Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ለአገር ሰላም መፍትሔው …

$
0
0

እኔም እንደ ዜጋ ለአገር ሰላም  አለኝ!!

ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሁላችንም እንጂ የተወሰኑ ግለሰቦች፣ ብሔሮች፣ ጎሳ፣ ዘር፣ …. አይደለችም፡፡ የተወለድኩት በንጉሡ ዘመን ሲሆን፣ ነፍስ ያወኩትና ፊደል የቆጠርኩት በደርግ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ደርግ እጅግ ክፉና ጨካኝ ወታደራዊ መንግሥት እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ብዙዎች ተገድለዋል፤ ተረሽነዋል፡፡

በአንጻሩ አሁን ያለው መንግሥት ከደርግ በምን ይሻልል? ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል፡፡

ደርግ በአርሶ አደሩና በከተሜው ሕዝብ ዘንድ አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን ተቀባይነት ነበረው፡፡ በተለይ አገራዊ አጀንዳን በሚመለከት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞአል፡፡ በ1969 ዓ.ም ትዕቢተኛው የሶማሊያ ወራሪ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ሕዝቡ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቶአል፡፡ ወረራውን ለመቀልበስ የሕዝቡ ድጋፍ ከደርግ መንግሥት ጋር ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወራሪውን ጦር ከአገር ጠራርጎ ያስወጣ ጀግና  ሠራዊት ሆ! ብሎ ተነሥቶ ገድሉን ለዓለም ሕዝቦች አሳይቶአል፡፡

ይሁን እንጂ በደርግ ዘመን የነበሩ የሠራዊቱ አባላት በጦርነት የመሰልቸት ጉዳይ እንደነበር አይካድም፡፡ በደርግ ውስጥ በነበረው ሽኩቻና መሰልቸት ምክንያት ወያኔ አጋጣሚውን ተጠቅሞ መላውን ኢትዮጵያ መቆጣጠር ቻለች፡፡ ወያኔ ለአገዛዝ እንዲመቻት በፌደራሊዝም ሰበብ ኢትዮጵያን በክልል ከፋፈለች፡፡ ዓላማው የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ መመለስ የሚል መርሐ ግብር ነበር፡፡ ሆኖም የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ተመልሶአል ማለት አያስደፍርም፡፡ የብሔሮች ጥያቄ ቢመለስ ኖሮ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ እና በሌሎችም ክልሎች አሁን እየታየ ያለው ሁኔባልተከሰተ ነበር፡፡

ስለዚህ በግልፅ እንደሚታየው በወያኔ መንግሥት እና በሕዝቡ መካከል መጠነ ሰፊ ክፍተት ታቶአል፡፡ ኢትዮጵያም በአደጋ ላይ ትገኛለች፡፡ ሕዝቡ ጥያቄ አንግቦ ሆ! ብሎ ተነሥቶአል፡፡ የሕዝቡን ጥያቄ የወያኔ መንግሥት መመለስ አልቻለም፤ ወይም ደግሞ ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡

ስለዚህ እኔም እንደ ዜጋ ለአገሪቱ ሰላም የመፍትሔ ሐሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

1. ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የታሰሩት እንዲፈቱ፤

2. የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የሚለው የወያኔ ፓርቲ ስም በአስቸኳይ መቀየር አለበት፤ ምክንያቱም ነፃ የመውጣት ዓላማ ከማን ነው? መቼ ነው? ይህ የሚያሳየው ወያኔ የራሱ ብቻ የሆነ ድብቅ ዓላማና አጀንዳ እንዳለው
አመላካች ነው፡፡

3. ወያኔ እኔ ከለሌሁ አገር ትፈርሳለች፤ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ … የሽብርተኞች መፈንጫ ትሆናለች የሚለው ፕሮፓጋንዳ መቆም አለበት፤

4. ወያኔ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መደራደር አለበት፤

5. ወያኔ የትጥቅ ትግል ላይ ከሚገኙት ጋር በድርድር ሰላም የሚፈጠርበትን መፍትሔ መፈለግ አለበት፤

6. ወያኔ እኔ ብቻ አገር አመራለሁ፤ አስተዳድራለሁ … ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ ባዕድ
በአገራችን የለም፤

7. ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ መልካም እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሆኖም ብሔር ተኮር የፌደራሊዝም ሥርዓት ፈርሶ መልክዓ ምድራዊ ይዘት ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓት እንዲካሄድ መፈቀድ አለበት፤

8. አሁን ያለው የምርጫ ቦርድ ፈርሶ ገለልተኛ የሆነ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን መቋቋም አለበት፤

9.  ወያኔ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣኑን መልቀቅ አለበት፤

10. ሁሉንም የሚያሳትፍ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት፤ ይህ ማለት በሰላማዊ እና በትጥቅ ትግል ለሚታገሉ ሁሉ በር መከፈት አለበት፡፡ አገራዊ አጀንዳ ያላቸው ሁሉ መሳተፍ አለባቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም ሲባል ዝቅ ማለት ያስፈልጋል፡፡

11.  አሁን በሥልጣን ላይ ለሚገኙ የወያኔ ባለ ሥልጣናት በሰላማዊ መንገድ፣ ለአገር ሰላም ሲባል ሥልጣን በመልቀቅ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ካመቻቹና ፈቃደኛ ከሆኑ ከዚህ በፊት ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ እንዳይሆኑ የደህንነት ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እስከ መቼ እየተጣላን፣ እየተብላላን፣ አንዱ ሥልጣን ሲይዝ ሌላው ወህኒ የሚጣልበት ዘመን ማብቃት አለበት፡፡

በቃ! በኢትዮጵያ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ጥላቻ፣ የዘር ልዩነት፣ ጎሰኝነት፣ …. ታሪክ መሆን አለበት፡፡

እውነቱን ለመናገር እነዚህን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ጥቅሙ ይበልጥ ለወያኔ ባለ ሥልጣናት ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ከአርባ ዓመታት በላይ ያለ እረፍት በፖለቲካ ሕይወት ሲሳተፉ የቆዩ ስለሆኑ ዕረፍት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ባለትዳርና የልጆች አባት /እናት/ ናቸው፡፡ ሰላማዊ ኑሮ በመኖር ልጆቻቸውን አሳድገው ወግ ማዕረጋቸውን ማየት አለባቸው፡፡ ሥልጣንን የሙጥኝ ብሎ መያዝ አስፈላጊ አይደለም፡፡ የአምባገነን የአፍሪካ መንግሥታት የጭካኔ አሠራር በኢትዮጵያ መታየትና መደገም የለበትም፡፡ ሰላማዊ ሕይወት መኖር አለብን፡፡ የትጥቅ ትግል ያነሱ ሰዎች ጥያቄአቸው በሰላማዊ መንገድ ከተመለሰላቸው ከጫካ ምን ይሠራሉ? ይምጡ፤ ከተማ ይግቡ፡፡

ከወዳጅ ዘመድ ጋር ይቀላቀሉ፡፡

በመሠረቱ ወያኔዎች ለአስራ ሰባት ዓመታት የታገሉት ትግራይን ለመገንጠል ነበር፡፡ የትግራይ ነፃ መንግሥት የማቋቋም ሕልም ነበራቸው፡፡ ሆኖም ትግራይን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ ትግራይን ብቻ መገንጠል አላረካቸውም ነበር፡፡ ለካስ መላውን ኢትዮጵያ መቆጣጠር ይቻላል የሚል አዲስ ራእይ ተከሰተላቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ተሳካላቸው፡፡

ነገር ግን ምን ለውጥ መጣ? እንጠይቅ!

ምንም ዓይነት ለውጥ አልመጣም፡፡ ወያኔ ደርግን አስወግዶ እራሱ ሌላኛው ደርግ ሆኖ መጣ! ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር በዘር ከፋፍሎና ሰነጣጥቆ በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የሆነ ጥላቻ እንዲነግሥ አደረገ፡፡

እንግዲህ የቀረበውን የመፍትሔ ነጥቦች ተግባራዊ ካልሆነ በመጨረሻ ሕዝብ ማሸነፉ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ለሚደርሰው ጥፋትና ውድመትም ተጠያቂው የወያኔ  ባለሥልጣናት ይሆናሉ፡፡ የመጨረሻ ዕድላቸው ወህኒ ቤት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ሥልጣን በሞኖፖል ይዤ ዘላለም እኖራለሁ ብሎ ማሰብ እጅግ ሞኝነት ነው፡፡

ሕዝቦችን አፍኖ ለዘላለም መግዛት አይቻልም፡፡ የሕዝቦች ጥያቄ በበቂ ሁኔታ መመለስ አለበት፡፡ ወያኔዎች  ይህን የመፍትሔ ሐሳብ ቢሰሙና ቢቀበሉ፣ አገር ሰላም ትሆናለች፤ ትረጋጋለች፡፡ ከዚህ ውጭ የክልል መሪዎችን መቀየር ሥር ነቀል ለውጥ አያመጣም፤ እንዲህ ማድረግ የሕዝቦችን ጥያቄ አይመልስም፡፡ ጉልቻ ቢለወዋጥ ወጥ አያጣፍጥ እንደሚባለው ዓይነት ብቻ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ያለ ምንም ለውጥ የኢትዮጵያ ሁኔታ አሁን ባለው መልኩ እንዲቀጥል ከተፈለገ እጅግ አደገኛ ሁኔታ እንደሚከሰት ከወዲሁ እንደ ነቢይ መተንበይ ይቻላል፡፡

የመፍትሔ ሐሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ ምኞቴ ነው፡፡

ደጉ ዘመን

ከአዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

E-mail: deguzemen@gmail.com


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles