Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የሜ/ ጀ አበበ /ጆቤ በጥናት ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ ትንታኔ በወፍ -በረር ሲፈተሽ// (ግርማ በቀለ)

$
0
0

(በተለይ ለአዲስ አድማስ ከተሰጠው ቃለምልልስ)

Abebebe9
የእኔ ድምዳሜ—ጆቤ እነ ሪፖርተርና አዲስ አድማስ ሊሰብኩን እንደሚሞክሩት፣ እርሳቸውም ሊያሳምኑን እንደሚታትሩት ቅንጣት የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ የአቋም ለውጥ አላደረጉም፤ የጽሁፎቹ ዓላማ ህወኃት/ኢህአዴግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በህዝብ የተነሳውን ፖለቲካዊ የለውጥ ትግል ለማዘናጋት አቅጣጫ የማስቀየሪያ ስልት ምክረ ኃሳብ ነው፡፡

መነሻዬ — ጆቤ ጽሁፉን በጥናት ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ ትንታኔ ለማስመሰል ያደረጉት ጥረት በግልጽ ይታያል፡፡ግን አልተሳካም፡፡ እንዴት ቢሉ ከሁሉም በአጭሩ ‹‹ …እንግዲህ 25 ዓመት ነው የቆየነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የሰራዊቱ የብሄር መመጣጠን እየተስተካከለ መጥቷል የሚል ግምት ነው ያለኝ።›› የሚለው የአደባባይ ምስጢር የሆነውን ጥናቱ ያለመመልከቱን ‹‹ ግምት›› በመስጠት ሊሸፍኑ መሞከራቸውን በግልጽ ያሳያል፡፡ ሌላ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ይህን እንኳንስ ‹ጄ/ል› ጆቤ እኔስ/ማንም በእርግጠኝነት አይናገረውም ? ከ95 % በላይ ጄነራሎች እነማን መሆናቸው ጆቤ ጠፍቶኣቸው ከሆነ ይህን ያሉት /የገመቱት አንባቢ ይፍረድ፡፡ የመነሻና ድምዳሜዬ ማሳያዎች ለዛሬ በጥቂቱ ፡-

1. ጆቤ ለማስተርስ ድግሪ መመረቂያ ጥናት እስከሚያደርጉ በአሰብ ላይ የኢትዮጵያኝ ህጋዊ ባለመብትነት አያውቁም ነበር፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት (በአልጀርሱ ስምምነት ወቅት) ከፍተኛ ወታደራዊ ሃላፊ መሆናቸውንና በዚያን ጊዜ ዛሬ ላይ የተረዱትን ሃቅ የሚናገሩና በሙያቺን እናግዛችሁ ይሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊ የህግና ታሪክ ምሁራን እነ ዶ/ር ያዕቆብን የመሳሰሉ ምን እንዳደረጉ፣ ሊያደርጉ ይችሉ እንደነበር ነው ጥያቄው፡፡ ጆቤ የዶ/ር ያዕቆብን ‹አሰብ የማን ናት›› መጽሃፍ ለማስተርስ ጥናት ማጣቀሻ አላነበቡ ይሆን? ያስብላል፡፡ ‹‹አውቆ የተኛን….››፤
2. ጆቤ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ማንም ሌላ መንግስት አድርጎ የማያውቀውን ‹‹ከራሱ ለተገነጠለ አገር ›› ከሁሉ ቀድሞ ዕውቅና የሰጡበትን እውነት ክደው ፣ዛሬም የህወኃት አቋም መሆኑ በይፋ እየተነገረ ባለበት በኮንፌደረሽንም ሆነ በፌደረሽን አንድ ሊሆኑ የሚችሉበትን ዕድል/ ሊኖረን የነበረውን ግንኙነት ያመከነው ሻዕቢያ ነው ይሉናል፡፡ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ፤
3. የአገር መከላከያ ሠራዊት ዛሬም የሚከተለው የጫካ ጎሬላ ውጊያ ትግል ልምዱን ነው፡፡ እንዲህ ገልጸውታል ‹‹ ከትጥቅ ጊዜ ጀምሮ ያለው ልምድ፣ በክብር የሚያርፉት እዚያው በተሰዉበት አካባቢ ነው፡፡ በየሄዱበት የመቅበር ነገር ነው የነበረው፡፡ ትክክል ይሁን አይሁን ባላውቅም የተሰዉ ወታደሮች ቁጥር መግለፅ ከሞራል አንፃር አስቸጋሪ ነበር የሚል አመለካከት ነበር፡፡ ይሄ ልምድ እስካሁን ዝም ብሎ የቀጠለ ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የተከፈለውን ዋጋና የተገኘውን ድል አውቆ ማመዛዘን ይኖርበታል፡፡…›› ሲሉ ሂስ አዘል በሆነ መንፈስ በድርጊቱ የተፈጸመውን ሰብዐዊነትና መንግስታዊ ኃላፊነት የመወጣት ውድቀት ይከላከላሉ፡፡ ‹፣ድመት መንኩሳ…››
4. ዛሬም በ1997ቱ ምርጫ የዲ/ሲን ግንባታ ቅልበሳ ለህወኃት/ኢህአዴግና ተቃዋሚ ያልተመዘነ (የእኩል) ድርሻ ይሰጣሉ፣ እንዲህ በማለት ‹‹ ግን በቅርቡ እንኳ ያለውን የ10 ዓመት ጊዜ ብናይ፣ 97 ምርጫ ለኛ አንድ ወርቃማ እድል ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ዲሞክራሲያዊ ጉዞ በከፍተኛ ደረጃ የገባበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በገዥው ፓርቲም በተቃዋሚውም በኩል በነበሩ ችግሮች ምክንያት ያ ተኮላሸ፡፡›› ማን ነበር ዋናውን/ወሳኙን የቅልበሳ ሚና የተጫወተው ? ትልቁ ድርሻ የማን ነበር ? የሚለውን ሳይመልሱ በደፈናው ሁለቱንም በእኩል ይከሳሉ፡፡ ‹‹የበላ ዳኛ….››
5. በአንድ በኩል ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ባይነግሩንም ‹‹ ….ኢህአዴግ ውስጥ መተጋገል የለም፡፡›› ካሉ በኋላ ከዩኒቨርስቲ ‹ኤ› የኢህአዴግ ‹ሲ› ይሻላል በሚል አስተሳሰብ ላይ የቆመ ሲቪል ሰርቪስ መኖሩን አክለውበት፤ በሌላ በኩል ‹‹ በመጀመሪያ ከህግ አኳያ ሲታይ፣ ሜቴክ ወታደራዊ ተቋም አይደለም፡፡ ወታደራዊ መሪዎች ያሉበት የሲቪል ተቋም ነው፡፡ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ስለዚህ ወታደራዊ ተቋም ሳይሆን የራሱ ሰውነት ያለው ተቋም ነው፡፡ ግን በህብረተሰቡ ዘንድ ይህ ግንዛቤ የለም፡፡ አብዛኛው ሰው የመከላከያ ተቋም እንደሆነ ነው የሚያስበው፡፡ ለሰው ሜቴክ ተጠሪነቱ ለመከላከያ ነው የሚመስለው፡፡ በእርግጥ የመከላከያ ታንክና የሜቴክ ገንዘብ ከተጨመረበት በጣም አደጋ ነው የሚሆነው፡፡›› በማለት…..

ያልቸገረንን የሜቴክ አደረጃጀት፣ ህጋዊ ሰውነትና ተጠሪነት ነግረውን 100 ከመቶ/100%/ የተመረጠውንና ዲሞክራሲን በላው በማለት የከሰሱትን የምርጫ ውጤት ተከትሎ የተቋቋመ ፓርላማና የሥልጣን ቁልፉ የት ነው በሚባልበት ጊዜ ላይ እያለን እና .ኢህአዴግ ውስጥ መተጋገል የለም፡፡›› ብለው ተነስተው ‹‹ ….ስለዚህ ከፓርላማው ብዙ እንጠብቃለን። ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ብዙ እንጠብቃለን፡፡ ተጣርቶ ለህዝብ መቅረብ አለበት። ለመሆኑ ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ይሄ ሁሉ ሲሆን የት ነበር? ከዚህ ጉዳይ በመነሳት ጠቅላላ ስርአቱንም መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ማየት ይጠይቃል፡፡›› ሲሉ ትልቅ ኃላፊነት ይጥሉበታል፡፡ ‹‹የቸገረው እርጉዝ …. ››
6. ጆቤ ዛሬም ከነበሩበት ኢንች ያለመንቀሳቀሳቸውን ‹‹ ለሕገ መንግስቱ በተሟላ መንገድ መተግበር የአቅሜን ያህል እታገላለሁ፡፡ ምክንያቱም ሕገ – መንግስቱ የአገራችንን ችግር የሚፈታና የሁሉም ሕጐች የበላይ በመሆኑ የማክበርም ግዴታ ስላለብኝ ነው፡፡ በተጨማሪም ከወጣትነቴ ጀምሮ የታገልኩለትን ዓላማ የሚያንፀባርቅና የህዘቦች መስዋእትነት ውጤት ነው፡፡ በተለይም እኔ ስታገልበት የነበረው በህወሓት መሪነት የትግራይ ህዝብ በከፈለው እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነት እንዲሁም፣ በተሰውት ጀግኖች፣ (በተደጋጋሚ በተቃጠሉ መንደሮች፣ በአውሮፕላን ድብደባ ወዘተ) የመጣ ውጤት በመሆኑ ሕገ መንግስቱን የማስጠበቅ ጉዳይ እንደሌላው ታጋይ ሞራላዊ ግዴታ አለብኝ ስለምል ነው፡፡››….. ቀጥለውም ለህዝቡ ‹‹ለዚሁም ሁሉም እንቅስቃሴ በሰላም እንዲሆን እና የነሱ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ለግላቸው ለመጠቀም ሁከት የሚጥሩትን ለመንግስት አሰልፎ በመስጠት ጭምር እንደታገሉ ነው፡፡ ›› ህዝቡ መንግስት የሚፈርጃቸውን ከጎኑ ቆሞ እንዲታገል ጥሪ በማቅረብ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ያደቆነ ሠይጣን…..››
7. በጽሁፋቸው ሻዕቢያ መወገድ አለበት ፣እንዲያውም የመፍትሄው ሁሉ መጀመሪያ ይህ ነው በማለት የሚከራከሩትና ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ የተቀናጀ ትግል ያስፈልጋል ብለው የሚመክሩት ጆቤ፣ ህወኃት/ኢህአዴግ ህገመንግስቱን እንዲያከብርና ተጠናክሮ እንዴት መውጣት እንደሚችል እንጂ ስለፈጸመው የመብት ጥሰትና ህዝቡ ስለሚያነሳው የዲሞክራሲ ጥያቄ ተገቢ፣ ቀጣይና ዘላቂ አስተማማኝ ፍትሃዊ ልማትና ሰላም ለማምጣት ህወኃት ማድረግ ስላለበት በፍጹም አያነሱም፡፡ የችግሩ ቁልፍ ያለበትን እንደማያውቁ ሆነው መንግስትና ኢህአዴግ እያሉ ያደባብሳሉ፡፡.. …፣ (ሌሎችም በርካታ አሉ፣ሁኔታው ታይቶ በክፍል ሁለት ይቀጥላል)
ይህ ለምን ያደርጋሉ ብለን ስንጠይቅ የእኔ መላምቶች ፣ በነጠላም ሆነ በተደማማሪነትና በመተመጋጋቢነት፡-
1. ህወኃት ቢወገድ ከተጠያቂነት አላመልጥም በሚል ስጋት ያለውን ዲክታተርሺፕ ማጠናከር የግድ መስሎኣቸው፣
2. በህወኃት ወታደራዊ አደረጃጀት በመደበኛነት ባይሆንም እንደ ጄ/ል ፃድቃን እንደ አማካሪ ሆነው ለመቀጠል፣
3. በዋናው የሙስና ዘመን ‹ያባረሩዋቸውን› ወታደራዊ ከፍተኛ ሹማምንት በተለይም ጄ/ል ሳሞራን በህወኃት ውስጥ ቦታ በማሳጣት ለመበቀል፤ ነው፡፡.
ከሶስቱ መነሻው የቱም በተናጠልም ሆነ በጥምረት ይሁን እንዲሳኩ ህወኃት/ኢህአዴግ መቀጠል አለበትና ነው፡፡
የዛሬው ማጠቃለያ ‹‹ እኔ ከመጀመሪያውኑ ስታገልላቸው ለነበሩ አላማዎች፣አሁንም በፅናት ቆሜያለሁ ነው የምለው፡፡ ገዥው ፓርቲ ነው ከትግሉ አላማዎች ወደ ኋላ እየተንሸራተተ ያለው፡፡ የ25 ዓመት ጉዟችንን ስናየው፣ ይሄን ልንገመግም እንችላለን፡፡ ›› ያሉትን ወስደን በዚህና ከላይ ባነሳኋቸው ምክንያቶችና የዚህን ምላሽ አይቼ በክፍል 2 የምመለስባቸው ያልተጠቀሱ ምክንያቶች ጥረታቸው በሙሉ ዛሬም ስለጥገናዊ ለውጥ ለመስበክና የህወኃት/ኢህአዴግን አገዛዝ አጠናክረው ስለማስቀጠል ይመክራሉ፣ ይሞክራሉ፡፡

ጆቤ ይምከሩም ይሞክሩም የተነሳው ህዝባዊ የነጻነትና የመብት ጥያቄ ደጋግመን እንዳልነው ከማይቀለበስበት ደረጃ ደርሷልና ምክሩም አይሰራም፣ ሙከራውም አይሳካም፣ ለዘላቂና አስተማማኝ ሰላምና ልማት ፣ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አያገለግልም፡፡ አዋጪ መፍትሄው– ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች፣ ከጠቅላይና አግላይ ፖለቲካና በኃይል ላይ የተመሰረተ የሥልጣን ሽግግር ወደ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላማዊ የሥርዓት ለውጥ መሸጋገር ነው፡፡ በብሄራዊ መግባባት፣ ዕርቅና የሽግግር መንግስት በኩል፡፡

ስለዚህ በዚህና በመሳሰሉት ማሰናከያና ማሳሳቻቻ አቀራረቦች ሳንዘናጋ ከፊታችን ባለው የቤት ሥራ ላይ እናተኩር መልዕክቴ ነው፡፡
ለአገራችንና ህዝቧ የሚበጀውን ያሰማን፣ ያሳስበን፣ ያስተግብረን፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡
ሰኔ 12/2008. UNITE.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles