም ወንድማማች ነን የሚሉት ጉጂና ቦረና ሳይቀሩ ደም ያፋሰሰ ጦርነት አደረጉ፡፡ የሸዋ ኦሮሞ የነፍጠኛ ተላላኪ የዳጬ ዘር (ጎበና ዳጬ ተላላኪ ሳይሆን በራሱ የመወሰን መብት የነበረው ጀግና ነበር) ተብሎ ዝም እንዲል ተደረገ፡፡ ወለጋና አርሲ የኦሮሞን ሕዝብ ተቀባባሉት፡፡ ሐረር በመጀመሪያው የኦነጋውያን ተሳትፎ ቢኖርም ከጊዜ በኋላ ለአርሲ አስረክቦ ወጣ፡፡ የአርሲው ኦነጋውያን ቡድን ነፍጠኛ ከሚለው አማራ በዘለለ ክርስቲያንን ሁሉ በጠላትነት የሚያይ ሆነ፡፡ ወለጋም ቀስ በቀስ እየተዳከመ መጣ፡፡ ዛሬ ላይ የአርሲው ቡድን ጥቂት በቀሩ የሀረርና ሌሎች የሙስሊም አካባቢ ኦሮሞ ተወላጆችን በማሳተፍ በአብዛኛው የኦሮሞ የነጻነት ታጋይ ቡድኖች የበላይነቱን ያዘ፡፡ ይህ የአርሲው ቡድን ዛሬ በሕዝብ ላይ የሚደረገውን ግፍና መከራ ወደ ጎን ትቶ የውሸት ታሪክን እየፈጠረ የኢትዮጵያን ታሪክ ማጥፋት ዋነኛው ሥራው አደረገ፡፡ ከላይ በሰፊው ያነሳሁት የአኖሌና አርሲ ጦርነት ታሪክ ለዚህ ቡድን ዋነኛ የፈጠራ ታሪክ መሻው ነው፡፡ ለዚህ ቡድን ታማኝ አባላት የሚጠበቅባቸው ሙስሊም መሆን እንጂ የፖለቲክ አመለካከት አደለም፡፡ በመሆኑም ሙስሊም የሆነ ከኦነግም ከኦፒዲዮም አባላት አሉት፡፡ የአኖሌው ሀውልት ለማስገንባት ይሄው ቡድን ዋና አንቀሳቃሽ እንደነበርና ሙስሊም የኦሮምያ መሪ ኦሮምያን በሚያስተዳደርበት ዘመን እንዲገነባ መደረጉ አንዱ ማሳያው ነው፡፡ የአርሲ ጦርነትን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተደረገ ዘመቻ በሚል ኦሮሞን ሁሉ በውሸት ታሪክ ያመከነውም ይሄው ቡድን በበላይነት የመምራት አድል ስላገኘ ነው፡፡ የኦሮሞ ሁሉ አልፎም የደቡብ ሕዝቦች ሁሉ ወኪል ሆኖ እንደልቡ ራሱን አጎላ፡፡
የአርሲው ሙስሊም ቡድን በበላይነት የሚመራቸው የኦሮሞ የትግል ቡድን ተብየዎች ኦሮሞ የኦርቶዶክስ እምነት የለውም የሚል ሴራ ማስተጋበትን ልዩ ስልት አደረጉት፡፡ የኦርቶዶክስ እምነት ያላቸውን ኦሮሞዎች የነፍጠኛ ተባባሪ በሚል ማሸማቀቅ ሁነኛ ሥራቸው ሆኖ ቀጠለ፡፡ የፕሮቴስታነት እምነት ተከታዮችን ለጊዜው ማስኮረፍ የአርሲው ሙስሊም አልፈለገም፡፡ ሆኖም 80 በመቶ ኦሮሞ ሙስሊም ነው ብሎ ማወጅን አላፈረም፡፡ ለዘመናት በዚህ የሙስሊም ቡድን ልምሾ ሆኖ በኖረው የኦሮሞ ትግል ቡድኖች አጫፋሪ በሆኑ ከክርስቲያን ኦሮሞ የተወለዱ ግለሰቦችን ለማሰመሰያነት ተጠቅሟል፡፡ ዛሬም ድረስ ከዚሁ አርሲ ቡድን በበላይነት በሚቆጣጠረው የሙስሊም ቡድን በአጫፋሪነት እያገለገሉ ያሉ የክርስቲያን ኦሮሞ ተወላጆች አሉ፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ እውነተኛ ወኪል የሆነው የመረራ ቡድን
