የትግራይ ህዝብ እና የህውሓት ግኑኝነት በተመለከተ በተለያዩ ሰዎች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች እስከዛሬ ድረስ አወዛጋቢ ሆነው ቀጥለዋል። እስከዛሬ ድረስ አወዛጋቢ መሆኑ በራሱ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳስብ ነገር ነው። ከዚህ ቀደም በርካታ ሰዎች ለጉዳይ ትኩረት ሰጥተው የጻፉ፡ የሚድያ ሽፋን የሰጡ፡ የግል ምስክርነታቸውንና ግንዛቤያቸውን በተለያየ መንገድ የገለጹ ቢሆንም፡ ወቅቱ የሚጠይቀው ርዕሰ ጉዳይ በመሆኑ እኔም የራሴን እይታ ማስቀመጥ እንዳለብኝ በማመን ይህን ጽሁፍ አዘጋጅቻለሁ። ጽሁፉ ምናልባትም ከዚህ ቀደም ያልነበራችሁን ግንዛቤ እንደሚያስጨብጣችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።
ቅድመ እይታ
በአንድ በኩል ህውሓት ደጋግሞ “እኔና የትግራይ ህዝብ የማንነጣጠል አንድ አካል ነን” የሚል ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ ከህዝቡ መካከል በግልጽ “የለም እኛና እናንተ ለየቅል ነን፡ ገዢና ተገዢ ወይም ጨቋኝና ተጨቋኝ ነን” የሚላቸው በጣም ጥቂት ነው። ጥቂት በመሆኑ የተነሳ እና በህውሓት የረዥም ጊዜ የፕሮፓጋንዳ ስራ የተነሳ፣ በአብዛኛው ሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ፕሮፓጋንዳው ተቀባይነትን አግኝቶ ቆይቷል። ህዝቡና ድርጅቱ የማይነጣጠሉ ናቸው ተብሎ ተደምድሟል።
“ህውሓት እኔና የትግራይ ህዝብ አንድ ነን ይላል፡ አይደለንም ብሎ የሚከራከር ሰው አልተገኘም። ስለዚህ እነሱ አንድ ነን ካሉ እኛ እንዴት አንድ አይደላችሁም ልንል እንችላለን” ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታ ነበረ። በተጨማሪም “የትግራይ ህዝብ ከሌላው በተለየ በዚህ ስርዓት ተጠቃሚ ነው፣ ከዚህ የተሻለ ሌላ ሊጠቅመው የሚችል ስርዓት አይኖርም፣ ስለዚህ ጥቅሙን ለማስከበር ከስርዓቱ ጎን የግድ ይሰለፋል” ብለው የሚከራከሩም ጥቂት አይደሉም።
![TPLF Tigray Flags in Ethiopia]()
የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚነት i
የተለየ አፈናበሌላ በኩል ደግሞ “ህዝቡ ህውሓት እኛን አይወክልም ብሎ ለመናገር ያልቻለው ከሌላው በተለየ በትግራይ አፈናው ስለሚያይል ነው።” እንዲህውም “ህዝቡ በተለየ ተጠቃሚ ሊሆን ቀርቶ ከሌላው በባሰ የባርነትና የድህነት ህይወት ውስጥ እየኖረ ነው።” ብለው ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ቁጥራቸው የማይናቅ ነው። የዛሬ ዓመት ትግራይን እንዲጎበኙ የተደረጉ አርቲስቶች አብዛኞቹ ራሳቸውን ከዚህ ጎራ መድበዋል። እነ አትሌት ፈይሳ፣ ፕ/ርመስፍን ወ/ማርያም፣ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ እና ለሌችም የትግራይ ህዝብ የሚኖረው እንደማንኛው ኢትዮጵያዊ ነው በሚል አቋማቸው እናውቃቸዋለን። እኔም ራሴን ከዚህ ጎራ እመድባለሁ። ክልሉ ውስጥ እንዳደገ፣ እንደተማረና እንደሰራ ሰው ነባራዊውን ሁኔታ ኖሬበት የማውቀው ነውና ይህን አቋም ብይዝ የሚገርም አይሆንም። ማስረዳት ግን ይጠበቅብኛል። እንሆ፥
ቀጥተኛ አፈና
