ሰንደቁን ሲሰቅል ጎርፍ ሆኗል፣
ታሪክን ሲደግም ተረጭቷል፣
ፍትህ ሲጠይቅ ጠብ ብሏል፣
የሰማእት ደም ይጮኻል!
ባንዳን በወኔ ተዋግቷል፣
ያያቱን ጀብዱ ደግሞታል፣
ለቀሪ አገሩን አውርሷል፣
“ትግሌን አደራ” ይለናል፣
የሰማእት ደም ይጮኻል!
የሰማእት ደም ይፈልቃል፣
ዓባይ ተከዜን አቅልሟል፣
አንገርብ ቀሃን አቅልቷል፣
ተምጫ ጨሞጋን ሱፋሌ፤
ጣና በለስን ጃኖ አርጓል፡፡
የሰማእት ደም ይጎርፋል፣
ደዴሳ ጊቤን ሞልቶታል፣
ባሮ ገናሌን አጉሽቷል፣
አዋሽን ቆቃን ጢም አርጎ፤
የቂሊንጦን መስክ አርሷል፡፡
የሰማእት ደም ይጮኻል!
ባድርባይ ምሁር ተከፍቷል፣
በጳጳሳቱ ልቡ አዝኗል፣
በአባ ማትያስ ያነባል!
የሰማእት ደም ይጮኻል!
በሆድ አደሮች ቆዝሟል፣
ባዘን ወቅት ዘፋኝ አልቅሷል::
የሰማእት ደም ይጮኻል!
ሰንደቁን ለብሶ ሸፍቷል፣
ጀግናን ሞረሽ ሲል ይጣራል፡፡
የሰማእት ደም ይጮኻል!
ጠበቃ ዳኛ ፈልጓል፣
ፍትህ ከችሎት ይመኛል፡፡
የሰማእት ደም ይጮኻል!
ጋዜጠኛውን ተማጽኗል፣
ኪነ-ጥበብን ለምኗል፣
ቀሳውስት ሼሁን ተማልዷል፣
እንዲዘክረው ጥይቋል፡፡
የሰማእት ደም ይጮኻል!
ለሕዝብ መልክቱን አትሟል፣
አደራን በምድር አስምሯል፣
ደመ-ከል ላይቀር ተማጥኗል፣
“ትግሌን አደራ” ብሎናል፡፡
የሰማእት ደሞ ይጮኻል!!
ይጮኻል!!
ይጮኻል!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ነሐሴ ሁለት ሺ ስምንት ዓ.ም.