Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ችጋር በሰው ዘር ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው

$
0
0

አለም እጅግ በሰለጠነበት በዚህ ክፍለ ዘመን፣ የሰው ልጅ በእውቀትና በቴክኖሎጂም በመጠቀበት ወቅት በሚሊዮኖች የሚገመቱሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው፣ ሰማይና ምድሩ ተዳፍኖባቸው ከሞት አፋፍ የሚደርሱበትና ከፊሉም የሚሞቱበት አገርና ስፍራ ቢኖር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ማሕበራዊ ፍትሕ የተጓደለባቸው፣ ሙሰኝነት መረን በለቀቀ መልኩ በተንሰራፋባቸው፣ ፍጹም የሆነ አንባገነናዊ ሰርዓት በሰፈነባቸው እና የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት አገሮች ወይም እንደ ሶማሊያ ባሉ መንግስት አልባ ሆነው ለረዥም አመታት በትርምስና እልቂት ውስጥ በቆዩ ጥቂት አገሮች ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰተውን ችጋር በተመለከተ እረዘም ላለ ጊዜ ጥናት ያካሄዱትን ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ ተመራማሪዎች በጥናቶቻቸው እንዳረጋገጡት የ‘ችጋር’ ምንጩ የተፈጥሮ አየር ንብረት መዛባት ወይም የእግዜር ቁጣ ሳይሆን ብልሹ የፖለቲካ አስተዳደርና የተሳሳተ የመንግሥት ፖሊሲ ወይም የአፈጻጸም ችግር የሚያስከትለው አደጋ ነው፡፡ ከአንድ መጥፎ ሥርዓት ወደ ባሰ መጥፎ ሥርዓት ስትንከባለል የመጣችው አገራችንም ከ1958 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ጊዜያቶች ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ችጋር አንጃቦባታል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል ግምት የማይሰጣቸውን ድሃ ልጆቿንም እንደ ጩልፊት አሞራ ነጥቋታል፡፡

ይህ አንባገነንና አፋኝ ሥርዓትን እንደ ጥላ የሚከተለው የችጋር አዙሪት ዛሬም አገሪቱ በልማት ገስግሳለች እየተባለ ሌት ተቀን በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር በሚዘፈንበት ወቅት የአሥራ አምስት ሚሊዮን ድሃ ልጆቿን ሕይወት ሊቀጥፍ እንደ ጩልፊት አሞራ እያንጃበበ መሆኑን ከአገዛዙ ልሳን ጭምር እየሰማን ነው፡፡ የአገዛዝ ስርዓቱ ለዚህ አደጋ አራሱን ተጠያቂ ላለማድረግ ሁለት ዋና ምክንያቶችን እየደረደረ ነው፡፡ አንድም ችግሩ የተከሰተው በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የአየር መዛባት መሆኑን እና በሁለተኛ ደረጃም ችግሩ የተባባሰው አገሪቱ በልማት ጎዳና ላይ ብትሆንም ገና በምግብ እራሱዋን ያልቻለች ደሃ አገር ስለሆነች ነው የሚል ነው፡፡ የመጀመሪያውን ምክንያት ድርቅን ከማስከተል ያለፈ የችጋር አደጋን ሊያመጣ እንደማይችልና ድርቅ ወደ ችጋር የሚለወጠው በምሁራኖቹ ጥናት እንደተረጋገጠው የብልሹ ሥርዓት ውጤት ስለሆነ እሱ ላይ በዙ ማለት አይጠበቅብኝም፡፡ ሁለተኛውን ምክንያት የተመለከትን እንደሆነ በእርግጥም ኢትዮጵያ ድሃ ልጆቿን በችጋር ከሚደርስ የሞት አደጋ ለመታደግ በሚያስቸግር ደረጃ ላይ የምትገኝ ደሃ አገር ነች ወይ የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡

በአገሪቱ የተላያዩ ክፍሎች የችጋር ምልክት መታየት የጀመረው ከአመት በፊት ነው፡፡ በተለይም በአፋርና በሶማሌ ክልል አካባቢ እንስሳቶች መሞት የጀመሩት፣ በምግብና በመጠጥ ውሃ እጦት ሰዎች ከቅያቸው መሰደድ የጀመሩትከወራቶች በፊት ነው፡፡ ጉዳዩም በተለያዩ የመገናኛ በዙሃን ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ እንደሚታወቀው እነዚህ አካባቢዎች በተለይም በሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ ለረዥም ጊዜ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጭምር ወደ ክልሉ እንዳይገቡና እርዳታ እንዳያደርጉ የአገዛዝ ሥርአቱ የከለከለ በመሆኑ እየደረሰ ያለውን የጉዳት መጠን እንኳን በትክክል ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የአገዛዝ ሥርዓቱም ችግሩን በማጤን አፋጣኝ እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ የሥልጣን ዘመኑን ለማደስ ባካሄደው የይስሙላ ምርጫና የተገኘውን መቶ ፐርሰንት ድል በማጣጣም ላይ ተጠምዶ ስለነበር በሚሊዮን የሚቆጠሩት ድሆች የሚያሰሙትን የድረሱልን ጥሪ የሚሰማበት ጆሮና የሚያይበት አይን አልነበረውም፡፡ መንግስት ከመደበኛ ስራዎች ባሻገር በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ከሚያፈስባቸው ጉዳዮች ጥቂቶቹን ብንመለከት አገሩቱ በችጋር እየተጠበሱ የሚረግፉ ልጆቿ ለመታደግ የሚስችለውን አቅሟን ሥርዓቱ በምን ላይ እያዋለው እንደሆነ በግልጽ ያመላክታል፡፡

  • በቅርቡ ሥርዓቱ በአለማችንየተለያዩ ከፍሎች ተበትነው ጥቂት ቅሪት ያካበቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ድል ያለ ድግስ ደግሶና 40 ፐርሰንት የአውሮፕላን ትኬታቸውን ወጪ ሸፍኖ ሲያበላ፣ ሲያጠጣና አገር ሲያስጎበኝ ቆይቷል፡፡ ለዚህም በሚሊዮኖች የሚገመት የአገሪቷን ሃብት እንዳፈሰሰ በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን አርድቶናል፡፡
  • ባለፉት ሁለትና ሶሰት አመታተ ውስጥ ሥርዓቱ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ሲል በየኤምባሲው እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ አፍሶድል ያለ ድግስ በመደገስ ከአገር ውጭ በተደላደለ ኑሮ ውስጥየሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ሲያበላና ሲያጠጣ ከርሟል፡፡ እኔ በምኖርባት አገር የሚገኘው ኤምባሲ እንኳን በተደጋጋሚ ጊዜያት ከ300-400 የሚገመቱ የቤልጂየምና የጎረቤት አገር ነዋሪዎችን እየጋበዘ ከኢትዮጵያ ድረስ አስጭኖ ያስመጣውን ምግብና መጠጥ በከፍተኛ ገንዘብ በተከራያቸው ውድ አዳራሾች ሲያበላና ሲያጠጣ ታዝበናለ፡፡ በችጋር ከሚረግፉት ሚሊዮኖች ጉሮሮ እየነጠቀ በድሎት ከሚኖሩ ጥቂቶች ጋር ቢራና ውስኪ የሚያራጭበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡
  • ከአነስተኛ ሹማምነት አንስቶ እሰከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ የአገዛዙ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ከገቡበት የሙስና አዘቅት ባሻገር ለሥርዓቱ ያላቸውን ታማኝነት ይዘው እንዲቆይ ሲባል ለነሱና ለቤተሰቦቻቸው ምቾት የሚባክነው ገንዘብ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ አፈ-ጉዔው አቶ አባዱላ ባለፈው አመት በተወካዮች ምክር ቤት የአፍ ወለምታ ይሁን ከልብ አስበውበት “እኔን ጨምሮ እያንዳንዱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከአንድም ሁለት የሰባት ሚሊዮን ብር እና ከዛ በላይ የሚያወጡ መኪኖችን ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው መገልገያ በመንግሥት ባጀት ማዘዛቸውን ማቆም አለባቸው” ሲሉ የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በርሃብ፣ በውሃ ጥም፣ በሕክምና እጦትና በሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ችግር በሚለበለቡበት አገር ባለሥልጣናቱ አይን ካወጣ ዝርፊያና ንጥቂያ አልፈውየድሎት በጀት አስበጅተውየአገር ሃብት ሲያባክኑ እየታየ ነው፡፡
  • የገዢው ፓርቲና አጋሮቹ በየጊዜው እየተነሱ የሚያከብሩዋቸው ድርጅታዊ በዓላት በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ የሚፈስባቸው ናቸው፡፡ በቅርቡ በጅጅጋ የተካሄደውን የወያኔን የድልበዓል አከባበር ማየት በቂ ነው፡፡ የክልሉ ሕዝብ በርሃብና በውሃ ጥም እየተሰቃየና እርዳታ እየተማጸነ ባለበት ወቅት የአገዛዝ ሥርዓቱ በመላ አገሪቱ ያሉትን ካድሬዎች ጅጅጋ ላይ ሰብስቦ ለአንድ ሳምንት ጉሮ-ወሸባዮ ይል ነበር፡፡
  • በየጊዜው እየተሰነጣተቀ የሚገጥመውን የገዢውን ፓርቲ የፖለቲካ ገጽታ ለማሳመርና ያገዛዙን ዘመን ለማራዘም የሚባክነውም ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በባለሥልጣናትና በካድሬዎቻቸው በስብሰባና የውጭ ጉዞዎች የሚባክነውን ከፍተኛ ገንዘብ እንተወውና ሥርዓቱ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ፖለቲከኞች፣ ስርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኞችንና የማህበራዊ ድረ-ገጾችን፣ የተቃዋሚና ገለልተኛ ሚዲያዎችን ለማፈንና ለመሰለል የሚያወጣውም ገንዘብ በሚሊዮን ዶላር የሚገመት እንደሆነ በቅርቡ በጣሊያንና በጀርመን ከሚገኙ በኢንተርኔት ጠለፋና ሥለላ ሥራዎች ላይ ከተሰማሩ ደረጅቶች ጋር የነበረው ግንኙነት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በሚራብበት አገር ከነሱ ጉሮሮ ነጥቆ በሚሊዮኖች የሚገመት ዶላ ወጪ አድርጎ አንድ ሺ የማይሞሉ ተቃዋሚዎቹንና ተቺዎቹን መሰለያ የሚሆኑ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን የሚገዛ ድርጅተ ነው፡፡

እነዚህን እና ሌሎች የአገዛዝ ሥርዓቱ በአገርና በሕዝብ ሃብትና ገንዘብ ላይ የሚፈጽማቸውን ብክነቶች እያሰብን ከፍለፊታችን የተጋረጠውን የችጋር አደጋ ስንመለከት ስርዓቱ ከጥይት፣ ከእስር፣ ከስደትና ከልመና የተረፉትን ድሃ የሃገሪቱን ዜጎች ለችጋር አሳልፎ የሰጣቸው መሆኑን ነው የምንመለከተው፡፡ ከላይ በተጠቀሱት መንገዶችና በተመሳሳይ ሁኔታዎች ከሚባክነው ከፍተኛ ገንዘብና በተለያዩ ጊዜያት ከአገር የሚሸሸውን የገንዘብ መጠን ስንመለከት ኢትዮጵያ ደሃ ሳትሆንየተፈጥሮ ሃብቷንና ገንዘቧን በአግባቡ የሚያስተዳድርላት ሰውና የፖለቲካ ሥርዓት ነው ያጣችው፡፡

ለአገርና ለወገን የሚቆረቆር ጤናማ የፖለቲካ አመራር ባለበት ሃገር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ዋስትና በማጣት ከሞት ደጃፍ አይደርሱም፡፡ ህሊናቸውን ያልሳቱ፣ በሕዝብ ገንዘብ አእምሮዋቸው ያልናወዘና ስብዕና የሚሰማቸው የፖለቲካ አመራሮች ባሉበት አገር ሹመኞች ከነልጆቻቸው በሚሊዮን ዶላር በሚገዙ መኪኖች እየተንፈላሰሱና በተንጣለሉ ቪላዎች እየተመናሹ የድሃ ልጆች ቁራሽ ዳቦ የሚታደጋቸው አጥተው በየመንገዱ ጠኔ አይጥላቸውም፡፡ ይህ የሚሆነው በተቃወሰ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ አንድ የመንግሥት ሹመኛ ወይም ወታደራዊ ባለስልጣን ወይም የሥርዓቱ ደጋፊ የሆነ ሰው ባጭር አመታት ውስጥ ከመንግሥት ደሞዝተኝነት ተነስቶ ምንጩ ባልታወቀ ሁኔታ ሚሊዮነር ሲሆንና የከፍተኛ ሃብት ባለቤት ሊሆን የሚችለው መረን የለቀቀ ሙስና በተንሰራፋበት ሃገር ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግስት የሚከፍላቸውን የወር ደሞዝ አንድም ሳንቲም ሳይቀነስለት ለመቶ አመታት እንኳን ሙሉውን በባንክ እንዲቀመጥ ቢደረግ ስሌቱ ባንድ ጀምበር ዛሬ ላይ ያፈሩትነ ሃብት የእሩብ እሩቡ እንኳ እንዲኖራቸው የሚያስችል አይደለም፡፡ ከትቢያ ተነስተው የግዙፍ ህንጻዎችና ኩባንያዎች ባለቤት የሚሆኑት ከሕዝበ ጉሮሮ በነጠቁት ገንዘብ ካልሆነ በቀር ከየት አምጥተው እንደሆነ ሕዝብ የማወቅና የመጠየቅ መብት አለው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 25(1) እንዲሁም በአለም አቀፉ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ድንጋጌ በአንቀጽ 11 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው እያንዳንዱ ሰው እራሱና ቤተሰቡን በተሟላ ጤንነትና ለሰው ልጅ ክብር በሚገባ ሁኔታ የመኖር ዋስትና እንዲረጋገጥለት፣ እንዲሁም በቂ የሆነ ምግብ፣ አልባሳት፣ መጠለያ ቤትና የህክምና ግብአቶችን የማግኘት መብት እንዳለውና መንግስትም እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች የማሟላት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህን ግዴታቸውን መወጣት ካልቻሉት ጥቂት የአለማች አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ዋስትና ማጣትን ተከትሎ ሚሊዮኖችን አደጋ ላይ እስከ መጣል የደረሰውን የችጋር አደጋ የከፋ የሚያደርገው የአገዛዝ ሥርዓቱ አደጋውን ችላ ከማለቱም ባሻገር ለማለባበስ የሚያደርገው አሳፋሪ ጥርት ነው፡፡ የBBC ጋዜጠኛ በNovember 9, 2015 ጥናታዊ ዘገባው ችግሩ በተከሰተባቸው ሥፍራዎች፤ በተለይም ወሎ ውስጥ ቆቦ አካባቢ በመዘዋወር የችጋሩ ተጠቂ የሆኑ ሰዎችን አነጋግሮና በችጋር ልጇን ያጣች አንዲት እናት ጨምሮ ምስክርነታቸውን የሰጡትን ሰዎች የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ልማታዊ ጋዜጠኞች ቃላቸውን እንዲያስተባብሉና በችጋር የሞተ የለም ብለው እንዲናገሩ አስገድደዋቸዋል፡፡ የሚያሳዝነው እንዲህ ያለውን አስነዋሪና ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር በራቀ መልኩ የቪኦኤው የመቀሌ ዘጋቢ ከመቀሌ ቆቦ ድረስ ተጉዞ የአገዛዙን ገበና ለመሸፈን ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙ ነው፡፡

ይህ እጅግ አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ከመሆኑማ ባሻገር የተራበን ሰው አልተራብኩም በል፣ በርሃብ ልጇን ያጣችን ድሃ እናት ልጄ በበሽታ ነው የሞተው ብላ እንድትናገር ማስገደድ የሥርዓቱን ብልሹነት በግልጽ ያሳያል፡፡ ለዚች እናት ህመሙ በደርግ ጊዜ የተገደሉባቸውን ልጆቻቸውን አስከሬና ለመውሰድ የጥይቱንዋጋ እንዲከፍሉ ከተገደዱት እናቶች እኩል ነው፡፡የእዚህች እናት ህመም የመንግስት አድራጎት በ1997 ዓ.ም. ምርጫውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት የትምህርት ቤት ደጃፎቻቸው ላይ በአጋዚ ጦር ግንባራቸውን እየተመቱ የወደቁትን ሕጻናት ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ነው የተገደሉት የሚል የማላገጫ ምክንያት እንደተሰጣቸው እናቶች ነው፡፡

ሥርዓቱና ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በችጋር ለሚሰቃየውና ለሚያልቀው ሕዝብ በታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ባለፈ በተለይም በኦጋዴንና በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በችጋር እየተጠቁ መሆኑን እየታወቀ ከአመት በላይ ተገቢውን እንዳታ ባለማድረጉና ለጋሽ ድርጅቶችም ሕዝቡን እንዳይታደጉ እቀባ በመጣሉ የተነሳ ለሚደርሰው ሰብአዊና ሌሎች ጉዳቶች ሁሉ በችጋር የሰውን ዘር ሆነ ብሎ አደጋ ላይ በመጣል በሕግ የሚያስጠይቃቸው መሆኑን ከወዲሁ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

አስተዋሽ አጥተው ለችጋር ለተጋለጡት ወገኖቻችን እጃችንን እንዘርጋ!

ያሬድ ኃይለማርያም

yhailema@gmail.com


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

<!–

–>

The post ችጋር በሰው ዘር ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles