የአርቦሬ የአገር ሽማግሌዎችን በአርበኞች ግንቦት 7 ሥም ለማስፈራራት ተሞክረ ፤
ባለፈው ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በአርቦሬዎች ይዞታ ሥር ባለው ቢልብሎ ቀበሌ የሀመር ወጣቶች ዘልቀው በመግባት ከብቶች በማሰማራታቸው ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ ግጭትበተያያዘ ስምንት/8/ ሀመሮችና ስድስት/6/ አርቦሬዎች መሞታቸውና ግጭቱ እስከዛሬም እንዳልተፈታና በባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ እንዲፈታ የዞኑ መንግስት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እስካሁን በአካባቢው ውጥረት መንገሱን የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡ አርቦሬዎች ዞኑ ችግሩን ሊፈታ ያልቻለው የሀመር ወረዳ አስተዳዳሪ/አቶ ወሌ ገርሾ/ እና የዞኑ ም/አስተዳዳሪ/አቶ አወቀ አይኬ/ ሀመሮች በመሆናቸው እንደሆነ፣ ነጻና ገለልተኛ የክልልና የፌደራል ጉዳይ ተወካዮች በተገኙበት ችግሩ በአጭር ጊዜ ካልተቋጨ የእርሻ ልማት ሥራ ተቋርጦ አካባቢው ለረሃብ እንዳይጋለጥ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ፡፡
የግጭቱ መነሻ የግጦሽ ጉዳይ ሲሆን ይህ ዓይነቱ ግጭት በቀድሞ ጊዜ በአካባቢው የተለመደ ቢሆንም በንጉሱ አገዛዝ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በአገር ሽማግሌዎች በባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት በመፈታቱ እስካሁን ሁለቱ ህዝቦች በሰላም ይኖሩ እንደነበር መረጃው ያስረዳል፡፡ በዚሁ የዕርቅ ጊዜ ይዞታው የአርቦሬ ከሆነ መሬት ሀመሮች እንዲጠቀሙ ‹ ጎላ › የሚባል ቦታ ተከልሎ የተሰጠ ሲሆን የአሁኑ ግጭት የተነሳው የሀመር ወጣቶች ይህን ቦታ አልፈው ቢልብሎ የሚባል ቀበሌ ዘልቀው በመምጣታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የአርቦሬ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ሀመሮች ወደዚህ ቦታ ለመምጣት ቢፈልጉ እንኳ የቀበሌውን አስተዳደርና የአገር ሽማግሌዎችን ማስፈቀድ ሲኖርባቸው ሳያስፈቅዱ ከመምጣታቸውም በላ የመጡበት ቦታ ለደከሙ ላሞች የተከለለ መሆኑንና ሀመሮች ይዘው የመጡት ደግሞ ‹ የፎራ ከብት › ማለትም( ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚግጡ ከብቶች) ስለሆነ በቀጣይ ደካማ ከብቶች በግጦሽ እጥረት ይጎዳሉ፣ ያልቃሉና ወደተከለለላችሁ ቦታ ተመለሱ ቢባሉ ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና ለግጭት በመጋበዛቸው ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በዱላ የጀመረው የወጣቶች ፀብ ወደ መሳሪያ/ጠመንጃ ተቀይሮ በዕለቱ 2 ሃመሮች ሲሞቱ፣ ሌሎች ቆስለዋል፤ በአርቦሬ በኩልም የቆሰሉ ሲኖሩ የሞተ አልነበረም፡፡ ችግሩ /ግጭቱ በባህላዊው የተለመደ ስርዓት እንዲፈታ፣ ይህ የዕርቅ ስርዓት ባህላዊ ስለሆነ ሂደቱ በቪዲዮ ቢቀረጽ ለታሪክ ሊተላለፍ፣ ሂደቱንም በግልጽ ሊያሳይ ስለሚችል እንዲቀረጽ ከአርቦሬ ሽማግሌዎች የቀረበውን ኃሳብ ሀመሮች በመጀመሪያ ፈቃደኛ ባይሆኑም ዘግይተው ተቀብለው ለዕርቁ ቀጠሮ ተይዞ ባለበት ፣ የሀመር ወጣቶች በሌላ አቅጣጫ በ ‹ቦንቆሌ › ቀበሌ በኩል ሰርገው በመግባት ግጭቱን እንደገና በመቀስቀሳቸው በተከታታይ ቀናት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ እስካሁን በድምሩ 8/ስምንት /ሀመሮች በአርቦሬዎች ሲገደሉ፣ ሀመሮች አራት/4/ አርቦሬዎች ገድለው፣ ሁለት አርቦሬዎች ደግሞ በጥበቃ ላይ እያሉ በሌሊት ከምሽግ ወጥተው በስህተት ተታኩሰው 2/ሁለት/ እርስ በርስ በመገዳደላቸው በድምሩ ስድስት/6/ አርቦሬዎች ሞተዋል፡፡ በተጨማሪም ከሁለቱም ወገን በርካታ ወጣቶች ቆስለዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአርቦሬ ሽማግሌዎች የቀረበውን የዕርቅ ኃሳብና በቪዲዮ ይቀረጽ አስተያየት ተከትሎ የሀመር ባለስልጣናቱ ከአርቦሬዎች ጀርባ በአርባምንጭ እንደታየው እዚህም አርበኞች ግንቦት 7 ገብቷል ብለው በግልጽ መናገራቸውን፣ ይህን አባባል የአርቦሬ ህዝብ እንዳልተቀበለው ግን አገላለጹ እንዳሳዘነው አንድ የአካባቢው የአገር ሽማግሌ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ አስተያየት የሰጡ ወገኖች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀመሮች በተመሳሳይ ከዳሰነችና ከኛንጋቶም ሲጋጩ፣ እንዲሁም በድንበር አካባቢ ዳሰነችባ ኛንጋቶሞች ከኬንያዊያን ጋር ሲጋጩ የዞኑ አስተዳደር ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ መስተት ባለመቻሉ በየጊዜው ተደጋጋሚ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በመሆኑም እንደነዚህ ያሉት ችግሮች ከዞኑ አስተዳደር አቅም በላይ በመሆናቸው ጉዳዩ የሚመከታቸው የክልልና የፌደራል ጉዳዮች ለተፈጠረውና በዞኑ ለሚታየው ግጭት በአካባቢው ባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት አስቸኳይ ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀለት ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ….. እንዳይዳርግ ያላቸውን ሥጋት በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ እኛም ጥሪ የተደረገላቸው ክፍሎች ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ብለው ለህዝቡ እንዲደርሱለት የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