ከላይ እንደጠቀስኩት አብዛኞቹ የኦሮሞ የትግል ቡድኖች ለዘመናት አውቀውም ሳያውቁም ልዩ ሙስሊማዊ ሴራ ባላቸው ግለሰቦች የተጠለፉ ሲሆን ለዘመናት ብቻውን ለየት ባለ ፍልስፍና ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ሲታገል የቆየው በተለያየ ጊዜ ጠንክሮ እንዳይወጣ ብዙ የተዶለተበት ፕ/ር መረራ በበላይነት የሚመራው ቡደን ነው፡፡ ይህ ቡደን ከሌሎች የኦሮሞ ነን ከሚሉ ቡድኖች ሁሉ ራሱን ጥርት አድርጎ የታሪክንም እውነት እንደወረደ ተቀብሎ ለሕዝብ እውነተኛ ፍትህ መውረድ የቆረጠ መሪዎቹም ዋናውን መረራን ጨምሮ ብዙ መስዋዕትነት ዛሬም ድረስ እየከፈሉበት ያለ ቡድን ነው፡፡ ለዘመናት ይህ ቡድን በሌሎች የሙስሊሙ ቡድን በተቆጣጠራቸው የኦሮሞ ቡድኖች የታሪክ ማዛባት ምክነያት በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ የመረራ ቡድን እውነተኛውን የቀደሙ ሥርዓቶች በተለይም የሚኒሊክን ታሪክ የኦሮሞም ሕዝብ ታሪክ ነው፡፡ ይልቁንም በሚኒሊክ ሥርዓት የኦሮሞ መሪዎች ድርሻ የበላይነት እንደነበረው የማይካድ ሀቅ ነው ብሎ የሚያምን በመሆኑ የነፍጠኛ ተባባሪ የሚል ሥም ተለጥፎለት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ መሪው መረራም ሆነ የቡድኑ አባላት ከሌሎች የኦሮሞ ነን ከሚሉ ቡድኖች በተሻለ ምን አልባትም ለማወዳደር ከማይቻል በላቀ ሁኔታ ምሁር መሆናቸው እውነትን መጋፈጥ ምርጫቸው እንዲሆንና በትዕግስትም እስከዛሬ ድረስ መዝለቅ ጉልበት እንደሆናቸው እንገምታለን፡፡ ይሄው መረራ የሚመራው ቡድን ከዘመናት ውዥንብርም በኋላ ቢሆን ለሕዝብ እየተገለጠለት ሲመጣና ድጋፉንም በይፋ መስጠት ሲጀምር እስከዛሬ ከምንም ያልተቆጠረው የአባቶቹን ታሪክ ዳግም ወድ ኦሮሞ ሕዝብ እንደሚመልስ ስለታወቀ ዛሬ ላይ ሁሉም ተለቅመው እስር ተከተቱ፡፡ የሙሰሊሙ ቡድን በበላይነት የሚቆጣጠራቸው ሌሎች የኦሮሞ ቡድኖች ዛሬ ላለው የወያኔ ቡድን ደጋፊዎቹ እንጂ ስጋቶቹ እንዳልሆኑ እናያለን፡፡ እነመረራ ሥጋት የመሆናቸው ዋነኛው ሚስጢር ከላይ ያልኩት በተለይም የሚኒሊክን ታሪክ የኦሮሞ ነው ብሎ ማመንና እድል አግኝተው መረራና ቡድኑ ይህን ታሪክ ወደ ሕዝብ አእምሮ ማስረጸ ከቻሉ የኦሮሞ ሕዝብ መካከል ቁጭ ብሎ እንደልብ መሆን እንደማይቻል ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ያኔ ነፍጠኛ የተባለው አማራና ዛሬ ታሪኩን የተቀማው ኦሮሞ አንድ ሕዝብ እንደሚሆኑም ወያኔዎች አሳምራው ያውቃሉ፡፡ እነዚህን ሁለት ታላላቅ ሕዝቦች ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሚኒሊክ ታሪክ እንደተጣመረ ወያኔዎች አስቀድመው ስላወቁት ነበር በዚህ ታሪክ ላይ ዘመቻ የከፈቱትና የኦሮሞ በሚል የተለያየ ቡድኖች ጋር በጋራ ሲሰሩ የነበሩት፡፡ ዛሬ ሌሎች የኦሮሞ ቡድኖችን በበላይነት የተቆጣጠረው የሙስሊሙ ቡድን ከወያኔ እኩል የእነ መረራ ቡድን ትልቅ ስጋቱ ነው፡፡ ለዛም ነው የእነመረራ ቡድን በሕዝብ ዘንድ ዕውቅና እያገኘ ሲመጣ የሕዝብን ትግል ለማምከን የተለያየ ሩጫ የሚያደርገው፡፡ የለንደኑ፣ የአትላንታው፣ በቅርብ የዲሲው ስብሰባዎች አላማ የኦሮሞ ታጋዮች እኛ ነን በሚል ቀድሞ ለመገኘት ነበር፡፡ ለሕዝብ በለው በእስር እየማቀቁ ያሉ እውነተኛ ታጋዮቹን እንዲዘነጋና ሌላ ውዥንበር ለመፍጠር ነበር፡፡ ሆኖም የተሳካ አይመስልም፡፡ የሙስሊሙ ቡድን አሁን ላይ የሚይዘው የሚጨብጠው ስላጣ ነገሮች ሳያውቃቸው እያፈተለኩበት ይመስላል፡፡
እስከዛሬ የሆነው ሁሉ ሆኗል የኦሮሞ ሕዝብ ግን ከዚህ በኋላም ቢሆን ሊነቃ ይገባል፡፡ ለዘመናት ድጋፍ የነፈገውን መረራን ዛሬ በተግባር መሥዋዕት እየሆነለት እንደሆነ መረዳት ይገባዋል፡፡ ሰሞኑን ለማ መገርሳን ለማጣጣል አንዳንድ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይሰማል፡፡ ከለማ ይልቅ ሙክታርን ማወደስ ተጀምሯል፡፡ ይህ የሙስሊሙ ቡድን ከወያኔ ጋር በትብብር የሚሰሩት ሴራ እንደሆነ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡ የሙስሊሙ ቡድን እንደነገርኳችሁ ነው፡፡ ለታማኝነት ሙስሊም መሆን እንጂ የፖለቲካ አመለካከት አደለም፡፡ የእነመረራ ቡድን ለሙስሊሙ ቡድን የሚመች አደለም፡፡ ሲጀምር የመረራ ቡድን የበሰሉ ምሁራንን ያካተተ ከተሻለ ኑሮዋቸው ተነስተው ለሕዝብ ፍትሕ ለማምጣት መስዋዕት ሊሆን የቆረጡ በገንዘብና በመደለያ የማይታለሉ አባላት የበዙበት ነው፡፡ ለዛም በተግባር ሳይቀር መሥዋዕትነትን እየከፈሉ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሕዝብ ትኩረቱን ወደነ መረራ እንዳደረገ ቢገባኝም መዘናጋትን ለመፍጠር ብዙ ቡድኖች ውዥንብር እየነዙበት ነው፡፡ አገር ቤት ያለው ሕዝብ የበለጠ ነገሮችን የመረዳት አቅም እያገኘ ነው፡፡ ዲያስፖራ የተባለው ለሕዝብ ትግል ዋነኛ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡ ትክክለኛ ኦሮሞ ነኝ የምትል ሁሉ ሌላውም የሕዝብህ ሕመም ይሰማህ፡፡ ባልተፈጠረ ታሪክ ዛሬ የመከነውን አእምሮህን እስኪ እውነታው ምንድነው ብሎ እንዲጠይቅ አድል ሥጥ፡፡
በውጭ ያሉ ሌሎች ቡድኖችና ሚዲያዎች
እስከዛሬ እንደምናያው ከላይ የጠቀስኳቸው ቡድኖች ያልሆነን ነገር ተደረገ እያሉ ለሕዝብ ሲናገሩ ያለከልካይ አልፎም በውጭ ያሉ ምሁር ተብዬዎችና፣ ሚዲያዎች ተሳታፊነት ነው፡፡ የሚኒሊክ የአርሲ ጦርነት ሚኒሊክን ያሳዘናቸው ሚኒሊክ ለሕዝብ አዛኝ ስለነበሩ ነው፡፡ በእርግጥም ያ ጉዳት መድረስ አልነበረበትም፡፡ ከዚያ በኋላ የተነሱትን መሪዎች እንይ እስኪ፡፡ ዛሬ እኮ ሕዝብ እያለቀ ያለው በጦርነት አደለም፡፡ በከተማ ላይ ነው፡፡ ለዛሬዎቹ ግን ሕዝብን መጨፍጨፍ ሰላም የማስከበር ጀግንነት ነው፡፡ የአርሲ ጦርነት ከሌላ ጦርነት የተለየ ታሪክ የለውም፡፡ ዛሬ ሴረኞቹ እንደሚያወሩት ሳይሆንም በወቅቱ ባለ የጦርነት ልክ ነው የሕዝቡም መጎዳት፡፡ ዛሬ ላይ እኮ በቀላሉ ወደ ጉድጓድ ተገፍትሮ በመቶ የሚቆጠር ሕዝብ እያለቀ ነው፡፡ በጦርነት ለማይረባው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከ70 ሺ በላይ ወገኖቻችንን ገብረናል፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ያስደሰተ እየመሰለው ስንት ምሁር ተብዬ ሴረኞች በፈጠሩት የውሸት ታሪክ ተባባሪ ሲሆን አይተናል፡፡ ሚዲያዎች ለዚህ ተባባሪ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቻችን እውነታዎችን ፊት ለፊት በዚህ መልኩ በጽሁፍ በማቅረብ የማንስተናገድበት ጊዜ ነበር፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ መነገጃ ያደረጉ ቡድኖችን ተፈርቶ የብዙዎች ድምጽ እንዳይሰማ ተደርጓል፡፡ ፕ/ር ኃይሌን ለቃለምልልስ የጋበዛቸው ሚዲያ ምሁሩ በሰጡት አስተያየት የሙስሊሙ የኦሮሞ ቡድን ያፈራቸው ጭንቅላቶች ተንጫጩ ተብሎ ምሁሩን በማጋፈጥ ለሚንጫጩት ይቅርታ እስከመጠየቅ ደርሷል፡፡ ከሚንጫጩት ግን እስኪ የእናንተንም እንስማ ብሎ ቃለመጠይቅ በማድረግ ለሕዝብ ማመዛዘን የሚያስችል ዝግጅት አላቀረበም፡፡ ከሚንጫጩትም ባይሆን ሌላ የኦሮሞ ምሁር ማቅረብ በተቻለ ነበር፡፡ በሌላ መልኩ አንዳንድ ሚዲያዎች ሌሎችን የሚያሳንስ ፕሮፓጋንዳ በመስራት በሕዝብ ዘንድ መከፋፈል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም እንድል ሊሰጣቸው አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ዛሬ ላይ ፌስ ቡክን የመሳሰሉ መረጃ መለዋወጫዎች በጎ ነገር ቢኖራቸውም ሌላው የውዥንብር ሥፍራዎች ሆነዋል፤፡ ሕዝብን የሚሳደቡ፣ ያለታረሙ ግለሰቦች በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው መርዛቸውን ይረጫሉ፡፡
እግዚአብሔር ለሁላችንም ማስተዋሉን ይስጠን!
ልዑል አምላክ እግዚአብሔር የወገኖቻችንን መከራ ያስወግድ! አሜን!
ሰርጸ ደስታ