ትግራይ ከሌሎች ክልሎች ለየት የሚያደርገው በህውሓት ቀጥተኛ አፈና ስር መሆኑ ነው። ህውሓት በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን የተቆናጠጠ ብቸኛ “ሉአላዊ” ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፡ ይህን የበላይነቱን ለማስጠበቅ ቁልፍ ቁልፍ የመንግስት ስልጣኖችን በመያዝና ሁሉንም መንግስታዊ መዋቅር በቁጥጥሩ ስር በማድረግ አገሪቱን በእግር ብረት ጠፍሮ እየገዛ እንደሆን ይታወቃል። በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ የሆኑ የጋራ የአፈና ዘዴዎች ተዘርግተዋል። የጸጥታ ሀይሉ፣ መከላከያው፣ የፍትህ ተቋማቱ፣ የደህንነት ክፍሉ ወዘተ በህውሓት ቁጥጥር ስር ውለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነቱን ለማስጠበቅ የሚጠቀምባቸው የፖለቲካ መሳሪያ መሆናቸው እሙን ነው።
ያም ሆኖ ሌሎች ክልሎች በህውሓት ቀጥተኛ አፈና ስር አይደሉም ያሉት። አፈናው በሌላ third party (ወይም ጠፍጥፎ በሰራቸው ተላላኪ ድርጅቶች) አማካኝነት የሚገለጽ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች የህውሓትን ያክል ጥንካሬና aspirations ኖሯቸው ህውሓት በሚያፍነው ወይም ማፈን በሚፈልገው ደረጃ ህዝብን የሚያፍኑ አይደሉም። እንዳውም አንዳንዴ የሚገዳደሩበት (resist የሚያደርጉበት) ሁኔታ አለ። በነዚህ ክልሎች ውስጥ ለሚኖር ህዝብ ይህ ክፍተት ተቃውሞውን በተለያየ መንገድ ለመግለጽ በአንጻራዊነት የተሻለ ዕድል ፈጥሯል። ለምሳሌ የግል ፕሬሶችን በመክፈትና ህዝብን በማነቃቃት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመመስረትና በህጋዊ ተቃዋሚነት በመንቀሳቀስ፣ ብሎም በአደባባይ ተቃውሞን በማነሳሳት ረገድ በሌሎች ክልሎችይህ ክፍተት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ትግራይ በቀጥታ በነሱ ቁጥጥር ስር መሆኑ እና ደግሞ በዚህ ክልል ተቃውሞ ከተነሳባቸው ለህልውናቸው የመጨረሻ አደገኛ በመሆኑ፣ እነዚህ በሌላ ክልል የሚታዩ የህዝብ የresistance መገለጫዎች ለረዥም ጊዜ በትግራይ እንዳይፈጠሩ ማድረግ ችለዋል። የግል ፕሬስ ትግራይ ውስጥ ከነ አካቴው እንዳይፈጠር አድርገዋል። በሌሎች አካባቢዎች አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ የግል ህትመቶችና መጻህፍቶች የትግራይን ምድር እንዳይረግጡ እገዳ ተጥሎባቸዋል። የግል ሚድያ ለመፍጠር የሞከሩ አንድ ወይም ሁለት ወጣቶችን ገና በለጋነታቸው ሳይበራከቱ ልክ አስገብተዋቸዋል። በትግራይ የሚናገረው ህውሓት ብቻ ነው። የሚደመጠው ህውሓት ብቻ ነው። ሌላ ድምፅ የለም።
በትግራይ ለረዥም ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዳይመሰረትና በክልሉ እንዳይንቀሳቀስ ግልጽ በሆነ አፈና አግደውታል። ዓረና ትግራይን ዘግይተውም ቢሆን የፈቀዱት አንድም የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በክልሉ እንደተጀመረ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለመጠቀም፣ ሁለትም መስራቾቹ የቀድሞ የህውሓት ታጋዮች በመሆናቸው ህዝብ ከኛ በተለየ መልኩ ሊቀበላቸው አይችልምና ለስልጣናችን አደጋ አይሆኑም በሚል እሳቤ መሆኑ ይታወቃል። ያም ሆኖ ሰርጎ ገቦችን ከትተው በየጊዜው ሲያፍረከርኳቸው ይስተዋላል። ስርዓቱን አምርረው የሚቃወሙ ወጣቶች አማራጭ ፓርቲ ሊመሰርቱ ቀርቶ ብሶታቸውን የሚጋሩበት፡ተቃውሞና ትችታቸውን የሚናገሩበት መድረክ ፈጽሞ አያገኙም። የህውሓት ቀይ መስመር በትግራይ ደመቅ ይላል። ህውሓት ተቃውሞ በትግራይ ፈጽሞ አይፈቅድም። እስከመቼውም ድረስ ሊፈቅድ አይችልም።
የመረጃ አማራጭ ከሌለ፣ በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ህውሓት እየሰራቸው ያሉ ወንጀሎች ህዝቡ የሚያውቅበት መንገድ ከሌለው፣ ህዝቡ ለነጻነቱ እንዲቆም በሰላማዊ መንገድ የሚያነሳሱና የሚያስተምሩ ወጣቶችና ፓርቲዎች ከሌሉ፣ በራሱ ጊዜ ህዝብ ተነስቶ ለመቃወም እድሉ ጠባብ ይሆናል። ወይም በጣም ጊዜ የሚጠይቅ ይሆናል። በአንድ በኩል ህዝቡ ከመታፈኑ በተጨማሪ በጥላቻ የተሞሉ ፕሮፓጋንዳዎችን በየቀኑ ሲለፍፉበትና ሲያሴሩበት ስለሚውሉ በፍርሃት እንዲሸበብ ተደርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ባልተነቃባቸው ተዘዋዋሪ የአፈና መሳሪዎችን በመጠቀም ህዝቡ በተለይ የገጠሩና የከተማ ድሃው ክፍል ሰጥ ለጥ ብሎ ለህውሓት እንዲገዛ ተደርጓል።
ተዘዋዋሪ የአፈና መንገዶች
የትግራይ እግሪ ምትካል /ትእምት/EFFORT/
ይህ ድርጅት የህውሓትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጡንቻ ያፈረጠመ ጠንካራ ድርጅት ነው። ስልጣን ላይ ለመቆየት የመንግስት መዋቅሮችን መቆጣጠር ብቻውን በቂ አይደለም በሚል እምነት የቆመና የራሱን የኢኮኖሚ ኢምፓየር በአገሪቱና በውጪ አገራት የዘረጋ ድርጅት ነው። እንደ ድርጅት financial freedom ከሌለውና እንደ መንግስት በውጭ እርዳታ የቆመ ከሆነ፣ ህውሓት በፈቀደው መንገድ አገሪቱን መግዛት አይችልምና ከጅምሩ የዚህ ዓይነት ምሰሶ መትከል ነበረበት።
ይህ ድርጅት ፓርቲው በማንኛውም ጉዳይ ፈርጣማና ፍሌክሲብል የሆነ ጡንቻውን እንዲጠቀም ከማስቻል በተጨማሪ፣ በስነልቦና ጦርነት ረገድ የማይናቅ ድልን አቀዳጅቶታል። ዛሬም ድረስ በርካታ ወጣቶች EFFORT የህዝብ ንብረት ነው በሚል ተስፋ ይኖራሉ። ይህን የህዝብ ንብረት “ከጠላት” የመጠበቅ አደራና ግዴታ አለብን ብለውም ያምናሉ። ይህ የህዝብ ሀብት ባለበት ሊጠበቅ የሚችለውና ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ህውሓት ሲኖርና ችግሮቹን በግምገማ በተሃድሶና በመሳሰሉት እንዲፈታ ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ብሎ የሚያምነው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ህውሓት ከስልጣኑ ከተነሳ ይህን ሀብት እናጣለን በሚል ስጋት ትግላቸው ለጥገናዊ ለውጥ ብቻ ይሆናል።
በእርግጥ ዛሬ በትግራይ ተቃውሞ አለ ከተባለ ከዚህ የዘለለ ተቃውሞ አይደለም ሊታይ የሚችለው። ይህ ደግሞ ለህውሓት ድልን አጎናጽፎታል። እኔ ከሌለሁ ትጠፋለህ ከሚለው ፕሮፓጋንዳ ጋር ስምም የሆነ አካሄድ በመሆኑ፣ ህዝቡ ህውሓት ላይ እንዳይነሳ ራሱን የቻለ አንድ ምክንያት ሆኗል። ባጭሩ በተዘዋዋሪ መንገድ የማፈኛ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል። ይሄ ወደፊትም አደጋ ያለው አካሄድ በመሆኑ በEFFORT ጉዳይ ላይ በግልጽ መነጋገር ለነገ የሚተው ጉዳይ መሆን የለበትም። በዚህ ዙሪያ ግልጽ የሆኑ ውይይቶችን ማድረግ በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ተገቢ ነው፥ በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ምክንያት ጥገናዊ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አያስፈልግም ብሎ ለሚያምነው ክፍል መልስ ለመሰጠት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በድህረ ህውሓት ለምትኖረን ኢትዮጵያ ይህ ኩባንያ ያልተጠበቀ ችግር ሳይፈጥር በፊት ውይይቱን ከወዲሁ መጀመር የነገ አካሄዳችንን ፈር ለማስያዝ ይረዳል።
ማሕበር ረድኤት ትግራይ /ማረት/REST/
ይህ ድርጅት ላይ ላዩን በእርዳታና በልማት ስራ የተሰማራ ሲቪክ ተቋም ይምሰል እንጂ በብዙዎች ዘንድ ያልተባነነበት mighty የፖለቲካ ድርጅት ነው። በክልሉ ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን ያለውና ህዝቡን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ የሚጠቀሙበት ቁጥር አንድ የፖለቲካ መሳሪያቸው ነው። የመሳሪያዎቹ ዝርዝር ከቀላል ወደ ከባድ፥
1• ማረት በህዝብ ስም እርዳታ ይጠይቃል። እርዳታ የፖለቲካ መሳሪያ ነው። የህውሓትን ትዕዛዝ የማያከብር ድሃ በእርዳታ ይቀጣል። ከምግብ ለስራ ይሰናበታል። ወዘተ። ድሃን በጉሮሮው ከቀጣኸው ጉልበት ኖሮት ሊቃወምህ አይችልም። ስለዚህ ቀዳሚው የህውሓት ስራ አብዛኛውን የህዝብ ክፍል አደህይቶ የመግዛት ፖሊሲውን ማስቀጠል መቻሉ ነው። በቁጥጥሩ ስር በሆነ የማረት ተቋም እርዳታና የምግብ ለስራ እድሎችን በመስጠትና በመንፈግ በቀላሉ ህዝቡን ለማንበርከክ የተዋጣለት ከፖሊሲው ጋር የተቀናጀ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ አገልግሎታል።
2• ህውሓት ማንኛውም ዓይነት የውጭ ግብረሰናይ ድርጅት (NGO) ትግራይ ውስጥ ራሱን ችሎ እንዳይንቀሳቀስ ገና ጫካ እያለ ጀምሮ በህግ አግዷል። ፕሮጀክታቸውንና ገንዘባቸውን ይዘው መጥተው ለማረት በማስረከብ፣ በማረት አማካኝነት ፕሮጀክቱ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚጠይቅ አሰራር ይከተላል። መያዶቹ ከተስማሙ የፕሮጀክቱን ሂደት አልፎ አልፎ ሱፐርቫይዝ ለማድረግ ብቻ ይፈቀድላቸዋል። ካልተስማሙ ገንዛባቸውንና ፕሮጀክታቸውን ይዘው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ያደረጋል። ህዝቡ መሃል ገብተው በራሳቸው እቅድና የአፈጻጸም መንገድ እንዲሰሩ ህውሓት ፈጽሞ አይፈቅድላቸውም፤ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች፥ የመጀመሪያው የውጪ ድርጅቶች ህዝቡን ቀርበው በማነጋገር ህዝቡ ያለበትን ትክክለኛ ሁኔታ እንዳያወቅ፣ አውቀውም ወደ ውጪ እንዳይወጡት በመፈለግ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከህውሓት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ገቢ ህዝቡ እንዲኖረው ስለማይፈለግ ነው።
እነዚህ ሁለቱ ምክንያቶች ህውሓት በክልሉ የሚኖረውን ሃይል ማዳከም የሚችሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል። ዛሬ NGOዎች ስፖንሰር ያደረጉትን ፕሮጀክት ሱፐርቫይዝ ሲያደርጉ የሚያነጋግሩት ህውሓት ያዘጋጀላቸውን ካድሬዎችን ብቻ ነው። ህውሓት ያላዘጋጃቸው በዕጣ የተመረጡ ተራ ሰዎች ስለሚኖሩበት ህይወት በትክክል እንዲናገሩ አይደረግም። ድንገት ተመርጠው ከሆነም ካድሬ በመሃከላቸው እንዲገኝ ተደርጎ ስለሚናገሩት ነገር እየተሰለሉ ነው። በተናገሩት መሰረት ከተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲገለሉ እንደሚደረጉ ስለሚያውቁ ያሉበትን ሁኔታ በትክክል ለመናገር ይፈራሉ። በዚህ ምክንያት በተለይ ለውጭ ሚድያዎችና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክልሉ ዝግ እንደሆነ እስከዛሬ ድረስ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ከህውሓት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ገቢ የሚያገኝ ሰው፣ በህውሓት መታዘዝን አሻፈረኝ ሊል ይችላልና ለፖለቲካ ህልውናቸው አደጋ ነው። ስለሆነም ህውሓቶች ይህን ሊፈቅዱ ፈጽሞ አይችሉም።
3• ማረት ከእርዳታ ውጪ በ”ልማት” ትርፍ በሚያስገኙ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው። “የልማት” ስራው ባብዛኛው ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በፕሮጀክት ስም ከውጪ ለሚያገኘው ገንዘብ እንደ ሽፋን የሚጠቀምበት የማጨናበሪያ መንገድ ሲሆን፣ ጎን ለጎን ደግሞ የማሳያውን ልማትም ቢሆን የሚሰራው ለድርጅቱ ታዛዥ የሆኑ አካባቢዎችንና ግለሰቦችን ታርጌት ባደረገ መልኩ ነው። ያም ሆኖ አንዱን የልማት ስራ ከሶስት ወይም አራት የተላያዩ ፕሮጀክቶች ሂሳብ እያወራረደ ኪሱን የሚሞላበት አሰራርን ዘርግቷል። በዚህ መንገድ የሚገኘው ትርፍ የህውሓትን ኪስ ከማደለብ ባሻገር ህዝቡን በሚከተለው መንገድ ለማፈን ይጠቀሙበታል።
4• ማረት የብድር ሰጪ ተቋም (ደደቢት) በውስጥ ስላለው በዚህ ተቋም አማካኝነት በተለይ ድሃው ገበሬ በተለያዩ ምክንያቶች ብድር እንዲወስድ በህውሓት ይገደዳል። የብድሩ ምንጭ የማረት ትርፍ ነው። የማረት ትርፍ የሚመጣው በተጨናበረ መንገድ ነው። ገበሬው ያለፈቃዱና ያለ በቂ ስልጠና ተገድዶ ለማዳበሪያ ለምርጥ ዘርና ለመሳሰሉ የምርት ግብዓቶች እንዲህውም መጤ የግብርና ፓኬጆች ብድር እንዲወስድ ይደረጋል። ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲህውም ሌሎች ግብዓቶችን የሚያቀርበው ጉና ነው። ጉና በEFFORT ስር ነው። ጉና ምርቱን ለገበሬ አስገድዶ በመሸጥ ያተርፋል። ገበሬው በራሱ ጥሬ ገንዘብ መግዛት ስለማይችል፥ ብድር ከማረት በከፍተኛ ወለድ እንዲወስድ ይደረጋል። ማረት ሌላ ትርፍ ያጋብሳል። ገበሬው ብድሩን ለመክፈል ፍዳውን ያያል። ብድሩን ለመክፈል የግድ በእርዳታና በምግብ ለስራ ፕሮጀክቶች ስር መታቀፍ መቻል ይኖርበታል። በነዚህ ስር ታቅፎ ተጠቃሚ ለመሆን ደግሞ፣ ለህውሓት ታዛዥነቱንና አሜን ባይነቱን ማረጋገጥ አለበት። ወዘተ።
በዚህ ሁኔታ ነው ገበሬውን ሸብበው የያዙት። በተለይ ትግራይ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ህዝብ (ገበሬው) በኛ ቁጥጥር ስር ነው ሲሉ ደጋግመው የሚፎልሉትም በዚህ ምክንያት ነው። ገበሬው መቼም ቢሆን አንገቱን ቀና ማድረግ እንዳይችል የተወሳሰበ አሰራር ዘርግተው አስረውታል። ዛሬ የጎንደር ምሊሻ ገበሬና የኦሮሚያ ገበሬ ለነጻነቱ እንደቆመው ዓይነት ተቃውሞ ከትግራይ ገበሬው ይነሳባቸዋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ገበሬው ካልተነሳ ደግሞ ሌላው ያን ያክል ስጋት ላይ የሚጥላቸው ባይሆንም ለሱም የሚቀጥለውን መሸበቢያ አሰራር ዘርግተዋል።
ማሕበር ልምዓት ትግራይ /ማልት/TDA/
ይህ ድርጅት ሲቋቋም በተለይ በዳያስፖራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በጦርነት የተዳከመችዋን ትግራይ ተረባርበው እንዲያለሙ እድል ይስጣል በሚል ዓላማ ነበር። ነገር ግን በዚህ መንገድ ለበርካታ ዓመታት ከዳያስፖራ ተጋሩ፣ በውጪ አገራት የትግራይ ወዳጆች እና በአገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ ባለሃብቶች ከፍተኛ ገንዘብ የተሰበሰበ ቢሆንም መድረሻው ሳይታወቅ እንደተነነና ይህም ጥያቄ አስነስቶ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ምክንያት ድርጅቱ አንዴ እንዲፈርስ፣ ሌላ ጊዜ ተመልሶ እንዲቋቋም ሲደረግ ቆይቷል። ከጅምሩ ዓላማው ፖለቲካዊ እንጂ ልማታዊ ባለመሆኑ፣ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ዳግም እየመጣ የህዝቡን የልብ ትርታ የሚያዳምጡበት ሁነኛ የፖለቲካ መሳርያ ሆኗል። እንግዲህ የኔ ጥርጣሬ በዚህ ድርጅት የተሰበሰበው ገንዘብ፣ ብዙዎች እንደሚሉት በግለሰቦች ተመዝብሮ ድራሹ ጠፍቷል ሳይሆን ወደ EFFORT ወይም የህውሓት ካዝና ገብቷል የሚል ነው። ይህም ማለት በልማት ስም የሚሰበሰበው የመዋጮ ገንዘብ በራሱ ህውሓትን በማደለብ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። የህውሓት የገንዘብ ምንጭ መሆኑ በራሱ የፖለቲካ መሳሪያ ቢሆንም ይህ ቀላሉ ጉዳይ ነው።
ከባለሀብት የተጀመረው ለማልት መዋጮ የመሰብሰብ አሰራር፣ ብኋላ የመንግስት ሰራተኛንና ተማሪውን የሚያሳትፍ እንዲሆን ተደርጓል። ከተማሪም ይሁን ከመንግስት ሰራተኛ የሚሰበሰበው ገንዘብ ያን ያህል የረባ ገንዘብ ባይሆንም በማልት ስም ህውሓት ለሚያቀርብላቸው ጥያቄ ባለሀብቶቹ፣ ሰራተኞቹና ተማሪዎቹ የሚሰጡት ምላሽ አወንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ የሚለውን የሚለኩበት የፖለቲካ መሳሪያ ነው። አሉታዊ መልስ የሚሰጡት በርከት ያሉ እንደሆን “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃዎችን ይወስዳሉ። እርምጃዎቹ ግለሰብ ተኮር ቅጣቶች በመሰንዘር ወይም systematic የሆኑ የአሰራር ለውጦችን በመከተል ሊፈጸሙ ይችላሉ። ማልት የህዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጡ ከስር ከስር እርምጃ የሚወስዱበት መሳሪያ በመሆኑ ከEFFORT እና ከማረት ቀጥሎ ሶስተኛው የተዋጣለት የፖለቲካ መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል።
ከነዚህ ሶስቱ ተቋማት በተጨማሪ እንደማንኛውም ክልል በትግራይ ሌሎች የማፈኛ መንገዶች ስራ ላይ ናቸው። 1ለ5 ጥርነፋ፣ የጸጥታ ሀይሉና መከላከያው በቁጥጥራቸው ስር መሆን፣ የፍትህ ተቋማትና ደህንነት በነሱ ስር መሆን፣ አስገድዶ አባል ማድረግ፣ አባል ላልሆነ ዜጋ የስራ ዕድልና ሌሎች ነገሮችን መከልከል፣ በአንጻሩ ደግሞ አባል ለሆነና ለሚደግፋቸው በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ወዘተ በሌላው ክልል እንዳለ ሁሉ በዚህ ክልልም አለ። ለየት የሚለው ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱ ተቋማዊ የአፈና መሳሪያዎች ናቸው።
የትግራይ የተለየ ተጠቃሚ
እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩትን የአፈና መሳሪዎች ላነበበ የትግራይ በተለየ ተጠቃሚነት ሊዋጥለት የሚችል አይሆንም። ትግራይ ከሌላው በተለየ ተጠቃሚ አይደለም። እንዳውም በተለየ የታፈነ ህዝብ ነው። ይህ ማለት ግን በተለየ የተጠቀመ ክፍል የለም ማለት አይደለም። በፍጹም። እንዳውም በተገላቢጦሽ በስርዓቱ በተለየ ተጠቃሚ የሆነው ክፍል የወጣው ባብዛኛው ከዚህ ክልል ነው። በቁጥር ጥቂቶች ናቸው ነገር ግን ፍጹም የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ተቆናጠውቷል። ህውሓት ዓይኑን ጨፍኖ ሊያሞኘን እንደሚሞክረው በኢህአዴግ ስር እንዳሉት እንደ ማንኛውም ድርጅቶች እኩል አይደለም። የተለየ ተጠቃሚምና ፍፁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን የተቆናጠጠ ብቸኛው ሉአላዊ ፓርቲ ነው።
ፌቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ቁልፍ ቁልፍ የመንግስት ቦታዎችን በቁጥጥሩ ስር አድርጓል። ሁሉንም የመንግስት መዋቅሮችና የገቢ ምንጮችን በቁጥጥሩ ስር አውሏል። መከላከያ፣ ደህንነት፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ አየር መንገድ፣ አየር ሀይል፣ ጉምሩክ፣ ናሽኛል ባንክ፣ ሚድያ፣ ት/ት ሚንስቴርና ከፍተኛ የት/ት ተቋማት፣ አስመጪና ላኪ ድርጅቶች፣ ግብር ሰብሳቢ ባለስልጣን፣ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ የውጭ ምንዛሪ (ጥቁር ገበያ)፣ የመሬት ንግድ፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ገንዘብ አጠባ (money laundary & illicit financing) ወዘተ በህውሓትና በህውሓት ሰዎች ያልተያዘና ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ አንድም ዘርፍ የለም። ባጭሩ አገሪቱ የግላቸው ንብረት ሆኗለች። ፓርቲውና ከፍተኛ ካድሬዎች የልዩም ልዩ! ተጠቃሚዎች ናቸው። የነዚህ ሰዎች ልዩ ተጠቃሚነትና የበላይነት፣ ከአጠቃላይ የትግራይ (ህዝብ) የበላይነት ጋር ተምታቶ ሲቀርብ ይታያል። ይህ ስህተት ነው። ሊታረም ይገባል።
ማጠቃለያ
ፕ/ር መስፍን እና ሌሎችም ከዚህ በፊት እንዳሉት የመጨረሻው የድህነት ወለል ላይ ያሉት፣ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በአዲስአበባና ሌሎች ከተማዎች ጎዳና ላይ ሲለምኑ የሚውሉ የኔ ቢጤዎች በብዛት ከትግራይ የተሰደዱ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም፣ የሚላስ የሚቀመስ የሌለው፣ የህውሓትን ይሁንታና ምጽዋት ሲጠባበቅ የሚኖረው ህዝብ በትግራይ ያለ ማጋነን ከ80 በመቶ በላይ ይሆናል። ምጽዋት የማይጠብቁ የሚባሉት የመንግስት ሰራተኞች ራሱ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ሲኖሩ ይታያሉ። በተዘረጋባቸው የፖለቲካ መሳሪያ አማካኝነት ታፍነው ይኖራሉ። ብሶታቸውን ለመግለጽ ይፈራሉ። እንደምንም ወደ ውጭ ቢወጡ እንኳን፣ ከወጡ ብኋላም ፍርሃቱ አይለቃቸውም። ህውሓትን ይፈራሉ፣ በዘራቸው ምክንያት እንዳያጠቃቸው ሌላውን ይፈራሉ። የአጣብቂኝ ህይወት ውስጥ ይኖራሉ።
በእርግጥ በዛው ልክ ደግሞ ከህውሓት ጋር አሸሸ ገዳሜ የሚሉ፣ በህዝብ ስም የሚነግዱ፣ በህዝብ ስም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚጋጩ፣ በሌላው ሀዘን ላይ የሚጨፍሩ፣ በሌላው ደስታ ላይ ማቅ የሚለብሱ፣ ሆን ብለው ህዝቡ በሌላ እንዲጠላ የሚሰሩ የህውሓት ገረዶች አሉ። ህውሓት የሚፈልገው ስለሆነ ያሰማራቸው ካድሬዎች ናቸው። በተጠና መንገድ ተግባራዊ እየሆነ ያለ፣ ትግራይንና ትግራዋይን ከሌላው የመነጠል ስራ ነው።
የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን በኢትዮጵያ ማስጠበቅ ካልቻሉ፣ ቢያንስ በትግራይ ማስጠበቅ ይኖርብናል ብለው ያስባሉ። ምሽጋቸውን ትግራይ ላይ እየቆፈሩ ነው። ትግራይን ቄጤማ አድርገዋታልና በከፋ ቀን ጉዝጓዛቸው ትሆን ዘንድ በዝግጅት ላይ ነች። የዚህ እንድምታ ለብዙዎቻችን ምናልባት በደንብ አልገባን ይሆን ይሆናል። ምናልባት ሊታወቅ የማይችል ሊሆን ይችላል። ዛሬ ደርሰው የዓፈርንና የሶማሌን ብሄርተኝነት የሚያራግቡት፡ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ በዘር ከፋፍለው በማበጣበጥ እነሱ በትግራይ ለመሸሸግ ይመስላል። ምናልባት ሌላው ሲባላ እነሱ ደልቷቸው የሚኖሩ መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ፍላጎታቸው ምንም ይሁን ምን ትግራይንና ኢትዮጵያን ከዚህ ድርጅትና ከነዚህ ሰዎች ማስጣል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀላፊነትና ግዴታ ሊሆን ይገባል።
በሌላው ክልል እንደምናዬው በአጭር ጊዜ ውስጥ በራሱ ተነሳሽነት የትግራይ ህዝብ በተቃውሞ ይነሳል የሚለው እምነቴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል። ምክንያቱም ህዝቡ ህውሓትን ይፈራል፣ ሌላውን ወገኑንም ይፈራል። በተቃውሞ ለመነሳት አንዳቸውን መፍራት የግድ ማቆም አለበት። ሌላውን ወገኑን መፍራት እንዲያቆም በሌላው ወገኑ በኩል የአወንታ ምልክቶችና የትግል አጋርነቶችን ማየት አለበት። ህዝቡን ማግለልና ከህውሓት ጋር ደርቦ መፈረጅ ስህተት ስለሆነ ሊታረም ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ሌላውን ወገኑን እየፈራ ህውሓትን ሳይፈራ ለመታገል ይከብደዋል። ምክንያቱም ሌላውን እየፈራ ህውሓትን ሳይፈራ ጭቆና በቃኝ ብሎ ለመነሳት፣ ጠንካራ ትግራዋይነትን (ትግራዋይ ድርጅትን) መፍጠር ይጠበቅበታል። ከህውሓት ብኋላ ህልውናውን ለማስጠበቅ በደንብ መደራጀት እንደሚኖርበት የግድ ማመን ካለበት፣ ያንን ለማሳካት ጊዜ ይፈጃልና በቅርቡ ተቃውሞ ሊያስነሳ አይችልም። ከጊዜው አንጻር የተሻለው አማራጭ ትግራይንም ያካተተ፣ ትግራይን ከህውሓት ነጻ ለመውጣት ጭምር ያለመ ኢትዮጵያዊ ትግል ማካሄድ ነው። ይህን ማድረግ ግድ ይላል።ህውሓት እንደ ድርጅት እስካለ ድረስ የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በሰላም ሊኖር አይችልምና ህውሓት ከኢትዮጵያ ምድር እስከወዲያኛው ማስወገድ ብቸኛው የማታገያ መንገድ ሊሆን ይገባል።
በመጨረሻ በተለይ ህዝባችን ያለበት ሁኔታ የሚያሳስበን በውጪ የምንኖር የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር በመተባበር በህውሓት ምክንያት ዜጎች እየደረሰባቸውን ያለ ግፍ በጋር በማውገዘ የትግል አጋርነታችንን በግልፅ ማሳየት አለብን። በትግራይ ያለዉን እውነተኛ ገፅታ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ማስረዳት ይጠበቅብናል። የትግራይ ህዝብም ለነፃነቱ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲቆም ማነሳሳት ይጠበቅብናል። በቃኝ የሚልበትን ጊዜ ለማፋጠን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። በፕ/ር መስፍን የቀረበ የመፍትሔ ሀሳብ በማካፈል ፅሁፌን ላጠናቅቅ።